ጌታው ባለህበት
አጋድመህ መዘንጠል ከለመድክበቱየሚታረድ ጠቦት ከምታስስበት
እዛው ካክራሞትህ ከበረት ከጋጡ
በሩን ተሸሽገህ በጥጋት ቀዳዳ
በሽንቁሩ አልፈው የሚጉረጠረጡ
እነዛ አይኖችህ ጨለማ ይሁኑ!
አልልህም እኔ
ድብስብስ ለሊትን የጭርታን ጊዜ
የዝለትን ሰበብ የቀንን ድንጋዜ
ብርታቱ አድርጎ የሚጣራ ድምፅህ
ዜማ እያምታታ
የእረኛውን ዋሽንት አምስሎ እየመታ
የሚያፏጭ ልሳንህ
ዘላለም ይደፈን ጎሮሮህ ይዘጋ!
አልልህም እኔ
ድንቃፍ ላይመልሱ ላያስጥሉ ከውርጭ
ጨብጠው ላይመሩ ረብ ላይሰጡ ቅንጣት
እቅፍ የዘረጉ - ምርኩዝ ቢያድርጓቸው ሰልትው የተዋጉ
ነፍስ ድረስ ዘልቀው ነፍስ ያስመረቀዙ
እነዚያ እጆችህ አመል የለመዱ
ሰይፍ ይረፍባቸው በጦር ይቀደዱ
አልልህም እኔ
ኮቴ ሳያሰሙ በመላ ተራምደው
ቁልፍ ማጀት ዘልቀው
ውጨ-ፀባይ ማልመድ
እንዳሻ ወደዚህ ሲሻ ወዲያ ማገድ
ጠግቦ መንጎራደድ
የሚያውቁ እግሮችህ ይሰነካከሉ
ካሰቡበት ማዶ ባላሰቡት ይቅሩ!
አልልህም እኔ
ከሁሉም ከሁሉም
ከነገረ- ፍጥርህ ከተግባርህ በላይ
ባለፈ ካልኩትም- ካልተናገርኩትም
እጅግ ተፅፍዬ ያለልክ አቅልዬ
ታዝቤም ታምሜ
ይማርህ ለማለት ብዙ ታግያለሁ
እሱን እንኳን ችዬ
"ይማርህ" ለማለት አቤት ስንት ስቃይ
ወየው ስንት ዋይ! ዋይ!
ግን ተበራትቼ
እስቲ ልበል ዛሬ
ታመሃል አንተ ሰው ይማርህ አቤቱ!
ጤና ነኝ የሚያሰኝ ዋሽቶሃል ልክፍቱ
ይማርህ በፍቅሩ
ይማርህ በምክሩ
ይማርህ ዝምታው
ይማርህ ትእግስቱ::
---------
ማረፍ በቀለ
it has been long since i.ve fallen in love with this magnificent piece. Bless your hands Marefyaye
ምላሽ ይስጡሰርዝ