ሙሉውን ለማንበብ |
ርዕስ - "አደፍርስ"
ደራሲ - ዳኛቸው ወርቁ
የታተመበት ዘመን ፲፱፻፷፪ ዓ.ም
ቅንጣቢ ዳሰሳ - በሔኖክ ሥጦታው
ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ባስነበበን መዝገበ-ስብሐት “ማስታወሻ”
መጽሐፍ ላይ ጋሼ ስብሐትን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡- “በአንተ የወጣትነት
ጊዜ በአማርኛ ሃሳብን መግለፅ አይቻልም ብላችሁ አንተም ሆንክ ጓደኞችህ በእንግሊዝኛ መጻፍ የወሰናችሁበት ወቅት እንደነበረ ይነገራል።
በኋላ ደግሞ ወደ አማርኛው ተመልሰህ ድንቅ ጸሐፊ ወጣህ። ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ብትገልፅልኝ?”
ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፦ “በወጣትነቴ አማርኛ በምፈልገው
መልኩ ሀሳብን መግለፅ አያስችልም የሚል እምነት ነበረኝ። በዚህም ላይ ያስተማሩን እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች መሆናቸውን አትርሣ። እኛ
አናውቅም እንጂ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ወጣቱን ትውልድ በቅኝ አገዛዝ ጥበባቸው ይዘውናል። በኋላ ዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስን” ጻፈ።
እኔ ሳነበው በአማርኛ መጻፍ እንደሚቻል ገባኝ። ስለዚህ በእንግሊዝኛ የመጻፍ ሀሳቤን ተውኩት። በወቅቱ አስታውሳለሁ “ሌቱም አይነጋልኝን”
በእንግሊዘኛ መጻፍ ጀምሬው ነበር። . . .”
ማስታወሻ (ስብሐት ገብረእግዚአብሔር)ከዘነበ ወላ ፤
1993 ዓ.ም የታተመ፤ ገጽ 238
****** ****** ****** *****
“ዳኛቸው ወርቁ «አደፍርስ» (፲፱፻፷፪ ዓ.ም.) በተሰኘ ልብ
ወለድ ድርሰቱ. . . .ጭብጦች እና የተራቀቀ የአጻጻፍ ስልቱ የአማርኛን ዘመናዊ ልብ ወለድ ወደ ድንቅ ከፍ ካለ እርከን ያወጣ፥ «እምቧ በሉ ሰዎች» በሚለው የግጥም መድብሉ
(፲፱፻፷፯ ዓ.ም.) ውስጥ
በተካተቱ ግጥሞቹ ስለሀገሩ ልማትና ዕድገት ተቆርቋሪነቱን የገለጠ ዕውቅ የሥነ ጽሑፍ ምሁር፥ ሐያሲና ተርጓሚ የነበረ ሲሆን በልሳነ
እንግልጣር(እንግሊዝኛ) በመጻፍም «The Thirteenth Sun» የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ በዓለም አቀፉ መድረክ
ካስተዋወቁ በጣት ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጸሓፍት አንዱ ነበር።” ይለዋል የአማርኛው ዊኪ
ፒዲያ፡፡ሲቀጥልም፡-
“የፊውዳል ኢትዮጵያን ሶሲዮሎጂና የታሪክ ጥራዞች ከማንበብ፥ «አደፍርስ» ድርሰቱን ማንበብ ይቀላል’ የተባለለት ዳኛቸው ወርቁ የካቲት ፲፮ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ በይፋትና ጥሙጋ በደብረ ሲናከተማ አቅራቢያ ከአቶ ወርቁ በዛብህና ከወይዘሮ አሰገደች ሀብተወልድ ተወለደ። ከቤተ ሰቡ አምሥት ልጆች ዳኛቸው በኩር ነበር።…
የዛሬዎቹን ወጣት ኢትዮጵያውያን በጥበቡ ዘርፍ የሚታደጉ የሥነ ጽሑፍ ጥበብ መመሪያ፣ የአማርኛ ፈሊጦች መጽሐፍት ያሳተመ ምሁር ሲሆን አንድም ለሀገሪቱ ቋንቋ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያላቸውን «የማርክሲዝም ሌኒንዝም መዝገበ ቃላት» እና «የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት» የመሳሰሉ ጥልቅ እና ምጡቅ ሥራዎች ዝግጅት ላይ በመሳተፍ ምሁራዊ ግዴታውን የተወጣ ኢትዮጵያዊ ነበር።