እሑድ 21 ፌብሩዋሪ 2016

ማንደፍሮሽ

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)

እውነተኛ ስሟ "ማንደፍሮሽ" ነው። እኔና መሰል አብሯ አደግ ጓደኞቼ ግን ፣ በቁልምጫ "ማኔ" እያልን እንጠራታለን። የመንደራችን ሴት ልጆች እንኳን በአካል አይተዋት ይቅርና፣ ገና ስሟ ሲጠራ በፍርሃት ይርዳሉ። ምግብ አልበላም ብለው ሲያስቸግሩ "ማኔን እንዳልጠራት!" ማለት በቂ ነው። ታዲያ እኩዮቿ ብቻ ሳይሆን ታናናሽ ወንድሞቻችንም ቢሆኑ የ"ማኔ" ስም ከተጠራ፣ የቀረበላቸውን ምግብ ጥርግ አድርገው እየበሉ አድገዋል።

ታዲያ ዛሬ ድረስ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር የማኔ እንዲህ የመፈራት መንስኤ ነበር። በርግጥ ከወንድ ጋር የሚያመሳስላት ምንም አካላዊ መለያ የላትም። በእነዚህ ሁሉ የጓደኝነት ዓመታት፣ እንደወንድ  ለመምሰልም ምንም አይነት ጥረት ስታደርግ ማየቴንም እጠራጠራለሁ።

ልጅ እያለን ኩሽና ውስጥ እቃቃ ስንጫወት የሆነው ሁሉ አይረሳኝም። "አንቺ ሴት ነሽ፤ ለምን ከመሰሎችሽ ጋር አትጫወቺም" ብለን ጠይቀናት ነበር። መልሷ ግን የከፋ ነበር። በሁለት እጆቿ ያፈሰችውን አመድ ዐይናችን ውስጥ ሞጅራ ሮጠች። ከዛኔ ጀምሮ ነው መሰል፣ ይኸው አድገን እንኳን አንጠይቃትም።

በሌላ ጊዜ ደግሞ፣ ወንድነታችንን ተጠቅመን የበላይነታችንን እንድታምን ለማድረግ በጉልበት ልናስገብራት ሞክረን ነበር። በትግል እንደምንጥላት ተማምነን ብቻ ለብቻ ድብድብ እንድትገጥመን ጠራናት ። ብቻ፣ እንኳን እኔ አቡቹን አልሆንኩ። በመላተም ብዛት ጠንካራ የሆነ የሚመስለው አቡቹ  ጉድ አደረገን!!! ተዝረክርኮ አዝረከረከን። በወቅቱ፣ የመጀመሪያው ተጋጣሚ አቡቹ ነበር። (እንኳን እኔ አልነበርኩ።) ለትግል እንዲመቸው እግሩን አንፈራጦ በመቆም ዝግጅት ላይ ሳለ ድንገት ከማኔ የተሰነዘረው ርግጫ ብልቱ ላይ አረፈና ለሳምንታት የአልጋ ቁራኛ ሆነ። ከዛ ቀድሞ ግን እኛ የበላይነቱን ሚና ያለምንም ማቅማማት ለማኔ አስረከብን። ምክንያቱም ማኔ፣ በቅፅበታዊ ምት እና የት ቦታ ላይ መማታት እንዳለባት ተክናለችና።

ከወንዶች ጋር መሆን ትመርጣለች። (በተለይ ከኔ ጋር) ።

ማኔ ወንድ አይደለችም። ወንድም እንዳልሆነች እናውቃለን። "እኔ ሰው ነኝ!" ያለችን ቀን ምን ማለቷ እንደሆን ባይገባንም፣ ያለምንም ማቅማማት "ነሽ!" ብለናታል። ምስኪን አቡቹ! ገና ከማገገሙ፣ አላራምድ ያለውን የታፋ ስር ንፍፊት ተቋቁሞ እንደተነሳ፣ "እኔ ሰው ነኝ!" ስትል፤ "አዎ ነው!" ማለቱ ሳይቀር ትዝ ይለኛል። (ሲያስቅ... የሰው ፆታው ምንድነው? )

ሴትነቷን እየፈራን እንድናስታውስ የሚያደርገን አስገዳጅ ሁኔታ የሚፈጠረው ከስንት አንዴ ነው። እስከዛሬ፣ "ሴቷ ወንድማችን" ብሎ የጠራት አንድ ሰው ብቻ ነው። እሱም "ፎርጃ" ይሰኛል። (ቅፅል ስሙ ነው፤ የትምህርት ቤት ስሙ ረጅም ነው። ቃል በቃል ባላስታውሰውም፣ 'ፈርቼ ማለድኩት እሱን ሰጠኝ ለኔ ጃንደረባው…') አይነት ነገር ይመስለኛል። ፎርጃ፣ የቅፅበታዊ ጥቃቷ ሰለባ ነበር። እስካሁንም ነው። (ዛሬ አቡቹ አግብቶ ወልዷል) ። በርግጥ የልጁ አባት እርሱ እንደሆነ ያመንው በግድ ነው። (ያሉትን ነው ያልኩት)

