እሑድ 10 ሜይ 2026

በተረት ምሳጤ

(ኄኖክ ስጦታው)


የተረቱ ዓለም ይበዛዋል ትንግርት፣
ጉንዳንና ዝኆን ፍቅር የሰሩ ዕለት
በምድር ተቆጠረ፣ አንድ ጣፋጭ ሌሊት።
* *
ነገሩ ነው እንጂ፣ የትዝታ ዳራ
አንዲት ጣፋጭ ሌሊት፣ ታጭታ ለመከራ፤
አቅም ያለውን ሰው፣ ሐዘን ማቅ አልብሶት
ዛሬውን ለመቅበር፣ ይቆፍራል ብሶት።
* *
ደግሞም አንዲት ሌሊት፣ የእድሜ ቁንጣሪ
በተስፋ ተሞልቶ፣ በምኞት ለጦዘ፣ ቢጤው አፍቃሪ
መለያየት ማለት፣ የዘመን ቁስል ነው፣ ሕልውን ሰባሪ።
* *
እናም በተረቱ፣
አንዲት ጣፋጭ ሌሊት፣ በቅፅበት ያለፈች
የጉንዳንን ሕይወት፣ በፍፁም ቀየረች
ከእንቅልፉ ሲነቃ፣ ዝኆኗ ሞታለች!
***
ለብርቱ ገበሬ፣ ሲያምርለት መኸሩ
ተስፋና ስጋት ነው፣ ውሎ’ና አዳሩ፤
እንደመልካም ቅዠት፣ ደስታ እንደማጠሩ
ክፉ ቅዠት ሲሆን፣ ይረዝም የለ አዳሩ?!

ጉንዳንም ያነባው፣ ያዘነው አምርሮ
መቅበር ቢሳነው ነው፣ እድሜ ልክ ቆፍሮ።
ያንዳንድ ሰው ኑሮ ይሄንን ይመስላል
ሌላውን ለመቅበር እድሜውን በሙሉ ጉድጓድ ይቆፍራል።

ጉንዳን ነገር ገባው...
መጥፎም ሆነ መልካም፣ ደስታና መከራ
ማርም ሆነ ኮሽም፣ ጣፋጭ ከመከራ
ለብቻ አይገፋም፤ ጓደኞቹን ጠራ!
*
ተረቱ ነው እንጂ፣ የሚሰብክ ህብረትን
አጀብ የሚያበዛው፣ ለሙት አካል በድን፤
የቆመን ለመጣል፣ ሺህ ምንተሺህ ቢያብር
የሰው ልጅ ከጉንዳን፣ አይማርም ፍቅር።