አዳር
(የአጭር ልቦለድ ንድፍ)
ኄኖክ ስጦታው
----------------------------
ከምሽቱ 1፡30ሰዓት
“አባትህ ጋር ዛሬም አትሄድም?” አሳዳጊው ነበረች ጠያቂዋ፡፡ ታማሚ አባቱ ሆስፒታል ከተኙ ሰንበትበት ቢልም ፣ ሄዶ አለመጠየቁ ውስጥ ውስጧን እየበላው፡፡
“ብዙ ሰዎች ስለሚኖሩ የኔ መሄድ ጥቅም የለውም . . . ” ብሎ ወደ መኝታ ክፍሉ ገባ፡፡
* *
*
2፡30 ምሽት
ቴሌቪዥን ሊያይ ወደሳሎን ሲገባ፣ አክስቱ፡-
“አባትህን ጠየከው ተክሉ?”
ዝም አለ፡፡ ያውቃሉ፡፡ እንዳልጠየቀው፡፡ ለነገር መምዘዣ ብቻ ነው ጥያቄያቸው፡፡ አፍ አፉን ሲያዩ ቆይተው መልስ ሲያጡ፡-
“አረመኔነት ነው! አወቅን፣ ተማርን ስትሉ ልባችሁ ይደድራል፡፡ ቆይ፣ ለምን አልጠየከውም?”
ቃላቱን እየረገጠ “እኔን ሲያይ የሚድን ቢሆን ኖሮ ለምን ሆስፒታል መውሰድ አስፈለገ? ” አለ፡፡ በእጁ ምንም ሳይደገፍ ከመቀመጫው ተነሳ፡፡ ክፍሉን ለቆ ወጣ፡፡ እዚህ አላሳይም ቢሉኝም ጎረቤትም ቤቴ ነው፡፡
* *
*
የጎረቤት ጓደኛ እናት ገና እንዳዩት በጥያቄ አጣደፉት፡፡
“ተክሉ፣ አባትህ በጎ ናቸው?”
“ምንም አይልም፡፡”
“የደም ግፊቱ መጠን ቀንሶላቸው ይሆን?”
“መሰለኝ፤ እስካሁን ይቀንሳል፡፡”
“ጦስኝ ጠጡ ብያቸው ነበር፤ ጠጥተው ይሆን?”
“አ-ያ-ይ፣ የጠጣ አይመስለኝም፡፡”
“ከነጋ ሄደህ ነበር?”
“እኔ እንኳን አልሄድኩም፤ እነ እታባ ሄደው ስለነበር ነው፡፡” ዝምታ፡፡ የምሽቱን የቴሌቪዥን ዜና በግማሽ ልብ ተከታትሎ ወጣ፡፡
* *
*
ንጋት ላይ
የበሩ መንኳኳት ከጣፋጭ ህልሙ አናጠበው፡፡ እየተነጫነጨ “ማነው?” አለ፡፡
“ለባብሰህ እንሂድ ተክሉ፤ ጋሼ በጎ ማደራቸውን ዓይተው እንመለሳለን፡፡ ፈጠን በል፡፡” አሳዳጊው እታባ ነበረች፡፡
ዐይኑን ጨፈነ፡፡ ድጋሚ ተኝቶ ህልሙን ሊቀጥል ሞክሮ ሳይሳካለት ቀረ፡፡ አንሶላና ብርድ ልብሱን እያተራመሰ ከአልጋው ወረደ፡፡
* *
*
ጠዋት
አባቱ ከተኙበት የግል ክሊኒክ ደረሰ፡፡ ክፍሉ ሁለት የሕሙማን አልጋ ይዟል፡፡ ሰፋ ያለ ክፍል . . . ሁለት አልጋ፣ በአልጋዎቹ መሐከል የአቡጀዲ መክፈያ፡፡
ዐይኑ የሁለተኛው አልጋ ታማሚን የምታስታምም ቆንጆ ሴት ላይ አረፈ፡፡ በጎን እያየችው ነበር፡፡ ዐይናቸው ተጋጠመ፡፡ እሷ አቀረቀረች፡፡ እሱ አባቱ ላይ አተኮረ፡፡ አላስችልህ አለው፡፡ ዐይኑን መልሶ ወደ ልጅቱ ወረወረ፡፡ እንዳቀረቀረች ነው፡፡ እዚሁ እንዳደረች ያወቀው በተመሰቃቀለው ፀጉሯ እና በአለባበሷ ነው፡፡ ብትኳኳል ምን ያህል ታምር ይሆን? እግዚኦ!
