ልጥፎችን በመለያ HENOK'S PAD ግጥሞቼ በማሳየት ላይ። ሁሉንም ልጥፎች አሳይ
ልጥፎችን በመለያ HENOK'S PAD ግጥሞቼ በማሳየት ላይ። ሁሉንም ልጥፎች አሳይ

ማክሰኞ 14 ማርች 2017

አባይ ጠባብ መንገድ

(ኄኖክ ስጦታው)

የወንዝ አገሩ መነሻው፤ የወንዝ አገሩ መድረሻው
ወንዝ የሌለበት አገር ነው፣ መውጫ መግቢያው የጠፋው¡
*
የወንዞች ህብር ውጤት፤ የውኆች ስብስብ ጥምር
አባይ ፀሎቴን ስማ፣ ልንገርህ አንዳች ምስጢር።

ወደሄድክበት ውሰደኝ፤ እኔም አፈር ነኝና፣
ከአገሬ አንዴ ከወጣሁ፣ ሌላ ወንዝ አላጣምና።
*
አባይ ፀሎቴን ስማ፣ ከነአፈሬ አብሬህ ልውጣ
ሺህ ቢጎድል ተገድቦ፣ ሺህ ቢሞላ የሚቆጣ
ወንዝ ብቻ እንደሆነ፣ አውቃለሁኝ፤ ታውቀዋለህ!
አብረን ታስረን፣ ነፃ እንውጣ።

ሐሙስ 5 ጃንዋሪ 2017

“የፅኑነት ሥሪት”

(ኄኖክ ስጦታው) 

(ሲያጣሙት ሚጣመም… ሲያቀኑት ሚቀና)
የቆመ ቢመስልም — ፍፃሜው ግን ገና።

ግትር ነው የሚባል — ላመነበት ፀንቶ
ፍፃሜው ላይ ቆሟል — መልመጥመጡን ረቶ።

የ"ፅኑነት'' ትርጉም― ለዚህ ዘመን ድርሻ
ለሟችም ለኗሪም…
አለመታመን ነው — መታመን እያሻ።

ሐሙስ 23 ጁን 2016

ውጣ—ውረድ

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)

“ነበር” ላይ ሊያበቃ፣ የ“ነው” ባይ  አቅጣጫ፤
ከ"ነው" እና "ነበር"፣ የታል የኔ ምርጫ?


መድረሻው መነሻ
          መነሻው መድረሻ
ጠይቅ “የታል” ብለህ… “የታል ውጣ—ውረድ”?
(ሕይወት መሰላል ነው፤ የእርብራብ መንገድ!)

የጥያቄ ምላሽ፣ በምጥ ላይወለድ
“እውነት” ካስጨነቀህ፣
  በስንዝር ቦታ ላይ፣ ጋት ጨምር… ተራመድ
መልሱን ተወውና፣ መጠየቅን ውደድ
                    ውጣ
           ወይም
ውረድ!

ሐሙስ 9 ጁን 2016

ፀሐይ

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)
የልቤን መሻት ለማድረስ፣ ውጣ ውረዱ ሲበዛ 
የመንፈስ ብርታት ልትሆነኝ፣ ሙቀቷ ሕይወት ሊነዛ
ፀሐይ ምድር ደርሳለች፣ ፍኖተ ሃሊብ ተጉዛ፡፡
ዝለቂ ከዋሻው ብርታቴ፣ ስንፍና ሰበቡን ይጣ
“ፀሐይ ልሞቅ ነው” በማለት፣ እኔም ከዋሻው አልውጣ፡፡

እሑድ 8 ሜይ 2016

ተራማጅ እሳቤ ፺፩

(ኄኖክ ስጦታው)

ባለሶስት ፉርጎ ነው፤ ይጓዛል ባቡሩ፤ ቆየሁ ተሳፍሬ 
            የኋላኛው – ትላንት፣
            የፊተኛው – ነገ፣
            መሀለኛው – ዛሬ …
*
የታለፈ ትላንት፣ ያልተኖረ ነገ፣ ሃሣብ ውስጤ ሰርጎ
(ወጥሮ ይዞኛል)
         ፊት ላይሆን—ወይ ኋላ፣ መሐለኛው ፉርጎ።

