ሰኞ 22 ፌብሩዋሪ 2016

ሠአት ሠሪው

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)

ሠአት ሠሪው ደጃፍ ላይ ቆሜያለሁ። ከውጭ ሆኖ ለሚመለከት ሰው ምንም የሚማርክ ውበት ላትመለከት ይችላል። የደጁን መስታወት ታክኮ የቆመው መደርደሪያ ያገለገሉ ሰዓታት ማረፊያ ሁነዋል። የተበላሹ፣ የተጠገኑ፣ የማይጠገኑ፣ ያልተጠገኑ፣… ሠአቶች ተሞልቷል። እኔ እራሴ ሁሌ የማያቸው ሰዓቶች እዚህ ምን እንደሚሰሩ አይገባኝም። አሰሪዎቹ ቢወስዷቸውና ሰዓት ሠሪው ያገልግሎቱን ቢያገኝ መምረጤን ግን አልሸሽግህም። 

መስታወቱ ላይ ሶስት ጥቅሶች አሉ። በእጅ የተሞነጫጨሩና ለንባብ የማይማርኩ ቢሆኑም፣ ከማንበብ የሚያግተኝ ነገር የለምና በታላቅ መስህብ ስሜት ተውጬ ተጠግቼ አነበብኳቸው፦

የመጀመሪያው እንዲህ ይላል፦

" ተመልከት ፤ እኔ ማንን የምጠብቅ ይመስልሃል? ጊዜ ከሌለህ እዚህ ምድር ላይ ሌላ ምንም ነገር አትጠብቅ!"

በለው ብሶት!! ሁለተኛውን አነበብኩት። 

"ሳምንቱን ሙሉ ክፍት ነው፤ የዕረፍት ቀናትን ጨምሮ" ይላል ።

አባባሉ የቁጥር መጭበርበር ያለበት ቢመስለኝም የሰዓት ሠሪው ቤት እዚሁ መሆኑ ታስቦ የተፃፈ መሆኑንና ደንበኞች ይህን ሊገነዘቡ የተቀመጠ (የቤት ስራ) መሆኑንአምኜ ወደሶስተኛው ጥቅስ አመራሁ።

ሶስተኛው ግን ለራሴም ገራሚ ነበር ፦

"ልክ እንደ ሰዓት የሚበላሽና እንደ ሰዓት ጠጋኝ የሚሰራ ሰዓት የለም!"

እናም ፣ እንዲህ እያልኩ ወደውስጥ ገባሁ፦

"የዛሬው ጥሩ ይመስላል፤ መቼስ እስከዛሬ ከለጠፍኳቸው ይሻላል!"

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