(ኄኖክ ስጦታው)
ምስር ባህል ነው። ምስር እውቀት ነው። አኗኗራችን ከምስር ጋር ተቆራኝቷል። ባህላችን፣ ልምዶቻችን፣ የሥነምግባር ተግዳሮታቸረን፣ የመረጃና የእውቀት መለዋወጫ መንገዳችንም ጭምር ነው-ምስር። በሀዘንና ደስታችን ውስጥም አለ በሃዘን ቤት ምስር አለ። በለቅሶ ቤት ውስጥ ምስር አለ። ምስር የወጥ ግብኣት ብቻ አይደለም። የሃዘናችን ተካፋይና የደስታችንም ተጋሪ ጭምር እንጂ።
አስደሳች ነገር ሲያጋጥመን “የምስራች!” እንላለን። “ምስር ብላ/ ብዪ)” አፀፋችን ነው። በሃዘናችን ጊዜ ገበታ ነው። በሞት ለተለየን ሰው ሃዘን በተቀምጥን ጊዜም ለሃዘንተኞች የሚቀርብ የገበታ ስርዓታችን አካልም ሆኖ ዘመናት ተሻግሮ ዛሬ ላይ ደርሷል።
ምስርን የነውራችን መሸፈኛና የጓዳ ውስጥ ገመናችን ቋንቋም ጭምር ነው። በአደባባይ ስንገልጠው ለማይገባቸው የተደበቀ፣ ለሚግባቡበት ግን የአደባባይ እውነታ ጭምር። ለሚያውቁት ብቻ የመግለጫ መግባቢያ መሳሪያችን ነው። በአዋቂዎች ዘንድ ሚስጥራዊ መግባቢያ በመሆንም ያገለግላል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ባል “እራት ምንድነው?” ብሎ በየቀኑ ይጠይቃል። ምክንያቱ እራቱን ምን እንደሚበላ ማወቁ ላይ እንዳይመስላችሁ። “እራት ምስር ነው” ከተባለ፣ ምላሹ ሁለት ተቃራኒ ትርጓሜ ያላቸውን ንግግሮች አጣምሮ ይይዛል። አባወራው ቀኑን ሲማስን ደክሞት ከዋለና ቤቱ ገብቶ እራቱን በልቶ መተኛት ብቻ ከሆነ ፍላጎቱ መርዶ ነው። ከሚስቱ ጋር “እንትን” አምሮት ከሆነ ደግሞ የምስራች!
ምስር ብሉ
እኛ እኮ ቃለ-ጽዩፎች ነን። እንኳን ተገላልጠን ይቅርና ተከናንበን እንኳን ምግባራችን በተከናነቡ ቃላቶች ውስጥ የመገለጥ ክዋኔው ክብርን የሚያዋርድ ሳይሆን የሚያገዝፍ የሚሆንብን። በሃዘን ቤት ውስጥ ባል ያላቸው ሴቶች ይግባቡባቸዋል ተብለው ውስጥ ውስጡን በእድሜ ደርሰን ከታዘብነው ንቁሪያ መካከል አንዱ ይሄን ይመስላል፦
ሚስት ለአዘንተኛው ምስር ወጥ ጨላፊ ናት። ምራት ደግሞ እንጀራ አቅራቢ። እና ምራት በቅናት ርር ብላ ለሚስት “ከምስሩ በደንብ ጨልፊለት” ስትል በነገር ትወጋታለች። ሚስትም ቀላል ሰው አልነበረችምና፦
ያንቺን እንጀራ በልቶ ሲጨርስ እጨልፍለታለሁ” አለች አሉ።
እስቲ ምን እንደተባባሉ የገባው ሰው ስንት ይሆኝ?
ከተረታችን ውስጥ “እንትን” ምን እንደሆነ በማይታወቅበት ዘመን አንድ ምሳሌያዊ አባባል ተፈጥሮ ነበረ። የሚገርመው ነገር የዚህ “እንትን” ምንነት ዛሬም ድረስ ግልጥልጥ ብሎ አልታወቀም። ዘመን ገስግሶ፣ መግባባት በዕድሜና በአቻ መሆኑ በቀረበት የሳይበር ዘመን ላይ ደረስንና በተግባር ሊመለሱልን ለሚገቡ ጥያቄዎች ጉግል በማሰስ ብቻ ተቆነፃፅለን ስናበቃ “እሱን ትደርስበታለህ” ስንባል፣ “እሱን ስትገረፍ ታወራዋለህ” በማለት እድገትና መድረስ በማይፈታው መደነቋቆር ዘመን ውስጥ ከታላላቆቻችንና ከታናናሾቻችን እኩል ቁመት ይዘን ሳንግባባ መኖር ከጀመርን ሁለት አስርታት እየተቆጠሩም አይደል? ታዲያ ለዚህ መፍትሄው መንድነው?