ረቡዕ 9 ማርች 2016

ተነሳ ተራመድ - ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ

ተነሳ ተራመድ
---------
"ተነሳ ተራመድ! ክንድህን አበርታ!
ላገር ብልፅግና ለወገን አለኝታ!!"
እምም…
*
መነሻችን መቼ ጠፋ?! ለመበልፀግ ስንገሰግስ
ተፈጥሮን ፊቷን አዞረች። እንዴት ወደኛ እንመልስ?!
*
"ተነሳ ተራመድ! ክንድህን አበርታ!
ላገር ብልፅግና ለወገን አለኝታ!!"
*
"ተፈጥሮ የግብአት ምንጭ፣ ተፈጥሮ የእድገት አለኝታ
ኢንዱስትሪ ነው መርሃችን፤ ድህነት ድባቅ ይመታ!!"
*
"ተነሳ ተራመድ! ክንድህን አበርታ!
ላገር ብልፅግና ለወገን አለኝታ!!"
*
የኃያላን ተሞክሮ ውጤት፣ የእድገት ጉዞ ትግበራ
ተፈጥሮን ሚዛን አስቶ፤ ለዜጎች ፍላጎት ሲሰራ
ዋስትና በገንዘብ ተለካ፤ ብልፅግና በሸቀጥ ተመራ…
ውራ የመሆን ጨዋታ፣ አይመራምና በጭራ…
ተቀበል!
*
"ተነሳ ተራመድ! ክንድህን አበርታ!
ላገር ብልፅግና ለወገን አለኝታ!!"
*
ወደፊት መጓዝ እንዳለው፤ ወደኋላም እንመለስ
ተፈጥሮን ማጥናት አይበቃም፣ ኗሪ ጎጆውን ሲቀልስ።
*
"ተነሳ ተራመድ!
ክንድህን አበርታ!
መጥረቢያ ነው ጠላትህ፣ አንተን በድርቅ የመታ!!!
"ተነሳ" ሲሉህ ተነሳ!
አምባገነን ነው ተፈጥሮ፣
"እንዳያልፉት የለም" ከማለት፤ የእልቂት ታሪክ ሞነጫጭሮ
ወደኋላ እንመለስ፣ እርቅ እንፍጠር ከተፈጥሮ
የደን ታሪክ ይሰራ፣ የደም ታሪክ ተሽሮ።
*
ተፈጥሮ ለጨቆኗት ጨቋኝ ነች፤ 
Sep 20, 2015 1:42:12 AM

ሐሙስ 25 ፌብሩዋሪ 2016

አዳም… (ኄኖክ ሥጦታው ናሁሰናይ)

አዳም…
(ኄኖክ ሥጦታው ናሁሰናይ)


"ጥፋት"፣ "ታዛዥነት" …
ቢጋጩ ከድንጋይ
                "ተቃጠልኩኝ" አትበል…
                 እሳት ፈጥረው ብታይ።
*
ፍላጎቱን ሳይኖር፣ "ሕግን" ያከበረ፣
በተጻፈው እንጂ፣ ራሱን መች ኖረ?!
*
አዳም ሰው አትስማ፣ ከትዛዝ ላይወጣ
"ሕግ ጣሰ" ይበል፤ "በበላው ተቀጣ"
የኖርከውን ሳይኖር፣ ያስብ ምን እንዳጣ!
*
አዳም ተለመነኝ፤ አንተ ኑረህ ብላ…፣ ቅጣት ምናባቱ

ያልበላው ይታዘዝ… ሕግን ማክበር "መብቱ…"
*
አዳም በአፈርህ፦
ብላ… ደግመህ ብላ… የሕግ አጥር ይፍረስ
"አምላክ ይጠራኻል"፤ ክልከላውን ስትጥስ!

ዓርብ 19 ፌብሩዋሪ 2016

ተራማጅ እሳቤ ፵፯

( ኄኖክ ሥጦታው ናኁሰናይ )

ውሃ…
*
ከፍታን መርጦ ሲጣበቅ፣ በረዶ ሆኖ ሲደድር
ውሃም ይወጣል ዳገት፣ ይወርዳል ሙቀቱ ሲንር።
*
በረዶ አቅላጩ ሙቀት፣ በድን አካል ካፈረሰ
ነዲድ ያገኘው አለት፣ ቀልጦ ቁልቁል ከፈሰሰ
መጠጠርስ እንደውሃ ፣
መቅለጥ …
መትነን…፣
 ሽቅብ መውጣት… ቁልቁል መውረድ…
(ቅዝቃዜ ፅሞና ነው። ርጋታን ለአፍታ ልውደድ)
ራስ…
ለራስ…
ከራስ…  ጋ
ጠምቶኛል ዘልቆ መዋኻድ
ከመትነን ከፍታ በታች፦
እንደበረዶ ጠጥሮ፣ ደግሞ እንደ ዥረት ለመውረድ።
*
ውሃ…
ወንዙ መንገድ ቀይሯል፣ የድርቅ ዱካውን ትቶ
ወዴት ወርዶ አለቀ? ከምድር ሰርጎ ገብቶ?
በሰማይ መንገዱ ተጓዘ? በትነት ሽቅብ ወጥቶ?
*
ራሴን ተጠማሁ…

