2016 ማርች 2, ረቡዕ

ጥያቄ ጥያቄ ጥያቄ

አንዳንዴ፣ ራሴን እንዲህ ስል እጠይቀዋለሁ፦
ሰፊውን አለም  ማን አጠበበው?

እውነት ጀግና ማለት ለአገሩ የሞተ ነው?  የገደለ?

ለአገር መሞት ማለት፣  በሌላው መገደል ብቻ ነው? ወይስ መግደል?

የመሞት ዓላማው ከመግደል በመጠኑም ቢለይም ስንኳን ፣ ሰውን ያክል አምሳያ መግደል በርግጥ ጀግነት ነው?  ወይስ አረመኔነት? ወይስ ተፈጥሯዊ የሆነ የማንነት መገለጫ?!

ለአገር መሞት ነው ጀግንነት? ወይስ ፣ በሰው መገደል ነው ጀግንነት?!

እራሱ «ጀግንነት» ምንድነው?!

ክብር ነው?
ስሜት ነው ?
ወይስ
ሌላ?

ጀግና ማለት፣ ላመነበት አላማ የተገደለ ነው?! ወይስ… የገደለ?!

ገድሎ የሞተው ፣ ሞቶ ካሸነፈው የሚለየው በምንድነው?
በሕይወት?
በሞት?
በድል?
በሽንፈት?

. .
.
.
.
.
.
.
.
. .
ከጦርነቱ የተረፈ በርግጥ ጀግና ነው ?!

.
.
በርግጥ የቱ ነው ጠባብ?!

አገር ከዓለም ይጠባል?!

ዓለም ከአገር ይሰፋል?!

አስፍቶ ለተመለከተው በርግጥ ዓለም የአገር አካል ናት? ወይስ

ዓለም ከሰፈር ትጠባለች?!

እናም፣ ጥያቄው ማብቂያ የለውም። መልሱ ግን ይብሳል¡

“ቀልድ የማያውቁ ቀልዶች”

“ቀልድ የማያውቁ ቀልዶች”

“ብሶት ሲኾመጥጥ የቀልድ ቡኾ ይሆናል።”

አባባሉ የአለማየሁ ገላጋይ ነው። ከዚህ በታች ላሉት “ቀልድ የማያውቁ ቀልዶች” መግቢያ የተጠቀመው።

✧✧✧
ወጣቱ የጋራ መፀዳጃ ውስጥ ቁጭ ብሏል። ብዙ ሰዎች እየመጡ ያንኳኳሉ፦

“ሰው አለ!” ወጣቱ ነበር። እንዲህ እየመለሰ ከተቀመጠበት ሳይነሳ፣ ከገባበት ሳይወጣ ብዙ ቆየ። በሁኔታው ብስጭትም፣ ህመምም የተሰማቸው አዛውንት ድምፃቸውን ጎላ አድርገው፦

“ማነህ የኔ ልጅ፣ መቼም ሽንት ቤቱ የጋራችን ነው። እኛም ልንጠቀም ነው አመጣጣችን። ለረጅም ጊዜ ስለቆየህ ምን አለ ብትወጣ?” አሉት።

ወጣቱ ከውስጥ ሆኖ ንቅንቅ ሳይል “ቢወጣስ የት ይኬዳል?”
✧✧✧

ሴትዮዋ ጤፍ አስፈጭተው በመመለስ ላይ ናቸው። ተሸካሚው ከፊት ከፊት እየሄደ ቤታቸውን በውል በወለማወቁ ፣ “ቤትዎ በየት በኩል ነው?” ሲል አቅጣጫ ይጠይቃቸዋል።

ሴትየዋ ለፀብ እንደተዘጋጀ ወገባቸውን ይዘው፦
“ምን አልክ? ቤቴን ነው የጠየኸኝ? እንዴት ያለኸው ነህ? የአንድ ሺ አምስት መቶ ብር ጤፍ እቤት ይቀመጣል? ቀጥታ ወደባንክ! ከዛ እየተቀነሰ ነው የሚቦካው”
✧✧✧

አባወራው ቤተሰቡን መመገብ ተስኖታል። ስለዚህ ያገኙትን ለልጆቹ እያቃመሱ ከባለቤቱ ጋር ጦም ማደር ግድ ሆነ። በይበልጥ ሚስቱ እጅግ ተጎሳውላለችና ቤተሰቡ ለጎረቤት አፍ እንደተጋለጠ አባወራው ጠርጥሯል። ስለዚህ አንድ ዘዴ ዘይዶ ጠዋት ሽማግሌ ሰበሰበ፦