ምስር ነዋ! ምስር ሃይል ነው! ምስር ብርታት ነው! ምስር አስተምህሮት የሚጠናበት አንዳች መላ መቀየሻ መንገድ ነው! ምስር አብሮነት ነው! ምስር ከላይ እንደተገለፀው “እንትን” ቀስር ነው! “እንትን” ማለት ግን ምንድን ነው? ብለን ብንጠይቅ ሁሉም ሰው በአንድ ድምፅ “እንትን ነዋ!” የሚል አይጠፋም። እንትን ግን ምስጢር ነው። በዘመናችን “እንትን” የሚለው ቃል ሳይወድ በግድ ትርጉም አልባ ቃል መሆኑ ቀርቶ ውስን ትርጓሜን ብቻ እንዲይዝ የተገደደ የግፍ እስረኛ ቃል ሆኗል! #እንትን_ይፈታ!
አንድ ጥንታዊ ተረት አለ። የገበሬዎች የእርሻ ማሳ ላይ የዘሩትን አተር በድብቅ እየገባች የምትበላ አንዲት ጦጣ ነበረች። በዚህ ድርጊቷ የተማረሩ ገበሬዎች ተመካክረው አንድ ውሳኔ ላይ ደረሱ። “ማሳችን በጦጣ እየተደፈረ፣ ያሸተው ፍሬም እየተበላሸ ምርታችን ቀነሰ። ድካማችን መና ቀረ። ምን እናድርግ?” ሲሉም ተመካከሩ። “ምስር ዘርተን ለምን አንገላገልም?” ሲሉ አንድ አዋቂ አባት መፍትሄ አመላካቱ። እናም ሁሉም ተስማምተው በአተር ፋንታ ምስር ዘሩ። ታዲያ ሰብሉ ሲደርስ ለማዳዋ ጦጣ ወደሰብሉ በመግባት ምስሩን ትቀምሰዋለች። ፍሬው ከማነሱ የተነሳ እንኳን ለመብላት ለመያዝና ለመፈልፈል አልመች ቢላት በሰው ልጅ ተበሳጭታ ስተሰበቃ፤
“አተር መዝራት ወይ ብልሃት
ምስር መዝራት፣ ሥራ ማጣት!” በማለት ተረተች።
የማይወዱትን ማጣጣል የሚወዱትን ነገር ከፍ ከፍ ማድረግ የሰው ልጅ ስር ሰደድ ጠባይ እንደሆነ ለማስተማርና ለማመላከት የቀረበ ቀላል የመወያያ ተረት እንደነበር ልብ ይሏል።
*****
ምስር፦
ለወጥ የሚኾን ፍሬው ዐነስተኛ አበባ እህል (ብርስን ምስር ([ግዕዝ])። በአፍሪቃ ሰሜን በሚዲቴራኔአን ባሕር ወሰን ያለ ከፍልስጥኤም ጋር የሚዋሰን ምስር በሚስራይም ምስር የተባለ የጥንት አንቲካ የሚገኝበት።
ምስር፦
ቃና የቀንድ ጡሩንባ የቀንድ መለከት በዐመት በዐል ቀን በንጉሥ ፊት የሚነፋ ነው ምስር ቡዋቡዋ ሠረገላ ማለት ነው የነፊው ትንፋሽ በቡዋቡዋው በሠረገላው ውስጥ እየተላለፈ ልዩ ልዩ ድምፀ ቃናን ስለሚአሰማ ምስር ቃና ተባለ ምስር ቡዋቡዋ ቃና ዜማ ([ዐረቢኛ])።ያይጥ ምስር ቅጠሉ ምስር የሚመስል ሐረጉ እንደ አደንጓሬ ሐረግ የሚሳብ ፍሬው ጠንካራ። ግብጥ ምስር አንድ ዐይነት ወጥ።
