ልጥፎችን በመለያ ቅኔ በማሳየት ላይ። ሁሉንም ልጥፎች አሳይ
ልጥፎችን በመለያ ቅኔ በማሳየት ላይ። ሁሉንም ልጥፎች አሳይ

እሑድ 2 ፌብሩዋሪ 2020

“አብሾ “፥ “አፍልሆ”፥ መድሃኒት (ኄኖክ ስጦታው)



አለቃ ለማ ትዝታቸውን ለልጃቸው ለመንግስቱ ለማ(ለአብዬ መንግስቱ) ያጫወቱት ነው ፤ በመምህሩ አፍልሆ ስለተደረገለትና በቅኔ ተወዳዳሪ ስለሌለው አንድ ተማሪ ነው ጨዋታው። መምህሩ አለቃ ተጠምቆ ይሰኛሉ። የተማሪው ስም ሠረገላ ብርሃን የተሰኘ በኋላም የታወቀ የቅኔ አስተማሪ የሆነ ሰው ነው። አለቃ ለማ በጣፈጭ አንደበታቸው ለልጃቸው እየተረኩለት ነው።

“ተማሪያቸው ነው አፍልሆ አርገውለታል ይመስለኛል ተጠምቆ፥ መዳኒት ጸሎት በውሃ እሚደግም - ለቅኔ ብቻ አይደለ፤ ለዜማም ለመጣፍም እንዲያው ለሚጠናው ሁሉ ነው። በውሃ ስለተደገመ ነው አፍልሆ የተባለው. . . እገሌ ሰው ያህለዋል አይባልም ቅኔ በማሳመር - ቅኔው ሌላ ነዋ ባያሌው። ሲመራ! ወዲያው መምራት ነው። አራት ተማሪ አቅርቦ ይመራል የሚባለው እሱ ነው። መምህር ሆኖ፤ . . . እሱን እንዲህ ያደረገው አለቃ ተጠምቆ ናቸውና እኔም እንደሱ እሆናለሁ ብዬ ተነስቼ ሄድኩ ኸሳቸው። . . .” (መፅሐፈ ትዝታ ዘዓለቃ ለማ፤ ገፅ 79)

ስለ አብሾ (አፍልሆ) በቃል የተናገሩት ሊቀ ጉባኤ ፈቃደ ስላሴ ተፈራ ናቸው። አያሌ ጥያቄዎችን የሚመልስና ብዙ ጥያቄዎችን የሚያጭር መረጃ ሆኖ ለዚህ ዕሑፍ የጀርባ አጥንት ሆኖኛል። “በአገራችን የቤተክርስቲያን ምሁራን ዘንድ ትምህርት ይገልፃል፥ አእምሮ ይስላል እየተባለ በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ተቀነባብሮ በተለያየ የእድሜ ደረጃ ላሉ ተማሪዎች የሚሰጥ መድሃኒት ሲሆን በተጨማሪ “ዘኢያገድፍ” እንዲይዝ የማይጥል፣ “መክሰተ ጥበብ” እና “መፍትሄ ሀብት” እየተባለ ይጠራል. . .” ሲሉም አክለውም ስለ አብሾ ምንነት ያብረራሉ።

ይህ ገለፃቸውን ለሚመረምር ሰው የአብሾን ጥቅም ከዕውቀት ገላጭ ከመሆኑ ጋር ብቻ እንዳልሆነ ይረዳል። የመጀመሪያው ደረጃ መድሀኒት “ዘኢያገድፍ” ተብሎ የተገለፀው በቤተክህነት ትምህርት ፊደለም ሆነ ቅኔ ለሚገድፉት የሚሰጥ ሲሆን የሚማሩትን በቃላቸው ቶሎ እንዲይዙ (እንዳይጥሉ) የማድረግ አቅም ያለው መድሃኒት እንደሆነ ግልፅ ነው። ሌላኛው “መክሰተ ጥበብ” የሚሰኘውም የቃላቱ ትርጓሜ እንደሚነግረን ጥበብ ገላጭ እንደሆነ ያመላክታል። ይህም ከዕውቀት አንድ ደረጃ ከፍታውን ወደ ጥበብ የሚያሳድግ መድሃኒት ነው።  ሶስተኛው “መፍትሄ ሀብት” ነው። ለነዋይ ማካበቻ ይረዳል ተብሎ የሚሰጥ መድሃኒት እንደሆነ ተረድቻለሁ።

[በተለይም የአብሾ አፍልሆ ለቅኔ ዘረፋ እድሜ ልክ የሚያነቃቃ አብነት ነው። እየተባለ ይጠጣል። በቃልም፥
ጠላ ያለጌሾ
ቅኔ ያለአብሾ . . . እየተባለ ይተረታል። አብሾ ሶስት አይነት ዝርያ ሲኖረው ጥቁር፥ ቀይና ነጭ ናቸው። ጥቁሩ በአገራችን በየትኛውም ቦታ በቅሎ የሚገኝ ሲሆን አስተናግር ተብሎ የሚታወቀውም ጥቁሩ ነው። (አብሾ የተሰጠው ተማሪ) . . . የሚነገረው ትምህርት የማይጠፋውና የሰማውን ነገር የማይረሳ ከሆነ ሆሳዕናው (መድሃኒቱ) ሰመረለት ይባላል። ካልሰመረለት የርኃወተ ሰማይ ቀን ጠብቆ እንደገና ይደረግለታል እየተባለ ይነገራል። (ርኃወተ ሰማይ የሰማይ መከፈት ነው) ይኸውም የሚሆነው በአመት አራት ጊዜ ሲሆን ጳጉሜ 3፥ ታህሳስ 13። የካቲት 4 እና ግንቦት ስምንት ቀን ነው። ]

ጥንታዊው የቤተክህነት መፅሐፍት መካከል፣ “ፅፀ ደብዳቤ” አንዱ ነው። በጥንታዊ አባቶቻችን በመድኃኒቶች ላይ የነበራቸውን ጥበብ በአውደ ነገሥት ላይ ሰፍረው ይገኛሉ። ከእነዚህም መድኃኒቶች ተራ ቁትር 56ኛው አብሾ (አብሶ) በሚል ስም ተጠርቷል። ስለሆሳእናው (መድሓኒቱ) ምንነት እና አድራጎት፣ በባህላዊና መንፈሳዊ ህክምና ጥበብ አማካኝነት ትምህርት ለማይዘልቀው ልጅ ሁነኛ መድሃኒት እንደሆነ እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፦

