ቅዳሜ 10 ሜይ 2014

ወጣትነት አቁሮ የማቆየት ግፊት - በ ኄኖክ ስጦታው

ወጣትነት አቁሮ የማቆየት ግፊት

ሰው እድሜውን የሚደብቀው ለሁለት ምክንያት ይመስለኝ ነበር፡፡ በግዳጅ ጦር ሜዳ ከመዝመት እና ጡረታን ፍራቻ ፡፡ አሁን ግን ብዙ ምክንያቶች ይታዩኛል፡፡ ከጥቃቅን ሰበባ አስባቦች በላይ ወጣትነትን ባለበት አቁሮ የማስቀረት ግፊት ማየል ሰፊ ሃተታ ቢወጣውም በስሱ ቃኘሁት፡፡
***
ትልቅ ለመሆን የተመኘንበት የልጅነት ሲዝናችን በዕድሜ ዑደት ተሽሮ ለጉርምስና ቦታውን ይለቃል፡፡ ጉርምስና እሳት ነው፡፡ ነዶ ለማለቅ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ አመዱን ትቶ ቦታውን ለወጣትነት ይለቃል፡፡ የሚግለበለበውን የእድሜ እሳት ለማርገብ የውሸት ውሃ መቸለስ የሚጀመርበት ሲዝን፡፡
ዕድሜ ግን አሪፍ አርቲስት ነው፡፡ ሌሎችን ለማሳመን የዋሸነውን ስዕል ሙሉ በሙሉ ሰርዞ የራሱን እውነተኛ ምስል እኛው ላይ የሚጠበብ ድንቅ አርቲስት! ዕድሜ፣ ተፈጥሯዊ ማስተባበያውን አካላችን ላይ በመሳል ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ እኛም ስዕሉን በሌላ ስዕል (ሜካፕ) ለማጥፋት እንጥራለን፡፡ ነጩን ስናጠቁር፣ ጥቁሩን ስናቀላ፣ የተጨማደደውን ስናቃና፣ የወደቀውን ስናነሳ፣ የረገበውን ስንወጥር፣ የበለዘውን ስናነጣ፣ . . .
***
ልደቷብለን ቅፅል ስም ያወጣንላት ጓደኛች አለችን፡፡ ቆንጆ ናት፡፡ ጭሰት የማይታክታት ቆንጆ፡፡ ፍቅረኛ አይበረክትላትም፡፡ አቤት! ከአንዱ ወደሌላው ለመሸጋገር ያላት ፍጥነት! “ፍቅረኛዬ ነውብላ ያስተዋወቀችን ወንዶች ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው አንድ ነገር አለ፡፡ ልደቷን በፌሽታ ያከብሩላታል፡፡ አድሜዋንም ሆነ የተወለደችበት ቀን ግን ከራሷ በቀር በትክክል የሚያውቅ የለም፡፡ልደቷን በአመት ውስጥ አራት አምስቴ ልታከብር ትችላለች፡፡ (ቁጥሩ የሚወሰነው በአመት ውስጥ በተጃለሷት ወንዶች መጠን ነው)፡፡ ዕድሜዋ ግን ጨምሮ አያውቅም፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ እንደ ሰዓት ወደኋላ አድርጋ የሞላችው ይመስለኛል፡፡
(በአንዱ የልደቷ ፓርቲዋ ላይ በብዙ ጉትጎታ ተገኝቼላት ነበር፡፡ ቦሌ መስመር ካሉ አንድ ክለብ ውስጥ ነበር ድግሱ፡፡ ደጋሹም አዲሱፍቅረኛ፡፡ ሸከከኝ፡፡እጮኛዬን ብሉልኝ እጮኛዬን ጠጡልኝ፤ ፍቅረኛዬን አጫርሱኝ. . .” ብላ የጋበዘችኝ መሰለኝ፡፡ በቃ፤ ማንም ሳያየኝ ሹልክ ብዬ ወጣሁ፡፡ )
በሌላ ቀን ሳገኛት እንዲህ ስል ጠየቅኳት፡- “አዲስ ፍቅረኛ በያዝሽ ቁጥር ለምንድነው ልደትሽን እንዲያከብሩ የምታደርጊያቸው?!”
መልሷ በናቲ ዘፈን አሳወቀችኝ -
በቃ፤ በቃ፤ ዛሬን ኑር በቃ! . . .በቃ!
ለምንድነው የምትጨነቃው...
በቃ . . . . .”
በቃ! ይህ ሁሉ ልደት ለዚሁ ነው በቃ! የሁሉ መዝናናት ለዚሁ ነው በቃ! ይህ ሁሉ መነ....(እንዝለላት በቃ፡፡)
***
ኮመዲያን ልመነህ ታደሰንአዲስ ቪው ሆቴልበረንዳ ላይ ነበር ያገኘሁት፡፡ ጥቁር በጥቁር ለብሷል፡፡ ጥቁር ቦርሳ ... ጥቁር ባርኔጣ ...፡፡ . አድናቆቴን ስነግረው በትህትና አመስግኖ ተቀበለኝ፡፡ በርግጥ መታመሙን በሚደያ ሲነገር ሰምቻለሁ፡፡ ሕመሙ ግን የማገናዘብ ብቃቱና እና ጨርቁን አላስጣለውም፡፡
አንድ ነገር ግን አስተዋልኩ፡፡ ፀጉሩ ላይ ሽበት አይታይም፡፡ በርሱ እድሜ ካሉትም አንፃር ልመነህ አሁንም ወጣት ነው፡፡ ለጨዋታ በር መክፈቻ እንዲሆነኝ ስል ወጣትነቱ ጠብቆ የቆየበት ምስጢር ምን እንደሆነ ጠየቅኩት፡፡
(በመልሱ ተመራመሩበት፡፡)ትኩር ብሎ አይቶኝ ሲያበቃ እንደህ ሲል መለሰልኝ፡-
ቀላል ነው፡፡ ዕድሜህን እያሰብክ አትቁጠረው፡፡ እንዲያውም ፈፅሞ እድሜህ ስንት እንደሆነ እርሳው፡፡