በደረቀው መንገድ ላይ፣ ቆሜ ነበር ሃሳብ ጠምቶኝ
አሁን አቅጣጫው ሲገባኝ፣ የወንዙን መንገድ መረጥኩኝ
ወደሄደበት ብሄድ ነው፤ ጥቂት ውሃ የማገኝ።

ጠምቶኛል…

ሐሙስ 8 ጃንዋሪ 2015

‘ከዕለታት አንድ ቀን’ (ኄኖክ ስጦታው)




ያው እንደ ልማዴ፣ በፅሞና ሳለሁ፣
ዝምታን ለብቻው ፣ ርጋታን ለብቻው፣ እያዳመጥኩ ሳለሁ—
የመቃብሩ በር ሲንኳኳ እሰማለሁ።

አንዳንዴ ስመሰጥ ፣
ትዝታችን እንዳይሞት፣ የቀበርኩት እለት
የአንድ ቀን ድምር፣ የአሃዝን ግዝፈት
ገንኖ ይታየኛል፣ ገና ሳልል ሁለት።

አንድ!
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ሲደመር ‘ከዕለታት’
አንዳለኝ እያልኩኝ፣ ዝም ብሎ ማስላት።

አንድ!
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ የተዋወቅንበት።
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ የተጣላንበት።
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ ተሳስመን ነበር።
ምራቅሽን ቀምሼ፣ ምራቄን ቀምሰሽው፣ "አቤት መጣፈጡ" ማለታችን ሳይቀር፣
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ ካንዱ ጋር ሲደመር፣
ደግሞም በሌላ ቀን፣ ተጋጭተን በነገር
ማሩ ምራቅሽን፣ ተፍተሽብኝ ነበር።

አንድ!


‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ እንዲህ ለብቻዬ፣
አንድን አሰላለሁ፤ አንድ አለችኝ ብዬ።
አንድ ዝምታ ነው። አንዱ ነው ርጋታ
አንዱ ካለአንዱ፤ አይቆምም ለአፍታ ።
          እና።
         ርጋታን ሳዳምጥ፤ ዝምታን ሳናግር ፣
         ከመቃብሩ ቤት፣ ይሰማኛል ጩኸት፣
‘ክፈት! ክፈት! ’ የሚል…
‘ክፈት ይህን በር!’
ያንቺ ድምፅ ነበር።
ድምፅሽን ስሰማ  ፤ "ክፈት" ስትይ "ክፈት"
                           ያስታወሰወኩት ነገር
ካቅሜ በላይ ሆነሽ፣ "ችግሬ" ያልኩሽ እለት
‘ከዕለታት አንድ ቀን’፤ ላንቺ መቀበሪያ
                           ጉድጓዱን ማስኩበት።

ምክንያቱም፦
አንቺን ከዝንጅብል፣ ያቆራኘ ምስጢር
አፈር ነው ህይወትሽ ፣ አትሞችም በቀብር።

አንቺ የኔ ችግር!
ባክሽ ፣ባክሽ ግቢ፤ "ምሳጤ" ና ውጣ
ሁሉም ይዘነጋል፣ ችግሬ ስትመጣ።
______
ኄኖክ ስጦታው

ማክሰኞ 12 ኖቬምበር 2013

*የሆድ አምላክ __~ኄኖክ ስጦታው

*የሆድ አምላክ __~ኄኖክ ስጦታው

ለማግኘቱ፣ ለማጣቱ
ለመውዛቱ፣ ለመንጣቱ
“እንጀራ” ነው ለሀበሻ፣
“እህል ውኃ” ምክንያቱ፡፡

ሕልውናው የጸናበት፣
መወጣጫ መሰላሉ
“የሆድ አምላክ” ተቀብቷል፣
 ይገለጣል “በእህሉ!”
ለረገጠው መሬት ሳይሆን፣
ከእግሮቹ በታች ላለው
ለማይነካው ሲንጠራራ፣
ለሰማይ ነው የቀረበው፡፡
“እህል ውኃ” በሀበሻ፣
አምላካዊ ክብር ለብሶ
“በጡር አለው” ተሰቅዞ፣
 “በክቡር ነው” ተወድሶ
ተሰጥቶ ነው ለሰማያት፣
የሚዘራው ምድር ታርሶ
“የሆድ አምላክ” ካለበቱ፣
 ከእኛው ሀገር ምግብ ነግሦ፡፡

