ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት
እና
የባለሙያዎች ማብራሪያ
ክፍል ሁለት
የሄኖክ ስብስብ(henoksitotaw65@gmail.com)
ታህሳስ 2005ዓ.ም
ውድ አንባቢዎች፤ ከዚህ በታች የምታነቡት ሀሳብ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ላይ የተነበቡ ሲሆን ምንጫቸውም ከየመጣጥፎቹ ግርጌ ይገኛል፡፡ ለዚህም ነው “ስብስብ” በሚል ለመግለፅ የተገደድኩት፡፡ በስብስብ መጣጥፎቹ ላይ የጨመርኩት አንዳች ነገር የለም፤ ምክንያቱም አላማዬ በሞክሼ ፊደላት እና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ለመበየን ሳይሆን፣ እንደኔው ግራ ለተጋቡት ማጋራት ነውና፡፡
-5-
በዲ/ን ኅሩይ
ባየ
.
. .ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ዐበይት ሀብቶቿ ውስጥ አንዱ የራሷ የሆነ ፊደልና ቋንቋ እየተጠቀመች ለትውልድ ስታስተምር መኖሯ
ነው፡፡ ለዚህም የፊደል፣ የቋንቋ ዕድገትና ሥልጣኔ ከፍተኛውን ድርሻ የምትይዘውና በር ከፋቿ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ዛሬም እንደ ጥንቱ የሆሄያቱ ታሪክ እንዳይረሳ መልክአቸው እንዳይጠፉ ለትውልዱ
ታስተምራለች፡፡ ስለሆነም በዘንድሮው የመስቀል በዓል በመስቀል ዐደባባይ አራቱ ሆሄያት እንዳይረሱ ትኩረት እንደሚያሻቸው ጥሪ
ቀርቧል፡፡
ሆሄ የሚለውን ቃል ፊደል ተብሎ ሲነገር እንሰማለን፤ በጽሑፍም እናነባለን፡፡ ፊደልን ፈደለ
ጻፈ ካለው የግእዝ ግስ አውጥተን ጽሑፍ የሚለውን ትርጉም እናገኛለን፡፡ በሌላ አተረጓጐም ፊደል የሚለው ግስ ጠብቆ ሲነበብ
ፈጠረ የሚለውን ትርጉም ያስገኛል፡፡ ፊደል ፈጣሪ /መፍጠሪያ/ መባሉም ቃላትን ስለሚያስገኝ ነው፡፡ አባቶቻችን “ዘእንበለ ፊደል
ኢይትነገር ወንጌል.. ያለፊደል ወንጌል አትተረጐምም” ማለታቸው ለመጻፍም ሆነ ለማንበብ፤ ለመተርጐምም ሆነ ለማመስጠር ፊደላት
ጉልሕ ድርሻ እንዳላቸው ሲያመለክቱ ነው፡፡
ፊደል መጽሔተ /መስተዋት/ አእምሮ ነው፤ በመስተዋት የፊትን ጉድፍ ማየትና ራስን መመልከት
እንደሚቻለው ሁሉ፤ ልብ ማድረግን፥ ዕውቀትንና ጥበብን የሚገልጡ ፊደላት ስለሆኑ መጽሔተ አእምሮ ተብለዋል፡፡ ፊደል ነቅዐ ጥበብ
ሊባልም ይችላል፡፡ የጥበብ መገኛ፣ መፍለቂያ፣ መመንጪያ ናቸውና፡፡ ፊደል መራሔ ዕውራን ማለት ነው፡፡ ዐይነ ስውር በበትር
እንዲመራ ዕውቀት ለጠፋበት ልቡናው ለደነዘዘበት የዕውቀት ድካም ላለበት ሰው ፊደልን ቢቆጥር ቢያጠናና ቢያውቅ ካለማወቅ
ዕውርነት ወደ ዕውቀት ብርሃንነት ስለሚመለስ ፊደላትን መራሔ ዕውራን እንላቸዋለን፡፡ ፊደል ጸያሔ ፍኖት ወይም መንገድ ጠራጊ
ነው፡፡ ንባብን ተገንዝቦ ምስጢርን ለማደላደል ፊደል ጥቅም አለው፡፡
ሆሄ /ፊደል/ በቁሙ ከምናየው መልክዐ ገጽ አልፎ በውስጡ የያዘው ታሪካዊ፣ አመክንዮአዊና
ምስጢራዊ መልእክቶች አሉት፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ የሁሉንም ሆሄያት ስያሜያቸውንና ምስጢራቸውን ማየት አንችልም፡፡
