ዓርብ 28 ጁን 2013

“ፍሩት” ቅድመ-ክትባት---- ኄኖክ ስጦታው




ወዳጄ ነው፡፡ የፍራፍሬ ጭማቂ መሸጫ ሱቅ አለው፡፡ የኑሮ ዘይቤው እና አመለካከቱ በሁለት ነገር የተገደበ ነው፡፡ በፍራፍሬ ጥቅም እና በፍራፍሬ ጥቅም ብቻ፡፡ ጭማቂ ልጠጣ በሄድኩባቸው ጊዜያት ሁሉ የገንዘብ መቀበያው ሳጥን ውስጥ  አላጣውም፡፡ የበሰለ ብርቱካን የመሰለ ፊቱን በፈገግታ አጅቦ ሰላም ይለኛል፡፡ ጭማቂው እስከሚመጣ አንዳንድ ፍልስፍናዎቹን ያዥጎደጉድልኛል፡፡

“የኛ ሰው ሲታመም ብቻ ነው አትክልትና ፍራፍሬ ይዘንለት የምንሄደው፡፡ በጤነኛነቱ ሰዓት ግን አረቄ ካልጋበዝንህ ብለን እናስጨንቀዋለን፡፡” ይለኛል፡፡

“እና ምን ማድረግ ነበረብን???” ብዬ እጠይቀዋለሁ ምን እንደሚለኝ ለመስማት፡፡

“ፍራፍሬ ሳትታመም በፊት ከተመገብክ እንደ ክትባት ነው፡፡ ከታመምክ በኋላ ግን ለጠያቂዎች የምታቀርበው የቡና ቁርስ ይሆናል፡፡” ይለኛል፡፡


ከሰባት ዓመታት በፊት ፣ ካልተሳካው አብዮት ጋር ተያይዞ የስራ ማቆም አድማና የንግድ ቤቶች መዘጋትን ተከትሎ ሥራው ላይ ከባድ ፈተና ገጥሞት እንደነበር የነገረኝን አልረሳውም፡፡ ለጭማቂ እና ለችርቻሮ ያዘጋጃቸው አትክልትና ፍራፍሬዎችን  “በመኪና ጭኜ እቤት አስገባሁ፡፡” አለኝ፡፡

“አስገብተህ ምንአደረግከው??” ስለው፡-

“ለሰፈር ሰው በነጻ አከፋፈልኩና በምትኩ ፍቅር ገዛሁበት” አለኝ፡፡


ሐሙስ 27 ጁን 2013

ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች ለሆነ ማንበብ ክልክል የሆነ ታሪክ

ኄኖክ ስጦታው

ልጅ እያለሁ የሰማኋቸው ተረቶች አስፈሪነት ያላቸው እና ከ18 ዓመት በታች ላለ ሰው እንዳይነገሩ መከልከል የሚገባቸው ነበሩ፡፡ የልጅነት አዕምሮዬ ከመዘገባቸው አስፈሪ ታሪኮች መካከል ዋንኛው “ቢሊጮ” ነው፡፡

“እኔ ቢሊጮ፣ ተንበላልጬ
የልጇን ስጋ፣ አበላሁ ልጬ…..!!!” (አበስኩ ገበርኩ!!!!)

/ቢሊጮ ብልጣብልጥ ልጅ ነው፡፡ የእንጀራ እናቱ ለሴት ልጇ “ዛሬ ቢሊጮን አጥበሽ፣ ቆዳውን ገፈሽ፣ ስጋውን ከትፈሽ ክሽን ያለ ምግብ ስሪልኝ” ብላ ወደገበያ ትወጣለች፡፡ ቢሊጮ ደግሞ የራሱን ብልጠት ተጠቅሞ የእንጀራ እናቱል ልጅ አጥቦና ቆዳዋን ገፎ ከሽኖ ፣…… ያበላታል፡፡/
እንደዚህ አይነት ተረቶች ይህም ዓለም በብልጣብልጦች እና ጨካኞች እንድትሞላ የራሳቸውን ሚና ይወስዳሉ፡፡  

