በእጅ ያልተቀረፀው የአበበ ቢቂላ ሐውልት
ልክ የዛሬ አርባ ዓመት፣ ከማራቶኑ አምበል ሻምበል አበበ ቢቂላ ቀብር መልስ፤ ኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ጸጋዬ ገብረመድህን "አበበ እንጂ መቼ ሞተ!!" ሲል የፃፈው ሥነግጥም እንዲህ ብሎ ይጀምራል፣ እንዲህ እያለ በዜማ ይፈሳል
በቅፅበት ፀንሶ ሞቱን
ድፍን አለም ደፍቶ አንገቱን
በልቡ ቀርፆት ፀሎቱን
በህሊናው ነድፎት ስሙን
በገፁ ፅላት ታሪኩን፡፡
አእዋፍን በደመና፣ ጀግናን በምድር ያስደነቀ
ማራቶን ጮራው ጠለቀ
በራሪው ኮከብ ወደቀ፡፡
በቃ ጀግናው ተከተተ
ይኸው የማይሞት ሰው ሞተ
ብለን አንበል እባካችሁ፤
አበበ ተስፋ ነውና
ተስፋ አይቀበርምና፡፡
“ከእንጨት መርጦ ለታቦት፣ ከቃል መርጦ ለኪነት” እንዲል ስመጥሩ ብዕረኛ ዮሐንስ አድማሱ፤ በቅፅበት ፀንሶ ሞቱን የሚሉት የግጥሙ የመክፈቻ ቃላት የዚያን ታላቅ ሯጭ ህይወት በምልዐት ለመወከል የሚችል ጉልበት አላቸው፡፡ ቅፅበት ማለት ፍጥነት ነውና፤ አቤም ክብረወሰን ሰባሪ ፈጣን አትሌት ነበረና። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ሩጫው ሁሉ ህይወቱም ቅፅበታዊ ነበረች፤ ብልጭ ብላ ድርግም ያለች። በራሪ ኮኮብ ነበረና፡፡ በነሐሴ 30 ቀን 1925 ዓ.ም በጃቶ ቀበሌ (ደብረብርሃን አውራጃ) እትብቱ ተቀብሮ፤ ጥቅምት 15 ቀን 1966 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ የመጨረሻ ትንፋሹን ሲጨልጥ፤ ገና አርባ አንድ አመቱ ነበር፡፡ ከአራት አመታት በላይ አሰቃይቶ ወደሞቱ የወሰደው ጎዳና አሁንም የፍጥነት ነገር አለበት -የቅፅበት! ሰሎሞን ተሠማ ጂ እንደሚከተለው ይተርከዋል፤
“መጋቢት 14 ቀን 1961 ዓ.ም ቀትር ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አምስት ኪሎ ካምፓስ የአሁኖቹ የተማሪዎች መኖረያ ሕንፃዎች የተሠሩበት ቦታ ላይ መሠረት ለመጣል ጉድጓድ ተቆፍሮ ነበር፡፡ ሦስት የፖሊስ ባልደረቦችን ተኩስና ዱላ የሚሸሹ ተማሪዎች እየሮጡ የአበበ ቮልስ ላይ ሊወጡባት ተጠጓት፡፡ አበበ በፍጥነት መሪውን ጠመዘዘ፡፡ ሆኖም በስተቀኙ በኩል የነበረውን ለግንባታ የተቆፈረ ጉድጓድ አላስተዋለውም ነበር፡፡ ነገሮች በፍጥነት ተከሰቱ፡፡….. የአበበ አከርካሪ አጥንት (Spinal Cord) ተቀጨ፡፡”
ህይወትን በቅፅበት፤ በቅፅበትም ወደሞት፡፡ በቅፅበት ፀንሶ ሞቱን ማለት ይኼው ነው፤ በህይወት እና በሞት መካካል ልዩነት የሌለ እስኪመስል ድረስ። ታላቁ ከያኒ ገብረክርስቶስ ደስታ በስንኝ እንደተፈላሰፈው
በመኖር በመሞት
ልዩነት የሌለው
ቢኖርም ልዩነት
ከነፋስ ከውሃ መልኩ የቀጠነ
አይን የማይጨብጥው።
ህይወትን ሲያነቡት ወደግራ ሞት ነው።
