(ኄኖክ ስጦታው)
‘ሙሽራው በዘገየ ጊዜ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ።’
(የነቁት ግን ይህን ለማንበብ ችለው ነበር)
ከአሥሩ ደናግላን መካከል አምስቱ ሞኞች ናቸው። አምስቱ ግን አንድ። አምስት ደናግል ብልሆች አንድ ብርሃንም ለመፍጠር መዘጋጀታቸውን የተመለከተ የዚህ ዘመን "አዛዥ" እንዲህ ሲል ሰማሁት፦
‘ለአንድ ኩራዝ አምስት ሰው ምን ያደርጋል?! አራታችሁ ተመለሱና ከአምስቱ ጎን ቁሙ!! ብርሃን ለመለኮስ አንድ ሰው ይበቃል!!! ዳይ!!!’
የተባረሩት አራቱ ብልሆችም፣ አምስቱን ጅሎች አስተባብረው ስሞታ ለማቅረብም ወደመምህራቸው አቀኑ። እንዲህ ሲሉ ጠየቁ፦
‘ጌታ ሆይ፣ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን ሳናገለግልህ ቀረን?’
እርሱም ተናገረ። በርግጥ መልሱ ግልፅ ቢሆንም፣ ማንም አልሰማውም ነበር።
‘ታዲያ ለምን ትጠይቁኛላችሁ? እኔስ ብሆን ያደረኩት ይህንኑ አይደል?!…’
✧
✧
☆
ነገሩ እንዲህ ነው። አንድ የግብረ ገብ መምህር የዳርት ውድድር አዘጋጀ። ለተማሪዎቹ። ዳርቱ ነጭ ወረቀት ተለብጧል። ኢላማውን በነጩ ወረቀት ላይ የሚስለው እራሱ ተወዳዳሪው ነው። ለምሳሌ፣ በነጭ ወረቀት የተለበጠው ዳርት ላይ የሚጠላውን ሰው ስም ይፅፋል። የፃፈውን ስም በፍላፀው አነጣጥሮ ከመታው ‘ጥላቱን ’ እንደተበቀለ ያህል ይረካል ።
ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ሁሉም ተማሪ የራሱን ጥላቻ ለመውጋት ኢላማ ይሆነኛል ያለውን ታናናሽ ምልክቶችን በዳርቱ ላይ አኖረ ። ኢላማውን ለመውጋት አነጣጥረው የወረወሩት ሁላ የራሳቸውን ኢላማ ባይመቱም እንኳን፥ በስህተት የሌሎችን ኢላማ ክፉኛ ወጋግተውት ነበር።
እናም በመጨረሻ፣ የዳርቱን መጫወቻ የሸፈነው ነጭ ወረቀት ሲገለጥ የኢየሱስ ምስል ክፉኛ ተወጋግቶ ለሁሉም ታየ። ይህን ያደረጉት የግብረ ገብ መምህሩ ነበሩ።
የራሱን ኢላማ ለመምታት አነጣጥሮ የወረወረው ተሜ ሁላ እንዲህ የሚል ንግግር ከመምህሩ አንደበት ተላለፈለት፦
‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል’
✧
☆
በሌላ ጊዜ፤
ሁለት አማኞች ስለ ሃይማኖት እያወሩ ነበር።
አንደኛው ለሌላው፣ "አንዳንዴ ፈጣሪን… ለምን ድህነት፣ ረሃብ፣ ኢፍትሐዊነት… በአለም ላይ ሊያስወግድ እንዳልቻለና የሆነ ነገር እንዲያደርግ በፀሎት ብጠይቀው እወድ ነበር።" ሲለው ሁለተኛው አማኝ ተገርሞ ፦
"ታዲያ እንዳትጠይቀው ምን አገደህ?!" ሲል ይጠይቀዋል ።
እናም፣ የመጀመሪያው አማኝ እንዲህ ሲል መለሰ፦ "አምላክ ፤ እነዚህኑ ጥያቄዎች እኔኑ መልሶ እንዳይጠይቀኝ ሰግቼ ነዋ!"
።።።።።።።።።።።።።።
እኔም ይህን አልኩኝ፦
‘ከዚህ በኋላ የምትጠይቀኝን መልሼ እጠይቅሃለሁና ስትጠይቀኝ ተጠንቅቀህ ጠይቅ!’
*መነሻ ሃሳብ (ማቴዎስ 25…)