[፶፮፤ አብሶ (ዕፀ ፋርስ አስተናግር) በበርኻ የበቀለ ነጩ ፍሬውን ደቍሶ በነጭ ሽንኵርት ብቻ በተደለዘ በርበሬ ሽሮ በነጭ ጤፍ እንጀራ እየፈተፈቱ መልክአ ኢየሱስን እየደገሙ ፯ ቀን ለክተው ለሕፃናት ቢያበሏቸው ትምህርት ከመ ቅጽበት ይገባቸዋል ፍቱን ነው። እንዲሁም ከመ ዘኢያገድፍም ፫ ቀን ጠዋት ጠዋት ማዋጥ ነው።]

ሊቀ ጉባኤ ፈቃደ ስላሴ ተፈራ ስለ መድሃኒቱ አዘገጃጀት ሰፋ ያለ ትንታኔን ሰጥተዋል።[“. . .የሚዘጋጀውም ከልዩ ልዩ እፅዋት ቅጠል፥ አበባ፥ ስርና ተቀፅላ በመሆኑ በማር ወይም ንፁህ ማር ወፍ ባልቀመሰው ውሃ (በጠዋት በተቀዳ ውሀ) በሞላ ብርሌ (በጥቁር ብርሌ) ውስጥ እስከ አንገቱ ውሃ ተሞልቶ ከተበጠበጠ በኋላ ለማፍሊያ የተዘጋጀ ፀሎት እየተፀለየበት አንድ ሱባኤ ይቆያል። እስከ ሰባት ቀን ይሰነብታል። ሱባኤው ሲያልቅ በሰባተኛው ቀን ተጠቃሚው ልጅ ወይም ደቀመዝሙር በባዶ ሆዱ ይጠጣዋል። ወዲያው እንደ ጠጣ ከሰው ተለይቶ ለሶስት ቀናት ብቻውን በአንድ ክፍል ውስጥ ይታቀባል/ ይቀመጣል። ከዚያም ለአንድ ሱባኤ ወይም ለሰባት ቀናት አልያም ለሰባት ሱባኤ ወይም ለአርባዘጠኝ ቀናት የተወሰኑ ምግቦችን እየበላ ማለትም የገብስ ቆሎ ፥ የገብስና የጤፍ እንጀራ በኑግ ጭማቂ በማጥቀስ እየበላና የኑግ ጭማቂ ብቻ እየጠጣ የሚያጠናውን ንግግር በማሰላሰል እንዲቆይ ምክር ይሰጠዋል። አደራረጉ የተለያየ ከመሆኑም በላይ የሚቀመሙትም እፅዋት እንደየመምህራኑ ጥናትና እንደየገቢሩ የተለያዩ ናቸው ይባላል. . .”]

መዛግብት ይህንን ቃል በምን መልኩ አንደፈቱት ተመልክቼ ነበር። አብሾ የመድሃኒት ስያሜ ሲሆን የተለያዩ አይነት አእምሮን አነቃቂ እፆች አማካኝነት ተቀምሞ ለመፍትሄነት ሲያገለግል የኖረ ጥንታዊ መድሐኒት እንደሆነ ይናገራሉ። ከኢትዮጵያ ውጪ የጥንት ስልጣኔ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ በሆኑት ሩቅ ምስራቅ አገራትም ውስጥ ተመሳሳይ መድሀኒቶች እንዳሉ ይታወቃል። በቻይና፣ በሕንድ እና በጃፓን እውቀት ገላጭ፣ አእምሮን አብሪ የሆኑ ባህላዊና መንፈሳዊነትን ያጣመሩ ተመሳሳይ መድሃኒቶች እንዳሉ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።

በቤተክርስቲያን ውስጥ ተወስኖ ስላለውና እንብዛም ጥናት ባልተደረገበት “አብሾ” ዙሪያ በቃልና በፅሁፍ ያገኘኋቸውን መረጃዎች ተቀነጣጥበውም ቢሆን ሰፍረው ይገኛሉ፤ ከነዚህም ውስጥ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ በመዕሀፈ ሰዋሰው አስተናግር ወይም ዕፀ ፋርስ አናግር አስለፍልፍ ስለሚሰኘው ዕፅ ምንነት ሲያብራሩ፥ ‘የቀመሰው ሰው ወደ ፊት የሚሆነውንና የሚያገኘውን ስለሚያናግር አስተናግር’ እንደሆነ ይጠቁሙናል።

ደስታ ተክለወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በተሰኘው መፅሐፋቸው ስለ ዕፁ
[ዕጠ፡ ፋርስ] ተመሳሳይ ሐሳብ አስፍረው አንብቤያለሁ። [የፍሬው ልብስ እሾህ ያለበት ተክልነት የሌለው የዱር እንጨት፤ ቅጠሉን በጎች ቢበሉት ራሳቸውን ያዞራል፤ ሰውም ቢቀምሰው ያሳብዳል። ባላገሮችም ዐጤ ፋሪስ ይሉታል። ይህ ሁለት አይነት እንጨት ባገዳ በቅጠል በፍሬ ልዩ ሲሆን ልብን በመንሳት ስለተባበረ ባንድ ስም ተጠራ። በካህናት ዘንድ ግን ሁለተኛው ከአንደኛው ተለይቶ አስተናግር ይባላል። ]

