ልጥፎችን በመለያ ልቦለድ በማሳየት ላይ። ሁሉንም ልጥፎች አሳይ
ልጥፎችን በመለያ ልቦለድ በማሳየት ላይ። ሁሉንም ልጥፎች አሳይ

ሰኞ 9 ጃንዋሪ 2017

በእንክርዳድ ማሳ ላይ (ስኬች)

(ኄኖክ ስጦታው)

*1*
ስንዴ እና ገብስ እንክርዳድ ተነቅሎ ከተዘጋጀው የማሳ ላይ ተዘሩ።

“ሞተን እየተቀበርን መሆን አለበት ” አለ ገብስ።

“አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” የተባለው ቃል እየተፈፀመ ነው። ሲል ስንዴ መለሰ።

*2*

ጥቂት ዘሮች በወፎች ተበሉ። ብዙዎችም መበስበስ ጀመሩ። መበስበሳቸው የህይወታቸው ፍፃሜ አልነበረም። የሌላኛው ሕይወት ጅማሬ እንጂ።

*3*
የማቆጥቆጥ ዘመን

“እነሆ የመጨረሻው ዘመን ፍሬዎች እንሆን ዘንድ ለፍርድ ተነስተናል።” ሲል አንዱ ስንዴ አጠገቡ ላለው ሌላ ስንዴ ተናገረ።

“አይደለም። ፀድቀን ነው። ዙሪያህን ተመልከት! እኛ ብቻ አይደለንም የፀደቅነው። ከመካከላችን ጥቂት ወንድሞቻችን ፀድቀዋል።”

ገብስ ተናገረ “እኔ ከመሰሎቼ ነጥሎ ከናንተ መካከል እንድበቅል ያደረገው ፈጣሪ ተቆጥቶ ቢሆን ነው።” አለ ዙሪያውን ለከበቡትን ስንዴዎች።

እንክርዳድ ግን ከመካከላቸው ሆኖ“ወዶኛልና አዳነኝ” እያለ ጮክ ብሎ ይዘምር ነበረ።

ሰኞ 22 ፌብሩዋሪ 2016

ሠአት ሠሪው

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)

ሠአት ሠሪው ደጃፍ ላይ ቆሜያለሁ። ከውጭ ሆኖ ለሚመለከት ሰው ምንም የሚማርክ ውበት ላትመለከት ይችላል። የደጁን መስታወት ታክኮ የቆመው መደርደሪያ ያገለገሉ ሰዓታት ማረፊያ ሁነዋል። የተበላሹ፣ የተጠገኑ፣ የማይጠገኑ፣ ያልተጠገኑ፣… ሠአቶች ተሞልቷል። እኔ እራሴ ሁሌ የማያቸው ሰዓቶች እዚህ ምን እንደሚሰሩ አይገባኝም። አሰሪዎቹ ቢወስዷቸውና ሰዓት ሠሪው ያገልግሎቱን ቢያገኝ መምረጤን ግን አልሸሽግህም። 

መስታወቱ ላይ ሶስት ጥቅሶች አሉ። በእጅ የተሞነጫጨሩና ለንባብ የማይማርኩ ቢሆኑም፣ ከማንበብ የሚያግተኝ ነገር የለምና በታላቅ መስህብ ስሜት ተውጬ ተጠግቼ አነበብኳቸው፦

የመጀመሪያው እንዲህ ይላል፦

" ተመልከት ፤ እኔ ማንን የምጠብቅ ይመስልሃል? ጊዜ ከሌለህ እዚህ ምድር ላይ ሌላ ምንም ነገር አትጠብቅ!"

በለው ብሶት!! ሁለተኛውን አነበብኩት። 

"ሳምንቱን ሙሉ ክፍት ነው፤ የዕረፍት ቀናትን ጨምሮ" ይላል ።

አባባሉ የቁጥር መጭበርበር ያለበት ቢመስለኝም የሰዓት ሠሪው ቤት እዚሁ መሆኑ ታስቦ የተፃፈ መሆኑንና ደንበኞች ይህን ሊገነዘቡ የተቀመጠ (የቤት ስራ) መሆኑንአምኜ ወደሶስተኛው ጥቅስ አመራሁ።

ሶስተኛው ግን ለራሴም ገራሚ ነበር ፦

"ልክ እንደ ሰዓት የሚበላሽና እንደ ሰዓት ጠጋኝ የሚሰራ ሰዓት የለም!"

እናም ፣ እንዲህ እያልኩ ወደውስጥ ገባሁ፦

"የዛሬው ጥሩ ይመስላል፤ መቼስ እስከዛሬ ከለጠፍኳቸው ይሻላል!"

