2016 ፌብሩዋሪ 21, እሑድ

ከሳንቲሞች መኻል የአንድ "ብር" ስሞታ

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ) 

የአንድ "ብር" ስሞታ

አንድ ብር ሳንቲሞች መካከል የቀላቀለውን አዲስ ማንነቱን ይዞ ነበር የተገኘው። ከል የለበሰ ያህል እየተሰማው፣ ቅሬታውን እንዲህ ሲል ለሳንቲሞች አሰማ፦

"…ህይወቴ ምስቅልቅል ብሏል። ወይ ከብሮች መካከል አልተመደብኩም። ወይም ለይቶልኝም ከሳንቲሞች መንደር ጠቅልዬ አልገባሁም ። እኮ እኔ ነኝ?

"ማንነቴን የሚንቁ በዝተዋል። የአምስት ሳንቲም መለያ የነበረው መርፌ የመግዛት አቅሟን ያሰጣት ቅፅል ስም ዛሬ የኔ መጠሪያ ሆኗል። "ባለብሩ ዳቦ" ተብሎ በግርማ ሞገሱ የሚታወቀው የጥንቱ መጠሪያዬ ዛሬ ተረት ሆኗል። ባለብሩ ዳቦም  እንደዛው።

"ውሎና አገልግሎቴ ሙዳየ ምፅዋት ውስጥ ከሆነ ቆየ። ለማኝና መፅዋች ሲቀባበሉኝ መዋል ሳያንሰኝ፣ ከታክሲ ረዳቶች መዳፍ ገብቼ ከበርና መስኮት ጋር ስታሽና ከእናንተ ሳንቲሞች መካከል ስፋጭ መዋል ታከተኝ። እኮ እኔ ማነኝ?! ስሜስ የማነው! ?"

"አይዞህ አንድ ብር " አለ አምስት ሳንቲም— በስላቅ። "ገና ምኑን አየህና ትማረራለህ?" ሲል አስር ሳንቲም አከለበት።

አንድ ሳንቲም በኩራት ወደ ስሙኒና ሽልንግ እየተመለከተ፤ "አምስትና አስር ሳንቲምን አትስማቸው። አንተን የምትመስለው እኛን ነው። እነሱን ተዋቸውና እኛን አማክረን" አለ ጸአዳ ነጭ ጥርሱን እያሳየ።

አምስት እና አስር ሳንቲም አንድ ሳንቲም ላይ እኩል አንቧረቁበት፦ "አንተ ደግሞ የምን ቤት ነህ?! ዋጋ ቢስ!!"

ሃምሳ ሳንቲም ተቆጣ ። "ፀጥታ! አንድ ብር ዛሬ እንደማናችንም ሆኗል። ይህ ብር የሁላችንንም መልክ እና ግብር ተላብሶ ከመኻከላችን ተገኝቶ ብሶቱን እያካፈለን ነው። እንስማው። …" አለና ጭቅጭቁን አብርዶ ወደ አንድ ብር ፊቱን መለሰ።

"አይዞህ አንድ ብር። ዛሬ ቀን ጥሎህ ከኛ መኻል ቢቀላቅልህም አትዘን ። አሁን ካቆምክበት መቀጠል ትችላለህ…" 

አንድ ብር ልቡ በኻዘን ተነክቶ ብሶቱን በዜማ ማተት ጀመረ…(ዜማው በእንባው ከመታጀቡ በቀር ፣ቁርጥ የሸዋንዳኝ ዘፈንን ይመስል ነበር)


"ስሜስ የማነው?! ላምጪው ምን ከፈለ?!
ሳንቲም ሲጠራ ፣ አፌ አቤት እያለ!!―"
.*
*
*
*
"እኔ እንደዚህ፣
እስኪነሳኝ አቅም
ተዋርጄ አላውቅም"


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