በቤተክህነት አካባቢ ያሉ አንድ አባት ስለ አብሾ ምንነት እንዲነግሩኝ ጠይቄ ነበር።  “ፍሬውን የቀመሱ ሁሉ ባለብሩህ አእምሮ ይሆናሉ። ትምህርት ገላጭ ነው። ትንቢትም ያናግራል። በጥንቃቄ ካልተደረገ ለእብደትና ለሞት የሚያበቃ ስካር ውስጥ ይጥላል” ሲሉ ሃሳቡን አጠናክረውታል። 
በተለምዶ አብሾ (አብሶ) ተብሎ የሚጠራው አንዱና ዋንኛው አድራጎታዊ መገለጫው ሲሆን አስተናግር ከተሰኘ ዕፅ ይቀመማል። አድራጎት አፍልሆ ተብሎ ይጠራል። በአንድ ቀን የሚፈላ አፍልሆ አለ ይባላል። የዚህም ቅመማ ከላይ እንደተገለፀው ሆኖ በተጨማሪም ዛጎል ተደቁሶ ይጨመርበታል። ዛጎል ፀሎት የሚደረግበትን መድሃኒት ቶሎ የማፍላት ሃይል ስላለው እለቱን እንዲፈላና እንዲገነፍል ያደርገዋል። እንደ ፈቃደ ስላሴ ተፈራ አባባል ከሆነ የዚህ አይነቱ አፍልሆ (ዛጎል የገባበት) ጥሩ እንዳልሆነ ሲነገር ሰምተዋል። ተማሪዎች ቅጠሉን አፍልተውና ከጤፍ እንጀራ ጋራ ፈትፍተው በቀመሱት ጊዜ አእምሯቸውን ለውጦ ማደሪያቸውን ያናጋል፤ ማርከሻውም የኑግ ልጥልጥ ወይም በሶ እንደሆነም ያምናሉ።

ቀዩ በቆላማ ቦታዎች አካባቢ በሚፈስ ወንዝና ወንዝ መጋጠሚያ ላይ ይገኛል። ነጩ አብሾ ከጎንደር በበሸሉና አባይ መጋጠሚያ በጎጃም በዚገም ወንዝና በአባይ መጋጠሚያ፥ በሸዋ በሙገርና በአባይ ወንዝ መጋጠሚያ ይበቅላል ሲሉ ፈቃደ ስላሴ ተፈራ ስለፍሬዎቹ አይነትና ጥቅም፣ ብሎም ጉዳት ጠቁመዋል። ከፍሬዎቹም ዓይነቶች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉት ቀዩ እና ነጩ ብቻ እንደሆኑ ይነገራል። አጠቃቀሙም የተለያየ ነው። አንዳንድ መምህራን ስለአብሾ መድሀኒት ሲናገሩ አብሾ ጠጥቶ ወይንም በልቶ እስከ አርባው ቀን አልክሆል መጠጥ መቅመስ ሰካራም ያደርጋል ይላሉ። ነገር ግን አርባው ቀን ካለፈ በኋላ አልኮል ቢጠጣም ምንም ጉዳት እንደማያስከትል ይናገራሉ። በተለይ አደራረጉን የማያውቁ መምህራንም ሆኑ ተማሪዎች ወይም ግለሰቦች አብሾ ጠጥተው ወይም አጠጥተው ወዲያው አልኮል ስለሚጋቱ ሰካራሞችና አልፈው ተርፈውም እብዶች ይሆናሉ።

“የአብሾ ነገር ሲነሳ አንድ ትዝ የሚለኝ ነገር አለ” ባሉት የሕይወት ገጠመኝ በሳቸው አንደበት እንዲህ ይተረካል፦
[በ1953 ዓ.ም በነሀሴ ወር በጎጃም ክፍለሀገር በደጋ ዳሞት አውራጃ ዋሸራ የቅኔ ትምህርት ቤት በነበርኩበት ጊዜ 3 ሰዎች አብሾ ሲጠጡ ጠብቀን ብለው እኔንና ጓደኛዬን ዛሬ የቅኔ መምህር ማሞ ሀብተ ማርያምን ከዋሸራ በግምት 15 ኪሎሜትር ርቆ በሚገ/ነው በአካባቢው ሰው በሌለበት በዮሀንስ ገዳም ወስደውን በአንድ ሰፊ ደጀ ሰላም ውስጥ ገብተን ሳለ ቀኑ መሸት ሲል አብሾውን በስንዴ ዳቦ ጋግረው ሶስቱም ከበሉ በኋላ በሩን በጥብቅ ዘግተን ፀሎት ጀመሩ። ከዚያ ፀሎቱን እየፀለዩ ለሁለት ሰአት ያህል እንደቆዩ አንዱ እሪ፥ እንሽሽ ያለንበት ቤት ተቃጥሏል አለና ውሸቱን አስተጋባ። ወዲያው ለመሸሽ ከግድግዳ ጋራ እየተላተመ ስለአስቸገረ እኛ እና ሁለቱ ያልሰከሩ ጓደኞቹ ከአንድ ወጋግራ ላይ በገመድ አሰርነው። ወዲያው ሁለተኛው ተማሪ አንዳንድ ትንቢት ብጤ ሲናገር ቆይቶ “ሸማ ስራዬን አላሰራ አላችሁኝ፥ ቁቲቴን ስጡኝ” እያለ ስላስቸገረን እንደፊተኛው ከአንድ ወጋግራ ላይ ሸብ አደረግነው። ወዲያው የቅዳሴ ዜማ እንደጀመረ አንቀላፋ። ሶስተኛወ ግን ስካር እንደጀመረው “ተው ና ውረድ ቡሬ” እያለ የአራሽ መሰል ንግግሩን ጀመረ። ከዚያም ቀጥሎ
የበሬው ውለታ ይገለፃል ማታ
እብቁ በግርግብ ውሃው በገበታ።
እያለ ሲያዜም ቆይቶ እንቅልፍ ወሰደው። ከዚያ በኋላ መጀመሪያ የሰከረው ሰው የቅኔ ዘረፋውን ቀጥሎ ዶሮ እስኪጮህ የጀመረ እስኪነጋ ድረስ እጅግ በጣም ብዙ ቅኔ ድርሰቶችን ሲደርስ አድሯል።

ከዚያ በኋላ ሶስቱ እንቅልፍ ወስዷቸው ቀኑን ከዋሉ በኋላ ሌሊቱን አድረው በሶስተኛው ቀን ሙሉ አእምሯቸው ተመልሶላቸዋል፥ አንዳንድ ጊዜ ሲገላበጡ እየጠራን እህል ውሃ እነዲቀምሱ ስንጠይቃቸው በጣም ይበሳጩ ነበር። የታሰሩትን ፈትተን ልብሳቸውን ሲጥሉ እያለበስን አስተኝተን ተራ በተራ ያለምንም ድንጋጤ ስንጠብቅ ሰንብተናል። ከዚህ ውስጥ አስገራሚው ሁኔታ ሰካራሞቹ እኛን ለመደብደብ አልሞከሩም። ስንቆጣቸው ቶሎ ደንግጠው ትእዛዛችንን ይቀበሉ ነበር።]