የግእዝን ቋንቋ ፊደል በተመለከተ ብዙ አስተያየቶች ቢኖሩም በአንድ ነገር መስማማት
ይቻላል፡፡ ሆሄ ወይም ፊደል በቁሙ ከምናየው መልክዐ ገጽ አልፎ በውስጡ የያዘው ታሪካዊ፣ አመክንዮአዊና ምስጢራዊ መልእክቶች
አሉት፡፡ የፊደልን ጠቀሜታ የትመጣና ሚና አስረስ የኔሰው ‹‹የካም መታሰቢያ የኢትዮጵያ ፊደል መሠረትነት መታወቂያ›› በተሰኘው
መጽሐፋቸው እንዳመለከቱት “ፊደል ሐውልት ነው፤ ሐውልትም ፊደል ነው፤ ፊደል መልክ ነው፤ መልክም ፊደል ነው፤ ፊደል አባት
ነው፤ አባትም ፊደል ነው፤ ፊደል ልጅ ነው፣ ልጅም ፊደል ነው፤ ፊደል ወሰን ነው፡፡ ወሰንም ፊደል ነው፣ ፊደል ዓላማ ነው፣
ዓላማም ፊደል ነው፡፡
በወትሯዊ የጽሑፍ ተግባራችን የምንጠቀምባቸው ወደ አራት የሚደርሱ ሆሄያት አሉ፡፡ እነዚህ
ፊደላት እነማን እንደሆኑ በቦታው እንገልጠዋለን፡፡ አራቱ ፊደላት በሥነ ድምፅ ትምህርት መካነ ፍጥረታቸው ተመሳሳይ እንደሆነ
ይታወቃል፡፡ ልዩነታቸው በጽሑፍ ላይ ቢሆንም የመገኛቸው ቦታና የድምፃቸው ጠባይ ሊመሳሰል ይችላል፡፡ እነዚህ ሆሄያት በቃላት
ውስጥ ሲገቡ የተለያየ የትርጉም ለውጥ የማምጣት ኀይል አላቸው፡፡ አራቱን ሆሄያት ጠንቅቀው የሚጽፉ ጸሐፍት ቢኖሩም ዕያወቁ
በቸልተኝነት ሳያውቁ በስሕተት እጃቸው እንዳመጣ የሚጽፉ ደግሞ አያሌ ናቸው፡፡
ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ “የሆሄያት አጠቃቀም ችግር” በተባለው መጽሐፋቸው ሆሄያትን በአግባቡ
መጠቀም የሚፈልጉና የማይፈልጉ ሰዎች ሦስት ምክንያቶችን እንደሚያቀርቡ አብራርተዋል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ለፊደላችን ሥርዐትና ወግ
ሊበጅላቸው ያስፈልጋል፡፡ በዘፈቀደ መጻፍ እንደግዴለሽነትና ሥርዓት አልበኝነት ያስቆጥራል፤ ያለሥርዐት የሚተገበር ማንኛውም
የሰዎች ሕግ ጠቀሜታ የለውም የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ በኹለተኛው በኩል ያሉ ወገኖች ደግሞ እንደተለመደው ለእጃችን የቀረበውን
ሆሄ ብንጠቀምበት ምን ችግር አለው ይላሉ፡፡ በሦስተኛው ወገን ያሉ ሰዎች ደግሞ ለጽሕፈታችን ሥርዐት ተሠርቶለት ከኹለት አንዱን
ፊደል መርጦ መጠቀም ይበጃል ይላሉ፡፡ ከሦስቱም ምሁራዊ አመክንዮዎች መካከል የፊደላቱን የትመጣና ብያኔ ምሥጢራዊ ፍቺ ጠንቅቀው
የሚተረጉሙ ሊቃውንት የመጀመሪያውን ሐሳብ ይደግፋሉ፤ ተገቢና ምክንያታዊ በመሆኑም ቤተ ክርሰቲያናችን ትቀበለዋለች፡፡
በግእዝ ሆሄያት ከሀ-ፐ ድረስ ያሉት ፊደሎች ቁጥር26 ናቸው፡፡ ከእነዚህም አራቱ
ሆሄያት ይገኙባቸዋል፡፡ እነዚህ ሆሄያት ከላይ እንደገለጥነው የራሳቸው የሆነ መጠሪያ ስም አላቸው፡፡ ስም ያለው አካል የተለያየ
ጠባይና ማንነት ቢኖረው እንጂ ፍጹም አንድነት ሊኖረው አይችልም፡፡ አራቱ ሆሄያት ናቸው የምንላቸው፡-
1. ሀ፣
ሐ፣ ኀ /ሃሌታው “ሀ”፣ ሐመሩ “ሐ”ና ብዙኀኑ “ኀ”
2. ሠ፣
ሰ፣ /ንጉሡ “ሠ” ና እሳቱ “ሰ”
3. አ፣
ዐ አልፋው “አ” ና “ዐይኑ “ዐ”
4. ጸ፣
ፀ /ጸሎቱ “ጸ” ና ፀሐዩ “ፀ” ናቸው፡፡.
