ልጅቱ ቆንጆ ናት መሰለኝ። እንጃ…
ለሥራ የምመላለስበት ቢሮ ውስጥ ተቀምጫለሁ። ስልኬን አውጥቼ ማስታወሻውን ከፈትኩ። (ይህ ማስታወሻ ወሳኝ ግብዓቴ ነው። የዳየሪዬ ዋናው አካል ከዚህ ይጨለፋል። እና ከዚህ ቢሮ እስክወጣ ድረስ ለምን አልቆዝምበትም?
ጸሐፊዋ፤
ጉዳዬ እስኪፈፀምልኝ ድረስ ሰረቅ እያደረኩ ተመለከትኳት። ከንፈሯን ደማቅ ቀይ ቀለም ቀብታዋለች። 【የሊፒስቲክ ጥቅም ከንፈር ከማለስለስና ከማስዋብ አገልግሎት ባሻገር ምንም ጉዳት አያስከትልም?!】የከንፈር ቀለም የውሽማ ሸሚዝ ላይ ከታተመ በቶሎ ታጥቦ የማይለቀው ቀለሙ ብቻ አይደለም። የሚያስከትለው መዘዝም እንጂ። (ለብዙ ቤተሰብ መበጥበጥ ምክንያት ሲሆን ያላሳየ የኢቲቪ ድራማ ይኖር ይሆን?!)
በድንገት ቀና ብላ "ተጫወት" አለችና ወደትየባዋ ተመለሰች። በዚህ ቅፅበት ምን ልጫወት? እቃቃ ልጫወት? ከማይገቡኝ ጨዋታዎች አንዱ ይህ ነው። "ተጫወት" ።
(አንዷ ናት አሉ፤ ፈረንጅ ተጃልሳ ነው። የቋንቋ ነገር አላግባባ ሲላቸው ሁለቱም ዝምታን መርጠው ይቀመጣሉ። ዝምታው እንዴት ይሰበር?! በመጨረሻ እርሷ እንዲህ አለች አሉ፦ "Play" ) ተጫወት፤ ተጫወቺ፤ እንጫወት፤ ፕሌይ …
የጸሐፊዋ ዓይን ያምራል። ፀጉሯ ያምራል። ፊቷ የኦቫል ቅርፅ አለው። ለብቻዬ ፈገግ አልኩ። የፊቷ ቅርፅ ከትላልቅ አይኖቿ ጋር ተዳምሮ ጥንታዊ የብራና ላይ ስእል አስመስሏታል። 【ያሰብኩትን ከፊቴ ላይ አንብባ ይሆን?!】ሰረቅ አድርጌ አየኋት። እሷ'ቴ፤ አንዳቀረቀረች ነው።
በምን ፍጥነት ከትየባ ወደ ጥፍር ሙረዳ አንደተሸጋገረች አላውቅም። ጣቷ ያምራል። ውበቱን ግን የጥፍሯ ርዝማኔ ያደበዘዘው ይመስላል።
"ተጫወት" እስክትለኝል ድረስ አፈጠጥኩባት። ይገርማል። ጥፍሯ ላይ ተመስጣለች።
ጥፍር!
የጥፍር እድገት ፍጥነትና፣ የወንድ ልጅ ጡት ሁሌም ይገርሙኛል። ጥፍርስ ይደግ፣ ይመንደግ። ቢያንስ ለሴቶች የውበት ሳሎን ባለሙያዎች የገቢ ምንጭ መሆኑን እያየን ነው። (ኧረ የማይገባኝ ነገር ፤ "እጅና እግር እንሠራለን" የሚሉ ፀጉር ቤቶች ከጥፍር የዘለለ አንዳች ጥበብ ላይ ደርሰው ይሆን?!) ። ከደረሱ ድንቅ ነው። ካልደረሱም እሰየሁ። እኔም ያልደረስኩበትን በነፃነት እንድናገር በር ከፍተዋል። ውሻ በቀደደው ጅብ እንደሚገባ ፈሪ አበዎች ከገለጹ ዘንዳ እነሆኝ በረከት ለክፉ… የወንድ ልጅ ጡት ጥቅም ምንድነው?! አጥብቶ ሊያሳድግበት… ወይስ ራሱ ጠብቶ ሊመነደግበት?!
ጸሐፊዋ፣
በዚህ ዓመት በሀቀኝነት ያየሁዋት ባትኖርም፣ ሰርቄ ካየኋቸው ሴቶች ውስጥ ግን "የአንበሳውን ድርሻ" ትወስዳለች። አሁን ከጥፍር ሙረዳ ወደ ወደትየባዋ ተመልሳለች። ጸሐፊዋ።
ጆሮዋን!
ኧረ ጆሮ! በአንድ ጆሮዋ ላይ ብቻ ስንት የጉትቻ ማንጠልጠያ ብስ እንዳለ ልቆጥር ሞክሬ አቅም አጣሁ። እውነት ለመናገር ያልተበሳው የጆሮዋ አካል ቢኖር እርሱም ተበሥቷል።
የጆሮ ጥቅም አናሳ እንደሆነ የገባኝም ዛሬ ነው። (አንድ ግጥም ትዝ አለኝ። ያኔ የጋዜጠኝነት ትምህርት ስንማር የቃላት ፈጠራን አስመልክቶ አንዱ መምህር "ልጂቱ ፣ የዘመነቺቱ " የሚለውን የደበበ ሰይፉን ግጥም በምሳሌነት አጣቀሰና የራሳችሁን ግጥም በፈጠራ ቃል ተጠቅማችሁ ጻፉ ሲል አዘዘን። ጫማዋን ጨምታ፣ ሱሪዋን ሶርታ፣ ቦርሳዋን ቦርሳ፣… ቲሽ! ሁሉንም አዲስ ቃላት ደበበ ሰይፉ አደብይቶታል። አንዷ ክላስ ሜታችን ግን ለምሳሌነት ያልቀረበ ምርጥ የቃላት ፈጠራ ይዛ ቀረበች፦
"ጆሮዬም ይጆርር፣ እጅ እግሬ ይጀግረር
ጆሬዬም ይደንቋ፣ ከደነቋ አይቀር…"
አለችና ተሜን በፈጠራዋ አስደምማ እርፍ!!"
መምህራችን ግን አልተዋጠለትም። ወይ ደበበ ፣ ደበበ ሸትቶት አልዋጥ ብሎት ይሆናል እንጃ፤ የተገጀረረውን የቃል ፈጠራ ገርጅጆት አለፈው። ቺኳ ገጣሚት ተቆጫበረች። እናም አለፈ። እንኳን አለፈ።
ዛሬ ያየሁት ጆሮ የተበሳ እንዳልሆነ ሳስበው ታወሰችኝ። በርግጥም ጆሮ ይደነቋል! ! እጅ እግርም ይጀገረራል!!
የቢሮዋ "ጸሐፊ" ተጫወት የምትለኝ መስሎኝ ቀና ብዬ አየዃት። ኤጭ። "ተጀግርራለች፣ አልያም ደንቁታለች…