ካፌ
ውስጥ ነኝ፡፡ አንድ ሰው ከፊቴ እጀ ጉርድ ካናቴራ አድርጎ ካፑቺኖውን ይጠጣል፡፡ ቡና ከረባቴን አዝዤ ሰውየው ላይ አፈጠጥኩ፡፡
በእጆቹ ክንዶች ላይ ተነቅሷል፤ ተነቃቅሷል፡፡
በደህና
ጊዜ የረሳሁትን “ታቱ”ዬን አስታወሰኝ፡፡
የንቅሳት
ጠበብት ፡- “ንቅሳት ዘመን የማይሽረው ውጨ-ተውብሆ ነው” ይላሉ፤ ሊሆን ይችላል፡፡ እናቴ አንገቷ ላይ ተነቅሳለች፤ የአጎቴ ልጅ
ደግሞ ድዱ ላይ ጉራማይሌ ተነቅሷል፡፡ እኔ . . . ሃሃሃ . . . ክንዴ ላይ ተነቅሼ ነበር፡፡ ጓደኞቼ ንቅሳቴን ዓይተው “ተነክሰህ
ነው ተነቅሰህ?!” እያሉ ሲያላግጡብኝ አስፈግፍጌ አስጠፋሁት፡፡ /አስጠበስኩት ብል ይቀለኛል፡፡/ ጥሎት ያለፈውን ጠባሳ ስመለከት
እውነታቸውን እንደሆነ አረጋግጣለሁ፡፡ አሁን ነዋ ከንቅሳትነቱ በላይ ንክሳት እንደሆነ የሚያስታውቀው፡፡
ሰውየው….
በእጆቹ
ክንዶች ላይ ተነቅሷል፤ ተነቃቅሷል፡፡ በቅጥልጥል የእንግሊዘኛ ፊደል የተጻፈ ነው፡፡ ትርጉሙን ለመረዳት ለማንበብ ሞክሬ አልተሳካልኝም፡፡
እንኳን ተቀጣጥሎ እንዲሁ በ“ARIAL font” ተጽፎም አይነበብልኝም፡፡
የድሮው ንቅሳት አንገት እና ጥርስ ብሎም ግንባር እና አገጭ ተኮር ነበር፡፡
ዘመንኛው ንቅሳት ጥቂት የማሸጋሸግ ሂደት ይስተዋልበታል፡፡ አንገት ላይ የነበረው፣ ወደ ደረት . . . ድድ ላይ የነበረው ወደጆሮ
ግንድ . . . የተጨመሩት ደግሞ፣ ጀርባ ላይ እና
እምብርት ላይ ያሉት ናቸው፡፡ /ዘለቅ ብዬ አላየሁም እንጂ ሌላም፣ ሌላም ቦታ ላይ ተነቅሰው ይሆናል፡፡/
ንቅሳታሙን
ሰው ምን እንደተነቀሰና ለምን እንደተነቀሰ ልጠይቀው አሰብኩ፡፡ ግን፣ ምንስ ቢነቀስ እኔ ምን አገባኝ?? አልኩና ተውኩት፡፡ ለምን ጥያቄውን ከእራሴው አልጀምርም፡፡እኔ ለምን ነበር የተነቀስኩት?!
“ብሌን”
የተባለች ቆንጆ ወደድኩና ተነቀስኩ፡፡ የተነቀስኩ ሰሞን ከቅጥነቴ የተነሳ “ቆዳ ቅብ” አይት ነበርኩ፡፡ ታቱ የሠራልኝ ሰው ብዙ
አሪፍ አሪፍ ዓይነት አማራጭ ምስሎች ነበሩት፡፡ ግን ምኔ ላይ ይንቀሰኝ??
አልወደድኩትም እንጂ የሚመጥነኝ “ታቱ” አግኝቶልኝ ነበር፡፡ ልክ እንደ እጅ አምባር ሆኖ ክንድ ላይ የሚነቀስ፡፡ ትርጉም አልባ
ነገር ከመነቀስ እስከነአካቴው አለመነቀስ ይሻላል፡፡ “ብሌን” ብለህ ነቅሰኘኝ አልኩት፡፡ ነቃሹ “አይሆንም” ብሎ ሞገተኝ፡፡ “ብሌን”
ሶስት ፊደላት ነው፡፡ ክንድህ ደግሞ ወደታች እንጂ ወደጎን ቦታ የለውም፡፡ ስለዚህ “የዓይን ምስል” ይሻልሃል፡፡ አለና አሳመነኝ፡፡
ተነቀስኩ፡፡ የንቅሳቴ ቀለም ባግባቡ ሳያጠግግ ከብሌን ጋር ተለያየን፡፡ እንዴት እንደተለያየን አላውቅም፡፡ ስጠረጥር ግን “ለምን
የአባቴን ስም አብረህ አልተነቀስክም??” በሚል አኩርፋኝ ሊሆን እንደሚችል እጠረጥራለሁ፡፡
እና
አሁን በካፌ ውስጥ ካፑቺኖ የሚጠጣውን ሰው ሰውነት እና ቅጥልጥል የበዛበት ንቅሳት ሳስብ አንድ ነገር ተገለፀልኝ፡፡ ይህን ጊዜ
እኮ “ብሌን ኃይለ ማርያም” ብሎ ይሆናል የተነቀሰው!
አንተ
ሰውዬ፤ ልብ በል!! “ንቅሳት ዘመን የማይሽረው መዋቢያ ቢሆንም ለተነቃሹ ግን ልዩ ምልክት ነው፡፡”
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