በ1952 ዓ.ም የመጨረሻ ቀን የዕንቁጣጣሽ ዋዜማ ዕለት፤ ሮም ላይ በኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ተንቆጥቁጦ፤ ይኼንንም ገድል ከአራት አመት በኋላ ቶኪዮ ላይ በመድገሙ -- ያውም ትርፍ አንጀት ለማስወጣት ቀዶ ጥገና ከአደረገ ስድስት ሳምንታት በኋላ! -- ብቻ አይመስለኝም አእዋፍን በደመና፣ ጀግናን በምድር ያስደነቁ እግሮቹ በሞት ሲታበቱ፤ “አበበ እንጂ መቼ ሞተ!!” ብለን እንድንል የጸጋዬ ብዕር የሚማፀነው። እርግጥ ነው አበበ አብቧል። ራሱን በእጥፍ ድርብ አባዝቷል። ከምሩፅ ይፍጠር እስከ መሃመድ አማን፤ ከደራርቱ ቱሉ እስከ ጥሩነሽ ዲባባ ድረስ ያሉትን የአገራችንን ውድ ልጆች ስፖርታዊ ድሎች ስንቆጥር፤ የአበበንም ዘር ፍሬዎች አብረን እንቆጥራለን። ነገር ግን አበበ ቢቂላ ከሜዳሊያ ሠንጠረዥ በላይ ነው፣ በተራ አኃዝ ከቶም የማይለካ። ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው የአበቦችን ውበት ለማድነቅ የተጠቀሙበትን ሐረግ ልዋስና፤ አቤ “ከሥፍር ባሻገር’’ ነው።
ለምን ይሆን ግን አበበ ቢቂላ ምናባችንን ሰቅዞ የመያዝ አቅሙ ዘመን የማያደበዝዘው፣ የጊዜም ሂደት የማያበልዘው? ማራቶን በባዶ እግሩ ሮጦ ማሸነፉን፥ በባዶ እግራቸው ቆንጥር ለቆንጥር ተፋልመው ነጻነታችንን በደማቸው በዋጁልን አባቶቻችን አምሳል ቀርፀን የጀግንነት ጥንፍ አርገን ማየታችን? ወይንስ ቢኒቶ ሙሶሊኒ ፋሺስታዊ ጦሩን ወደ ኢትዮጵያ በላከባቸው የሮም አደባባዮች፡ ቀጥ እና ኮራ ብሎ በድል አድራጊነት መንፈስ መሮጡን ባሰብን ቁጥር፥ ከቶም ሞቶ የማይሞተውን የአገር ፍቅር ስሜታችንን ማላወሱ? አሊያስ ለጥቁር አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ፣ በወቅቱ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ሲማቅቁ የነበሩት አፍሪቃውያን ወንድሞቻችንን በ “ይቻላል” ስሜት አንቅቶ፤ የልባቸውን መቅረዝ በተስፋ ዘይት መሙላቱን ከታሪክ ስላነበብን? ወይስ የአትሌቲስክ ድሎቻችንን ወደሌላ መስክ “መመንዘሩ” አንደማይገደን አልፎ አልፎ የሚታየን ጣፋጭ ራዕይ ቀዳማዊ ደራሲ ስለሆነ?
“አበበ ተስፋ ነውና” የሚለው የጸጋዬ ሐረግ፤ ወዲ ቢቂላ ሯጭ ብቻ ሳይሆን የዘመኑ መንፈስ (zeitgeist) አብይ አካል እንደነበር ያመለክታል። ከአዝማሪ ቤቱ ሆይሆይታ (“ያገባሻል ያገባሻል፤ አበበ ቢቂላ ያገባሻል፤ጥላሁን ገሠሠ ይድርሻል’’ የሚለውን ህዝባዊ ዘፈን ያስታውሷል) እስከ ለውጥ አራማጅ የተማሪዎች ንቅናቄ ድረስ ያ ብጡል (mighty) አትሌት ስሙን ለድፍን አገር አውሶ ነበር። ለዚህ አባባል ማስረጃ ያህል፤ በኅዳር 1957 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ተማሪዎች ለጀግናው አትሌት የክብር ግብዣ ባደረጉበት ዕለት፤ ትንታጉ ገጣሚ ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) ምነው አገራችን እንደአበበ ያሉ በርካታ ሁነኛ ሰዎች በኖራት በሚል የቁጭት መንፈስ “ኧረ የወንድ ያለህ!” ብሎ ካሰማው የብዕር እንጉርጉሮ በጥቂቱ እንንጠቅ
ለወገኑ እሚቆጭ ሁለተኛ ሙሴ
አንደአበበ ያለ የማይል ለራሴ
ብታገኝ አገሬ ምንኛ ደስ ባላት ውስጣዊቷ ነፍሴ።
…..