“ምንድነው ችግሩ?” አሉ ሽማግሌዎች።

“ይኸው አንደምታዩት ነው። ብዪ እላለሁ፣ ብዪ እላለሁ…” አለ አሉ።

ሚስት አልተማከረች ኖሮ “የታል የሚበላው?” ብትል

“ሳገኝ አልኩሽ’ንጂ” አለ አሉ።
✧✧✧

አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ፣ በህብረተሰቡ የኑሮ ውድነት ደረጃ ላይ የአሰሳ ጥናት እያካሄደ ነው አሉ። ጥናት አድራጊው ወደ አንድ ሊስትሮ ጠጋ ብሎ አንዳንድ የመግባቢያ ጥያቄዎችን ካቀረበ በኋላ ፦

“እስኪ አሁን ደግሞ ወደ ቀን ወጪህ እንግባ”

“እሺ”

“ጠዋት ቁርስህን ምን ትበላለህ?”

“ሻይ በዳቦ”

“ምሳህንስ?”

“ባይ በዳቦ”

ጥናት አጥኚው፣ ልጁ በደሰቦና በሻይ ከዋለ እራቱን አጠራቅሞ በደንብ ሊበላ ነው ብሎ “እሺ ማሙሽዬ እራትህንስ?” ቢለው ልጁ ድንግጥ እያለ፦

“በልቶ ለመተኛት?!” ሲል መልሶ ጠየቀው…።
✧✧✧

"ቀልድ የማያውቁ ቀልዶች"
ዓለማየሁ ገላጋይ
"ኢህአዴግን እከሳለሁ" የወግ ስብስብ መጽሐፍ የተቀነጨበ

2016 ፌብሩዋሪ 28, እሑድ

የ“ሸኖ ቤት ሃሳቦች”

‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬የ“ሸኖ ቤት ሃሳቦች”
(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)

‪‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬
የ“ሸኖ ቤት ሃሳቦች” የማንበብ ሱስ የተጠናወተኝ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ነበር፡፡ በርግጥ ብዙዎቹ ሃሳቦች በጨዋ ቋንቋ “ፀያፍ” ተብለው የሚነገሩ ቢሆንም ብሶትና ምክርን በጨዋ ገለፃ የሚቀርቡ ሃሳቦችም አይታጡም፡፡ ያም ሆኖ ሕዝብ የሚጠቀምባቸው መፀዳጃ ቤቶች ስገባ በግድግዳው ላይ የተጻፉ ጽሑፎችን ማንበብ ያዝናናኛል፡፡

ሸኖ ቤትን ለመውደድ የፎክሎር ተማሪ መሆን አይጠይቅም፡፡ ከማይረቡ መፅሐፍት የተሻለ ምልከታን እና ሂዩመርን በሸኖ ቤት ሃሳቦች መቃረሜ በራሱ ለመፀዳዳት የማባክነውን ጊዜ የሚክስ ቁምነገር አላጣበትምና፡፡

“የዘርሲዎች ፍቅር” የተሰኘው ልቦለድ መፅሃፍ ላይ አንድ ገፀባሕርይ አስታውሳለሁ፡፡ በተለይ መፀዳጃ ቤት ስገባ ብዙ ጊዜ ትዝ ይለኛል፡፡ (አብሮኝ ይገባል - - ብል ይቀላል፡፡) ይህ ሰው ቁምነገርን የሚቃርመው ከመፀዳጃ ቤት ነው፡፡ ግድግዳ ላይ የሚጻፍ ግራፊቲ አልነበረም የሚያነበው፡፡ ሰዎች “ካካቸውን” የጠረጉበትን ወረቀት ሰብስቦ ኪሱ በመክተት እና በማንበብ ነበር፡፡

እነዚህ የግድግዳ ላይ ጽሁፎች ስለምንስ ይጻፋሉ? ግባቸው ምንድነው? ... ምክንያቱን እርሱት፡፡ ከየት መጡ የሚለው ምርምር አያሳስበኝም፡፡ ባለቤት አልባነታቸው በራሱ በቂ ምክንያት ነው፡፡ ምክንያት ከስም ይጀምራልና፡፡ ማንነቱን ለማወጅ የመፀዳዳት ባህሉን አደባባይ ላይ ከሚፈጣጥም ሰው ምንም አልጠብቅም፡፡ ማንነቱን በመጸዳጃ ቤት ግድግዳ ላይ የሚያሰፍር ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ግን ታዳሚ ነኝ፡፡ (እስቲ ዛሬ የተመረጡ ትውስታዎቼን በሹካ ጨልፌ ላካፍላችሁ፡፡)