*        *        *

የት ነው ያለህ የሆድ አምላክ?!
ላነገሡህ ምን አደረክ?!
ላመለኩህ መች አጠገብክ?!
ምዕመንህ ጠኔ ጥሎት፣ የሚበላው ተቸግሮ
በእርጥባን መኖር በቅቶት፣ ሀገር ላገር ተዟዙሮ
“የሆድ አምላክ” እውነት ካለህ፣
እስቲ ይጥገብ ለዘንድሮ?!?
____________

2003 .
ኄኖክ ስጦታው፣ -ሞት የግጥም መድበል

እሑድ 10 ኖቬምበር 2013

“የቱባ ክር ጫፎች” ~~ኄኖክ ስጦታው

የቱባ ክር ጫፎች

________

ጥምጣመ - ውሥብሥብ፣ ሕይወት እንደ ድውር፤

ጫፉን ለመያዝ ነው፣ የሰው ልጅ የሚጥር፡፡

የተጠቀለለው. . . መፈታት ሲጀምር

መልሰህ ጠቅለው፤ ተተብትቦ እዳይቀር፡፡

የለውም ጫፍ ብሎ፣ ቆርጦ የሚጀምር፣

አራት ጫፍ ያገኛል፣ ክሩን ሲተረትር፡፡

ጫፍ መያዝ በጥሶ፤ በጥሶ መቌጠር

ኢትዮጵያን አርጓታል፤ የብዙ ጫፍ ሀገር፡፡

ሞልቷታል እምዬ፤ አያልቅም ቢቆጠር፣

አያሌ ጫፍ ወራጅ፣ ዕልፍ ቆርጦ - ጀምር፣

ተብትቦ የሚተው፣ ደህነኛውን ድውር፤

ለመፍታት ሲነሳ፣ ጠቅልሎ ማይጀምር፡፡

____________

12/10/2004.
~~ኄኖክ ስጦታው፣ -ሞት የግጥም መድበል

ረቡዕ 30 ኦክቶበር 2013

የተዘጉ አንደበቶች ______(ኄኖክ ሥጦታው)

የተዘጉ አንደበቶች
______(ኄኖክ ሥጦታው)

1ኛው ቀን
ዓያት - ዓየችው
ዘጋት - ዘጋችው !
ቤቱ ገባ፤ ቤቷ ገባች
በሩን ዘጋ፤ በሯን ዘጋች!
መሸ ፤ ነጋ
2ኛው ቀን -
እሱም ወጣ፤ እሷም ወጣች
እሱም ዓያት፤ እሷም ዓየች
ኮራ...ኮራች፤
እንዳላያት፤ እንዳላየች
ሄደ...ሄደች፡፡

3ኛው ቀን-
4ኛው ቀን-
5ኛው ወር-
6ኛው ወር...
ለውጥ የለም፤ ለውጥ አለ፤
ምንም የለም፤ ምንም አለ!
በተዘጉ አንደበቶች፣
ሊግባቡበት የቀለለ
የቀየሱት መንገድ አለ፡፡
በዝምታ ሚግባቡበት...
ፈጥረው ነበር
አንድ ነገር
ለሌላ ሰው ’ማይነገር፡፡
_____________________

ኄኖክ ሥጦታው - "-ሞት" የግጥም መጽሐፍ

አርዝም አደንድን ______(ኄኖክ ሥጦታው)


አርዝም አደንድን
______(ኄኖክ ሥጦታው)

ስሜት ልጓ በጠሰ፤ አስማት ዋለ ለምንዝር
በአርዝም አደንድን ድግምት፣ አቅም ተሰዋ ለግትር፡፡
መሰዋቱ ባልከፋ፣ ለዚያችኛዋ (‹‹ቂንጥር››)
አስማት ስሜት ታቅፎ፣ ካሸነፈው ያስማት ቀመር
ወንድነቱን ክዷልና ቀድሞውንም ወንድ አልነበር፡፡
______________
23-08-2005.

ኄኖክ ሥጦታው - "-ሞት" የግጥም መጽሐፍ

የቆሻሻ ወደብ ______(ኄኖክ ሥጦታው)

የቆሻሻ ወደብ
______(ኄኖክ ሥጦታው)

የስልጣኔ ዝቅጥ መጣያ፣ የጥራጊያቸው ወደብ ነን፤
የጣሉትን የምንለቅም፣ ካልጣሉልን የምንለምን፤
ፈረስም ነን ለነዚሁ፣ እንዳሻቸው የሚያደርጉን፤
ካሻቸው የሚለጉሙ፣ ካሻቸውም የሚጋልቡን፤
ካሻቸው የሚጭኑ፤ ካሻቸውም የሚዋጉብን፡፡

የገደልም ማሚቶዎች ነን፤ የጮኹትን የምንደግም፤
በለኮሱት ስንቃጠል፤ በቃ ሲሉን የምንከስም!

