ቅዳሜ 19 ጃንዋሪ 2013

ቅዥት - ሄኖክ ስጦታው




ቅዥት

የህልም ዓለምን ሳካልል፣
በቁም ሳለሁ ተኝቼ
ከወደቅሁበት ፀሊም ዓለም፣
ሳልፈልገው ተገፍቼ፤
እንደ ሌሊቱ ቅዥቴ፣ መሮጥ ተስኖት እግሬ
ሳልፈልገው ተተብትቤ፣ እግር-ተወርች ታስሬ፤
ልክ እንደዚያው ቅዥቴ፣
በቁም ታፍኖ አንደበቴ
እንዳላመልጥ ከእስራቴ፣
በኖ ጠፋና ብርታቴ . . .

ዘመኔን በግድ ታቅፌ
በቃ እንዳልል ጋት አልፌ
ተወግቼ አንዳች መርፌ፤

ተውሰብስቤ በእልፍ ቅዥት
ስንቱን ዓለም አካለልኩት?!
መሬት ለመሬት ስንፏቀቅ፣
ሰማየ-ሰማያት ስንሳፈፍ
ድንገት መጋለብ ጀምሬ፣
ድንገት ባሕር ስቀዝፍ . . .
ስንቱን ዓለም አካለልኩት?!

የማላውቀው ፤ ግን ያየሁት
የምኖረው፤ ግን ያከልሆንኩት
የማፈቅረው፤ ግን ያጣሁት፤
የምመኘው፤ ግን ያልሆንኩት. . . !

ትላንት ቅዥት፣ ዛሬ ቅዥት
መዋል ቅዥት፤ ማደር ቅዥት፤ መኖር ቅዥት፣
ያሻሁትን ብቃዠውም፤
ቅዥቴን ግን አልኖረውም
የኖርኩትን አልቃዠውም!

መጋቢት፣ 28፣ 1999ዓ.ም
ሄኖክ ስጦታው ከ(ሀ-ሞት የግጥም ስብስብ መጽሐፍ፣ በቅርብ ቀን የሚወጣ)

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