እነዚህን ሆሄያት እየቀላቀሉ መጻፍ የትርጉም ለውጥ የሚያመጡ ቃላትን እንደመፍጠር ነው፡፡
አንዱን ከሌላው እያቀላቀሉ መጻፍ ምን ያህል አሳፋሪ እንደሆነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ
ቃላት ሐዲስ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ሲገልጡ፡-
“እንዳገኙ መጣፍ በድፍረት በመላ
የቋንቋ ደረመን የመጽሐፍ ቢስገላ
ንባብ የሚያሳክክ ምስጢር የሚቆምጥ
መልክዐ ትርጓሜ የሚለውጥ” ብለዋል
በዘመናዊ መንገድ በጽሑፍ ማሽን መጻፍ ከመጀመሩ በፊት ከሸምበቆ /መቃ/ ብዕር ተቀርጾ
ከዕፀዋት ቀለም ተዘጋጅቶ ከእንስሳት ቆዳ ብራና ተዳምጦ በእጅ ጽሑፍ ይጻፍ ነበር፡፡ ጸሐፊውም ቁም ጸሐፊ ተብሎ ሲጠራ ጽሑፉም
ቁም ጽሑፍ ይባላል፡፡ በዚህም መሠረት ቁም ጸሐፊ መሆን የሚፈልግ ሰው ጽሕፈት ሲማር የፊደሎችን አገባብ ጨምሮ ትክክለኛ
ቅርፃቸውን ጠብቆ እንዲያውቅ ይደረጋል፡፡
በዐፄ በካፋ ዘመነ መንግሥት ሃሌታውን “ሀ” ከሐመሩ “ሐ” ንጉሡን “ሠ” ከእሳቱ “ሰ” ፥
ጻድቁን “ጸ” ከፀሐዩ “ፀ” ለይቶ በሥፍራቸው ያልጻፈ፤ ፊደል አዛውሮ የተገኘ ጸሐፊ እጁን ይቆረጥ እንደ ነበረ የጽሑፍ
መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በኋላ ግን በቀን ብዛት የመጻሕፍትን ምስጢር ሳያውቁ የፊደሎችን አገባብ ሳይጠነቅቁ የብዕሩን
አጣጣል በማሳመር ብቻ የሚራቀቁና በድፍረት የሚጽፉ ጸሐፍት እየበዙ ስለመጡ ሆሄያቱ ተዘበራርቀው የተቀመጡባቸው መጻሕፍት እየበዙ
መጡ፤ ይህም አሠራር የመጻሕፍትን መልክ የምስጢራትን አሰካክ እያበላሸው ይገኛል፡፡
“ባንድ የሚጻፈው በሌላው ሲጻፍ
ቋንቋው ተበላሽቶ ይሆናል ጸያፍ
የጸሐፊ ደዌ ያታሚ መከራ
ጠንቅቆ አለማወቅ የፊደልን ሥራ”
እንዳሉት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሆሄ ያለቦታው ሲቀመጥ አንባቢን ግራ ያጋባል፤
ምስጢር ያፋልሳል፤ መልእክት ያጓድላል፤ ንባብ ያጣርሳል፡፡
በእነዚህ ሆሄያት ዙሪያ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ክርክር ሲነሣበት እንደነበረ ፕሮፌሰር ባየ ይማም
ለሐመር መጽሔት ሲገልጡ እንዲህ ነበር ያሉት፤ “ከቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ የፈደል ማሻሻያ ተብሎ ሲነሣ ከቆየ በኋላ
በመንግሥቱ ኃይለማርያም ጊዜ የቋንቋ አካዳሚ ጉባኤ ትርፍ የሚባሉ ፊደሎች ይወገዱ ብሎ ወስኗል፡፡ የሆሄው ትምህርት አሁን
ቀርቷል ሁሉም እንደፈለገ ነው የሚጽፈው” ብለዋል፡፡ ይኸን ውሳኔ ተግባራዊ በማድረግ የቋንቋዎች አካዳሚ ክብረ ነገሥት
የተባለውን መጽሐፍ በአንድ ፊደል ብቻ አሳትሟል፡፡ ሐዲስ ዓለማየሁም አራቱን ሆሄያት እንደገደፏቸው አስታውቀዋል፡፡
ሆሄያቱ እንዲቀነሱ ከ1950ዎቹ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ ውዝግብ እንደነበረ በመንግሥቱ ለማ
ግለታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡ ፊደላቱ መቀነስ የለባቸውም ከሚሉ ሊቃውንት መካከል መርስኤ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ
በአንድ ወገን፣ ፊደላቱ መቀነስ አለባቸው የሚለውን ሐሳብ በመደገፍ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አበበ ረታ በሌላ ወገን
ሆነው በአራት ኪሎ ቅድስት ሥላሴ ግቢ እንደተከራከሩ ይታወሳል፡፡ መንግሥቱ ለማን ጨምሮ ጥንታዊው ሆሄ ሳይቀነስ ሳይበረዝና
ሳይከለስ ባለበት እንዲቀመጥ መሟገታቸውንም እንረዳለን፡፡ በቤተ ክህነት በኩል ፊደላችን ይቀነስ ወይስ አይቀነስ የሚል መንታ ሐሳብ
ቀርቦ ሊቃውንቱ ተወያይተውበት ፊደላቱ ባሉበት እንዲቀመጡ የሚለው ወገን መርታቱን አለቃ ለማ አብራርተዋል፡፡ /ደማሙ
ብዕረኛ 1988፥115-128/
የሥነ ልሳን ተመራማሪና ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ባየ ይማም ሆሄያቱ ባሉበት ተከብረው
በቦታቸው እየገቡ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ይገልጣሉ፡፡ “የእነዚህ ፊደላት ምንጩ የግእዝ ግስ እንደሆነ ዐውቃለሁ፡፡
የግእዝን ቋንቋ ከእንግሊዝኛ “የስፔሊንግ” ችግር ጋር ስናነጻጽረው እዚህ ግባ የሚባል ችግር የለውም፡፡ ስለዚህ እንደ ዜግነቴ