ብርስን (ግዕዝ ሲሆን ቃሉ ትርጓሜው ‘ምስር’ ነው)፦ በቁሙ ብርስን (መ፡ ፈ)፡፡ ስመ ሀገር ግብጥ የሚጽራይም ክፍል ሚጽር፡፡ ሊጣፍ የሚገባው በጻዴ ነው እንጂ በሳት ሰ፡ አይዶለም፡፡ ደለወ ምስር፡፡ ማዕልቃ ዘምስር፡፡
ቮልቴር ስለ ቃላት የሃሳብ መሸሸጊያ መሳሪያነት ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ዋናው የቃል ጠቃሚነቱ ሃሳባችንን ለመሸሸግ ማገልገሉ ላይ ነው”
ለምሳሌ በ“የምስራች” ውስጥ “ምስር ብላ” ተሸሽጓል። በምስር ውስጥ “ወሬ የለውም ፍሬ” የሚለው አስተምህሮ ተቀብሯል። የምስራች ወሬ ቢሆን ኖሮ “ወሬ- የለውም ፍሬ!” የሚለው ቃል ምስር ወጥ ሆኖ በተበላ ነበር። ወሬ የደቃቋን የምስር ፍሬ ያህል ዋጋ ከሌለው ታዲያ ስለምንስ “የምስራች!” ይበሰራል? በርግጥ ብስራት በሚለው ቃላት ውስጥ (ብስል-ዕራት እና ምስር) ተሸሽገው ይሆን? ወይስ ራሱ “ምስራች” የሚለው ቃል (ምስ-እራት) ከሚለው ተወልዶ?
አያሌ “የምስራቾች ወሬ ሆነው ለፍሬ ሳይበቁ እንደሚያልፉ ምሳሌ የሚሆን ሰሚ ያጣ ተናጋሪ ምርር ብሎ እንዲህ ተናግሯል ሲሉ ሰማሁ፦
“ወሬኛ ሳይጠፋ ሞልቶ ተትረፍርፏል
ራብ የሚያስታግስ፣ የሚሰማኝ የታል?”
ምስር የወሬን ያክል አቅም ባይኖረውም ወሬን በተግባር (በቅንጣት ፍሬው አልመሽምሾታል። ወሬ አቅም አልባ እንደሆነ ከቅንጣት ያነሰው ፍሬ ምስክር ተጠርቷል። ምክንያቱም ዛሬ ስለ ምስር የማበስረው ገድሉን እንጂ ወሬ ብቻ ባለሞኑም ጭምር ነውና ተከተሉኝ፥
በአበው እና እመው አንደበት “ጦር ከፈታው፣ ወሬ የፈታው” እንደሚበልጥ ስነገረን እያደመጥን አድገናል። ያም ሆኖ ግን ወሬ የምስርን ያህል ቅንጣት ፍሬ የለውም። “ወሬ- የለውም ፍሬ!” ለአበባ የለውም ገለባ! ሲባል ያለምክንያት አልነበረም። ፍሬ ያለው ወሬ እንዳለ ጭምር ለማመላከት ነው። ያ ፍሬ ያለው ወሬ ደግሞ “የምስራች” ነው!
“የምስራች!”
ምስር ብሉ!