እሑድ 21 ፌብሩዋሪ 2016

☆እግረ-መንገድ

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)
‪‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬

የምሰማው ሁሉ አልጥምህ ብሎኛል፡፡ የሬዲዮኑን ጣቢያ እየቀያየርኩ የሚጥመኝ ፕሮግራም ፍለጋ ጀመርኩ፡፡ ዘፋኙ ሁሉ ዘማሪ ሆኗልና! . . . ሬዲዮኑን ዘጋሁትና ቲቪ ከፈትኩ፡፡

በቲቪ፣ የአንድ አዲስ ምርት አምራች ድርጅት ማስታወቂያ እየተላለፈ ነበር፡፡ አስተዋዋቂው፣ ድምፁን ከሌላ ሰው የተዋሰው ይመስላል፡፡ በግነት በተዋቀረ ድምጽ እንዲህ እያለ ነበር፡-

“ልብ ይበሉ! ምርታችን በአይቱ አዲስ እና አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ ነው!!”

በለው ውሸት!

“አዲስ እና አስተማማኝ” ማለት ምን እንደሆነ የገባቸው አልመሰለኝም፡፡ አዲስ ከሆነ አስተማማኝነቱ ገና አልተረጋገጠም ፤ የተረጋገጠ ለመሆን ከዚህ ቀደም የሚታወቅ መሆን አለበት፡፡ ይህን እንኳን አያስቡም፡፡

ተጨማሪ ውሸት ሽሽት ቲቪውን ዘጋሁትና ከቤት ወጣሁ፡፡ ትንሽ በእግሬ ዞር ዞር ብዬ ብመለስ እንደሚሻል በማሰብ ነበር አወጣጤ፡፡

ማምሻ ግሮሰሪ የማውቀው አንድ ሰው ከሩቁ “እንኳን አደረሰህ!” ሲለኝ፡፡ “እንኳን!” አልኩት ከሩቁ፡፡

“እንኳን ምን? ” አለና መልሶ ጠየቀኝ፡፡

“እንኳን ብቻ!” ብዬ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡

“አይ አንቺ ሰው ፤ በጊዜ አግለሻል መሰል...” ሲል ከጀርባ ይሰማኛል፡፡ ሰው ግን በዓል ሲመጣ ብቻ ነው እንዴ “መድረሴ” ትዝ የሚለው?

መንገዱ ጭር ብሏል፡፡ አንድ ሰው ብቻ ከሩቅ ይታየኛል፡፡ የሆነ ነገር እያወራ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ እየቀረብኩት ስሄድ ምን እያለ እንደሆነ ተሰማኝ፡፡
“የበግ ቆዳ ያለው? ” እያለ ነበር፡፡

አጠገቤ ሲደርስ ወደኔ እያየ ጮክ ብሎ ፤ ”የበግ ቆዳ ያለው!” አለ፡፡ ዝም ብዬው አለፍኩ፡፡ “ሰዉ ዛሬ ምን ነክቶታል?! ” ስል አሰብኩ፡፡ እውነት የበግ ቆዳ ቢኖረኝ መንገድ ለመንገድ ይዤው የምዞር መስሎት ይሆን?!

ሳላውቀው ብዙ ርቀት በእግሬ ተጓዝኩ፡፡ .... አምስት ሴቶች ከሩቅ ይታዩኛል፡፡ ታክሲ እየጠበቁ መሆን አለበት፡፡ እየቀረብኳቸው ስሄድ አለባበሳቸውን ለየሁት፡፡ አራቱ ሴቶች ነጭ የአገር ባሕል ልብስ ለብሰሰዋል፡፡ አንዷ ግን በጅንስ ተወጣጥራለች፡፡ ፀሐዩን ሽሽት በዣንጥላ አናቷን ከልላለች ፡፡ ተስፋ ቆርጣ መሆን አለበት ከመሃከላች ወጥታ በእግሯ መጓዝ ስትጀምር አየኋት፡፡

ነጭ የለበሱት አራቱ ካሉበት አልተንቀሳቀሱም፡፡ በአጠገባቸው ሳልፍ ከመሃከላቸው አንዷ፡- “ወንድም ፤ ሰዓት ይዘሃል? ” ስትል ተሰማኝ፡፡

“አዎ!” አልኳትና መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ ልጅቱ ስንት ሰዓት እንደሆነ እንድነግራት እየጠበቀች ነበር መሰለኝ፡፡ ግን የጠቀየቀችኝ ሰዓት መያዜን ነው፡፡ እርሱንም “አዎ” ብያታለሁ፡፡

