“ቀልድ የማያውቁ ቀልዶች”
“ብሶት ሲኾመጥጥ የቀልድ ቡኾ ይሆናል።”
አባባሉ የአለማየሁ ገላጋይ ነው። ከዚህ በታች ላሉት “ቀልድ የማያውቁ ቀልዶች” መግቢያ የተጠቀመው።
✧✧✧
ወጣቱ የጋራ መፀዳጃ ውስጥ ቁጭ ብሏል። ብዙ ሰዎች እየመጡ ያንኳኳሉ፦
“ሰው አለ!” ወጣቱ ነበር። እንዲህ እየመለሰ ከተቀመጠበት ሳይነሳ፣ ከገባበት ሳይወጣ ብዙ ቆየ። በሁኔታው ብስጭትም፣ ህመምም የተሰማቸው አዛውንት ድምፃቸውን ጎላ አድርገው፦
“ማነህ የኔ ልጅ፣ መቼም ሽንት ቤቱ የጋራችን ነው። እኛም ልንጠቀም ነው አመጣጣችን። ለረጅም ጊዜ ስለቆየህ ምን አለ ብትወጣ?” አሉት።
ወጣቱ ከውስጥ ሆኖ ንቅንቅ ሳይል “ቢወጣስ የት ይኬዳል?”
✧✧✧
ሴትዮዋ ጤፍ አስፈጭተው በመመለስ ላይ ናቸው። ተሸካሚው ከፊት ከፊት እየሄደ ቤታቸውን በውል በወለማወቁ ፣ “ቤትዎ በየት በኩል ነው?” ሲል አቅጣጫ ይጠይቃቸዋል።
ሴትየዋ ለፀብ እንደተዘጋጀ ወገባቸውን ይዘው፦
“ምን አልክ? ቤቴን ነው የጠየኸኝ? እንዴት ያለኸው ነህ? የአንድ ሺ አምስት መቶ ብር ጤፍ እቤት ይቀመጣል? ቀጥታ ወደባንክ! ከዛ እየተቀነሰ ነው የሚቦካው”
✧✧✧
አባወራው ቤተሰቡን መመገብ ተስኖታል። ስለዚህ ያገኙትን ለልጆቹ እያቃመሱ ከባለቤቱ ጋር ጦም ማደር ግድ ሆነ። በይበልጥ ሚስቱ እጅግ ተጎሳውላለችና ቤተሰቡ ለጎረቤት አፍ እንደተጋለጠ አባወራው ጠርጥሯል። ስለዚህ አንድ ዘዴ ዘይዶ ጠዋት ሽማግሌ ሰበሰበ፦
“ምንድነው ችግሩ?” አሉ ሽማግሌዎች።
“ይኸው አንደምታዩት ነው። ብዪ እላለሁ፣ ብዪ እላለሁ…” አለ አሉ።
ሚስት አልተማከረች ኖሮ “የታል የሚበላው?” ብትል
“ሳገኝ አልኩሽ’ንጂ” አለ አሉ።
✧✧✧
አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ፣ በህብረተሰቡ የኑሮ ውድነት ደረጃ ላይ የአሰሳ ጥናት እያካሄደ ነው አሉ። ጥናት አድራጊው ወደ አንድ ሊስትሮ ጠጋ ብሎ አንዳንድ የመግባቢያ ጥያቄዎችን ካቀረበ በኋላ ፦
“እስኪ አሁን ደግሞ ወደ ቀን ወጪህ እንግባ”
“እሺ”
“ጠዋት ቁርስህን ምን ትበላለህ?”
“ሻይ በዳቦ”
“ምሳህንስ?”
“ባይ በዳቦ”
ጥናት አጥኚው፣ ልጁ በደሰቦና በሻይ ከዋለ እራቱን አጠራቅሞ በደንብ ሊበላ ነው ብሎ “እሺ ማሙሽዬ እራትህንስ?” ቢለው ልጁ ድንግጥ እያለ፦
“በልቶ ለመተኛት?!” ሲል መልሶ ጠየቀው…።
✧✧✧
"ቀልድ የማያውቁ ቀልዶች"
ዓለማየሁ ገላጋይ
"ኢህአዴግን እከሳለሁ" የወግ ስብስብ መጽሐፍ የተቀነጨበ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