ሥርዐተ ጽሕፈቱ ከታሪካችንና ከማንነታችን አኳያ እያየን ይዘነው ልንሔድ ይገባል” /ሐመር 8/18-19/፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶ/ር ኀይሉ ሀብቱ
በሆሄያቱ ጠቀሜታ በሰጡት አሳብ ፊደሎቻችን ከፊደልነታቸው በላይ አኀዝንም እንደሚወክሉ ጠቁመው የአውሮፓው ሳይንቲስት ጋሊሊዮ
ጋሊሊ እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር ከቁጥር ጋር በተያያዘ ቀመር እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ በዚህም መሠረት ባላወቅነው ምስጢር
ገብተን፤ ባልተረዳነውና መንገድ ፊደላቱን በትክክል አለመጠቀማችን የስንፍና ምልክት ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ቻይናዎች 200
ፊደላት አሏቸው፡፡ የፊደሎቻቸው መብዛት በሳይንሱና በፍልስፍናው ያላቸውን ጉዞ አላቆመውም” ሲሉ ዶ/ር ኀይሉ ተናግረዋል፡፡
የሆሄያቱን አኀዛዊ ምስጢር ጠለቅ ባለ መንገድ አስረስ የኔሰው “ትቤ አክሱም መኑ አንተ” በተባለው መጽሐፋቸው
አብራርተዋል፡፡ /ስምዐ ጽድቅ ነሐሴ 1/15፣ 1999/12/
ታሪካዊ ልብወለድ በመድረስ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ የተወጣው አቤ
ጉበኛ ለምን ፊደሎቻችንን እንዳልቀነሰ አብራርቷል፡፡
“ፊደሎቻችንን መቀነስ ጠቃሚነቱ ስላልታየኝ በራሴ በኩል አልተከተልሁትም፡፡ ሥራ ለማሳጠር
ይጠቅማል፡፡ ስለተባለውም ሥራ ጨምሮ ከማየቴ በቀር ቀንሶ አላገኘሁትም፡፡ በራሴ አስተያየት እንዲያውም ሥራ የሚያበዛ ሆኖ
ታይቶኛል፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑትና በዓለም የታወቁበት ልዩ ሙያቸው የዚሁ ቋንቋ ጥናት የሆነው አሜሪካዊ ዶ/ር
ዊልፍሬድ ፊንክ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ውስጥ ያለውን አስቂኝ የሆነ የፊደል አቀማመጥ አስቂኝነቱን በሚገልጽ ሁኔታ አብራርተዋል፡፡
ከሁሉ በፊት የፊደሎች አገባብ ሕግና ወሰን የለውም፡፡ ስለዚህ ከዶ/ር ፊንክ ጽሑፍ ጥቂት
ብጠቅስ መልካም መስሎ ይታየኛል፡፡ . . . ‹ፊደላችን እንኳ የራሱ የሆኑ ያልተሻሻሉ አስቸጋሪ መንገዶች አሉት፡፡ ዊልያም
ፍሬማን ግልጽ እንግዝኛ በተባለ መጽሐፉ ላይ ስለ አስገራሚው ፊደላችን ብዙ ያዋየናል፡፡ እሱ እንደሚለው ከፊደሎቻችን ዐሥሩን
አንድ ብቻ ያልሆነ ድምፅ ያላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ‹a› የምንለው ፊደላችን ሰድስት ድምፅ አለው፡፡ ይኸውም fat, fate,
father, swallow, water, any በሚሉት ቃሎች እንደምንጠቀምበት ነው፡፡ በአሜሪካዊ እንግሊዝኛ ‹e› የተባለው
ፊደል አራት ድምፆች ይሰጣል፡፡ እነዚህም me, men, clerk, pretty በሚሉት ቃሎች እንደምንጠቀምበት ነው፡፡ ‹i›
የሚባለው ፊደልም fin, fine, machine በሚባሉ ቃሎች እንጠቀምበታለን፡፡ ‹o› እንዲያውም ከቅጥና መጠን
ወጥቶ እንደ not, note, bosom, women, also, who ባሉ ቃላት ገብቶ እናገኘዋለን፡፡
ድምፅ ተቀባዮቹም (consonants) የራሳቸው ድርሻ የሆነ ልክስክስነት አላቸው ለምሳሌ C
እና X ለማንም ጎልቶ እንደሚታየው ዋጋ ቢሶች ስለሆኑ ሊተው የሚገቡ ናቸው፡፡ እንዲሁም ሌሎች b comb በሚለው p
receipt በሚል ቃል ላይ እየተደነቀሩ ምንም አገልግሎት ሳይሰጡ ይዘለላሉ፡፡ በመሆኑም ቋንቋችን በብዙ መንገዶች የተዘበራረቀ
አስደሳችና ሥነ ሥርዓት የሌለው ነው፡፡
ለምሳሌ Ough የሚሉት ፊደሎች ሰባት የተለየዩ ድምፆች አሏቸው፡፡ እነሱም though,
bough, rough, through, hough, (hock) hiccough (hiccup) በሚሉት ቃሎች እንደምንጠቀምባቸው
ነው፡፡›
የቋንቋው ሊቅ ከዚህ ጋር ብዙ መረጃዎችን በመስጠት በራሳቸው ቋንቋ ላይ የሚታዩትን ከፍተኛ
ችግሮች ገልጸዋል፡፡ ከታላላቆቹ የእንግሊዝ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች አንዱ ጆርጅ በርናርድ ሾውም፤ ኢጣሊያንኛንና እስፓኝኛን
የመሳሰሉት ቋንቋዎች ለሌሎች ሕዝብ በቀላሉ ሊገቡና ሊታወቁ ሲችሉ እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ በአስቸጋሪነታቸው ምክንያት የቋንቋው
