2016 ሜይ 21, ቅዳሜ

ለምን አልስቅ?!

እስቃለሁ!
(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)

የክልከላ እና የተግሳፅ ህግ ተሸብበን ሳቅ አልባ ሆንን። የሳቅ መንስኤዎች በሙሉ ከጊዜ ወደጊዜ እየተመናመኑ መጡ። ሳቅ አጠር ሆነን የሚስቁትንም አሳቀቅን። የሚያስቀው አያስቀንም። ለቀልድም ሆነ ጨዋታ መራር ትርጉም ፍራቻ ቁጥብ ሆንን። የክልከላ ህግ ለስሜት ቅድመ ሳንሱርነት ተሹሞ በላያችን ላይ ሰለጠነ። ስሜት ፈንቅሎት እንዳይወጣ በሳቃችን ላይ ከመርግ የከበደ ጭፍግ ቆለልንበት።

የሚስቅና ሌሎችን ለማሳቅ የሚወድ እንደ "ተራ ቧልተኛ" ተቆጠረ። መሳቅም ሆነ ማሳቅ ከበደ። ለአሳሳቅ ስልት ተበጀለት።

እንዴት እንደማይሳቅ የሚመክሩ ጭፍግ መካሪዎች በዙ። ሳቃቸውን አፍነው የሚወቅሱ በዙ። በፍራቻ ተሸብሸው የሚገስፁ በዙ። በይሉኝታ ታፍነው ፊታቸውን የሚጨፈግጉ በዙ። በንዴት ቱግ ብለው የሚንጨረጨሩ በዙ። "አያስቅም" የሚሉ በዙ።

ሳቅ ጠፋን። አሳሳቅ ጠፋን። ከአዘኑት በላይ ያዘንን መሳይ፣ በሚስቁት ላይ የምንበሳጭ…  የተውሶ ፊቶች ጥርቅም ሆንን። ሳቅ ጠፋን! አሳሳቅ ጠፋን። በላያችን ላይ እንዴት እንደሚሳቅ የሚያስተምር ትምህርት ቤት ተከፈተ።

እናም ዛሬ ከዚህ በታች ያለውን ቀልድ ከአመት በኋላ ድጋሚ ሳነበው በድጋሚ ሳቅኩ።

————
አንድ ሰሞን በአንድ አገር ዋና ከተማ ውስጥ ብዙ የጦር መሳሪያ ስለጠፋ የቤት ለቤት ፍተሻ ተጀምሮ ነበር፡፡ ሁሉም ተፈትሾ፣ ተፈትሾ ጳጳሱ ቤት ይደረርስና እዛ ገብተው ሁሉንም ክፍሎች ፈትሸው ምንም ስላልተገኘ በስተመጨረሻ እሳቸው ወደ ተቀመጡበት ሄደው ሲፈትሹ በጣም ብዙ መሳሪያ ያገኛሉ፡፡ ፈታሾቹም ተገርመወው፡-

“ይሄን ሁሉ መሳሪያ ከየት አገኙት?” ብለው ሲጠይቋቸው ፡-

“ሚኒስትሩ በስለት ያስገባው ነው”

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