እንደ “ቢሊጮ” አይነት ተረቶች ልጅን ለማነጽ ሳይሆን ለማፍረስ የሚነገሩ ለመሆናቸው አሌ የማይባል ሀቅ ቢሆንም ፋይዳቸው ግን ምንም ነበር፡፡

 አሁን ጊዜው ተለውጧል፡፡ ቢሊጮም ተረስቷል፡፡ ሆኖም ግን የቅርፅ ለውጥ እንጂ ይዘታቸው አንድ የሆኑ ፊልሞች ተበራክተዋል፡፡

በአስማት እና በጥንቆላ ላይ የተመሰረቱ ፊልሞች ቦታውን ይዘውታል፡፡ በአንድ ወቅት የአክሽን ፊልሞች “ቦንባርድ” የተሰኙ “ግሩፖች” በየመንደሩ እንዲፈለፈሉ ምክንያት እንደነበሩት ሁሉ አሁንም ትልቅ ስጋት ከፊታችን ተጋርጧል፡፡



በነካ እጄ ይቺን ሃሳብ ባክልስ¡?!¿
(/ለአዋቂ ተብለው የተሰሩና በየሲኒማ ቤት እየታዩ ያሉ ፊልሞችም አላጋጭ ትውልድ ቢፈጠር ተጠያቂ ናቸው!!!/)


እሑድ 23 ጁን 2013

ው-ዝ-ግ-ብ-ግ-ብ (ሌላው ገጽ) ---- ኄኖክ ስጦታው


----- ግብግብ ውስጥ እነሆ 1 ቅጠል

--
---
-----
---“ሩጫዬን ጨርሻለሁየሚሉት አይነት ጥቅሶች ያመራምሩኛል፡፡ ለምን መሰለህ በድንጋይ ድሪቶ እሱ ያላለውን መለጠፍህ ስለሚያሳዝነኝ ነው፡፡ የኔ ምርጥ አምላክ ሞተህ የተጻፈልህን የማንበቢያ ጊዜ የለውም፡፡ ሳትሞት የጻፍከውን ግን ሳይሰለች ያነብልሃል፡፡ ነው ትርጉሙ፡፡

ሩጫህን ለመጨረስ ሳትሮጥ ሞትህን መጠበቅ እንደሌለብህ እነግርሃለሁ፡፡ ባጭሩ ስንዝር በረጅሙ ሁለት እግርህን ተጠቅመህ የሮጥከው ሩጫ የፈጣሪን ልብ ለማራሪያነት አትጠቀም፡፡

ከሰሞኑ አንድ እናት ቂጣ ሰጡኛናነፍስ ይማር በልአሉኝ፡፡

የማንን?” አልኳቸው፡፡
የገድለ ገብርኤልንአሉኝ፡፡

ሀሳባቸው ገብቶኛል፡፡ የሟችን ክርስትና ስም እየነገሩኝ ነበር፡፡ እውነት ሆዴን ለመሙላት ስልይማር አይማርየማላውቀውን ነፍስ ለምን ልሸንግል?

መለስኩላቸው፡፡ ቂጣውን መለስኩላቸው፡፡

ምነው ልጄ?” አሉኝ፡፡

ነፍስ በስንዴ አትደለልም፡፡ ነፍስ በገንዘብ ኃይል አትፈታም፤ በቁጥር የጋገሩትን ቂጣበነፍስ ይማርሽንገላ ሆዳቸውን ለሚሞሉ አስመሳዮች ይስጡ፡፡አልኳቸው፡፡

ፊታቸው ከለበሱት ማቅ ጋር ሲመሳሰል አስተዋልኩ፡፡እኔ ነኝ እብዷ፡፡ ለእብድ መመፅወቴእያሉ ሄዱ፡፡ ትክክል ነበር የተናገሩት፡፡ ያለማስተዋል እብደትን ሊያጋቡብኝ አይችሉም፡፡

