ወፍ እና ማለዳ
እንኳንስ
ችግኙ፥ ሰዎች የተከሉት
ሥር
ይዝ ነበረ፥ አዕዋፍ የዘሩት።
ዘንድሮ
ግን ወፎች፥ እንኳንስ ሊዘሩ
ናፍቆኛል
ማለዳ፥ መስማት ሲዘምሩ።
ወፎች ከማለዳ-
በምን ተቃቃሩ?!
ፅልመቱ ሲገፈፍ-
እንዳላበሰሩ፤
ማዜም ተስኗቸዉ-
ተዘግቶ ጀንበሩ
ወደሚነጋበት-
ወዴትስ በረሩ?!
-----------------------------------------------------
ምንጭ
= ሀ-ሞት [የግጥሞች ስብስብ]
ኄኖክ
ስጦታዉ
--------------------------------------------------------------
[ ገጣሚ
ኄኖክ ስጦታዉ የግጥም ስብስብ መፅሀፉን ሁለት ሶስቴ... ሊያሳትም ሲችል፥ በነፃ ሁላችንም እንድንመሰጥበት በድረ ገፁ ለቆታል። ገንዘብ እያስፈለገዉ ለሥነፅሁፍ ፍቅርና ልክፈት
ማደሩን አስቀደመ። ሀ-ሞት በጥሞና ለመነበብና ለማወያየት ጥበባዊ አቅም የቋጠረ መፅሃፍ ነዉ። ለጊዜዉ አንድ ዘለላ የተዋጣ ግጥሙን አብረን share በማድረግ በመጠኑ እናንብብ።
የምስጋና ያክል ነዉና - አብደላ ዕዝራ ]
---------------------------------------------------------------------------
<ወፍ እና
ማለዳ> አጭር እምቅ ተራኪ ግጥም ነዉ። ትረካዉ እንደ ማዉጋት የሚወረዛ ሳይሆን ገጣሚዉን ለመዘመዘ ጉዳይ መተንፈሻና ማዉጠንጠኛ ሆነ። የርዕሱ ስክነት ፈጠጠ እንጂ ጉጉት አልቀሰቀሰም። ርዕሱ ግጥሙ ዉስጥ ባደፈጠዉ ስንኝ በተተካ ያሰኛል፤ <ወፎች ከማለዳ በምን ተቃቃሩ?> የሚነሰንሰዉ አሻሚነት የሚከሶክስ፤ ከመነሻዉ በዉስጠምት -rhythm- የሚያባንን በሆነ። ተናጋሪዉ (persona) - የወንድም የሴትም አንደበት ሊሆን ይችላል - የቆረቆረዉ፥ ያሳሰበዉ የመምከን አባዜ አለ፤ እንዴት ሳይሆን ለምን በበለጠ ያብሰከስከዋል።
ደበበ
ሠይፉ <ወፊቱ> በሚለዉ ግጥሙ ቀን-ቀን አየሩን እየቀዘፈች አድማስ ሳይወስናት የቦረቀች ወፍ፥ ለአይን ያዝ ሲያደርግ መድናገሯን ተቀኘበት።
ኧረ
ምን መለሰሽ ?
ወደኋላ
ያዘሽ ?
መሸት
ከማለቱ ያደነቃቀፈሽ ?