ባለቤቶች በሆኑት ሕዝብ ዘንድ እንኳ በሚገባ የማይታወቁ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡
ይህን ስናይ የኛ ፊደሎች ብዛት ጎጂነቱ የጎላ አይደለም፡፡ ‹ደ› ለማለት (dough) ይህን
ሁሉ ፊደል ከማስፈር ‹ደ› ብሎ መሔድ እንዴት ቀልጠፉ ነው) የኛ ፊደሎች ሁሉም ራሳቸውን ችለው ድምፅ የሚሰጡ በመሆናቸው
ቁጥራቸው በርከት ስላለ ‹እንደሰማይ ከዋክብት የበዙ› የሚባል የማገናኛ አስተያየት ሲሰጣቸው እንሰማለን፡፡ የሰማይ ከዋክብት
እንደዚህ ጥቂቶች ቢሆኑ የከዋክብት አጥኚዎች /አስትሮኖመሮች/ ሥራ ይህን ያህል ከባድ ባለሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን ለማጋነን
ነፃ ዕድል ከተሰጠ ዘንድ የኛ ፊደሎች ይሁን እንደሰማይ ከዋክብት የበዙ ናቸው ይባሉ፡፡ ነገር ግን በሌሎች ቋንቋዎች ያሉት ያለሕግ፣
ያለወሰን፣ ያለ ሥራ እንደክፉ ሌባ ስማቸውን እየለዋወጡ የሚያወናብዱት ፊደሎች ደግሞ ከምድር አሸዋና ከሰማይ ከዋክብት በብዛት
ይወዳደራሉ ብንል ለኛ አጋናኝነት ይቅርታ ሊደረግለት አይገባምን) . . .የኛዎቹ አራቱ ሆሄያት የምንጠቀምባቸው የግእዝ ቋንቋ
ለቃሉ ትርጓሜ መለያ በአማርኛ እንደጌጥ እንደውበት አድርገን ድምፃቸውን ሳይለውጡ እንጂ ‹‹መምህር›› ለማለት እንደሌሎች
“መኘምህሕርኅ” እያልን ማለት ኘን፣ ሕን፣ ኅን ያለ ዋጋ ደንጉረን ግራ እያጋባን ስላልሆነ የፊደሎችን መልክ ጠንቅቆ ያጠና ሁሉ
እንደልቡ ሊያነብባቸው የሚችሉት ከሚያቀልሉት ከፍተኛ ችግር ጋር ሲመዛዘኑ እንኳን እንደሰማይ ከዋክብት እንደጭብጥ ጥሬ ብዙ
ሊባሉ የማይገባቸው ፊደሎቻችን በዚህ መጠነኛ ምክንያት ለመቀነስ ከሌላው ተግባር ቀድሞ የሚያስገድደን ችግር ያለ አይመስለኝም፡፡
. . .ስለዚህ የፊደሎችን ቁጥር ለመቀነስ ያልሞከርኩት ከፍ ብሎ በገለጸኩት ምክንያት ብቻ መሆኑን በትኅትና እገልጻለሁ፡፡
/አንድ ለእናቱ 1985 ዓ.ም/
ማጠቃለያ
አራቱ ሆሄያት ትርፎች ሳይሆኑ ቀዋምያን ቅንጣቶች ናቸው፡፡ ራሳቸውን ችለው ትርጉም
የሚያስተላልፉ የቃላት መቆሚያ ውኃ ልኮችም ናቸው፡፡
በምስጢርም በኩል ያየነው እንደሆነ ንጉሡን “ሠ” ተጠቅመን “ሠረቀ” ብለን ብንጽፍ ወጣ
የሚለውን ቃል ያስገኝልናል፡፡ “ሰረቀ” ብለን በእሳቱ “ሰ” ብንጠቀም ሌባ /ሽፍታ/ አንድን ነገር ሰረቀ /ያለፈቃድ ወሰደ/
የሚለውን ትርጉም ያስገኛል፡፡ እነዚህ ኹለት ፊደላት ያለቦታቸው ከገቡ ቋንቋውን ብላሽ ምስጢሩን ፈራሽ ያደርጉታል፡፡
አራቱ ሆሄያት ቦታቸውን ጠብቀው ቢቀመጡ የሚፈለገውን መልእክት ማስተላለፍ እንደሚቻል
ተመልክተናል፡፡ ተግባራዊነቱን ለማከናወን ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያሉ
ጽ/ቤቶች የሚጽፉትን ደብዳቤ አርመውና ትኩረት ሰጥተው ማውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የፊደላቱ ጉዳይ ሃይማኖታዊ ፋይዳ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊና ታሪካዊ ምስጢር ያላቸው ናቸው፡፡
ትውልዱ ከሃይማኖቱና ከታሪኩ ጋር ለመተዋወቅ እነዚህ ፊደሎች ያስፈልጉታል፡፡ ተከራካሪዎች እንደሚሉት ፊደሎቹ ተቀንሰው በአንዱ
ብቻ ብንጠቀም፤ ሳናውቀው የምናስቀረው ትልቅ ዕውቀት እንዳለ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ፊደል ሲቀነስ ዕውቀት ይቀንሳል፡፡
ዕውቀት ሲቀነስ ታሪክ ይጓደላል፤ ታሪክ ሲጓደል ማንነት ይጠፋል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ ፣ ብሉያቱ፣ ሐዲሳቱ፣ ድርሳናቱ፣ ተኣምራቱ፣ ገድላቱ፣ ቅዳሴያቱ፣
ውዳሴያቱ፣ ዜና መዋዕሉ፣ ቅኔያቱና ሌሎች መጻሕፍት የተጻፉበት የግእዝ ቋንቋ አማርኛን ወልዶ ለዚህ ዘመን በመድረሱ የማንነታችን
መገለጪያ የታሪካችን ቅርስ ነውና መልኩን ሳይቀር መቀጠል አለበት፡፡
ሆሄያቱ ተቀንሰው በአንድ ሆነው እንጠቀም ብንልና ሆሄያቱ ከተረሱ ብሎም ከጠፉ ቀጣዩ ትውልድ
ወደ ኋላ ተመልሶ የሀገሩን ታሪክ ሥነ ጽሑፍና ሌሎች የኪነ ጥበብ ውጤቶችን አንብቦ ለመረዳት እክል /እንቅፋት/ ያጋጥመዋል፡፡
የማያውቀውን ፊደል እንዴት ያነበዋል፤ ያላነበበውን እንዴት ይረዳዋል፤ ያልተረዳውንስ እንዴት ይመረምረዋል?
