፩
ያው እንደ ልማዴ፣ በፅሞና ሳለሁ፣
ዝምታን ለብቻው ፣ ርጋታን ለብቻው፣ እያዳመጥኩ ሳለሁ—
የመቃብሩ በር ሲንኳኳ እሰማለሁ።
አንዳንዴ ስመሰጥ ፣
ትዝታችን እንዳይሞት፣ የቀበርኩት እለት
የአንድ ቀን ድምር፣ የአሃዝን ግዝፈት
ገንኖ ይታየኛል፣ ገና ሳልል ሁለት።
አንድ!
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ሲደመር ‘ከዕለታት’
አንዳለኝ እያልኩኝ፣ ዝም ብሎ ማስላት።
አንድ!
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ የተዋወቅንበት።
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ የተጣላንበት።
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ ተሳስመን ነበር።
ምራቅሽን ቀምሼ፣ ምራቄን ቀምሰሽው፣ "አቤት መጣፈጡ" ማለታችን ሳይቀር፣
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ ካንዱ ጋር ሲደመር፣
ደግሞም በሌላ ቀን፣ ተጋጭተን በነገር
ማሩ ምራቅሽን፣ ተፍተሽብኝ ነበር።
አንድ!
፪
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ እንዲህ ለብቻዬ፣
አንድን አሰላለሁ፤ አንድ አለችኝ ብዬ።
አንድ ዝምታ ነው። አንዱ ነው ርጋታ
አንዱ ካለአንዱ፤ አይቆምም ለአፍታ ።
እና።
ርጋታን ሳዳምጥ፤ ዝምታን ሳናግር ፣
ከመቃብሩ ቤት፣ ይሰማኛል ጩኸት፣
‘ክፈት! ክፈት! ’ የሚል…
‘ክፈት ይህን በር!’
ያንቺ ድምፅ ነበር።
ድምፅሽን ስሰማ ፤ "ክፈት" ስትይ "ክፈት"
ያስታወሰወኩት ነገር
ካቅሜ በላይ ሆነሽ፣ "ችግሬ" ያልኩሽ እለት
‘ከዕለታት አንድ ቀን’፤ ላንቺ መቀበሪያ
ጉድጓዱን ማስኩበት።
ምክንያቱም፦
አንቺን ከዝንጅብል፣ ያቆራኘ ምስጢር
አፈር ነው ህይወትሽ ፣ አትሞችም በቀብር።
አንቺ የኔ ችግር!
ባክሽ ፣ባክሽ ግቢ፤ "ምሳጤ" ና ውጣ
ሁሉም ይዘነጋል፣ ችግሬ ስትመጣ።
______
ኄኖክ ስጦታው