ወፊቱ
በሌሊት ምን ይሆን ታስቢ
እኔኑ
መሰልሽኝ ጐጆሽ ስትገቢ።
ደበበ
የተናጋሪዉንና የወፊቱን የጓዳ ህይወት ቅዝቃዜ፥ የብቸኝነት ወጥመድ ... ህዋና የአራት ግድግዳ ስፋትና ጥበት የተወሳሰበበት ሥነልቦናዊና ኑሮዋዊ ጣጣ አነፃፀረ። ሄኖክ ግን ጐህ ሲቀድ ይህች ወፍ የማለዳ ብርቅነቷ ነዉ የረበሸዉ። መዝሙሯን፥ የአዲስ ቀን ምስራቿን እንዴት ነፈገችን ? ይቅርና እንደ ድምፅ ለእህልም -ወፍ ዘራሽ- ትበቃ የነበረዉ ከማለዳ ጋር ለምን ተቃቃሩ ? ቅኔያዊ፥ ዘይቤያዊ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ሥር ከሰደደ ሥጋት ተፋትጐ የተቀጣጠለ ዕንቆቅልሽም ነዉ::
እንኳንስ
ችግኙ፥ ሰዎች የተከሉት
ሥር
ይዝ ነበረ፥ አዕዋፍ የዘሩት።
ዛሬ
ግን የአማርኛዉ ፈሊጥ “ወፍ ዘራሽ” ብሎም “ገና ወፍ ሳይንጫጫ” ምን አደበዘዘዉ ? ገጣሚዉ ቃላት ሳይከምር፥ እንደ ዘገባ ፊት ለፊት እሳቦቱን ሳይዘረግፍ ሰወኛ ዘይቤን በማጠላለፍ ዕምቅ ግጥም አስነብቦናል። በአርምሞ የአካባቢዉን ቁሳዊና ህሊናዊ ዐዉድ ከቃኘና ከታከከ በኋላ ጥያቄና ግርምታ ያደነደነዉን ስንኝ ያቀብለናል፤ ስናስብበት የተዳፈነዉ ረመጥ ፋታ አያዉቅም።
ማዜም
ተስኗቸዉ-
ተዘግቶ
ጀንበሩ
ወደሚነጋበት-
ወዴትስ
በረሩ?!
እኛ
ዘንድ መንጋት አቆመ ወይ ? ሰፈራችን ህይወታችን ለጨለማ ገብሮ፥ ለብርሃን ሽንቁር እስከመቼ አቴቴ ቢስ እንሆናለን ? ወፎች ጐህ ወደ ቋጠረዉ ተሰደዉ፥ ጀንበር እንደ ጣራ ተደፍኖ ሲቀር፥ ስጋቱ ያዉካል። “ጀምበር ካለ እሩጥ፥ አባት ካለ አጊጥ” እንደ ቅዠት ሊፈረካከስ ? ተስፋ ላለመቁረጥ የሄኖክ ግጥም ጀርባ እንዳለዉ ማወቅ ሊኖርብን ነዉ። የግጥሙን ተናጋሪ መጠራጠር እንጀምራለን፤ ቀን-ቀን እያንቀላፋ ለወፍ ዜማና ለንጋት መፍካት የሚቀሰቅሰዉስ ካጣ ? ይህንን ሄኖክ በሌላ ባለአንድ አንጓ ግጥሙ < ታሽጓል> የሚለዉን ግለሰብ ይገረምማል። እንዴት ከግሉ ደጃፍ ተገትሮ የራሱን በር ያንኳኳል ? የአደባባይ ሳይሆን ከዉስጡ የተጋረደዉ ንጋት ይብሳል።
ቢጠሩት
ላይሰማ፥
ልቤ
ተጠርቅሞ
የሚያንኳኳዉ
ማንነዉ፥
ደጃፉ
ላይ ቆሞ ?!
ይህ
ግለሰብ ብንን ሲል፥ በወፍና ንጋት ልክፈት ተቀንብቦ ፍለጋዉን አይገታም። እያደባ የደረሰባት ወፍ ግን < ጉጉት> ሆና ታሸማቅቃለች።
ከእርግቦች
መሐል፥
እርግብ
ተመስላ፤
“እርግብ
ናት”
ያልናቱ፥
ላባ
ተከልላ፤
ሥትከፍተዉ
አፏን፥
አየን
ጥርስ አብቅላ።
ያቺ
የምትዘምረዉ፥ ጨለማን ተርትሮ ብርሃን ሲያንሰራራ የሚያቅበዘብዛት ወፍ ሲያልም ይኑር፥ ወይስ ተስፋን እያማሰለ እያቦካ የህይወት በገናውን እየቃኘ የግሉን ዜማ ያፈልቅ የሆን ? የግጥሙ ጥንካሬ አለማብቃቱ። ይህን ንባብ በህዝብ ቅኔ - መንፈስ ለማርገብ ያክል - እንቋጨዉ። ፀሐይ የተባዕት መጠሪያ ሆኖ እንደ ሰምና ወርቅ ቢዳዳዉም፥ ለሄኖክ < ወፍ እና ማለዳ > ማንፀሪያም ነዉ። ማለዳ የናፈቀን ያህል፥ ፀሐይ የሚፈታተናትም ሄዋን ታቃስታለች።
በሐምሌ
በነሀሴ እንድያ ስዋትት
እንዴት
በመስከረም በፀሐይ ልሙት ?
****************************************
ምንጭ፡- ቤተ-መጻሕፍ ወጻሕፍት