“የደገኛ ነወይ ወይስ የቆለኛ፣
የምሥራች ሞተች የሚል አማርኛ፣
እኛም ብንመረምር ሰውም ብንጠይቅ፣
የምሥራች ሞተች ተብሎም አያውቅ”
ጥንታዊ ከሆኑ ሰብሎች መካከል የሚመደበው ምስር የጥንታዊውን የግብርና አብዮት ካቀጣጠሉት ሰብሎች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። በቅርቡ በግሪክ፣ በግብፅ እና በቱርክ የተገኙ የአርኪዮሎጂ ግኝቶች የሚመሰክሩትም ይሄንኑ እውነታ ነው።
ከስምንት ሺህ አምስት መቶ አመት በፊት የሰው ልጆች ምስርን አምርተው ለምግብነት አውለውት የነበረ ከመሆኑም ባሻገር፣ በቅዱስ መፃሕፍትና በጥንታዊ መዛግብት ላይ ሳይቀር ብዙ ተብሎለታል።
በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኤሳው ብኩርናውን በምስር ማጣቱ አንዱ ምሳሌ ነው። ኤሳውና ያዕቆብ መንታ ወንድማማቾች ናቸው። ኤሳው ቀድሞ በመውለድ ይበልጠዋል። ኤሳው አዳኝ በመሆኑ አንድ ቀን ደክሞት ወደቤቱ ሲመለስ ያዕቆብ ምስር ወጥ እየሰራ ይደርሳል። የይስሐቅ የመጀመሪያ ልጅ የነበረው ኤሳው የብኩርና መብቱን በማራከሱ የተነሳ አንድ ቀን ኤሳው ተርቦ ሳለ ምግቡን ባየ ጊዜ ብኩርናውን (ውርሻው) መብቱን ለስጋ ድክመቱ አሳልፎ የሚሰጥበት አጋጣሚ ይፈጠራል። ይህም በዘፍጥረት 25:30 እንዲህ ተገልጿል።
“ቶሎ በል እባክህ፣ በጣም ስለደከመኝ ከዚያ ከቀዩ ወጥ የተወሰነ ስጠኝ!” አለው። በዚህ ጊዜ ያዕቆብ “በመጀመሪያ የብኩርና መብትህን ሽጥልኝ!” አለው። ኤሳውም “እኔ ለራሴ ልሞት ደርሻለሁ! ታዲያ የብኩርና መብት ምን ይጠቅመኛል?” አለው። ያዕቆብም “በመጀመሪያ ማልልኝ!” አለው። እሱም ማለለት፤ የብኩርና መብቱንም ለያዕቆብ ሸጠለት። ከዚያም ያዕቆብ ለኤሳው ዳቦና ምስር ወጥ ሰጠው፤ እሱም በላ፣ ጠጣም፤ ተነሥቶም ሄደ። በዚህ መንገድ ኤሳው የብኩርና መብቱን አቃለለ።” ከዚያ በኋላ ስሙ ኤዶም (ቀይ) ተባለ። ቄእ ወጥ? ቀይ ምስር? (ብቻ ከሁለት አንዱን ነው)
ምስር በዋነኝነት ለሰው ልጅ ምግብነት ብቻ ሳይሆን በአንፃሩ ሲታይ አነስተኛ መጠን ቢሆንም ለእንስሳት መኖ ጥቅም ላይ ይውላል። በፕሮቲን የበለፀገ ሲሆን፣ ካርቦሃይድሬት 47-65% ፕሮቲን 20-33%፣ 2-4% መአድናት እና 2% ቅባት ይዟል። በተለምዶ “ደም ማነስ” የሚለው አገላለጽ በደም ውስጥ በቂ ሂሞግሎቢን አለመኖሩን የሚያመለክት ነው። በሂሞግሎቢን ሞለኪውል ውስጥ የሚገኙት አራት ወሳኝ የብረት አተሞች ከሌሉ በዚህ ሞለኪውል ውስጥ የሚገኙት የተቀሩት 10,000 አተሞች ምንም ፋይዳ አይኖራቸውም። ስለዚህ ጤናማ ምግብ በመመገብ በቂ የብረት ማዕድን ማግኘት በጣም አስፈላጊ ነው። በብረት ማዕድን የበለጸጉ የምግብ ዓይነቶች ውስጥ ዋንኛው ደግሞ ምስር ነው።
*ምስር ለብርታት!
የአይረን (ብረት) እጥረት ለጤና መዛባትና ለአካላዊ መዳከም እንደሚያጋልጥ ተደርሶበታል። ምስር ብርታትን ለመጨመር ይጠቅማል። ልብ በሉ፤ በተለምዶ “ደም ማነስ” የሚለው አገላለጽ በደም ውስጥ በቂ ሂሞግሎቢን አለመኖሩን የሚያመለክት ነው። በሂሞግሎቢን ሞለኪውል ውስጥ የሚገኙት አራት ወሳኝ የብረት አተሞች ከሌሉ በዚህ ሞለኪውል ውስጥ የሚገኙት የተቀሩት 10,000 አተሞች ምንም ፋይዳ አይኖራቸውም። ስለዚህ ጤናማ ምግብ በመመገብ በቂ የብረት ማዕድን ማግኘት በጣም አስፈላጊ ነው። በብረት ማዕድን የበለጸጉ የምግብ ዓይነቶች ውስጥ ዋንኛው ምስር ነው።
ምስር ብሉ!
ቀላሉ ነገር ምስር “እንትን” የከላከላል። እውነቴን ነው፤ ማለት ካንሰርን ይከላከላል!
ምስር ብሉ!