ቀባሪዬ፣ አርባ - ሰማንያ በሚል ስንክሳር ለመወጠር በዓመት - ሰባት ዓመት ዝክር፣ የቁርባን ክፍያ፣ በነፍስ ይማር ደፋ ቀና መፈታት መኖሩን አልነግርህም፡፡ አንተ በክፋት ጎዳና ያሰርካትን ነፍስ እራስህ እንድትፈታ እንጂ በቂጣና ሳንቲም ሽንገላይህን በልእንድትለኝ አልሻም፡፡

ለእኔ ገነትም ሲዖልም መሬት ነት፡፡ የመሬት እጅ የፈጣሪ እጅ ነው፡፡ እሳትም በረዶም ከመሬት ውጪ አይታየኝም፡፡ የኔ ፈጣሪ ጨካኝ አይደለም፡፡ ነፍስ ይማርቂጣ በተጀቦኑ ቃላት አይደለልም፡፡ በሬሳ ላይ ክምር የተጻፉ ጥቅስ ራርቶ ቀና ብለህ የምታየውን ሰማይ ከፍቶ ከጎኑ መቀመጥን አይቸርህም፡፡ ላንተ ከሰማይ በላይ ቤት እንዳለ ይታይሃል፡፡ ለእኔ ግን አይታየኝም፡፡ መሬት ግን ትታየኛለች፡፡ አንዴ የመኖር እድል ተሰጥቶኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜገነት - ሲዖልበሚባሉ ስፍራዎች አንገናኝም፡፡ ትልቁ ጽድቅና ለሰዎች ፍቅር መስጠት ነው፡፡ ምድራዊ ጽድቅና፡፡

ንብረቴ የምትለው ሁሉ የመሬት ንብረት ነው፡፡ ሃብቴ የምትለው መኮፈሻህ ከመሬት ውጪ የትም ሊሄድ አይችልም፡፡ አንተ እራስህ ከመሬት መኖርን እየተበደርክ ነው፡፡ ቁጥ-ቁጥ ብድርህን አንድ ጊዜ ትከፍላታለህ፡፡ ዕዳህን ሽሽት ከመሬት ልታመልጥ ከቶም ቢሆን አይቻልህም፡፡

ዛሬ ሕሊናዬ ገነትን ፈጥሮልኛል፡፡ አንተን ልጎዳ የማልፈልገው የሕሊናዬን ቅጣት ስለማልፈልግ ነው፡፡ ውስጤ እንዲነድ አልሻም፡፡ በመጠላለፍ ውጣውረድ የባዘነውን እግሬን ሞት ሲያቆመውሩጫዬን ጨረስኩብዬ መዘላበድ አልፈቅድም፡፡ሩጫውን ጨረሰእንድትለኝም አልፈልግም፡፡ ምድራዊ ሃብትህን እየለካህፍትሃ ቀብርየሚያስፈፅም ቄስ አታምጣብኝ፡፡ አንተ እራስህ ይህን ብቻ በለኝ፡- “አፈር ነህና ወደአፈር ትመለሳለህአዎ!ያኔ መሬት ደስ ይላታል፡፡ ሀቁን አንተ እራስህ ታውቀዋለህ፡፡

ድንጋይ በዘመናት ዑደት ወደአፈር ይለወጣል፡፡ ብረት ከአፈር ወጥቶ በአፈር ይበላል፡፡ ዛፎች ከአፈር ተወልደው ወደ አፈር ይመለሳሉ፡፡ እንጨትን ብታከስለው እንኳን አመዱ አፈር ነውና፡፡ ተረዳኝ፡፡ ውሃ እንኳን በአየር ላይ ተንጠልጥሎ ሀይቅን አልፈጠረም፡፡ አንተ ግን ዓለምን የብስ እና ባህር ብለህ ትከፋፍላታለህ፡፡ ምድር ሽንቁር ባልዲ አይደለችም፡፡ ብትሆን ኖሮ ከባህሩ በታች መሬት መኖሩን ትረዳ ነበር፡፡


