2016 ሜይ 20, ዓርብ

ቆይታ (ከቀብር አስፈፃሚዎቹ ጋር)


☞ኄኖክ ስጦታው

ለሞት ያለኝ ግንዛቤ ግልፅና አጭር ነው። ሞት እድገት ነው፤ መወለድም እድገት። "የሰው ልጅ ከሞት በኋላ ያለውን ካለማወቅ ፍራቻ አያሌ መሸሸጊያ ፈጥሯል" ያለው ዲካርት መሰለኝ ።

ጓደኞቼ "እንሳለም" ብለው ሚካኤል ቤተክርስቲያን ጋር መኪናዋን አቆሙ።"ዛሬኮ አርሴማና ተክልዬ ይነግሳሉ፤ አትሳለምም?"

"አልሳለምም፤ እናንተ ደርሳችሁ እስክትመጡ ቀብር አስፈፃሚዎቹ መደብር ውስጥ እጠብቃችኋለሁ።"

ወደ ሬሳ ሳጥን መሸጫና ማደሻ መደብር አመራሁ። ብዙ አይነት የአስክሬን ሳጥኖች ተደርድረዋል። ሁለት አይነት አበቦች (በወረቀት ተሰርተው ቀለም የተነከሩ እና ከበቀሉበት የተዘነጠፉሸአበቦች) ደጃፉ ላይ አየሁ። ፊትለፊት ሆነው እይታዬን ያልሳቡት ለምን ይሆን? ስልኬን አውጥቼ ፎቶ ማንሳት ጀመርኩ።

ሰዎች እንዳላዩ ሆነው ከሚያልፏቸው ነገሮች አንዱ እንደዚህ አይነት መደብሮችን ነው። መደብሩ በራፍ ላይ አበቦች አሉ። ከአበቦቹ በላይ ያሉት በላይ በላያቸው የተደራረቡ ሳጥኖች ግን አበቦቹን ጋርዷቸዋል። አ አ!  አይደለም። አስክሬን ሳጥኑ ከፊት ካልሆነ በቀር አበቦቹን እንዴት ከዕይታ ሊጋርዳቸው ይቻለዋል?

"ሄይ፣ ፎቶ ማንሳት ክልክል ነው!" የሚል ድምፅ ሰማሁ። ሁለት ወጣቶች ወደኔ መጡ።

ፎቶ ማንሳት ክልክል መሆኑን የሚገልፅ ምንም ምልክት የለም። ለምን ክልክል እንደሆነ ጠየኩ።

"የአስክሬን ሳጥኖቹ ዲዛይን ይሰረቅብናል። አይቻልም።"

"የሳጥኑ ዲዛይን ከሌላው በምን እንደሚለይ ማወቅ እችላለሁ?"

"የማትገዛ ከሆነ ብነግርህ ምን እጠቀማለሁ?"

"እኔ ባውቅ ምንስ የምታጣው ነገር አለ?"

"ለምንህ ነው ማወቅ የምትፈልገው?" ሲል ሌላኛው ጠየቀኝ።

"በቃ፣ ደስ ይለኛል። ሳጥኖቹን በቅርብ ሆኜ ባይ፣ አብሬያችሁ ውዬ ቀብር ባስፈፅም ደስ ይለኛል። በተለይ ከሳጥኖቹ መሐል የማስታወሻ ፎቶ ብነሳ… ደስ ይለኛል" አልኩ። እውነቴን ነበር።

እርስ በራሳቸው ተያዩና ፈገግ አሉ። ወደ ውስጥ እንድገባ ፈቀዱልኝና ትልቅ አልበም እንድመለከት ጋበዙኝ።
ለጨዋታ መጀመሪያ ያክል "ስራ እንዴት?" አልኩ።

"እግዚአብሔር ይመስገን"
(ምሥጋና ጥሩ ነው) 😱

የሚያምር የሬሳ ሳጥን አየሁና ዋጋውን ጠየኩ፦

"12ሺ ብር።" አለ።

"ዋጋው እንደዚህ የተወደደበት ምክንያት ምንድነው?"

"በኤምዲኤፍ ነው የተሰራው። እንደምታየው የሳጥኑ የላይኛው ክፍል ሙሉ መስታወት ነው። አስክሬኑ በሱፍ ሽክ ተደርጎ ይገነዛል።"

"ዋጋው አስክሬኑ የሚለብሰውን ሱፍ ጨምሮ ነው? "

"ልብሱን ቤተሰብ ነው የሚያዘጋጀው።"

"ለሴቶች ሲሆንስ?"

"አይቀንስም"

ሳቅኩ።
"ዋጋውን አልነበረም የጠየኩህ። አስክሬኑ የሴት ከሆነ ምን አይነት ልብስ ነው የምትገነዘው?"

እርስ በራሳቸው ተያዩ። መቼስ ሱፍ አያለብሱ።
ሁለተኛው መለሰልኝ፦
"የአገር ባህል ልብስ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ባለሙሉ መስታወት ሳጥኖችን ግን እስካሁን የተጠቀምነው ለወንዶች ነው።"

"የአሜሪካ ሳጥንም አለን።" አለ ሌላኛው።

"የትኛው ነው?"

"እዚህ የለም። አልበሙ ላይ ላሳይህ…።" አልበሙን ተቀብሎኝ ገለጥ ገለጥ አድርጎ "ይኸው!" አለ።

ያምራል።

"ዋጋው ምን ያህል ነው?"

"35 ሺ ብር"

"እ?"
ደገመልኝ። በሰላሳ አምስት ሺህ ብር የ1972 አዲስ ብራንድ አፍሮ ቮልክስ መሸመት የሚችል ብር እንደሆነ አሰብኩት። የገረመኝ ግን ሌላ ነበር፦
"ሳጥን አስመጪ አለ ማለት ነው?"

"አስመጪ የለም። ከአሜሪካ አስክሬን ይመጣበትና የአገር ውስጥ ሳጥን ላይ ብር ጨምረን ከቤተሰቦቹ ላይ እንገዛዋለን።"

"እዝጎ!" (አልኩ በውስጤ)

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