ማክሰኞ 14 ማርች 2017

አባይ ጠባብ መንገድ

(ኄኖክ ስጦታው)

የወንዝ አገሩ መነሻው፤ የወንዝ አገሩ መድረሻው
ወንዝ የሌለበት አገር ነው፣ መውጫ መግቢያው የጠፋው¡
*
የወንዞች ህብር ውጤት፤ የውኆች ስብስብ ጥምር
አባይ ፀሎቴን ስማ፣ ልንገርህ አንዳች ምስጢር።

ወደሄድክበት ውሰደኝ፤ እኔም አፈር ነኝና፣
ከአገሬ አንዴ ከወጣሁ፣ ሌላ ወንዝ አላጣምና።
*
አባይ ፀሎቴን ስማ፣ ከነአፈሬ አብሬህ ልውጣ
ሺህ ቢጎድል ተገድቦ፣ ሺህ ቢሞላ የሚቆጣ
ወንዝ ብቻ እንደሆነ፣ አውቃለሁኝ፤ ታውቀዋለህ!
አብረን ታስረን፣ ነፃ እንውጣ።

ማክሰኞ 6 ሴፕቴምበር 2016

ከራስ ባህሪይ ጋር ጦርነት

አንድ የቼሮኬ አዛውንት ለልጃቸው ልጅ ይህን ታሪክ አጫወቱት፣
"የእኔ ልጅ፣ በሁለት ተኵላዎች መካከል ታላቅ ጦርነት ተፈጠረ። አንደኛው ተኩላ #ክፉ ነው። ይህም ማለት፣  ቁጣ፣ ቅናት፣ ስግብግብነት፣ ቂመኝነት፣ በየበታችነት ስሜት እና በውሸት የተሞላ ነው።
“ሌላኛው ተኩላ ደግሞ #ጥሩ ነው። ይህም ማለት… ደስታ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ተስፋ፣ ትህትና፣ ደግነት፣ አዘኔታ፣ እና ሀቀኝነት ያሉት ነው።”
ህፃኑ ልጅ እንዲህ ሲል አያቱን ጠየቀ፦ "የትኛው ተኵላ አሸነፈ?"
አዛውንቱ ለጥቂት ጊዜ ያክል ዝም ብለው ቆይተው ይህን መለሱ፦
"አሸናፊው ያለው ከውስጥህ ነው።"

ሐሙስ 23 ጁን 2016

ውጣ—ውረድ

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)

“ነበር” ላይ ሊያበቃ፣ የ“ነው” ባይ  አቅጣጫ፤
ከ"ነው" እና "ነበር"፣ የታል የኔ ምርጫ?


መድረሻው መነሻ
          መነሻው መድረሻ
ጠይቅ “የታል” ብለህ… “የታል ውጣ—ውረድ”?
(ሕይወት መሰላል ነው፤ የእርብራብ መንገድ!)

የጥያቄ ምላሽ፣ በምጥ ላይወለድ
“እውነት” ካስጨነቀህ፣
  በስንዝር ቦታ ላይ፣ ጋት ጨምር… ተራመድ
መልሱን ተወውና፣ መጠየቅን ውደድ
                    ውጣ
           ወይም
ውረድ!

ሐሙስ 9 ጁን 2016

ፀሐይ

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)
የልቤን መሻት ለማድረስ፣ ውጣ ውረዱ ሲበዛ 
የመንፈስ ብርታት ልትሆነኝ፣ ሙቀቷ ሕይወት ሊነዛ
ፀሐይ ምድር ደርሳለች፣ ፍኖተ ሃሊብ ተጉዛ፡፡
ዝለቂ ከዋሻው ብርታቴ፣ ስንፍና ሰበቡን ይጣ
“ፀሐይ ልሞቅ ነው” በማለት፣ እኔም ከዋሻው አልውጣ፡፡

ረቡዕ 8 ጁን 2016

ወጣ ያሉ የግዕዝ ቅኔያት

ወጣ ያሉ የግዕዝ ቅኔያት

በአጋጣሚ አግኝቼ ያነበብኩት መጽሐፍ ነው። “ቅኔያዊ የእውቀት ፈጠራ“ ይሰኛል ርዕሱ። በማርዬ ይግዛው ተሰናድቶ በ የጀርመን የባህል ማዕከል፣ 2006 ዓ.ም የታተመ ነው።

“…አብዛኛዎቻችን ቅኔ ኃይማኖታዊነት ብቻ የሚንጸባረቅበት ይመስለን ይሆናል። ቅኔ የማይዳስሰው ነገር የለም። የጾታ ተራክቦን (የግብረ—ሥጋ ግንኙነትን) እና መዳራትን ጨምሮ።…” እያለ ይቀጥላል የመጽሐፉ ትንታኔ።
ቀነጫጭቤ ጋበዝኳችሁ፦

ቅኔ ፩

ኢይጠፍእ ሕልጽ እሳት ላዕሉ ወታህቱ፣
እስኪት ጉልጥምት እስመ ተዳፈነ ቦቱ።
ትርጉም፦
          እምስ የላይና የታቹ እሳት አይጠፋም፤
          ቁላ/ጉልጭማ (እንጨት) ተዳፍኖበታልና።
ምስጢር ፦

ጉልጭማ የተዳፈነበት እሳት እንደማይጠፋ ቁላ የሚገባበት እምስም ሙቀት አይለየውም። በተለምዶ እሳት የሚጠፋው በውሃ፣ ሙቀት የሚበርደውም በቀዝቃዛ ነገር ነው። እምስ ግን ራሱ የቁላን ትኩሳት የሚያስታግሰው በማይጠፋ ሙቀት ነው እንጂ ከቀዘቀዘ አስተናጋጅነቱ ይቀራል።

እሳቱ/ሙቀቱ የማይጠፋ የሚለው የመራባት የሰው እንስሳዊ ህይወት ምንጭ መሆኑንም ያመላክታልና በዚህ ግልፅ ወሲባዊ ቅኔ ውስጥም ስለ ሕይወት ቁም ነገር አልጣበትም።

ቅኔ ፪

እታገኝ ደመርኪ እምላእለ ክብርኪ ክብር፣
ለነዳይ እስኪት እስመ ወሀብኪ ቂንጥር።

ትርጉም ፦
         እታገኝ በክብር ላይ ክብር ጨመርሽ
         ለድሃው ሰው ቁላ ብልት በመጽውተሽ። (መጽውተሽዋልና)