እኔ ብቻ አይደለሁም አፈሩ፡፡ ሁሉም ነገር አፈር ነው፡፡ የሰው አዕምሮ ከፈጠራቸው ፀረ-አፈር ነገሮች ውስጥ አንዱን ብትጠቅስልኝ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ግን ሁሉም ከመሬት ማሕፀን የተበዘበዙ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው መሬትን የምሻት፡፡ አፈር ነኝና ወደ አፈር መመለሴን እንድታዜምልኝ የምሻው፡፡ ......

ው-ዝ-ግ-ብ-ግ-ብ --- በ-ኄኖክ ስጦታው



((በመጽሐፍ መልክ ተዘጋጅቶ ከተቀመጠ ዓመታት ካለፉት ጽሑፎቼ አንዱ ላይ ቀንጭቤ ጋበዝኳችሁ፡፡፡፡፡))



…….እዛው መንገድ ላይ ነኝ፡፡ በመንደሬ መጋረጃ ጀርባ፤ ከጌጣጌጥ መሸጫ አብረቅራቂ ደጃፍ ስር፤ ከመንደሬ ጀርባ እገኛለሁ፡፡ አሁን በማልወደው የሰው ጫካ ውስጥ ቆሜያለሁ፡፡ የሕሊናዬ እውነታ ይታየኛል፡፡ በሰው ጫካ ውስጥ ብሆንም እታያለሁ፡፡ አላፊው አግዳሚው እርስ በርሱ ከሚተያየው የበለጠ እኔን ያያል፡፡ እያየም ያልፋል፡፡ ዳር መቆሜን መረዳት ችያለሁ፡፡ ውስጥ ሳይሆን ውጪ መሆን አለብኝ፡፡ ከሰዎች መሀል መሆን የምችል አይመስለኝም፡፡ ዳር ላይ ወጥቻለሁ -- ወይም -- መሀሉ ዳር ሆኗል፡፡

ባዶው እጄ ትከሻዬ ላይ ተንጠልጥሏል፡፡ ምንም ነገር አልያዝኩበትም፡፡ እግሮቼ ላይ እንደቆምኩ ቆሜያለሁ፡፡ ጭንቅላቴን የተሸከመውአንገቴ በትከሻዎቼ መሀል እንዳለ አለ፡፡ ከዚህ ውጪ መሆን ያለብኝን ሆንኩ እንጂ በተለየ የፍራቻ ዓይን እንድታይ የሚያደርግ ነገር የለኝም፡፡

አሁን ይበልጥ ከዳር ቆሜያለሁ፡፡ ቅድም ከነበርኩበት ግን ጋት ያህል ፈቅ አላልኩም፡፡ መንገድ ዘግቼ ይሆን? ሰፊ ቦታ ይታየኛል፡፡ በወዲያኛው ተቃራኒ የእግረኛ መንገድ ላይ ግን እግረኞች ይርመሰመሳሉ፡፡ እኔ ከቆምኩበት ቦታ ጋር እኩል መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ለምን እንደጠበበም ግልፅ ነው፡፡ ሰዎች የሚጓዙት በወዲያኛው መንገድ ስለሆነ ጠበበ፡፡ ለምን እኔ በቆምኩበት መንገድ መጓዝ አቆሙ?

ሰዎች ወደበዙበት መንገድ ተሻግሬ ቆምኩ፡፡ ከምጠላው የሰው ጫካ መደባለቅ ፈልጌያለሁ፡፡ እንደፈለግኩት ሆነና መጀመሪያ ቆሜበት ወደነበረው ቦታ አሻግሬ ተመለከትኩ፡፡ በተቃራኒው በሰዎች ተጨናንቆ ታየኝ፡፡ አሁን የቆምኩበት ጠባብ መንገድ ደግሞ ሰፍቶኛል፡፡ ለምን እንደሰፋኝ ተረድቻለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች እኔ በቆምኩበት ማለፍ አይፈልጉም፡፡ …….


