አክስት አዛሉ
እውነተኛ ስሟ “አዛለች” ይሰኛል፡፡ እኛ ቤተሰቦቿ “አንቺ” የሚለውን ድምፀት ከአንደበታችን ለማጥፋት “አዛሉ” ብለን በመጥራት አንቺን ከአንቱ አስታርቀነዋል፡፡
አዛሉ ሞባይል የያዘች ሰሞን ጥቂት ተቸግራ ታስቸግረን እንደነበር አይረሳኝም፡፡ በተለይ “የቴሌዋ ሴትዮ” ብላ ከምትጠራት ጋር ያነበራት ጠብ እጅግ የከረረ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
አዛሉ፣ በሞባይል ስልኳ ስትደውል (የቴሌዋ ሴትዮ) ... “የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም...” ስትላት ነው መሰል እንዲህ ስትል ሰምቻታለሁ፡-
“ምነው እቴ! አሁን ብታገናኚኝ ክብርሽ አይቀንስ...”
አዛሉ ሚሴጅ ሲደርሳትም “የቴሌዋ ሴትዮ” ትብጠለጠላለች፡፡ “እንግሊዝ ያስተማረችኝ አይመስልም አሁን?! ጉድ እኮ ነው! አበስክ ገበርኩ.....ና እስቲ ፤
ይህች ሴትዮ ምን እንደምትል አንብብልኝ...” ብላ ስልኳን ትሰጠኛለች፡፡ በቁጥር ስህተት ካልሆነ፣ አልያም የቴሌዋ ሴትዮ ካልተላከላት በቀር፣ ከማንም መልዕክት ደርሷት አያውቅም፡፡
እናም መልዕክቱን አነብላታለሁ፡-
“Dial *808*3# and call up to 6o
minutes for only Br 4.99 or *808*4# for unlimited calls with only Br 9.99 from
11:00PM -6 :00AM (NIGHT TIME).”
“ደግሞ አሁን፣ ምን አድርጉ ነው የምትለው?” ትላለች አፏን በሽርደዳ መልክ እያሞጠሞጠች፡፡ እንምንም ላስረዳት እጥራለሁ፡፡ እስኪገባት ድረስ ግን ታግሳ አትሰማኝም፡፡ ተቋርጠኝና፤
“መልሰህ ላክላት! ʿእንኳን ዘንቦብሽ እንዲሁም ጤዛ ነሽʾ ብለህ ላክላት!” ትላለች እየተንጨረጨረች፡፡ ከንዴት ጋር ያላት ቅርበት፣ ለማወቅ ካላት ትዕግስት አልባነቷም ያይላል፡፡
አክስት አዛሉ፣ “የቴሌዋ ሴትዮ” ከምትላት ባላንጣዋ ጋር ሳትነታረክ ውላ አታውቅም፡፡ አንዳንዴ፣ “ያለዎት ቀሪ ሂሳብ አነስተኛ ነው... እባክዎን ተጨማሪ ሂሳብ...”
የሚለውን ንግግር ትሰማና መልስ ትሰጣለች፡፡
“እሺ፣ እሞላለሁ፡፡ እኮ ምን አለብሽ?! እኔ በሞላሁት ካርድ የምታወሪው አንቺው....”
አንድ ጊዜ “የቴሌዋን ሴትዮ” ድምፅ መስማት ት-ክ-ት
ብሏት እንዲህ በማለት የጠየቀችኝ አይረሳኝም፡-
“እንደው ይህቺን ሴትዮ የሚተካ አንድ ደህና ወንድ በአገሩ ጠፍቶ ነው እንዲህ ቀን ተሌት ቦርቂባቸው ብለው የለቀቁብን?! ”
“አክስቴ፣ምን ወንድ አለ ብለሽ ነው....” እላታለሁ ነገሯ እንዲራዘም ስለምፈልግ፡፡
“እውነት ብለሃል! ይህ መንግስት ሴቱን የሚያደራጀው ለምን ሆነና?! ወንዱንማ ደርግ ጨርሶታል....”