ምስጢር ፦
ይህ ቅኔ እማሆይ ገላነሽ እታገኝ የተባለች ልጃቸው ስታገባ የተቀኙት ነው ይባላል። ሰሙ በዚህ ዓለም ለተራቡ ሰዎች የሥጋ ብልት ሳይቀር የሚመጸውቱ ሰዎችን ይገልፃል። ባለቅኔዋ እታገኝ የተባለችው ልጅ ስታገባ ለተራበ ቁላ የሚገባውን ምግብ በመስጠት የጽድቅ ሥራ ማድረጓን አስመስጥረዋል።

እሑድ 8 ሜይ 2016

ተራማጅ እሳቤ ፺፩

(ኄኖክ ስጦታው)

ባለሶስት ፉርጎ ነው፤ ይጓዛል ባቡሩ፤ ቆየሁ ተሳፍሬ 
            የኋላኛው – ትላንት፣
            የፊተኛው – ነገ፣
            መሀለኛው – ዛሬ …
*
የታለፈ ትላንት፣ ያልተኖረ ነገ፣ ሃሣብ ውስጤ ሰርጎ
(ወጥሮ ይዞኛል)
         ፊት ላይሆን—ወይ ኋላ፣ መሐለኛው ፉርጎ።

እሑድ 10 ኤፕሪል 2016

Rumi "ልብስና ሰው"

"ይታዩኛል ብዙ ሰዎች
ዕራፊ አልባ፣ ልብስ የለሾች፤
ይታዩኛል ብዙ ልብሶች
በውስጣቸው የሉም ሰዎች።"

~ ሩሚ
ትርጉም ኄኖክ ስጦታው

ሐሙስ 25 ፌብሩዋሪ 2016

አዳም… (ኄኖክ ሥጦታው ናሁሰናይ)

አዳም…
(ኄኖክ ሥጦታው ናሁሰናይ)


"ጥፋት"፣ "ታዛዥነት" …
ቢጋጩ ከድንጋይ
                "ተቃጠልኩኝ" አትበል…
                 እሳት ፈጥረው ብታይ።
*
ፍላጎቱን ሳይኖር፣ "ሕግን" ያከበረ፣
በተጻፈው እንጂ፣ ራሱን መች ኖረ?!
*
አዳም ሰው አትስማ፣ ከትዛዝ ላይወጣ
"ሕግ ጣሰ" ይበል፤ "በበላው ተቀጣ"
የኖርከውን ሳይኖር፣ ያስብ ምን እንዳጣ!
*
አዳም ተለመነኝ፤ አንተ ኑረህ ብላ…፣ ቅጣት ምናባቱ

ያልበላው ይታዘዝ… ሕግን ማክበር "መብቱ…"
*
አዳም በአፈርህ፦
ብላ… ደግመህ ብላ… የሕግ አጥር ይፍረስ
"አምላክ ይጠራኻል"፤ ክልከላውን ስትጥስ!

ዓርብ 16 ኦገስት 2013

መርፌ ትሠራለህ? - ያልተፈታው ቅኔ (በ ግሱ)

መርፌ ትሠራለህ? - ያልተፈታው ቅኔ (በ ግሱ)

ስለአብዬ መንግሥቱ ቅኔ ሙያዊ ዳሰሳ ለአንባቢዎቼ እንዳካፍል በማሰብ ይህን ጽሑፍ ላደረስከን (ግሱ) ልባዊ ምስጋናዬ ይድረስህ፡፡ ውድ የእልፍኜ ተከታታዮች እና አንባቢያን ሙሉ ጽሁፉ በ ፒዲኤፍ ፋይል ከዚህ በታች ያገኙታል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ኄ.ስ  



merefe teseraleh?

ቅዳሜ 9 ማርች 2013

ረሃብ ስንት ቀን ይፈጃል?- ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን



ረሃብ ቀጠሮ ይሰጣል?
ወይስ ቀን ቆጥሮ ይፈጃል?
"የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል"
ይባላል፡ ድሮም ይባላል፡
ይዘለዝላል ይከትፋል
ብቻ እስከሚጨርስ ድረስ፣ ሆድ ለሆድ ጊዜ ይሰጣል?
ወተት አንጀት ነጥፎ ሲላብ
ሆድ ዕቃ ደርቆ ሆድ ሲራብ
ተሟጦ አንጀት በአንጀት ሲሳብ . . . .
የጣር ቀጠሮው ስንት ነው
ለሰው ልጅ ሰው ለምንለው 

እሑድ 24 ፌብሩዋሪ 2013

እንዳይነግርህ አንዳች እውነት ! - ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን


እንዳይነግርህ አንዳች እውነት ! - ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን

ደንስ ጎበዝ ! ደንስ ጀግና
ክራቫትህን አውልቅና
ሃሳብህን ልቀቀውና
ኮትክን ሸሚዝክን ጣልና
ርገጥ ፣ ጨፍር ፣ ደንስ ጀግና !

ያን የሙዚቃህን ናዳ ፣ የኮንትራባሱን መብረቅ
ልቀቀውና ይድብለቅለቅ
ምድር በሆይታ ይጥለቅለቅ !
ምንም-ምንም እንዳታስብ ፣ ሁሉን-ሁሉን እንድትረሳ
ደንስ ! ካካታው ይነሳ
ጨፍር ፣ ወለሉ እስኪበሳ ....

