2016 ሜይ 27, ዓርብ

ጭምብል

ጭምብል

በፈገግታ ተከልለን፣ የክፋት ጥርሶች ስናገጥ
እኩይ ሥራችን ገፅ ሆኖ፣
            አድርጎናል መልከ-ቅይጥ።
“አስመሳይነት”
               መንታ ስለት፣
                          በጥርስ ሞረድ ሲሞዠጥ
አንደበት በውሸት ሲከፈት፣ ገፅ በጭምብል ሲለበጥ
ሰይፍ ይወጣል ከአፎት፣ መልካም ልቦችን የሚቆርጥ።

~Paul Laurence Dunbar
ውርስ ትርጉም ፦ ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ

2016 ሜይ 26, ሐሙስ

"የለ_ዓለም"

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ) 

"ከዚህ ቀደም በሰው ልጅ በማንም ያልተሞከረ አዲስ ሃሳብ እና የአፃፃፍ ስልት እውን አለ?"

የአጻጻፍ ቅርፅ ሃሳብ የማስተላለፊያ መንገድ ነው። የስነጽሑፍ አላባዊያን የተውጣጡት፣ ከተለያዩ ቀደምት ፀሐፍት ስራዎች ተወራራሽ መዋቅረ ውጤት (ውበት) አንፃር መሆኑም የሚያሳየው ይሄንኑ ነው። 

ይነስም ይብዛ፣ እያንዳንዱ ሰው በተመሳሳይ ሃሳብ ላይ በተመሳሳይ መንገድ ንፅረተ—ዓለምን ለመግለፅ ቢሞክር አንዳች ልዩነት አያጣውም። kahlil gibran "jesus the son of man" ላይ ሃሳቡን ለማስተላለፊያነት ከተጠቀመበት ቅርፅ በዋንኛነት ሊገለፅ የሚችለው ተፅፎ ያነበበውን ታሪክ መድገም ወይም መተንተን አልነበረም። በአንፃሩ ግን ተፅፎ በነበረው ውስጥ ጥያቄ ጭሮበት ያለፈውን ታሪክ እስከ ምናቡ ጥግ አሰላስሎና ጥያቄ ለነበረው መልስ ሰጥቶ፣ ወይም፣ መልስ ለነበረው ታሪክ አንዳች መጠይቅ በመቀመርና ተጨማሪ ታሪክን በማዋቀር ላይ የተመሰረተ አጻጻፍ ስልት ነበር የተጠቀመው። 

ሌሎች ፃህፍት በርሱም ሆነ የፈጠራ ስራዎቹ ላይ "ተፅእኖ" እንዳላሳደሩ የሚናገሩት ውስጥ አዳም ረታ ተጠቃሽ ነው። ታዲያ መንገዱም ሆነ (እውነቱ) ከ"ከየት መጣ" ጥያቄ "እከሌ" ተብሎ የሚጠቀስ ተዛማጅ አካል አለመኖር አይደለም። በምን ወጣ እንጂ።

የፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍ እና ታይታኒክ ፊልም ታሪካዊ መዋቅራቸው ተመሳሳይ ነው ማለት፣ የታይታኒክ ፊልም በፍቅር እስከ መቃብር መፅሀፍ ላይ ተፅእኖ አሳድሯል ማለት ነው? 

ችግሩ የተዳቀሉ ቅርፆች ስርወ ምንጭ፣ እከሌ የሚባል አንድ ሰውን ለማመሳከር ከአለመቻል ይወለዳል። ይህ ውስብስብ "ወጥነት" ሳይሆን በግልፅ ቃል ‘ቅይጥነት’ ነው። ቅይጥ ውጤት ደግሞ በቀያጭ ግብአት ተፅእኖዎች ሊያመልጥ አይቻለውም። 

አዲስ ቅርፅ ከየት ተወለደ ጥያቄን ፍፁም የሚያደርገው ሐቅ ግን አለ። ሃሳብን (ጭብጥ) እንደ ፅንስ፣ ውልደቱንም እንደ ውበት (ቅርፅ) ብንወስደው የውሻ ልጅ ቡችላ…ነው፤ የቡችላስ አባቱ ማነው?! ያስረገዘው ነው ወይስ ያደረገው?! የቡችላ አባቶች ብዛት፣ የእናቱን ማንነት ከጥርጣሬ ላይ አይጥልም። 

የሐሳብ ምንጭም ሆነ ድርቅ፣ ሰው ነው። ምልከታ የማንም ሆነ የምንም፣ ከአንድ ገበታ አብረው እንደተመገቡ ሁለት ሰዎች ይመሰልብኛል። 
አበላሉ እንዳለ ሆኖ አወጣጡ ላይ ግን ብዙ ልዩነት አለ። 

አዲስ መንገድ ሆነ አዲስ ሃሳብ "የለ_አለም!"