መለያዎች

ልጥፎችን በመለያ ግጥሞች በማሳየት ላይ። ሁሉንም ልጥፎች አሳይ
ልጥፎችን በመለያ ግጥሞች በማሳየት ላይ። ሁሉንም ልጥፎች አሳይ

ማክሰኞ 14 ማርች 2017

አባይ ጠባብ መንገድ

(ኄኖክ ስጦታው)

የወንዝ አገሩ መነሻው፤ የወንዝ አገሩ መድረሻው
ወንዝ የሌለበት አገር ነው፣ መውጫ መግቢያው የጠፋው¡
*
የወንዞች ህብር ውጤት፤ የውኆች ስብስብ ጥምር
አባይ ፀሎቴን ስማ፣ ልንገርህ አንዳች ምስጢር።

ወደሄድክበት ውሰደኝ፤ እኔም አፈር ነኝና፣
ከአገሬ አንዴ ከወጣሁ፣ ሌላ ወንዝ አላጣምና።
*
አባይ ፀሎቴን ስማ፣ ከነአፈሬ አብሬህ ልውጣ
ሺህ ቢጎድል ተገድቦ፣ ሺህ ቢሞላ የሚቆጣ
ወንዝ ብቻ እንደሆነ፣ አውቃለሁኝ፤ ታውቀዋለህ!
አብረን ታስረን፣ ነፃ እንውጣ።

ሐሙስ 5 ጃንዋሪ 2017

“የፅኑነት ሥሪት”

(ኄኖክ ስጦታው) 

(ሲያጣሙት ሚጣመም… ሲያቀኑት ሚቀና)
የቆመ ቢመስልም — ፍፃሜው ግን ገና።

ግትር ነው የሚባል — ላመነበት ፀንቶ
ፍፃሜው ላይ ቆሟል — መልመጥመጡን ረቶ።

የ"ፅኑነት'' ትርጉም― ለዚህ ዘመን ድርሻ
ለሟችም ለኗሪም…
አለመታመን ነው — መታመን እያሻ።

አምናለሁ

(ኄኖክ ስጦታው)

አምናለሁ፣
     አምናለሁ፣
              አምናለሁ፣  
                         አምናለሁ
(አምኜ እጥራለሁ)
ጥሬ፣ ጥሬ፣ ጥሬ ፦ እምነት እገነባለሁ።
ስጠረጥር ጊዜ፣ (ሁለት) እንዳለሁ!
ታጥሮ በእምነቴ፣ ንጄው የሚሰፋ
“አንዱ” ራሱ እምነት፣ ሌላኛው ነው “ተስፋ”።
ተስፋ እገነባለሁ፦ እምነት አንፃለሁ፦ ጥላቻን ጠልቼ
(ጥርጣሬን ንጄ፣ እምነትንም ንጄ፣ ሌላነትን ሽቼ)
ማፍረስም መስራት ነው፣ መስራትም ነው ማፍረስ፣ አምናለሁ ተግቼ።

ሐሙስ 23 ጁን 2016

ውጣ—ውረድ

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)

“ነበር” ላይ ሊያበቃ፣ የ“ነው” ባይ  አቅጣጫ፤
ከ"ነው" እና "ነበር"፣ የታል የኔ ምርጫ?


መድረሻው መነሻ
          መነሻው መድረሻ
ጠይቅ “የታል” ብለህ… “የታል ውጣ—ውረድ”?
(ሕይወት መሰላል ነው፤ የእርብራብ መንገድ!)

የጥያቄ ምላሽ፣ በምጥ ላይወለድ
“እውነት” ካስጨነቀህ፣
  በስንዝር ቦታ ላይ፣ ጋት ጨምር… ተራመድ
መልሱን ተወውና፣ መጠየቅን ውደድ
                    ውጣ
           ወይም
ውረድ!

ሐሙስ 9 ጁን 2016

ፀሐይ

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)
የልቤን መሻት ለማድረስ፣ ውጣ ውረዱ ሲበዛ 
የመንፈስ ብርታት ልትሆነኝ፣ ሙቀቷ ሕይወት ሊነዛ
ፀሐይ ምድር ደርሳለች፣ ፍኖተ ሃሊብ ተጉዛ፡፡
ዝለቂ ከዋሻው ብርታቴ፣ ስንፍና ሰበቡን ይጣ
“ፀሐይ ልሞቅ ነው” በማለት፣ እኔም ከዋሻው አልውጣ፡፡

ዓርብ 27 ሜይ 2016

ጭምብል

ጭምብል

በፈገግታ ተከልለን፣ የክፋት ጥርሶች ስናገጥ
እኩይ ሥራችን ገፅ ሆኖ፣
            አድርጎናል መልከ-ቅይጥ።
“አስመሳይነት”
               መንታ ስለት፣
                          በጥርስ ሞረድ ሲሞዠጥ
አንደበት በውሸት ሲከፈት፣ ገፅ በጭምብል ሲለበጥ
ሰይፍ ይወጣል ከአፎት፣ መልካም ልቦችን የሚቆርጥ።

~Paul Laurence Dunbar
ውርስ ትርጉም ፦ ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ

እሑድ 8 ሜይ 2016

ተራማጅ እሳቤ ፺፩

(ኄኖክ ስጦታው)

ባለሶስት ፉርጎ ነው፤ ይጓዛል ባቡሩ፤ ቆየሁ ተሳፍሬ 
            የኋላኛው – ትላንት፣
            የፊተኛው – ነገ፣
            መሀለኛው – ዛሬ …
*
የታለፈ ትላንት፣ ያልተኖረ ነገ፣ ሃሣብ ውስጤ ሰርጎ
(ወጥሮ ይዞኛል)
         ፊት ላይሆን—ወይ ኋላ፣ መሐለኛው ፉርጎ።