ሃይ-ሃይ ! ዋይ ! ሃይ-ሃይ ! በልበት
የጃዝ ፋንፋር አንኳኳበት
ራስክን እንዳታስብበት ፤
ሆ ! በል እሪ ! በል ምታበት
ፎክርበት ፣ አቅራራበት
አናፋበት ፣ ሸልልበት
የሲቃ ሳቅ አስካካበት
ሆያ-ሆዬ ! በል ጩኽበት
ኡኡታህ መንኮራኩርክን ፣ እስኪያሰጥመው አጓራበት
ጭንቅላትክን ግዘፍበት ፣ ውቀጥበት ፣ ውገርበት ፣ ....
ዝግ ብሎማ ያሰበ እንደሁ ፣ ይነግርሃል አንዳች እውነት !
-----------
ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን

እሑድ 10 ፌብሩዋሪ 2013

እውነት አሁን አንቺ እሷ ነሽ! ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን


እውነት አሁን አንቺ እሷ ነሽ! ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን
---------
እሷ ነኝ በዪኝ ግድ የለም! . . . .
ሁሉ ላፍ አልተፈጠረም
ቢሉም አፍ አይለው የለም።
ልወቀውና ላውጣ እርሜን፥
የስንት ዘመን ረሃቤን
ልጋረጠው በዓይንሽ አይኔን።
ልጅነቴን የዳኽኩበት፥ የስንት ዘመን ፈለጌ
በናፍቆት ቋት ተሰግስጌ
በእግረ ሕሊና ጠርጌ
በትዝታ በዳሰሳ፥ በፈለግሽ የናዳ ዳር
ስዋትት ስማስን በጣር
ዛሬ ያገኘሁሽ ባሣር
በስንት ዘመን የዕድሜ ምጥ
እውነት አንቺ እሷ ነሽ እርግጥ?!
መምሰል ትመስያለሽ
ማከልማ ታክያለሽ
የደም ግባቷን ተላብሰሽ
መጠሪያዋን ተሰይመሽ . . . .
ያቺን የኔን .... ያቺን የኔን
የኔን የመጀመሪያዬን
የጥንቴን የልጅነቴን
የስንት ዘመን ሕመሜን
የሕልም ዓለም ሰመመኔን
የት አረግሻት? የት ደበቅሻት?
ዋጥሻት? . . . .
አጥንቷን በአጥንትሽ ለብሰሽ
ወዟን በላቦትሽ ታጥነሽ
በልጅነቷ ልጅ ሆነሽ
ገጿን በግንባርሽ ነድፈሽ
አበቧን አደብዝዘሽ
መልኳን በመልክሽ አክስለሽ
ቡቃያዋን በዕድሜሽ ውጠሽ
በስም ብቻ እሷን ሆነሽ
ማነሽ? እውነት አንቺ ማነሽ
እኮ ንገሪኝ እሷ ነሽ?

እሑድ 27 ጃንዋሪ 2013

የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ - ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን





የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ

ተስፋ ባጣ ምድረ በዳ
ያንድ እውነት ይሆናል ዕዳ፡፡
እና ትንፋሼ አልሆነሽም፥ ሆኜብሽ መራር መካሪ
“ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ፣”
እውነት ላንቺ መች ተስፋ ናት፥ ጉስቁል ልሳንሽን ነክሳሽ
ክንድሽን ካዘለ ቅርስሽ፥ መጠላለፍ ሲሆን እጣሽ
ከእንግሊዝ የሞት አማልክት፥ መተናነቅ ሲሆን ድርሻሽ
መልመጥመጡ፥ መሽቆጥቆጡ፥ መስሎሽ ድንገት የሚያዋጣሽ
የኔ እውነት ሆነብሽ ዕዳሽ ፡፡  …..
ወራሪም ፈጣሪን ላያቅ
የጣለውን በስሏል እንጂ፥ ወድቋል ብሎ ግፉ ላያልቅ
መች ትተርፊያለሽ ኢትዮጵያ፥ ሕዋስሽ አብሮኝ ካልሠራ
አንገትሽ ብቻ መቅደላ፥ አፋፍ ወጥታ ብታበራ
የቀረው ሠራ-አከላትሽ፥ በየጥሻው ተዘርሮ
ከአባት በወረሽው ንፍገት፥ ነብዞ ደንዝዞ ተቀብሮ
ባጉል ወጌሻ ታጅሎ
እጅና እግርሽ ታሽቶ ዝሎ
እኔን ለጥንብ አንሳ ጥሎ፤
ከደቀቀ ከደከመ፥ ክንድሽ አልነሣ ካለ
ሞት እንጂ ለኔስ ምን አለ?.....
ሆኖም ጐስቋላ አልምሰልሽ፥ የሚያዝንልኝ አልፈልግም
ጠላትሽን በክንድሽ እንጂ፥ በእንባሽ ወዝ ባላሸንፍም
የልቤን ፍቅር በሰተቀር፥ እማወርስሽም ውል የለኝ
የኮሶ ሻጭ ልጅ ደሃ ነኝ፡፡ …..

ቅዳሜ 12 ጃንዋሪ 2013

ወንድ ብቻውን ነው እሚያለቅስ- ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን



ከወዳጅ ከዘመድ ርቆ
አንጀቱን በአንጀቱ ታጥቆ      
ተሸሽጎ ተገልሎ፥ ተሸማቆ ተሸምቆ
ከቤተ-ሰው ተደብቆ
መሽቶ፥ የማታ ማታ ነው፥ ሌት ነው የወንድ ልጅ እንባው
ብቻውን ነው የሚፈታው፡፡ . . .
ብቻውን ነው የሚረታው፡፡ . . .
ችሎ፥ ውጦ፥ ተጨብጦ፥ ተማምጦ ተጣጥሮ
በሲቃ ግት ተወጥሮ
እንደደመና ተቋጥሮ
እውስጥ አንጀቱ ተቀብሮ . . .
መሽቶ፥ ረፍዶ፥ ጀምበር ጠልቆ
የጨለማ ድባብ ወድቆ
በእንቅልፍ ጥላ ሲከበብ፥ በዝምታ ሲዋጥ አገር
ፍጡር ሁሉ ተስለምልሞ፥ ብቸኝነት ብቻ ሲቀር . . .

