እኔ ዛሬ ምኒልክን ስለምን አደንቀዋለሁ ?
ከቶ ለምን አብዲስ አጋን - ጐበናን አወድሳለሁ ?
ስለምን ገረሱ ዱኪን - ካዎ ጦናን አነሳለሁ ?
ከእንግዲህ ለአያ በላይም - ለቋረኛውም አልዘፍንም
ለሰሜኑ ልጅ አሉላ ያማረ ቅኔ አልቀኝም
ኃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ በእርስዎ ስምም አልፎክርም
እኔ የገብርዬ ባርያ! የአባ ጅፋር ልጅ አልልም !!
አልልም! ከቶም! አልልም!
አይኔን ወደፊት ነው እንጂ ወደኃላዬስ አልጥልም!!
ከእንግዲህ ኩራት ፍለጋ አልሄድም ወደትላንቱ
ከገዛ ትውልዴ መሀል ተገኝታለች አንዲት ‘ብርቱ’
ለምን ወደኃላ ሄጄ ሙታን እቀሰቅሳለሁ?
አዲስ ኮከብ ስትወለድ በአይኔ ብረቱ አይቼአለሁ!!
ዛሬማ ልቤን ሞልቼ ፣
ዛሬማ ታሪክ አይቼ ፣
የግንቦት ጭጋግ ደመናን፣ ጨለማን የተቃወመች
ይኸው አዲስ አበባ ላይ አዲስ ኮከብ ተወለደች
ሎሚ መቼም መድሃኒት ነው፣ ማንጐም - ትርጐም ደስ ይላል
ግና ከፖም - ከመንደሪን ብርቱካንን ያህል የታል ?
የታል? የታል? የታል? የታል?
ከስንቱ ጥሬና ብስል ብርቱካንን ያህል የታል?