ከዚህ ቀደም፣ (ወንዱ እህታችን) ያለው ፎርጃ ግን በሃኪም መውለድ እንደማይችል እንደተነገረው ካወቅን በኋላ የሁላችንም ጥያቄ ይህ ነው… 'እውን አቡቹ መውለድ የቻለው እንደኛው ሁሉ እሱም በሆነውና በሚሆነው ስላመነ ነው?! ወይስ… እንደ ፎርጃ ፣ ሃኪም ስላላየው?!"

ማኔ በሁሉም የልጅነት ጨዋታዎቻችን ውስጥ የመረጠችውን የመሆን ስልጣኗ ዛሬ ላይ ቆም ብዬ ሳስበው ይደንቀኛል። "ባል እና ሚስት" ስንጫወት እሷ የምታገባው እኔን ብቻ ነበር። እሷ ባል ስትሆን፣ እኔ ደግሞ ሚስቷ እሆናለሁ፡፡ የባልና ሚስት የጨዋታው ስርዓት በርሷ የበላይነት ተጀምሮ ያበቃል፡፡ እንደ ሚስትነቴ ምግብ የማዘጋጀት፣ ልጆችን የማጠብ፣ ቤቱን የማፀዳዳት …. ተግባራትን እከውናለሁ፡፡

ልጆቻችን ሆነው የሚጫወቱት አቡቹ እና ፎርጃ ናቸው፡፡ (እስካሁን ድረስ ማን እንዳረገዘ፣ ማን እንዳስረገዘ ባይገባኝም)፡፡ ፎርጃ እንደሴት ልጅ እንዲጫወት የምታደርገው ፎርጃን ነው፡፡ አቡቹ ደግሞ ወንዱ ልጃችን እንዲሆን ሚና ይሰጣቸዋል፡፡ ታዲያ በማኔ የሚታዘዘው አቡቹ ነው፡፡ ማኔ ትእዛዝ በመዛኙ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ አቡቹን ጠርታ የባህርዛፍ ፍሬ (ሳንቲም መሆኑ ነው) ቆጥራ እየሰጠችው፡-

"አቡቹዬ፣ ከቃሲም ሱቅ የአስር ሳንቲም ስኳርና የስሙኒ ቡና ግዛልኝ" ትለዋለች፡፡

"እሺ፣ እማዬ" ካለ አለቀለት፡፡ የማኔ ቅፅበታዊ ምት ጭንቅላቱ ላይ ይዘንብበታል፡፡ በኩርኩም  ገጭ! ገጭ!  ገጭ! ... "እሺ አባዬ፣ ረስቼው ነው አባዬ! ይቅርታ አባዬ!" እስኪል ድረስ ኩርኮማዋን አታቆምም፡፡ አቡቹ ጥሎበት ድንገተኛ ኩርኩም ሲቀምስ ምድር ዓለሙ ስለሚዞርበት "አትምቺኝ..." ብሎ ማለቃቀስ ይመርጣል፡፡ እንዲህ ሲሆን የእናትነት ሚናዬን ተጠቅሜ ያስቀጣውን ጥፋት ልነግረው እሞክራለሁ፡፡ "አቡቹ፣ አባትህን እንዴት እማዬ ትላለህ..." ይህኔ "አባዬውን" ያዥጎደጉደዋል፡፡

ማኔ አባትነቷን አስከብራ ስታበቃ፣ "በል ፣ ሁለተኛ እንዳይለምድህ! አሁን ከቃሲም ሱቅ ግዛልኝ ያልኩህን በቶሎ ገዝተህ ና!" ካለችው በኋላ እንደ ሴት ልጅ ሆኖ ወደሚጫወተው ፎርጃ በመዞር እንዲህ ትላለች፡-
"ወንድምሽ እንዳይፈራ አብረሽው ሁኚ..."