ፊደል ይቀነስ ተብሎ የሆነ ስምምነት ላይ ቢደረስ ከአንድ ትውልድ በኋላ የኢትዮጵያን ታሪክ
የያዙ ሃይማኖታዊና ፍልስፍናዊ መጻሕፍትን አንብቦ ሙሉ ለሙሉ ለመረዳት አስቸጋሪ መሆኑንም ማሰብ ይጠይቃል፡፡
ሥርዐተ ጽሕፈትን አስተካክሎ ወጥ የሆነ ሕግ አውጥቶ በማስተማርና በማለማመድ የስካንድኒቪያን
ሀገሮች የፈጸሙት ተግባር ጥሩ መፍትሔ አስገኝቶላቸዋል፡፡ ወደ ራሳችን ስንመለስ ችግሩን ለመቅረፍ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ሥርዐተ ትምህርት ተዘጋጅቶ ቢቀርብ መልካም ነው፡፡ ሥርዐተ ጽሕፈትን ሳያስተምሩ ለምን
ይኸን ሆሄ አልጻፍኅም ብሎ መኰነኑ አግባብ አይደለም፡፡ ሥርዓተ ጽሕፈቱ በወጉና በሕጉ እንዲሆን ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚሉ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትን፣ የባህልና ቱሪዝም፣ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች፣ ደራስያንንና ታዋቂ
ግለሰቦችን ያቀፈ ውይይት ማካሔድና አንድ ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን በ2005ቱ የመስቀል ደመራ በዓል ያስተጋባችው ድምፅ ቢቀጥል፡፡ በዚህ
ዙርያ የተሠሩ ጥናቶች እንደአስፈላጊነቱ እየታዩ ሥራ ላይ ቢውሉ ወደ ተግባርም ቢለወጡ ተጨማሪ ዐውደ ጥናቶች ቢቀርቡ ውይይቶች
ቢካሔዱ ለተፈጻሚነቱም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ቢወጡ፡፡ የሆሄያቱ መብት መከበር የታሪክ፣ የባህል የእምነትና የማንነት
መብት መከበር ነውና ህልውናቸውን እንጠብቅ፡፡ መልካም ነው፡፡ የተላለፈው መልእክት ጋዜጣ ለሚያዘጋጁ መጽሔት ለሚያሳትሙ
እጃቸውን ከወረቀት ላይ ለሚያሳርፉ ሁሉ ነው፡፡ በመሆኑም በቀና ልቡና መልእክቱን ተቀብለን ስንፍናን አስወግደን ወደ ዕውቀት
ማእድ ልንሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ ወደር
የለሽ ጥንታዊ ስልጣኔያችን በእጃችን ያለ ዛሬያችንን አኮስሶ፣ አስተሳሰባችንን ያለ ልክ ተጭኖታል፡፡ ማንነታችንን
የምንገልጸው በሱ ነው፤ የምንኮራው በሱ ነው፡፡ ይህ ባልከፋ፤ ክፋቱ ጉድፉን ልንነቅስለት አለመድፈራችን ነው፡፡ ጉድፉን ነቅሰን
ለመታደግ ይቅርና ስለ ጉድፉ ማውራት የሚያስቀስፍ ይመስለናል፡፡
ጥቅምት 19 ቀን 2005 ዓ.ም
ምንጭ፤ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ
ቅዱሳን http://www.eotcmk.org
(ይቀጥላል)
በፌስቡክ ከተሰጡ አስተያየት እና ውይይት በጥቂቱ
ምላሽ ይስጡሰርዝEmebet Muche, Adil Mohammed, Firew Bekele and 4 others like this.
. . . . . . .. . . . .