እሑድ 28 ኦክቶበር 2012

"የኢትዮጵያ ግጥም ፈርጥ" ለአጼ ይስሓቅ በዘመኑ ከተገጠመላቸው የተወሰደ


ዓፄ ይስሐቅ




ቀዳማዊ አጼ ይሥሓቅ በዙፋን ስማቸው "ዳግማዊ ገብረ መስቀል" ሲባሉ እ.ኤ.አ ከ1414-1429 የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩ ናቸው። የቀዳማዊ አጼ ዳዊት ሁለተኛ ወንድ ልጅ ሲሆኑ የቀዳማዊ ቴዎድሮስ ታናሽ ወንድም ናቸው።

በግብጽ ቆብጦች ላይ በሚካሄድው ዘመቻ ምክናያት ብዙ ኮብቶች ወደኢትዮጵያ በዚሁ ዘመን ተሰደዱ። ከነዚህ ውስጥ ፋቅር አል-ዳዋ የተሰኘው የግብጹ ማምሉክ ባለሟል ይገኝበታል። ይህ ባለሟል በይስሓቅ ግዛት ውስጥ ተሰሚነት በማግኘቱ የአገሪቱን የግብር ስርዓት በመለወጥ በግብጽ ማምሉኮች በሚሰራበት መልኩ እንዲሆን አድርጓል። የንጉሱንም አለባበስ በመቀየርና መስቀል እንዲይዝ በማድረግ ንጉሱ ከቀሪው ህዝብ ለየተ እንዲል አድርጓል። በኋላም በራሳቸው በግብጽ እስላሞች መካከል በተነሳ ጠብ የቁስክፍለ ሃገር ገዢ የነበርው አሚር አል-ቱንቡጋ አል-ሙፍሪቅ በአጼ ይስሓቅ መንግስት ባለሟልነትን አግኝቶ በኋላ የንጉሱ ሰራዊት እንዲሻሻል አድርጓል። ይህ ግብጻዊ ለኢትዮጵያው ሰራዊት ካስተዋወቃቸው ነገሮች ውስጥ የእሳት ችቦ መወርወሪያ ዘዴንና የሻሞላ ውጊያን ይይዛሉ። እንደ ታሪክ አጥኝው ጅ.ቢ.ኸንቲንግፎርድ አባባል ከሆነ የኢትዮጵይ ነገስታት ቋሚ ዋና ከተማ ማድረግ ያቆሙት በዚሁ ንጉስ ዘመን ነበር።

ሰኞ 1 ኦክቶበር 2012

ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት እና የባለሙያዎች ማብራሪያ ክፍል ሁለት


ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት

እና

የባለሙያዎች ማብራሪያ

ክፍል ሁለት




የሄኖክ ስብስብ(henoksitotaw65@gmail.com)


ታህሳስ 2005ዓ.ም

ውድ አንባቢዎች፤ ከዚህ በታች የምታነቡት ሀሳብ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ላይ የተነበቡ ሲሆን ምንጫቸውም ከየመጣጥፎቹ ግርጌ ይገኛል፡፡ ለዚህም ነው “ስብስብ” በሚል ለመግለፅ የተገደድኩት፡፡ በስብስብ መጣጥፎቹ ላይ የጨመርኩት አንዳች ነገር የለም፤ ምክንያቱም አላማዬ በሞክሼ ፊደላት እና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ለመበየን ሳይሆን፣ እንደኔው ግራ ለተጋቡት ማጋራት ነውና፡፡


-5-

በዲ/ን ኅሩይ ባየ

   . . .ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ዐበይት ሀብቶቿ ውስጥ አንዱ የራሷ የሆነ ፊደልና ቋንቋ እየተጠቀመች ለትውልድ ስታስተምር መኖሯ ነው፡፡ ለዚህም የፊደል፣ የቋንቋ ዕድገትና ሥልጣኔ ከፍተኛውን ድርሻ የምትይዘውና በር ከፋቿ የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ዛሬም እንደ ጥንቱ የሆሄያቱ ታሪክ እንዳይረሳ መልክአቸው እንዳይጠፉ ለትውልዱ ታስተምራለች፡፡ ስለሆነም በዘንድሮው የመስቀል በዓል በመስቀል ዐደባባይ አራቱ ሆሄያት እንዳይረሱ ትኩረት እንደሚያሻቸው ጥሪ ቀርቧል፡፡

ሆሄ የሚለውን ቃል ፊደል ተብሎ ሲነገር እንሰማለን፤ በጽሑፍም እናነባለን፡፡ ፊደልን ፈደለ ጻፈ ካለው የግእዝ ግስ አውጥተን ጽሑፍ የሚለውን ትርጉም እናገኛለን፡፡ በሌላ አተረጓጐም ፊደል የሚለው ግስ ጠብቆ ሲነበብ ፈጠረ የሚለውን ትርጉም ያስገኛል፡፡ ፊደል ፈጣሪ /መፍጠሪያ/ መባሉም ቃላትን ስለሚያስገኝ ነው፡፡ አባቶቻችን “ዘእንበለ ፊደል ኢይትነገር ወንጌል.. ያለፊደል ወንጌል አትተረጐምም” ማለታቸው ለመጻፍም ሆነ ለማንበብ፤ ለመተርጐምም ሆነ ለማመስጠር ፊደላት ጉልሕ ድርሻ እንዳላቸው ሲያመለክቱ ነው፡፡

እሑድ 30 ሴፕቴምበር 2012

ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት እና የባለሙያዎች ማብራሪያ ክፍል አንድ


ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት
እና
የባለሙያዎች ማብራሪያ

ክፍል አንድ

የሄኖክ ስብስብ
ታህሳስ 2005ዓ.ም
{PDF}
ውድ አንባቢዎች፤ ከዚህ በታች የምታነቡት ሀሳብ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ላይ የተነበቡ ሲሆን ምንጫቸውም ከየመጣጥፎቹ ግርጌ ይገኛል፡፡ ለዚህም ነው “ስብስብ” በሚል ለመግለፅ የተገደድኩት፡፡ በስብስብ መጣጥፎቹ ላይ የጨመርኩት አንዳች ነገር የለም፤ ምክንያቱም አላማዬ በሞክሼ ፊደላት እና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ለመበየን ሳይሆን፣ እንደኔው ግራ ለተጋቡት ማጋራት ነውና፡፡
-1-
የፊደል ዘር ይጠበቅ ባህሉም ይከበር
በፊታውራሪ አበበ ሥዩም ደስታ
በፊደሎቻችን ላይ ሦስት ሀ - ሐ - ኀ፣ ሁለት አ - ዐ -፣ ሁለት ሠ - ሰ ሁለት፣ ጸ - ፀ አሉ፡፡ እነዚህ ፊደሎች የራሳቸው የሆነ የስም አጠራርም አላቸው፤ ሀሌታው ሀ፣ ሐመሩ ሐ፣ ብዙኃን ኀ፣ ንጉሡ ሠ፣ እሳቱ ሰ፣ ጸሎት ጸ፣ ፀሐዩ ፀ ይባላሉ፡፡ በጽሑፍ የሚገቡበትን ተገቢ (ተስማሚ) ቦታም አላቸው፡፡ ለምሳሌ በሁለት ፊደሎች መጠቀም ይቻላል፡፡ ሀገር አገር ይህ ትክክለኛ አጻጻፍ ሲሆን፤ ነገር ግን ከዚህ ውጪ ሐገር፣ ኀገር ብሎ መጻፍ ግን ስሕተት ይሆናል፤ የሚከተሉትን ደግሞ እንመልከት፤

