2015 ጃንዋሪ 8, ሐሙስ

‘ከዕለታት አንድ ቀን’ (ኄኖክ ስጦታው)




ያው እንደ ልማዴ፣ በፅሞና ሳለሁ፣
ዝምታን ለብቻው ፣ ርጋታን ለብቻው፣ እያዳመጥኩ ሳለሁ—
የመቃብሩ በር ሲንኳኳ እሰማለሁ።

አንዳንዴ ስመሰጥ ፣
ትዝታችን እንዳይሞት፣ የቀበርኩት እለት
የአንድ ቀን ድምር፣ የአሃዝን ግዝፈት
ገንኖ ይታየኛል፣ ገና ሳልል ሁለት።

አንድ!
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ሲደመር ‘ከዕለታት’
አንዳለኝ እያልኩኝ፣ ዝም ብሎ ማስላት።

አንድ!
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ የተዋወቅንበት።
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ የተጣላንበት።
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ ተሳስመን ነበር።
ምራቅሽን ቀምሼ፣ ምራቄን ቀምሰሽው፣ "አቤት መጣፈጡ" ማለታችን ሳይቀር፣
‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ ካንዱ ጋር ሲደመር፣
ደግሞም በሌላ ቀን፣ ተጋጭተን በነገር
ማሩ ምራቅሽን፣ ተፍተሽብኝ ነበር።

አንድ!


‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ፣ እንዲህ ለብቻዬ፣
አንድን አሰላለሁ፤ አንድ አለችኝ ብዬ።
አንድ ዝምታ ነው። አንዱ ነው ርጋታ
አንዱ ካለአንዱ፤ አይቆምም ለአፍታ ።
          እና።
         ርጋታን ሳዳምጥ፤ ዝምታን ሳናግር ፣
         ከመቃብሩ ቤት፣ ይሰማኛል ጩኸት፣
‘ክፈት! ክፈት! ’ የሚል…
‘ክፈት ይህን በር!’
ያንቺ ድምፅ ነበር።
ድምፅሽን ስሰማ  ፤ "ክፈት" ስትይ "ክፈት"
                           ያስታወሰወኩት ነገር
ካቅሜ በላይ ሆነሽ፣ "ችግሬ" ያልኩሽ እለት
‘ከዕለታት አንድ ቀን’፤ ላንቺ መቀበሪያ
                           ጉድጓዱን ማስኩበት።

ምክንያቱም፦
አንቺን ከዝንጅብል፣ ያቆራኘ ምስጢር
አፈር ነው ህይወትሽ ፣ አትሞችም በቀብር።

አንቺ የኔ ችግር!
ባክሽ ፣ባክሽ ግቢ፤ "ምሳጤ" ና ውጣ
ሁሉም ይዘነጋል፣ ችግሬ ስትመጣ።
______
ኄኖክ ስጦታው

2015 ጃንዋሪ 2, ዓርብ

ይመሻል ፤ ይነጋል...(ኄኖክ ስጦታው)



ጊዜ ለውጥ አልባ ፤ የአሁን ጉዞ ቅጣይ
የቆመ ዑደት ነው ፤ ምንም ሲጓዝ ቢታይ ።
አዲስ ነገር ብርቁ ፤ ሰው ዘመን ይዋጃል
እንኳን አዲስ ዘመን
ወለሃንቲ የለም ፤ አዲስ ቀን የሚባል ።

ለምሳሌ ፦

የዕድሜ ግስጋሴ ፣ በመኖር ይለካል
በመሞት ይዘጋል ።

ይመሻል ፤ ይነጋል...

መሽቶ እንደነጋው ፤ ያው ነግቶም መምሸቱ
የቆመ ሀቅ ነው ። የታለ ዑደቱ?

ለምሳሌ ፦
ዛሬ
ልክ እንደ በፊቱ ፣
ይነጋል ፤ ይመሻል
ከምናውቀው ውጪ ፤ አዲስ ዑደት የታል?
በርግጥ ያንተ ለውጥ ፣ ጊዜን ይለውጣል?

መምሸትና መንጋት ፣ መንጋትና መምሸት ፣ የቆመ ሂደት ነው
መጥቶም እንደመሄድ ፤ ሄዶም እንደመምጣት ፣ የማልቀበለው ።

በቀጠለው ነገ ፣ አዲስ ቀን ጠብቆ
በቀጠለው ነገ ፣ አዲስ ተስፋ ናፍቆ
በቀጠለው ነገ ፣ ብርታትን ሰንቆ
የዛሬውን ሌሊት ፣ የሚተኛ ሞልቷል...
ጊዜ ግን ባለበት ፤ ጉዞው ይቀጥላል...

ለምሳሌ ፦
አሁን!

ቸጨ∴የኄኖክ diary