ለምን??!! እኮ እኔ ማነኝ???!!!

ሰኞ 17 ጁን 2013

ማነው…. ‘ምንትስ’? ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን


ማነው…. ‘ምንትስ’?
ያው መቸም እኔም እንደሰው
አንዳንዴ÷ አንዳንዴ ብቻ÷ ሕሊናዬን እውነት ሲያምረው
ሰብሰብ ብዬ እማስበው
ቀድሞስ ቢሆን ለኔ ብጤ÷ ለኔ ብጤ የሔዋን ዘር
አዳሜ በኔ ላይ በቀር÷ ለኔ መስክሮ አይናገር”
ብዬ ከልቤ ስማከር
እኔው ከኔው ስከራከር
ተጨብጨ እማብላላው
ያው መቸም እኔም እንደሰው
የሐቅ ራብ ነፍሴን ሲያከው
ልቤ ልቤን ሲሞግተው….
እውነትስ ምንትስ ማነው?”
እያለ ነው፡፡ …..

ቅዳሜ 15 ጁን 2013

ቆቅ እና “ማሽሟቀቅ” . . . ከሰማሁት ያስታወስኩትን ያህል - - ኄኖክ ስጦታው



በ1993 መጨረሻ ይመስለኛል፡፡ በሩሲያ ሳይንስና ባህል ማዕከል ገጣሚና ጋዜጠኛ ነቢይ መኮንን የትምህርት ቤት ትዝታውን አንስቶ ተሞክሮውን ያካፈለበት ላይ ሲናገረው የሰማሁት ነው፡፡ አማርኛ አስተማሪያቸው “ቆቅ” በሚል ርዕስ ሁለት መስመር ግጥም እንዲጽፉ አዘው ነው ነገርየው፡፡ ከተማሪዎቹ መካከል አንዱ አማርኛ ቋንቋ ሁለተኛ ቋንቋ ኖሮ የጻፈው ግጥም ለመምህሩ ሊገባቸው አልቻለም፡፡

 እዚያ ማዶ አነዲት ቆቅ
አየኋትኝ ስታሽሟቅቅ፡፡

ተማሪውን አስነስተው “ማሽሟቀቅ” ምን ማለት እንደሆነ ይጠይቁታል፡፡ መልሱን ሰምተው ማርክ ሊሰጡ መሰለኝ፡፡ ተማሪውም እንዲህ ብሎ መለሰ፡-

“እኔ ለራሴ አማርኛ ለማወቅ እያሽሟቀቅኩ ነው”

ታዲያ የቃሉን ፍቺ በቅርቡ (ቅርቡ ጊዜ ያኔ ነው) እንደተረዳው ነቢይ መኮንን ለዛ ባለው አንደበቱ ተናግሮ ነበር፡-
“ገዢው ፓርቲ እያሽሟቀቀብን እንደነበረ የገባኝ አሁን ነው” ብሎ ታዳሚውን አስፈግጓል፡፡(በነገራችን ላይ ይህች የቆቅ “ግጥም” ከግዜያት በኋላ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “የነገር ጥግ” አምድ ስር  ማንበቤን አስታውሳለሁ)


ነቢይ መኮንን ለታዳሚዎቹ አንድ የግጥም ርዕስ ሰጠ፡፡ “ትዝታ” በሚል ሁለት ስንኝ ግጥም ጻፉ ፤ አለ፡፡ በብርሃን ፍጥነት አንድ ሰው ጽፎ ሰጠው፡፡ አነበበልን፡-

ትዝታሽ ዘወትር ወደኔ እየመጣ
ስለሚያስቸግረኝ ፖሊስ እጠራለሁ፡፡

(አንታራም ግጥም ይሉሀል እንዲህ ነው፡፡)