ሁሌም ለሚስትነት እኔን እንደምትመርጥ አይገባኝም ነበር። በኋላ እንደገባኝ ከሆነ፣ አቡቹና ፎርጃ ለርሷ "ገና ልጆች" ናቸው፤ (ሚስት ለመሆን ገና አላደጉም)፡፡

በሌላ ጊዜ አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ፡፡ የሆነ ጊዜ ግን እየፈራሁ፡- "ዛሬም ሚስት የምሆነው እኔ ነኝ?" ብዬ ጠየኳት፡፡

"እና መጀመሪያ ሚስቴ እንድትሆን ስመርጥህ እስከመጨረሻው ድረስ ባልህ እንደሆንኩ አታውቅም?!" ብላ ተቆጣች፡፡ አ-ቤ-ት ቁጣዋ! አንድ ጊዜ የምታሳየው የቁጣ ገፅታ፣ ሶስት ሆነን አንሸከመውም፡፡ "እሺ" አልኩ፡፡ ምክንያቱም፣ በዚያ የልጅነት ዕድሜ የተቀረፀብኝ የ"እምቢታ" ትርጓሜው ግልፅ ነበር፡፡ "እንቢ" ማለት... በባሎች ዘንድ እንደጥፋት ተቆጥሮ በ"ሚስቶች" ላይ ለሚያደርጉት ያልታሰበ "ቅጣት" ምክንያት ይመስለኝ ነበር፡፡ (በዚህ ዘመን "ቅጣት" የሚለው ቃል "ጥቃት" በሚል ተቀይሯል፡፡)

የሚስትነት ሚናን ይዤ ስተውን፣ ትዕዛዝ መፈፀም የኔ ግዴታ ሲሆን ማዘዝ እና ማሽቆጥቆጥ ደግሞ የማኔ ስልጣን ነበር፡፡ ታዲያ በጨዋታ መሃል "ጎመን ገዝተህ ና፤ ደግሞ እነዛ መንገድ ዳር የሚቆሙ ሴቶች ካስቸገሩህ ፊት አትስጣቸው!" ብላ ታዘኛለች፡፡

የመንገድ ዳር ተሰብስበው የሚቆሙ የመንደራችን ወንዶች፣ ሴቶች ባለፉ ባገደሙ ቁጥር በነገር መተንኮስ (መላከፍ) ዋንኛው የአራድነት መገለጫቱ  ዛሬም ድረስ ቢቀጥልም፣ በማኔ ዘንድ ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ምንም ጨዋታው እቃቃ ቢሆንም፣ ምንም ጨዋታው ባልና ሚስት ቢሆንም… የዓለም ነባራዊ አካሄድ በማኔ ፊውራሪነት ተለውጧል፡፡ በተላካፊ  ሴቶች መግቢያ እና መውጫ አጥተው የተማረሩ ወንዶች እንደ አንዱ ሆኜ "ሴቶች እንዳይተናኮሉኝ" እየተጠነቀቀኩ የታዘዝኩትን ለመፈፀም መተወኔና ማሰብ በራሱ ለማኔ ያለኝ አድናቆት ይበልጥ ይንራል፡፡

የማኔ ባል መሆን እየተመኘሁ፣ ሚስቷ መሆኔን ያመንኩበትን ዓለም ምን እንሚመስል በምናቤ ለመሳል ሞከርኩ፡፡ "ማጅራት መቺ አለ፤ በጊዜ ልግባ…" ሲባል መስማት የተለመደ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ሴት ማጅራት መቺ አላውቅም፡፡ ሰው መጅራት መቺንም ሆነ ዘራፊን ሽሽት በጊዜ ቤቱ ለመግባት ከተጣደፈ፣ ከወንዶች ከሚሰነዘር አደጋ እራሱን ላለማጋለጥ ለመሆኑ ርግጥ ነው፡፡ እናም ወንዶች ለሁለቱም ፆታዎች የስጋት ምንጭ ናቸው፡፡

ከማኔ ጋር ከተዋወቅንበት ሶስት አስርት አመታት ተቆጠሩ። ያለጥርጥር ከ15 ዓመታት በኋላ ነው ያገኘኋት። አድራሻችንን አፈላልጋ እዚህ እንድንገናኝ በስልክ የቀጠረችን ራሷ ማኔ ናት፡፡ አቡቹና ፎርጃ እስኪመጡ እየጠበቅን ነው፡፡ ስለርሷ ያለኝ ግንዛቤ ባይለወጥም፣ አስተያየቴ ግን ተለውጦ ነበር። እንዴት አባቷ አምሮባታል?!? የሌለ ውስዋስ ለኳሽ ሆና ታየችኝ። የተሰማኝን ስሜት ግን ለመናገር አቅም አልነበረኝም። ምክንያቱም ፣ ማን እንደሆነች እድሜ ዘመኔን ሙሉ እንዳልረሳ አድርጋ ነግራኛለች።

ያቀራረበን እድሜ አራርቆናል፡፡ መልሶም አገናኝቶናል፡፡  እድሜ  የለወጠው ብዙ ነው፡፡ እቃቃ መጫወቻዎቻችን ተበትነዋል፡፡ በልጅነት የተጀመረው የባልና የሚስት ጨዋታ ይቀጥል አይቀጥል አይታወቅም…

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