እሑድ 10 ኤፕሪል 2016

Rumi "ልብስና ሰው"

"ይታዩኛል ብዙ ሰዎች
ዕራፊ አልባ፣ ልብስ የለሾች፤
ይታዩኛል ብዙ ልብሶች
በውስጣቸው የሉም ሰዎች።"

~ ሩሚ
ትርጉም ኄኖክ ስጦታው

ረቡዕ 9 ማርች 2016

ተነሳ ተራመድ - ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ

ተነሳ ተራመድ
---------
"ተነሳ ተራመድ! ክንድህን አበርታ!
ላገር ብልፅግና ለወገን አለኝታ!!"
እምም…
*
መነሻችን መቼ ጠፋ?! ለመበልፀግ ስንገሰግስ
ተፈጥሮን ፊቷን አዞረች። እንዴት ወደኛ እንመልስ?!
*
"ተነሳ ተራመድ! ክንድህን አበርታ!
ላገር ብልፅግና ለወገን አለኝታ!!"
*
"ተፈጥሮ የግብአት ምንጭ፣ ተፈጥሮ የእድገት አለኝታ
ኢንዱስትሪ ነው መርሃችን፤ ድህነት ድባቅ ይመታ!!"
*
"ተነሳ ተራመድ! ክንድህን አበርታ!
ላገር ብልፅግና ለወገን አለኝታ!!"
*
የኃያላን ተሞክሮ ውጤት፣ የእድገት ጉዞ ትግበራ
ተፈጥሮን ሚዛን አስቶ፤ ለዜጎች ፍላጎት ሲሰራ
ዋስትና በገንዘብ ተለካ፤ ብልፅግና በሸቀጥ ተመራ…
ውራ የመሆን ጨዋታ፣ አይመራምና በጭራ…
ተቀበል!
*
"ተነሳ ተራመድ! ክንድህን አበርታ!
ላገር ብልፅግና ለወገን አለኝታ!!"
*
ወደፊት መጓዝ እንዳለው፤ ወደኋላም እንመለስ
ተፈጥሮን ማጥናት አይበቃም፣ ኗሪ ጎጆውን ሲቀልስ።
*
"ተነሳ ተራመድ!
ክንድህን አበርታ!
መጥረቢያ ነው ጠላትህ፣ አንተን በድርቅ የመታ!!!
"ተነሳ" ሲሉህ ተነሳ!
አምባገነን ነው ተፈጥሮ፣
"እንዳያልፉት የለም" ከማለት፤ የእልቂት ታሪክ ሞነጫጭሮ
ወደኋላ እንመለስ፣ እርቅ እንፍጠር ከተፈጥሮ
የደን ታሪክ ይሰራ፣ የደም ታሪክ ተሽሮ።
*
ተፈጥሮ ለጨቆኗት ጨቋኝ ነች፤ 
Sep 20, 2015 1:42:12 AM

ሐሙስ 25 ፌብሩዋሪ 2016

አዳም… (ኄኖክ ሥጦታው ናሁሰናይ)

አዳም…
(ኄኖክ ሥጦታው ናሁሰናይ)


"ጥፋት"፣ "ታዛዥነት" …
ቢጋጩ ከድንጋይ
                "ተቃጠልኩኝ" አትበል…
                 እሳት ፈጥረው ብታይ።
*
ፍላጎቱን ሳይኖር፣ "ሕግን" ያከበረ፣
በተጻፈው እንጂ፣ ራሱን መች ኖረ?!
*
አዳም ሰው አትስማ፣ ከትዛዝ ላይወጣ
"ሕግ ጣሰ" ይበል፤ "በበላው ተቀጣ"
የኖርከውን ሳይኖር፣ ያስብ ምን እንዳጣ!
*
አዳም ተለመነኝ፤ አንተ ኑረህ ብላ…፣ ቅጣት ምናባቱ

ያልበላው ይታዘዝ… ሕግን ማክበር "መብቱ…"
*
አዳም በአፈርህ፦
ብላ… ደግመህ ብላ… የሕግ አጥር ይፍረስ
"አምላክ ይጠራኻል"፤ ክልከላውን ስትጥስ!

ረቡዕ 17 ፌብሩዋሪ 2016

"እሾህን በሾህ"

✧(ኄኖክ ስጦታው)
(የአጭር አጭር አጭር ልቦለድ)

ለእራት የሚሆን ነገር ለመግዛት ወደ ሱቅ አመራ። እንደ ሁልጊዜውም፣ ጎረቤቱ የአይጥ መርዝ እየገዛ ነበር። ከጎረቤቱ ቤት መርዝ በልተው እሱ ቤት ኮርኒስ ውስጥ የሚሞቱ አይጦች ሽታ ረፍት ነስቶታል።
"ለምን በወጥመድ አታጠምዳቸውም?" አለና መፍትሄ ይሆናል ያለውን ሃሳብ አቀረበለት። ለጎረቤቱ።
"ሞክሬ ነበር። ወጥመድ ማለት የአይጥ ገበታ ነው። አይጦቹ ወጥመዱ ላይ ያለውን ምግብ በልተው ይሄዳሉ። ጠዋት ስነሳ ወጥመዱ የሚይዘው እኔኑ ነው።"
ዝም አለ።
አስቦ ፣ አስቦ… አንድ መፍትሄ አገኘ። እናም ጎረቤቱ ዞር እስኪል ጠብቆ፦
"የአይጥ መድሃኒት አለ?" ሲል ጠየቀ። ለባለሱቁ።
"የለም። መርዝ ነው ያለው"
"እሱንም ቢሆን ስጠኝ"