2016 ሜይ 21, ቅዳሜ

ለምን አልስቅ?!

እስቃለሁ!
(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)

የክልከላ እና የተግሳፅ ህግ ተሸብበን ሳቅ አልባ ሆንን። የሳቅ መንስኤዎች በሙሉ ከጊዜ ወደጊዜ እየተመናመኑ መጡ። ሳቅ አጠር ሆነን የሚስቁትንም አሳቀቅን። የሚያስቀው አያስቀንም። ለቀልድም ሆነ ጨዋታ መራር ትርጉም ፍራቻ ቁጥብ ሆንን። የክልከላ ህግ ለስሜት ቅድመ ሳንሱርነት ተሹሞ በላያችን ላይ ሰለጠነ። ስሜት ፈንቅሎት እንዳይወጣ በሳቃችን ላይ ከመርግ የከበደ ጭፍግ ቆለልንበት።

የሚስቅና ሌሎችን ለማሳቅ የሚወድ እንደ "ተራ ቧልተኛ" ተቆጠረ። መሳቅም ሆነ ማሳቅ ከበደ። ለአሳሳቅ ስልት ተበጀለት።

እንዴት እንደማይሳቅ የሚመክሩ ጭፍግ መካሪዎች በዙ። ሳቃቸውን አፍነው የሚወቅሱ በዙ። በፍራቻ ተሸብሸው የሚገስፁ በዙ። በይሉኝታ ታፍነው ፊታቸውን የሚጨፈግጉ በዙ። በንዴት ቱግ ብለው የሚንጨረጨሩ በዙ። "አያስቅም" የሚሉ በዙ።

ሳቅ ጠፋን። አሳሳቅ ጠፋን። ከአዘኑት በላይ ያዘንን መሳይ፣ በሚስቁት ላይ የምንበሳጭ…  የተውሶ ፊቶች ጥርቅም ሆንን። ሳቅ ጠፋን! አሳሳቅ ጠፋን። በላያችን ላይ እንዴት እንደሚሳቅ የሚያስተምር ትምህርት ቤት ተከፈተ።

እናም ዛሬ ከዚህ በታች ያለውን ቀልድ ከአመት በኋላ ድጋሚ ሳነበው በድጋሚ ሳቅኩ።

————
አንድ ሰሞን በአንድ አገር ዋና ከተማ ውስጥ ብዙ የጦር መሳሪያ ስለጠፋ የቤት ለቤት ፍተሻ ተጀምሮ ነበር፡፡ ሁሉም ተፈትሾ፣ ተፈትሾ ጳጳሱ ቤት ይደረርስና እዛ ገብተው ሁሉንም ክፍሎች ፈትሸው ምንም ስላልተገኘ በስተመጨረሻ እሳቸው ወደ ተቀመጡበት ሄደው ሲፈትሹ በጣም ብዙ መሳሪያ ያገኛሉ፡፡ ፈታሾቹም ተገርመወው፡-

“ይሄን ሁሉ መሳሪያ ከየት አገኙት?” ብለው ሲጠይቋቸው ፡-

“ሚኒስትሩ በስለት ያስገባው ነው”

የሁለት አህዮች ወግ

ሁለት አህዮች … እያወሩ ነው።

የመጀመሪያው አህያ፣ “የእኔ ባለቤት እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ በዱላ ይደበድበኛል” ይለዋል በምሬት።

ሁለተኛ አህያ፣ “ታዲያ ለምን ትተኸው አትሄድም?”

የመጀመሪያ አህያ፣ “እሱስ እውነትህን ነው። እንዳልከው ለማድረግ በተደጋጋሚ አስቤ ነበር። ነገር ግን እጅግ በጣም ውብ እና መልካም ፀባይ ያላት ሴት ልጁን ሳስብ ሃሳቤን እቀይራለሁ።” 

ሁለተኛው አህያ፣ “እንዴት ማለት? አልገባኝም”

የመጀመሪያው አህያ፣ “አሳዳሪዬ በዚህች ቆንጆ ልጁ ሲበሳጭ… ‘አህያ ካልሆነ በቀር የሚያመዛዝን ሰው አያገባሽም!’ ሲል ይናገራታል፤ እኔም የምታገሰው ይህ ሁኔታ እስከሚፈጸምበት ጊዜ ብቻ ነው።”

2016 ሜይ 20, ዓርብ

ቆይታ (ከቀብር አስፈፃሚዎቹ ጋር)


☞ኄኖክ ስጦታው

ለሞት ያለኝ ግንዛቤ ግልፅና አጭር ነው። ሞት እድገት ነው፤ መወለድም እድገት። "የሰው ልጅ ከሞት በኋላ ያለውን ካለማወቅ ፍራቻ አያሌ መሸሸጊያ ፈጥሯል" ያለው ዲካርት መሰለኝ ።

ጓደኞቼ "እንሳለም" ብለው ሚካኤል ቤተክርስቲያን ጋር መኪናዋን አቆሙ።"ዛሬኮ አርሴማና ተክልዬ ይነግሳሉ፤ አትሳለምም?"