ሰኞ 10 ጁን 2013

“ነወር”፣ “ነውረኛ”፣ “ነዋሪ” - ኄኖክ ስጦታው

“ነወር”
“ነውረኛ”
“ነዋሪ” 
-
-
-
-

“ነወረ” ማለት . . . “አነወረ፣ አስነወረ፣ አሳፈረ፣ ነውረኛን አደረገ፣ ወይም ተነወረ፣ በነውር ነገር ተከሰሰ” ይለዋል ከሳቴ ብርሃን የአማርኛ መዝገበ ቃላት ፤ በተሰማ ሀብተ ሚካኤል ግጽው የተዘጋጀው፡፡ 

“ነውረኛን” ማለትን ሲፈታው ደግሞ፡- “ነውርን የተመላ፣ ነውርን ከመስራት የማያርፍ(ተነወረ፣ ነውረኛ ሆነ) ” 

“ነዋሪ” ማነው? ካላችሁ . . መልሱ. . . አንድም በመንግስቱ ኅልፈት ጥፋት የሌለበት፣ ሳይለዋወጥ ፣ ጊዜ ሳይወስነው የሚኖር አምላክ ነው፡፡ ሌላም፣ በሕይወት ሥጋ የሚኖር፣ ከቦታው የማይላወስ…. ባለበት ጠንቶ የሚኖር ነው፡፡ ስለዚህም ነው መሰል፣ “ነወር” ስንባል ፣ በተለምዶ “በእግዜር” እንላለን፡፡ 

አሁን አሁን እየተስተዋሉ ያሉት እውነታዎች ስንገመግም አንድ ትልቅ ቁም ነገር ትርጉም አልባ እየሆነ ለመሆኑ ማስረጃ መጥቀስ የማያሻው ጉዳይ ነው፡፡ በማሕበረሰቡ ድንጋጌ (ይህ ድንጋጌ በነዋሪዎች ቅቡልነት /ተለምዷዊ ስምምነት/ አቋም የያዘ ነጥብ ፤ በአብላጫው ተቀባይነት ድምፅ የፀደቀ፡፡) ? 

“ነወር” የሚለውን ቃል ስንበረብረው “ኖር” ከሚለው ቃል በተጨማሪ “ነውር” የሚል ተጻራሪ ፍቺ አቅፏል፡፡ /እንግዲህ እኔ እንደተረዳሁት ነው ትንታኔው/ . . . አንድም ለክብር አንድም ለተግሳጽ የምንጠቀምበት ይህ ባህል ከመጥፋት እንታደገው!

ኄኖክ ስጦታው

ዓርብ 7 ጁን 2013

እግር ኳስና ልጅነት



የኳስ ፍቅር አጠርነቴን የተረዳው ጓዴ ባንድ ወቅት እንዲህ ብሎኝ ነበር፡-
ልጅ ሳለህ አንግል ነበርክ እንዴ?”

አዎ! ልጅ ሳለን እንደዛሬው የመጫወቻ ሜዳ በሊዝ ሳይቸበቸብ በፊት፣ እንደዛሬው ኪስ ቦታዎች ለእነ እንቶኔ በማህበር ሳይመሩበት በፊት፣ የላስቲክ እና የካልሲ ኳስ ብርቅ በነበረበት የልጅነት እድሜያችን፣ እኛ ታናናሾች ለታላቆቻችን የእግር ኳስ ጨዋታ የግብ አንግል እንሆን ነበር፡፡ አሁን ሳስበውካፖርተኒ” /የቆዳ ኳስ/ በሽ ሆኖ፣ እንኳን ሊጫወቱበት አንግል ለመሆን ያልታደሉ የእድሜ ታናሾቻችን እድል አሳዘነኝ፡፡

ኄኖክ ስጦታው- henoksitotaw.blogspot.com