ዣንጥላ የያዘችው ሴት ከፊት ከፊቴ ስትሄድ አየሁ፡፡ የሚገርም ጀርባ አላት፡፡ እውነት የተፈጥሮ ከሆነ መቀመጫዋ ያምራል፡፡ (ሴቱ እንደ ውስጥ ሱሪ የሚጠለቅ አርቴፊሻል መቀመጫ መጠቀም ጀምረዋል አሉ! ) ይሁን ፡፡ መጠቀማቸው ክፋት የለውም፡፡ የሚቆረቁር ወንበር ላይ ሲቀመጡ እንዳይቆረቁራቸው ከሆነ መልካም ነው፡፡ (ምቾት በሌለው ወንበር ላይ ረጅም ሰዓታት ለሚቀመጡ ወንዶችም ይህ ዘዴ ይጠቅማል መሰል፡፡ )

ሰውነቷ ያምራል፡፡ ዕድሜዋን ለመገመት ሞከርኩ፡፡ በጥቂት ዓመታት ብትበልጠኝ ነው፡፡ “ታላቄ” እንደሆነች ሳስብ አንድ አባባል ትዝ አለኝ፡፡ “ከእያንዳንዷ ታላቅ ሴት ጀርባ መቀመጫዋን የሚያይ ወንድ አይጠፋም!” ሆሆሆ . . . ለጀመሪያ ጊዜ ፈገግ አልኩ፡፡
‪‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬
“ልመለስ!? ወይስ መንገዴን ልቀጥል!?” . . . ስል አመነታሁ፡፡ ሉፒዶ (ሽፍደት) ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ይህ ተፈጥሮ ግን መገለጫው ብዙ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው እንደየምልከታው ግንዛቤ የሽፍደት አካል መረጣውም ይለያል፡፡

የሰውነት አካላት ሁሉ የዚህ ምልከታ ውጤት ናቸው፡፡ በርግጥ መቀመጫዋ የሚያምር ሴት አይቶ “አሪፍ መቀመጫ አላት” ያለ ሁሉ ይህቺን ሴት ተመኛቷታል ማለት አይደለም፡፡ ማድነቅም ሌላው ተፈጥሮ ነውና፡፡ ከፊቴ ያለችውም ሴት ለእኔ እንደዚሁ ናት፡፡ ያየሁትን ማራኪ ሰውነት አለማድነቅ እንደማልችለው ሁሉ፣ ያደነቅኩትን ማራኪ ሰውነት ሁሉም አልመኝም፡፡ ይህም ተፈጥሮአዊ ነው!

ጥቂት መንገድ የመግፋት ሃሳብ አጋደለና መጓዜን ቀጠልኩ፡፡ ከፊቴ ግን ታላቅ ውሳኔ የሚሻ ነገር እየተውረገረገ ነው፡፡ ከቤቴ የወጣሁት ዳሌ ለመከተል አልነበረም፡፡ አሁን ግን ባጋጣሚ ዳሌ ተከታይ ከመሆንም አልፌ አድናቆት ገላጭ አባባል ቀማሪም እየሆንኩ ነው፡፡ ʿይህን ታላቅ ዳሌ እስከምን ድረስ ነው የምከተለው?! ከዚህ በላይ ከመከተል፣ ዳሌዋን ስካን ማድረግ ይቀላል፡፡ʾ ስል አሰብኩ፡፡

በነገራችን ላይ ፤ ከኋላ መሆን መከተል ነው ያለው ማነው?! (ከእረኛን ተመልከቱ፡፡ ከብቶቹን የሚያግደው ከፊት ከፊታቸው እየሄደ አይደለም፡፡ በጉዞ ላይ ያሉ ከብቶች ካያችሁ ፣ ከኋላቸው እረኛ መኖሩን አትዘንጉ) በዚህ ምሳሌ ብቻ ተገፋፍቼ ለዚህ ታላቅ ዳሌ እረኛ የሆንኩት እንዳይመስልብኝ ስል ርምጃዬን አፍጥኜ አለፍኳት፡፡ አሁን ተራው የርሷ ነው፡፡

ሴቶች ግን . . . ወንድን ከጀርባው ሲመለከቱት ምኑን ይሆን ቀድመው የሚያት?! (ዋሌቱ እንደማይሆን ግን ርግጠኛ ነኝ፡፡)

አልፌያት ጥቂት እንደተራመድኩ ፡- “ይቅርታ፣ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ እችላለሁ?” የሚል ድምጽ ሰማሁ፡፡ እኔን እንደሆነ ርግጠኛ ሆኜ ፊቴን አዞርኩና ልናገር ስል አንድ ነገር አገደኝ፡፡ ዳሌ ዳሌዋን ሳይ ያላየሁት ሌላ ሰው የስልክ እንጨት ፖል ተደግፎ ቆሞ ነበር ለካ፡፡ እሱን ነበር የጠየቀችው፡፡ እምም . . . ተረፈች፡፡ እንኳንም እኔን አልጠየቀች!