Tesfakiros Arefe Sahle አላውቅም:: አስተያየት ከመስጠት ግን ይገድባል እንዴ? ያልኩት ደግሞ አማርኛ ከግእዝ ተለይቶ ራሱን ችሎ ይሂድ፤ደባልነቱ የግእዝን ፊደላት በአግባቡ እንዳናውቅ እየጎዳን(ከተጎጂዎቹ እንደ አንዱ ልትቆጥረኝ ትችላለህ) ነው፤ቅርስም እየጠፋ ነው መሰለኝ፡፡ ቁምነገሩ ላይ እናተኩርና አንተስ ባልኩት ነገር ላይ ምን ትላለህ?
about an hour ago · Like
Junior Dee በትክክል ይገድባል:: ምክንያቱም አስተያየትህ ሰዋሰዋዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው:: ያንን በቅጡ ለመመለስ ደግሞ የግዴታ በእውቀት የተደገፈ አስተያየት ያስፈልጋል:: ግእዝ አማርኛን ወልዶ ብቻ አልተወውም ዛሬም ድረስ የአማርኛ ጌጥ ሆኖ ቋንቋውን ያሳምረዋል:: አማርኛ ግእዝን እንዴት እንደጎዳ በምሳሌ አስረዳኝ::
56 minutes ago · Like
Tesfakiros Arefe Sahle Junior Dee ፅህፉ ላይ እኮ ተደርድረውልሃል-ሞክሼዎቹ ፊደላት፡፡ ሀ፣ሐ፤ኸ፤ኀ፤አ፤ዐ፤ፀ፤ጸ-እነዚህ ፊደላት እኮ አማርኛ ሳያጠፋው(ልብ አድርግ ይህ በማድረጉ ወንጀለኛ አይደለም ብያለሁ-የቋንቋው ተፈጥራዊ ባህሪው ነዋ፤) የሚወክሉት ትርጉምና የተለያየ ድምፅ ነበራቸው፡፡ ግን ግን ስለ ሰዋሰው አውርቻለሁ እንዴ?
46 minutes ago · Like
በግጥም ልተንፍሥ (The New Generation Poetry) ውድ አንባቢዎች፤ ከዚህ በታች የምታነቡት ሀሳብ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ላይ የተነበቡ ሲሆን ምንጫቸውም ከየመጣጥፎቹ ግርጌ ይገኛል፡፡ ለዚህም ነው “ስብስብ” በሚል ለመግለፅ የተገደድኩት፡፡ በስብስብ መጣጥፎቹ ላይ የጨመርኩት አንዳች ነገር የለም፤ ምክንያቱም አላማዬ በሞክሼ ፊደላት እና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ለመበየን ሳይሆን፣ እንደኔው ግራ ለተጋቡት ማጋራ ነውና፡፡
39 minutes ago · Like
Junior Dee hahaha ተስፍሽ እኔ ያልኩት አማርኛ ፊደላትን ቢጨምርም ቢቀንስም ተጽእኖው ያለው እዛው አማርኛ ላይ ነው:: የአማርኛ ፊደላትን ስላወቅን ግእዝ ተናገርን ማለት አንችልም:: አማርኛ ግእዝን የሚያጠቃበት ሁኔታ ነው እኔ ያልገባኝ:: ግእዝ አማርኛ ላይ በፊደላትም በቃላትም እየተቀየጠ ይገባል:: አማርኛ ግን ግእዝ ላይ ሲቀየጥ አላየሁም :: ምሳሌ ያልኩህ ለዛ ነው:: ግእዝ እኔ ባይ ብሄር ስለሌለው ቢለፋበት ኖሮ ብዙወቻችን የምንናገረው ቋንቋ በሆነ ነበር:: የአማርኛን የታሪክ ተጠያቂነት ነው ያልገባኝ ሌላው ነገር:: ሰዋሰው ያልኩት የመጀመሪያው ኮመንትህ ስለጠፋ sorry
36 minutes ago · Like
Tesfakiros Arefe Sahle Junior Dee ሰዎቹ ፈሪዎች ነገር ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ይሄንን አስተያየቴን ሰረዙት፡፡ ይህችን ኮላሊት ይዘው አደባባይ መውጣታቸው አስገረመኝ፡፡ ይሄንን አመል ያለበት ሰውማ ሃሳቡን ለፀሃይ ብርሃን ማጋለጥ አልነበረበትም፡፡ ፅህፉ ምቺ እንደሚያገኘው አልተገነዘቡም ነበር እንዴ፡፡ እና ካንተ ጋር የቀጠልነው ዉይይትም የተቆራረጠ ስለሚሆን ለማቆም ተገዲጃለሁ፡፡እንደ በፊቱ እፍርታሞች በሌሉበት ሜዳ እንገናኛለን፡፡
ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት እና የባለሙያዎች ማብራሪያ የሚል ርእስ ሳይ አዲስ ነገር አገኝበት ይሆናል ብየ ለማንበብ ጉጉት አደረብኝ፡፡ ነገር ግን እንደጠበቅኩት ሳይሆን መልክ የሌለው ድብልቅልቅ ያለ ብዥታየን የበለጠ ያጠናከረ ሆኖ አገኘሁት፡፡ ፅህፉ የሚያትተው ስል ግእዝ ይሁን ስለ አማርኛ ፊደላት አይታወቅም፡፡ እዚህም እዛም እየዘለለ ጥራዝ ነጠቅ ሆኖ አረፈው፡፡የሚከተሉት ጥያቄዎች እንድትመልስሉኝ እየጠየኩኝ አማርኛና ግእዝ ግን እንዳትቀላቀሉብን አደራ እላለሁ፡፡
1. ሞክሼ ፊደላቱ በግእዝም ተመሳሳይ ድምፅ ነው ያላቸው? ሞክሼነታቸው በአማርኛ ቋንቋ ወይስ በግእዝም?