እንዳበበ ያለ ጀግናና ጎበዝ ልጅ ቢኖር ኖሮ ለሀገር
የጎሳ ልዩነት መች ያናጥር ነበር?
የተዋረድ ኑሮስ መች ይሰፍን ነበር?
እውነትን ውሸት መች ያደባይ ነበር?
ፉራፉሬስ ሆነን መች እንዞር ነበር?
በየካቲት 1999 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ ቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ለአበበ ቢቂላ እና ለማሞ ወልዴ መታሰቢያ የቆሙት ሐውልቶች ባልታወቁ ወንጀለኞች እጅ መፍረሱ አስደንጋጭ እና አሳዛኝ ዜና ሆኖ ነበር። ቢሆንም የአበበ ቢቂላ ገድል “ከሥፍር ባሻገር’’ ነውና፤ እልፍ አዕላፍ ዜጎች በእጅ ያልተቀረፁ በጊዜም ሆነ በውለታ ቢስ ወገን መዶሻ የማይናዱ ቋሚ ሐውልቶች በልባቸው ፅላት አኑረውለታል፡፡ ሩሲያዊው ገጣሚ አሌክሳንደር ፑሽኪን ለነገስታት እና ለምድር ኃያላን ማስታወሻ ከቆሙት ግዙፍ ሐውልቶች ይልቅ፤ ለሰው ልጆች ነፃነት ወግኖ የጻፋቸው ግጥሞቹ በእጅ ያልተሰራና ከቶም የማይፈርስ ሐውልት ሆነው ዘመንን ተሻግረው እንደሚዘልቁ የተነበየውን፤ አያልነህ ሙላቱ እንደዚህ አርጎ ወደ አማርኛ መልሶታል
ግርማ ሞገስ ያለው እጅግ የሚያኮራ
በእጅ ያልተቀረፀ በሰው ያልተሰራ
ሐውልት አቁሜያለሁ ለመታሰቢያዬ
ለሚመጣው ትውልድ ለወደ ኋላዬ።
ለአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ከቆሙ በእጅ ያልተቀረፁ ሐውልቶች መካከል፣ የጸጋዬ ገብረመድህን “አበበ እንጂ መቼ ሞተ!” ሥነግጥም እጅግ ውቡ እና ጠንካራው ይመስለኛል።
የጎበዝ ነባቢት ነፍሱ
የሰው መዝርዕቱ አርአያ፤ የማይታጠፍ መንፈሱ
በጥራት የታጠፈለት፤ የምድር አጥናፍና አድማሱ
የየብስ የአየሩ ነበልባል
የማራቶን እፁብ አይጣል
የምድር አለሙ ገሞራ
አገሩን በክብር ያስጠራ
ሳተናው እግረ ጆቢራ
ሎጋ ቢቂላ ዋቅጂራ፤
የጎበዛዝ ንጥረ ወዙ
የተስፋ ብርሃን መቅረዙ።
ስሙን ላገር ስም ሰይሞ፤ የምስራች ያስደወለ
ስንቱን ስንቱን ልበ ሙሉ፤ ከአድማስ አድማስ ያስከተለ፡፡
የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ
ያረጋት የኦሎምፒክ አርማ
በወገኖቹ ልቦና፤ ቀና ኩራት ያሳደረ
እንደፍላፃ በአክናፉ፤ የአየርን ሰርጥ የሰበረ
የፍስሃዋን አዋጅ ለአለም፤ በአቅመ ወዙ ያስነገረ
በአገር ፍቅር ልቡን ሞልቶ፤ ላቡን ነጥቦ የዋተተ
የአለምን ጀግና በአድናቆት፤ በቅን ቅናት ያስሸፈተ
አልሞተም እንበል እባካችሁ፤ “አበበ እንጂ መቼ ሞተ!”
ግሱ
ጥቅምት፤ 2006 ዓ.ም
ሀገረ-እንግሊዝ
(የወደር የለሹን አትሌት አርባኛ የሙት ዓመት፣ በባዶ እጅ ላለማዘከር የተደረገ ግለሰባዊ መፍጨርጨር)