ወደታማሚው ተጠግታ ስትናገር አዳመጠ፡፡ “. . . ብዘገይም እመጣለሁ፡፡”
ምን ማለቷ ይሆን? ታድር ይሆን? ጉድ ይታያል፡፡
ለእሱ የልጅቱ ቤተሰቦች እንደሆኑ የተሰሙት ሶስት ሰዎች ወደክፍሉ ገቡ፡፡ከቆይታ በኋላ፣ “እየሩስ፣ አንቺ ሄደሽ አረፍ በይ . . .”የሚል ድምፅ ሰማ፡፡ እየሩስ ላይ ዐይኑን ሲጥል ድንገት በሚመስል ሁኔታ ዐይኗን ስትወረውር በድጋሚ ተጋጩ፡፡ ቦርሳዋን ካስቀመጠችበት አንስታ ዕቃ እንደዘነጋ ሰው እያንገራገረች አልፋው ሄደች፡፡ ሊከተላት ፈልጎ ነበር፡፡ ምንነቱ ያልታወቀ የስሜት ገመድ አስሮ አቀረው፡፡
“ዛሬ እኔ ነኝ የማድረው!” አለ፡፡ የተናገረው ለአባቱ ቢሆንም ድምፁ ግን ለሌሎቹም ይሰማ ነበርና ንግግሩ ግርምትን ፈጠረ፡፡
“አሁንስ ልብ እየገዛ ነው” አሉ አክስቱ፤ “ተመስገን”፡፡
“ገብርኤል ጸሎቴን ሰምቶታል” አለች አሳዳጊው እታባ፡፡
* *
*
አብረው ሲያድሩ ምን እንደሚያወራት ሲያስብ ዋለ፡፡ አስተያየቷ ናፍቆታል፡፡ ቆንጆ እያዩ ማንጋት ጥሩ እንቅልፍ ተኝቶ ከመነሳት የበለጠ እንደሚሆን ገመተ፡፡
ትተኛ ይሆን? ከክፍሉ ማዕዘን ላይ አነስተኛ የስፖንጅ ፍራሽ አይቷል፡፡ አተኛኘቷ እንዴት ይሆን? አብሯት የሚያድር ሰው መቼስ አይኖርም፡፡ ምን አይነት ሞኝ ነኝ? እስከዛሬ ለምን አልሄድኩም ኖሯል? የመቆጨት ስሜት ዳበሰው፡፡
* *
*
2፡00 ሰዓት ከምሽቱ
ለማሸነፍ ወይም ለመሸነፍ ነበር ተዘጋጅቶ የሄደው፡፡ እታባ እሱ እስኪመጣ ስትጠብቀው አገኛት፡፡ ውስጡ ጭር ብሏል፡፡ እየሩስ የለችም፡፡ የምታስታምማቸውም ሕመምተኛ የሉም፡፡ አሳዳጊው ተሰናብታው ልትወጣ ስትል ያዝ አድርጎ፤ “ለሽንት ወጥተው ነው?” አለና ጠየቀ፣ ልቡ እየመታ፡፡
“ለቀዋል፤ የግል ክሊኒክ ክፍያ አማሯቸው ዛሬ ከሰአት ለቀቁ፡፡ እስካሁን የገባበት የለም፡፡ በል ደህና እደር፡፡”
ተፈጸመ