ሕገ መንግሥት፣ ሕገ ወጥ፣ ሕዝብ፣ ሕብረት፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ወዘተ. የመሳሰሉት አጻጻፋቸው ትክክል ነው፡፡ ከዚህ ልማዳዊ አሠራር ውጪ ህገ መንግሥት፤ ህገወጥ፤ ህዝብ፤ ህብረት፤ አቃቤ ህግ ስሕተታዊ አጻጻፍ ይሆናል፤ ሌላ ማስረጃ ቢፈለግ፤ ኃይለሥላሴ የሚለው ስም ሦስት የተለያዩ ፊደሎች ይዟል፡፡ የመጀመርያው ፊደል ብዙኀን - ኃ - ሲሆን፣ ከንጉሡ -ሥ- ሳድስ፣ ከእሳቱ -ስ- ሃምስን በመጻፍ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ ሀይለ ስላሴ ብሎ ቢጻፍ ግን የፊደሎቻችን የአጻጻፍ ሥርዓት ማፋለስ ይሆናል፤ በአቦ ሰጡኝ ፊደሎቻችን አለቦታቸው መግባትም፣ መጻፍም የለባቸውም፡፡

በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በማስታወቂያ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር የነበሩት የተከበሩ ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ የቅድሚያ ዓይነተኛ ሥራቸው የፊደሎች ዘሮች አለቦታቸው እንዳይጻፉ መጠበቅ ነበር፤ በዚያን ወቅት ተማሪ ሁኜ አልፎ አልፎ በጋዜጣ እንዲወጣልኝ አንድ አንድ ሐሳብ በማመንጨት እጽፍ ስለነበር ብዙ ጊዜ አርመውኛል፡፡

ከእሳቸው በተማርኩት ትምህርትና ባገኘሁት ልምድ አእምሮዬን አሻሽያለሁ፡፡ በቀድሞው የንጉሠ ነገሥቱ ዘመነ ሥርዓት የክፍል ሹም የመጀመርያ ሹመት ሆኖ ወደ ላይ እንደሚከተለው ይዘልቃል፡፡ ዲሬክተር ዋና ዲሬክተር፤ ረዳት ሚኒስትር ምክትል ሚኒስትር፣ ሚኒስትር ዲ-ኤታ፤ ሚኒስትር፡፡ ከምክትል ሚኒስትር ወደ ላይ ያሉት እስከ ሚኒስትር ማዕረግ የደረሱት ክቡር ይባላሉ፡፡ ከዚህ በታች ያሉትን ግን ክቡር አይባሉም፡፡ በተመሳሳይ ያሉትን ማለት ኮሚሽነሮች፤ ሌ/ጀኔራሎች፣ አምባሳደሮች ክቡር ይባላሉ፡፡ ሚኒስትሮች የነበሩ በዳሬክተርና በሥራ አስኪያጅነት ሥራ ቢመደቡ እንኳን የቀድሞውን የሚኒስትር ማዕረጋቸውና ክብራቸው አይቀነስባቸውም፡፡ ክቡር መባል አለባቸው፡፡ ሥርዓት ነውና፡፡ ይህንኑ መለመድ ይገባዋል፤ በወታደሩ ሹመት አሰጣጥ ግን ያለው ሥርዓት የተጠበቀ ስለሆነ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ከዚሁ ሌላ የምለው አለኝ፡፡ ባሁኑ በኢሕአዴግ መንግሥት ዘመን አምባሳደር ነዋሪ የማዕረግ መጠሪያ ስም ሆኖአል፡፡ አንድ አምባሳደር የዲፕሎማሲውን ሥራ አቁሞ ሲዛወር ልክ በሥራው እንዳለ ተቆጥሮ “አምባሳደር” እየተባለ መጠራት የለበትም፡፡

ለምሳሌ በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አምባሳደርነት ተሹመው የነበሩት ክቡር አቶ ጋሻው ዘለቀ፣ ክቡር አቶ ዘነበ ኃይለ፣ ክቡር ልጅ መንበረ ያየህ ይራድ፤ ክቡር ፊታውራሪ መሐመድ ሲራጅ ብዙ ዘመን በአምባሳደርነት ሲሠሩ ቆይተው ተልእኮዋቸውን ፈጽመው ወደ አገራቸው ሲመለሱ አምባሳደር የሚል ቀርቶ በቀድሞ ስማቸው አቶ ተብለው ነበር የሚጠሩት፤ ይህንኑ ጠይቆ ለማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ፊታውራሪ የነበሩትም፤ ፊታውራሪ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ዘላቂ ሆኖ ከሰው ጋር ቅጽል የማዕረግ ስም ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡ በራሴ ምሳሌ ልውሰድ፤ ከግርማዊ ጃንሆይ በአዋጅ የተሰጠኝ የማዕረግ ስም ፊታውራሪ ነው፤ በዚህ ምድራዊው ዓለም እስካለሁ ድረስ የምጠራበት ሲሆን፣ ከሞትኩም በኋላ እጠራበታለሁ፡፡ እንዲሁም በንጉሠ ነገሥቱ መልካም ፈቃድ የሚሰጠው የሥልጣንና ማዕረግ ተዋረድ ባላምባራስ፣ ግራዝማች፣ ቀኛዝማች ፊታውራሪ፣ ደጀዝማች፣ ቢትወደድ፣ ራስ ቢትወደድ፣ ልዑል ራስ፣ አልጋ ወራሽ፣ ንጉሥ ንጉሠ ነገሥት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብላታ፣ ብላቴን ጌታ፣ ፀሐፊ ትዕዛዝ፣ ሊቀ መኳስ በሕይወት ሳሉ ይጠሩበታል፡፡ ከሞቱም በኋላ ስማቸውና ታሪካቸው በተነሣ ቁጥር ከመቃብር በላይ ሆኖ በማዕረጉ ስም ይጠሩበታል፡፡