ለመጀመሪያ ጊዜ ካነበብኳቸው ውስጥ የሚመደብ የመፀዳጃ ቤት ሃሳብ እንዲህ የሚል ነበር፡-

“God is dead!” -Nietzshce
“Nietzshce is dead!” -God

ያኔ ይህን ሳነብ ያልገባኝ ብዙ ነገር ነበር፡፡ በርግጥ ኒቼ “እግዚአብሔር ሞቷል” በሚለው ግንዛቤው ዛሬም ድረስ (ሞቶም) ያወዛግባል፡፡ በሕይወት በነበረበት ጊዜ “እግዚአብሔር ሞቷል ፤ ሰዎችም ነፃ ወጥተዋል...” እያለ መስበኩን የተረዳሁትም ከጥቅሱ በኋላ ነበር፡፡ አመታት አልፈው፡፡ የኒቼን ሞት ጠብቆ እግዚአብሔር እንዲህ ማለቱን ግን መፀዳጃ ቤት እንደ ትንቢት ቀድሞ አሳውቆኛል፡፡ ጥበብ ከጲላጦስ መፅሐፍ ላይ ይህን ጥቅስ ሳነበው አልደነቀኝም፡፡ ጥቅሱን ሲያስታውሰኝ ግን የሆነ ነገር ግን ሸቶኝ ነበር፡፡ ያም ጠረን፣ ይህን አባባል ያነበብኩበት መፀዳጃ ቤት አጉል ጠረን ነበር፡፡

በአንድ ኮሌጅ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ያነበብኩት ደግሞ እንዲህ የሚል መልዕክት ግድግዳው ላይ ተፅፎ አነበብኩ፡- “ምን ግድግዳው ላይ ታፈጣለህ!? አርፈህ አትፀዳዳም!?” ሆሆሆ... ሰዉ ጨምሯል!

በሌላ ዩኒቨርስቲ መፀዳጃ ቤት ውስጥም እንዲህ አይነት ትዕዛዝ አጋጥሞኝ እንደነበር አልረሳውም፡፡ በደቃቅ ጽሑፍ የተጻፈ መልዕክት ከመጸዳጃው በር ላይ ሰፍሮ አየሁና ከቅምጤ በመጠኑ ብድግ ብዬ ላነብ ስሞክር ያገኘሁት መልዕክት አስደንግጦ “የሚያስቀምጥ” ነበር፡፡ሃሳቡ እንዲህ የሚል ነበር፡- “ሰው ማለት አንተ ነህ፡፡ አሁን ወደነበርክበት ተመልሰህ አርፈህ እራ! ” የሚል ትዕዛዝ ፡፡

የሸኖ ቤት ግድግዳ ላይ ከተፃፉ ሃሳቦች ሌላው የማርከኝ እንዲህ የሚል ነው ፡-

“ቺክህን ጥሩ ነገሮች እንዴት እንደምታሳያት በማሰብ አትጨናነቅ፡፡ አሁን እየጣልክ ያለውን እንቁላል ግን ጠብሰህ እንዳታበላት አደራ! ስትጨርስ ውሃ ድፋበትና ከሌሎች እይታ ሰውረው!”

የሸኖ ቤት ግድግዳ ሃሳቦች አንዳንዴም ፍልስፍና ይቃጣቸዋል፡፡ በአንድ የሕዝብ መፀዳጃ ቤት ውስጥ ያነበብኩትሃሳብ ለዚሁ ምስክር ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-

[“መኖር ማለት፣ በምታባክነው ጊዜ የምታጣው ብኩንነት ነው፡፡ ለመኖር ስትል ከምታባክናቸው ሰዓታት ትልቁን ቦታ የሚይዘው ምን እንደሆነ ታውቃለህ?”

“አውቃለሁ” ካልክ ተሳስተሃል! በዚህ ሰዓት ማራት አልነበረብህም!!”]

ትውስታዬን ተደብቄ በተጠቀምኩበት የሴቶች መጸዳጃ ቤት ግድግዳ ላይ ባነበብኩት ልቋጭ፡፡

“በወንዶች ከሚነገሩ ብ-ዙ ውሸቶች መሃከል የማላምነው “ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም” የሚሉትን ብቻ ነው፡፡”