2. አነዚህ ፊደላት እየቀላቀሉ መፃፍ በአማርኛ ቋንቋ የትርጉም ለውጥ ያመጣሉን? እስቲ በምሳሌ አስደግፋችሁ አሳዩን(የግእዝ ሳይሆን የአማርኛ ምሳሌ)
3. እነዚህ ፊደላት የነበራቸውን የተለያየ ድምፅ ያጠፋው የአማርኛ ቋንቋ አይደለምን?
4. አማርኛ የራሱ ፊደላት አሉት?
ለፊደላቱና ለታሪካችን/ቅርሳችን የምንጨነቅ ከሆነ መድሃኒቱ አማርኛ ከግዝ ማፋታት ነው፡፡ አማርኛ ከቋንቋው ባህሪ የተነሳ የግእዝ ፊደላትን ሊወርስ አይችልም፡፡ እንዲያውም ያለ አቅሙ ወራሽ ልናደርገው በጣርን ቁጥር የግእዝ ፊደላት ድምፅ፤ትርጉም/ውክልና የባሰ እያጠፋ ነው፡፡ አማርኛ ቋንቋ ለግዝ ፊደላት ተቆርቋሪ መሆን አይችልም፡፡መሆን ካለበትም እንደዛ አይነት የቋንቋ ባህሪ/ድምፅ ይዞ በመፈጠሩ መወንጀል ባይገባውም ለግእዝ ፊደላት ድምፅና ዉክልና መጥፋት ግን የታሪክ ተጠያቂ ነው፡፡
የግእዝ ፊደላት ከአማርኛ ቋንቋ ድምፅ ጋር ሳይቀላቀል ራሱን ችሎ ብንማረው ታሪካችን/ቅርሳችን እናቅባለን፤የፊደላቱ ድምፅና ዉክልና በግልፅ ገብቶን ከትውልድ ትውልድ ሊተላለፉ ይችላሉ፡፡
Junior Dee ተቀብያለሁ
24 minutes ago · Like
tiru idea new!at all wedjawalehu!thank you!
ምላሽ ይስጡሰርዝግዕዝ ከአማርኛ እንለየው ማለት ምን ማለት ነው?
ምላሽ ይስጡሰርዝፊደላቱ የራሳቸው ድምጽ እንዳላቸው መረዳት እንዴት ይሳነናል?
እስቲ “ቋንቋ” የሚለውን ቃል ተመልከቱ፡፡ “ቋንቋ” በግዕዝ ፍንድቅ የተመሠረተ ቃል ነው ፡፡ “ቋ” ግዕዝ መሆኗን አትዘንጉ፡፡ ግዕዙን ከአማርኛው ስንነጥለው ልንል ነው፤ ቋንቋ በ“ቁዋንቁዋ” ሲተካ የሚያወጣው ድምጽ የእኛን ንግግር የማይወክል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሌሎች ቃሎችን እስቲ እንመልከት፡-
አንኳኳ . . .አንክዋክዋ . . .አንኩዋንኩዋ
የቱ ነው ለአጠቃቀም የሚመቸው? የትኛውስ ነው ከአንደበታችን የሚወጣውን ቃል በትክክል የሚገልጸው?
ፊደላትን መቀነስ የአንድን ቃል ድምጽ አጉድሎና ትክክለኛውን ድምጽ ለማስመሰል ሲባል የፊደላት ድርብታን ካስከተለ፣ ድርብታ/ድምጽ ለማምጣት የጨመሩ ፊደላት/ ካበዛና የቃሉንም ገላጭነት ካንዛዛ ፋይደው ምንም ነው ማለት ነው፡፡ አንድን ድምጽ በአንድ ፊደል መግለጽ ምን ያህል እንደሚከብድ የተገነዘበ፣ የራሳችን በሆኑት ድንቅ ፊደላት ተፈጥሮአዊ ባህርይ ሊኮራ በተገባው ፡፡ እባካችሁን የፊደል ለውጥ ያስፈልጋል አትበሉ፡፡ የሚያስፈልገን ወደ ራሳችን ማየት ነው! የሚያስፈልገን ያሉንን ድንቅ ፊደሎች በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችለንን የእውቀት ደረጃ መጨመር ነው! የእውቀት ደረጃችን፣ ያሉንን ድምጽ ወካይ ፊደላቶችን የሚከረክም ሳይሆን በፊደላት አጠቃቀም ላይ የምንገድፈውን የሚያርም፣ ብሎም ለፊደሎቹ ተጠቃሚዎች ትርጓሜን የሚያቀርብ ግብአት መፍጠር ነው!
ሁሉም የግዕዝ ቀለሞች ዕውቅና ኣግኝተዋል። http://www.ethiopic.com/ethiopic_alphabet.htm
ምላሽ ይስጡሰርዝበሁሉም የአማርኛ ሆህያት መጠቀም አላስቸገረም።
http://freetyping.geezedit.com