"አልሳለምም፤ እናንተ ደርሳችሁ እስክትመጡ ቀብር አስፈፃሚዎቹ መደብር ውስጥ እጠብቃችኋለሁ።"

ወደ ሬሳ ሳጥን መሸጫና ማደሻ መደብር አመራሁ። ብዙ አይነት የአስክሬን ሳጥኖች ተደርድረዋል። ሁለት አይነት አበቦች (በወረቀት ተሰርተው ቀለም የተነከሩ እና ከበቀሉበት የተዘነጠፉሸአበቦች) ደጃፉ ላይ አየሁ። ፊትለፊት ሆነው እይታዬን ያልሳቡት ለምን ይሆን? ስልኬን አውጥቼ ፎቶ ማንሳት ጀመርኩ።

ሰዎች እንዳላዩ ሆነው ከሚያልፏቸው ነገሮች አንዱ እንደዚህ አይነት መደብሮችን ነው። መደብሩ በራፍ ላይ አበቦች አሉ። ከአበቦቹ በላይ ያሉት በላይ በላያቸው የተደራረቡ ሳጥኖች ግን አበቦቹን ጋርዷቸዋል። አ አ!  አይደለም። አስክሬን ሳጥኑ ከፊት ካልሆነ በቀር አበቦቹን እንዴት ከዕይታ ሊጋርዳቸው ይቻለዋል?

"ሄይ፣ ፎቶ ማንሳት ክልክል ነው!" የሚል ድምፅ ሰማሁ። ሁለት ወጣቶች ወደኔ መጡ።

ፎቶ ማንሳት ክልክል መሆኑን የሚገልፅ ምንም ምልክት የለም። ለምን ክልክል እንደሆነ ጠየኩ።

"የአስክሬን ሳጥኖቹ ዲዛይን ይሰረቅብናል። አይቻልም።"

"የሳጥኑ ዲዛይን ከሌላው በምን እንደሚለይ ማወቅ እችላለሁ?"

"የማትገዛ ከሆነ ብነግርህ ምን እጠቀማለሁ?"

"እኔ ባውቅ ምንስ የምታጣው ነገር አለ?"

"ለምንህ ነው ማወቅ የምትፈልገው?" ሲል ሌላኛው ጠየቀኝ።

"በቃ፣ ደስ ይለኛል። ሳጥኖቹን በቅርብ ሆኜ ባይ፣ አብሬያችሁ ውዬ ቀብር ባስፈፅም ደስ ይለኛል። በተለይ ከሳጥኖቹ መሐል የማስታወሻ ፎቶ ብነሳ… ደስ ይለኛል" አልኩ። እውነቴን ነበር።

እርስ በራሳቸው ተያዩና ፈገግ አሉ። ወደ ውስጥ እንድገባ ፈቀዱልኝና ትልቅ አልበም እንድመለከት ጋበዙኝ።
ለጨዋታ መጀመሪያ ያክል "ስራ እንዴት?" አልኩ።

"እግዚአብሔር ይመስገን"
(ምሥጋና ጥሩ ነው) 😱

የሚያምር የሬሳ ሳጥን አየሁና ዋጋውን ጠየኩ፦

"12ሺ ብር።" አለ።

"ዋጋው እንደዚህ የተወደደበት ምክንያት ምንድነው?"

"በኤምዲኤፍ ነው የተሰራው። እንደምታየው የሳጥኑ የላይኛው ክፍል ሙሉ መስታወት ነው። አስክሬኑ በሱፍ ሽክ ተደርጎ ይገነዛል።"

"ዋጋው አስክሬኑ የሚለብሰውን ሱፍ ጨምሮ ነው? "

"ልብሱን ቤተሰብ ነው የሚያዘጋጀው።"

"ለሴቶች ሲሆንስ?"

"አይቀንስም"

ሳቅኩ።
"ዋጋውን አልነበረም የጠየኩህ። አስክሬኑ የሴት ከሆነ ምን አይነት ልብስ ነው የምትገነዘው?"

እርስ በራሳቸው ተያዩ። መቼስ ሱፍ አያለብሱ።
ሁለተኛው መለሰልኝ፦
"የአገር ባህል ልብስ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ባለሙሉ መስታወት ሳጥኖችን ግን እስካሁን የተጠቀምነው ለወንዶች ነው።"

"የአሜሪካ ሳጥንም አለን።" አለ ሌላኛው።

"የትኛው ነው?"

"እዚህ የለም። አልበሙ ላይ ላሳይህ…።" አልበሙን ተቀብሎኝ ገለጥ ገለጥ አድርጎ "ይኸው!" አለ።

ያምራል።

"ዋጋው ምን ያህል ነው?"

"35 ሺ ብር"

"እ?"
ደገመልኝ። በሰላሳ አምስት ሺህ ብር የ1972 አዲስ ብራንድ አፍሮ ቮልክስ መሸመት የሚችል ብር እንደሆነ አሰብኩት። የገረመኝ ግን ሌላ ነበር፦
"ሳጥን አስመጪ አለ ማለት ነው?"

"አስመጪ የለም። ከአሜሪካ አስክሬን ይመጣበትና የአገር ውስጥ ሳጥን ላይ ብር ጨምረን ከቤተሰቦቹ ላይ እንገዛዋለን።"

"እዝጎ!" (አልኩ በውስጤ)