በስማ በለው ተብትበውን፣በቁሳቸውእንዳጨቁን፣
ስንዳክር ዳናው ጠፍቶን፣ እስከ መቼ እንዘልቃለን!?

ሲጋልቡን ስንጋለብ፣ የጫኑንን ስንሸከም፤
የጣሉትን ስንለቅም፣ የሚሉትን ስንደግም!
እንደ አራስ ልጅ በሰው ጀርባ
እስከ መቼስ እንዘልቃለን!?
እስከ መቼስ እንከርማለን!?
______________
መስከረም 2005.

ኄኖክ ሥጦታው - "-ሞት" የግጥም መጽሐፍ

ሐሙስ 24 ኦክቶበር 2013

አሸባሪው ማነው? --በኄኖክ ስጦታው

አሸባሪው ማነው?

በቀይዋ ብዕሬ፣ የከተብኩት ሁሉ፤
አንዴ ከኔ ወጥቷል፣ እስቲ ተቀበሉ።

እውነትን ሊናገር፣ አፉን የከፈተ፤
ንቅዘቶችን ነቅሶ፣ ድክመትን ያተተ፤
በዚህች ጉስቁል አገር፣ ምሣር በበዛባት፤
በሚቀጥለው ቀን፣ ለርሱ ወየውለት!!

ለምን!?
ፈራጅ ነው ዘራፊ፤ ተዘራፊው ሌባ
ትችት ያሳስራል፤ በማሸበር ደባ

የታል!?
"ነፃ አውጪው" የታል!?
ሆኗል ጨቋኝ መሪ
"ለምን" ባዩን ፈራጅ፤ "በሽብር ፈጣሪ"
ደፍሮ የሚናገር፣ ዘብጥያ ታሣሪ።

ማነው!?
ፀረ—ሠላም ማነው!? ማነውስ ነፃ አውጪ!?
አሸባሪ ማነው!? ማንኛው ነው ቀጪ!?
ወንጀለኛው ማነው!? ማነውስ ታሳሪ!?
ፀረ—ሠላም ከሣሽ፣ እራሱ መስካሪ፤
"ለምን" ባይ ተከሣሽ፣ ላገር ተቆርቋሪ!!

2004 ዓ. ም.


(ከ "ሀ-ሞት" የግጥም መጽሐፍ/ በኄኖክ ስጦታው)

ተጠየቁ ዳኞች! ~በ ኄኖክ ስጦታው —

ተጠየቁ ዳኞች!
  
~በ ኄኖክ ስጦታው —

ችሎት እንዴት ዋለ?!
          ማን ተፈረደበት?!
          ማንስ ተቀጠረ?!
ይህ ሁሉ እስረኛ ወኅኒ የታጎረ
በፍርዱ ረካ?! ወይስ ተማረረ?!
ተጠየቁ ዳኞች! መልሱልኝ እውነት….
የነገር ግራ ቀኝ፣ የምትመረምሩት
ግዜው ምን ያህል ነው?! ቀናት ወይስ ሳምንት?!
ዓመት ሁለት አመት?!
ሰምታችሁ ምትፈርዱት?!
ይግባኝ!
ይግባኝ!
ይግባኝ!
ይግባኝ ደረጃ አንድ፣ ይግባኝ ከፍተኛ
ይግባኝ ዐቃቤ ሕግ፣ ይግባኝ ሰሚ ዳኛ!
ተጠየቁ ዛሬ፣ መልሱልኝ እውነት
ግዜ አላችሁ ወይ ሰምታችሁ ለመፍረድ?!
ምን ያህሉ ሰው ነው ወኅኒ የተጣለ?!
ሰሚ ጆሮ አጥቶ ፍትህ ያልታደለ፡፡
ባላጠፋው ጥፋት በሀሰት ውንጀላ
ክርክር ረትቶት የአግቦ ፍተላ
“ይግባኝ!” ብሎ ሲጮኽ፣ “ልስማኽ” የማይሰኝ
ምን ያህል ነፍስ ነው፣ ወኅኒ ውስጥ የሚገኝ?!
ይግባኝ!
ይግባኝ!
ይግባኝ!
ይግባኝ ደረጃ አንድ፣ ይግባኝ ከፍተኛ
ይግባኝ ዐቃቤ ሕግ፣ ይግባኝ ሰሚ ዳኛ!
  
“ሀ -ሞት”  የግጥም መጽሐፍ
 ኄኖክ ስጦታው —