ሰኞ 21 ጃንዋሪ 2013

ጌታው ባለህበት - ማረፍ በቀለ













ጌታው ባለህበት

አጋድመህ መዘንጠል ከለመድክበቱ
የሚታረድ ጠቦት ከምታስስበት
እዛው ካክራሞትህ ከበረት ከጋጡ
በሩን ተሸሽገህ በጥጋት ቀዳዳ
በሽንቁሩ አልፈው የሚጉረጠረጡ
እነዛ አይኖችህ ጨለማ ይሁኑ!
አልልህም እኔ
ድብስብስ ለሊትን የጭርታን ጊዜ
የዝለትን ሰበብ የቀንን ድንጋዜ
ብርታቱ አድርጎ የሚጣራ ድምፅህ
ዜማ እያምታታ
የእረኛውን ዋሽንት አምስሎ እየመታ
የሚያፏጭ ልሳንህ
ዘላለም ይደፈን ጎሮሮህ ይዘጋ!
አልልህም እኔ
ድንቃፍ ላይመልሱ ላያስጥሉ ከውርጭ
ጨብጠው ላይመሩ ረብ ላይሰጡ ቅንጣት
እቅፍ የዘረጉ - ምርኩዝ ቢያድርጓቸው ሰልትው የተዋጉ
ነፍስ ድረስ ዘልቀው ነፍስ ያስመረቀዙ
እነዚያ እጆችህ አመል የለመዱ
ሰይፍ ይረፍባቸው በጦር ይቀደዱ
አልልህም እኔ