*በራስ ምስል ዛቢያ
ልጅ ሆኜ ነበረ ያደረብኝ ፍቅሩ
ዝናብ እና ምሽት-
ካፊያና ነጎድጓድ በአንድ ሲጣመሩ
በእንቅልፌ ሰመመን እያየሁ ሲዳሩ
ያሸለብኩት ሌሊት-
ቅዠቴ ጣፋጭ ነው ጥዑም ነው አዳሩ፡፡
ለአቅመ-አዳም በቅቼ ከጎኔም ሰው ኖሮ
ዝናባማ ምሽት ማፍቀሬ ጨምሮ
ጨለማ ሲያረብብ ደመናው ተቋጥሮ
እናፍቅ ነበረ ማየት ሰማይ ጠቁሮ፡፡
ጮርቃነቴ የታል? የታል ልጅነቴ?
ጓደኞቼም የሉ ሰው የለም ከቤቴ
መታሰሬን ባዩ በብቸኝነቴ፡፡
ህመሜን ባዩልኝ
ጭንቀቴን ባዩልኝ
ናፍቆቴን ባዩልኝ-!
መሽቶ ዝናብ ሲጥል
ከራሴ ስጣላ በስቃዬ ስዝል
ምን እንደምመስል፡፡
,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,
ኄኖክ ስጦታው
1998ዓ.ም