፠
፠
ውሾቼን ገደሏቸው! መርዝ የተቀባ ስጋ ሰጥተው ውሾቼን ገደሏቸው፡፡
ቀባሪዬ፣ መግደል እንጀራ በሆነበት አገር እንደመኖር ውስብስብ ነገር እንደሌለ ተረዳሁ፡፡ “ውሾች ለጤና ጠንቅ ናቸው” በሚል መርዝ አበሏቸው፡፡ ውሾች የመኖር መብት አላቸው፤ ፍጥረት ናቸውና፡፡ ባለቤት የሌላቸው መሆናቸው ግን አስገደላቸው፡፡ ልከላከል ሞክሬ ነበር፤ እንዳይበሉት ለማድረግ ጥሬ ነበር፤ ገዳዮቹን ለማባረር ጥሬ ነበር፤ ግን ብቻዬን ነኝ! ውሾቼኮ የበጋ ወዳጆቼ ናቸው፡፡ ይህ ክፉ ክረምት ውሾቼን ዳግም እንዳላያቸው የመሰናበቻ ጊዜ ሆነ፡፡ አለቀስኩ፣ ጮህኩ፣ ጉልበቴ ደክሟል፡፡ በጎረምሶች እጅ እግሬ ተይዟል፡፡
የመንደሪቷ ነዋሪዎች የውሾቹን አሟሟት በማየት ለራሳቸው ደስታን ሲፈጥሩ እውነቴን ነው የምልህ ይበልጥ ጠላኋቸው፡፡ ለዚህች መንደር ነዋሪዎች የሞት ስቃይ ማየት የሚፈጥረውን ደስታ ማጣጣም አዲስ አይደለም፡፡ ሰዎች የሞት ቅጣት ይበየንባቸው የነበረበት ቦታ እዚህ መሆኑን እወቅ! ከብዙ ዓመታት በፊት የሞት ፍርደኞች በአደባባይ ይሰቀሉ እንደነበር ቦታ ላይ ነኝ፡፡ ይህ ታሪክ የማይረሳው ሰው በአደባባይ በሞትና በህይወት መሀል በነፍስ ከስጋ ለመለየት የሚደረግ መንፈራገጥን ምንነት የተገለጠበት ቦታ ነው፡፡ ይግባህ! የማወራው ድሮ ማነቂያ ስለነበር ስፍራ ነው፡፡ በክር አንገትህ ታንቆ መሞት ምን እንደሆነ የምታይበት ስፍራ፡፡ መንደሬን ያወካት መሰለኝ፡፡ ሞትን ወደህ ሳይሆን ተገደህ መጎንጨት ሰውን ሳይሆን የሞትን ክብር መንካት ነው፡፡
መርዝ የተለወሰ ስጋ የበሉ ውሾች ሲዳከሙና ለሀጫቸውን ማዝረክረክ ሲጀምሩ ቦት ጫማና የጎማ ጓንት ያጠለቁ ገዳዮች በእጃቸው የያዙትን የብረት ማነቂያ አንገታቸው ውስጥ እየከተቱ አነቋቸው፡፡
ተፈጥሮ በህይወት ጉዞ ውስጥ ከለገሰቻቸው ሞቶች የበለጠ የሰዎች ፈጠራ ውጤት የሆነ የመግደያ ብልሃቶች ዘግናኝ ናቸው፡፡ ምስኪን….፣ ውሾቼ ሰዎችን ማመናቸው አሳዘነኝ፡፡ ትላንት በአደባባይ፣ ሊያውም በጠራራ ፀሐይ ጎዳና ላይ ሲተኙ ኮቴም ሆነ የመኪና ጥሩንባ አይቀሰቅሳቸውም ነበር፡፡ ሰው በመኖሩ ብቻ መኖር የቻሉ አድርገው የወሰዱ ይመስለኛል፡፡ ሰው ሳይኖር መኖር የሚሳነው ሰው ብቻ መሆኑን አውቀዋለሁ፡፡ ውሾቼ አለቁ! እንቁራሪቶቼም ለህፃናት መጫወቻ እየሆኑ ነው፡፡ ከሞት የተረፉትን በጋ ላይ አልሰማቸውም፡፡ የውሾቼ በድን መኪና ላይ ሲጫን የሞት ትርኢቱ ተደመደመ፡፡ የመንደሬ ለቅሞ አዳሪዎች ወደሬሳነት ተለውጠዋል፡፡ ገና ለገና አብደው ሰው የጎዳሉ በሚል ፍራቻ የመኖር መብታቸውን አጡ፡፡ አንድ ቀን እኔም `ጭራቅ” ሆኜ ደማቸውን እንዳልመጥ ይገድሉኝ ይሆናል፡፡ እጅ እግሬን ጠፍረው ይዘውኝ የነበሩ ወጣቶች ለቀውኝ ሄደዋል፡፡ ምሽት ብርታት እስቲሰጠኝ ባለሁበት መቆየትን መረጥኩ፡፡
ቀባሪዬ፣ ይህች የሰዎች ታንቆ መሞቻ መንደር ከስሟ ጀምሮ የብቻዬ እንጉርጉሮ እንዲያገረሽ አደረገብኝ፡፡
አንቺ ዶሮ ማነቂያ የሆንሽው ዶሮ ማነቂያ ሆይ! ዛሬ ምኒሊክ አደባባይ የሆነው ስፍራሽ ላይ የነበረው ትልቅ ዋርካ ይታየኛል፡፡ ያን ጊዜ አለመፈጠሬ ዋርካሽ በፈረሰኛው ምንሊክ ሃወልት ቢተካም፣ የግሪኮች ጣሪያ አልባ (አንፊ) ቴአትር የመሰለው ዘመንሽን ውስጤ በከሰተልኝ ዋርካሽ የጥቁር ብካይ ሂደትሽ ይታየኛል፡፡ አንቆ መግደልን “ፍትህ” ነው ብለው የሚያምኑ ነገሥታቶችሽ አጣብተውሽ ከሄዱት ክፉ ባህርይ ጋር ዛሬም ያው መሆንሽ፣ ዛሬም ማነቂያ መሆንሽን አወጋሻለሁ፡፡