በጣም ከሚያናድዱኝ ጥያቄዎች አንዱ ይህ ነው፡፡ “አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ?” ብሎ መጠየቅ በራሱ አንድ ጥያቄ ነው፡፡ እንዲህ ብለው የሚጀምሩ ሰዎች ሌላም ችግር አለባቸው፡፡ ያስፈቀዱት አንድ ጥያቄ ለመጠየቅ ሆኖ ሳለ መልሱን ተከትለው ተከታታይ ጥያቄ ማዥጎድጎዳቸው ነው፡፡

የመጀመሪያውን ፈገግታ የፈጠረው ስሜት በምን ፍጥነት ጥሎኝ እንደጠፋ እንጃ፡፡ ብሽቅ!

መቼስ በበዓል ቀን ታክሲ ከመጠበቅ ታክሲ መሸከም ይቀላል፡፡አውቶቢስ ፊርማታ ሳገኛ ቆምኩ፡፡ በእግሬ የመጣሁትን መንገድ በእግሬ የመመለስ አቅም አልነበረኝም፡፡ ታክሲ ቢጠፋ እንኳን ባስ እንደማላጣ ርግጠኛ ነበርኩ፡፡

(ሞራል)፡-
ጥቂት ሰዎች የባሷን መምጫ በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡ እኔም እነርሱ ወደሚያዩበት አቅጣጫ አፍጥጫለሁ፡፡ አልፌያት የመጣኋት ቆንጂዛ አልፋኝ ከሄደች ቆይታለች ፡፡ (ማሳለፍ ትልቅ ችሎታ ነው፡፡ ማለፍም፡፡) አለማለፍ ግን ደካማነት፡፡ አለማድነቅ ስሜትን ለሌላው አለማሳወቅ ነው፡፡ ለራስ የተሰማን የአድናቆት ስሜት መሸሸግም ያው አልሸሹም ዞር አሉ ነገር፡፡ የአድናቆት ስሜትን ለሌላው ለማሳወቅ ሲባል ግን እንደኔው ሁሉ ተረጋግተው የሚጓዙትን ሰዎች መልከፍ ግን በነፃው መንገድ ላይ ነፃነትን ከመንፈግ አይተናነስም!!

አድናቆት በሰፊ ቦታ ጠባብነትን ማግዘፍ ሳይሆን ሌላ ስፋትን መጨመር ነው ብዬ አምናለሁና፡፡ ስለዚህም በማለፍ አምናለሁ፡፡ በማሳለፈፍም፡፡

ማሳሰቢያ፡- የእግረ መንገድ ወግ እንደ መዋቅር የተጠቀምኩበት መንገድ፣ ቅርፅ እንጂ እውነተኛ ገጠመኝ አይደለም፡፡ ምልከታን የመግለጫ አንድ መንገድ እንጂ፡፡

ረቡዕ 17 ፌብሩዋሪ 2016

"እሾህን በሾህ"

✧(ኄኖክ ስጦታው)
(የአጭር አጭር አጭር ልቦለድ)

ለእራት የሚሆን ነገር ለመግዛት ወደ ሱቅ አመራ። እንደ ሁልጊዜውም፣ ጎረቤቱ የአይጥ መርዝ እየገዛ ነበር። ከጎረቤቱ ቤት መርዝ በልተው እሱ ቤት ኮርኒስ ውስጥ የሚሞቱ አይጦች ሽታ ረፍት ነስቶታል።
"ለምን በወጥመድ አታጠምዳቸውም?" አለና መፍትሄ ይሆናል ያለውን ሃሳብ አቀረበለት። ለጎረቤቱ።
"ሞክሬ ነበር። ወጥመድ ማለት የአይጥ ገበታ ነው። አይጦቹ ወጥመዱ ላይ ያለውን ምግብ በልተው ይሄዳሉ። ጠዋት ስነሳ ወጥመዱ የሚይዘው እኔኑ ነው።"
ዝም አለ።
አስቦ ፣ አስቦ… አንድ መፍትሄ አገኘ። እናም ጎረቤቱ ዞር እስኪል ጠብቆ፦
"የአይጥ መድሃኒት አለ?" ሲል ጠየቀ። ለባለሱቁ።
"የለም። መርዝ ነው ያለው"
"እሱንም ቢሆን ስጠኝ"