እሑድ 10 ፌብሩዋሪ 2013

እውነት አሁን አንቺ እሷ ነሽ! ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን


እውነት አሁን አንቺ እሷ ነሽ! ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን
---------
እሷ ነኝ በዪኝ ግድ የለም! . . . .
ሁሉ ላፍ አልተፈጠረም
ቢሉም አፍ አይለው የለም።
ልወቀውና ላውጣ እርሜን፥
የስንት ዘመን ረሃቤን
ልጋረጠው በዓይንሽ አይኔን።
ልጅነቴን የዳኽኩበት፥ የስንት ዘመን ፈለጌ
በናፍቆት ቋት ተሰግስጌ
በእግረ ሕሊና ጠርጌ
በትዝታ በዳሰሳ፥ በፈለግሽ የናዳ ዳር
ስዋትት ስማስን በጣር
ዛሬ ያገኘሁሽ ባሣር
በስንት ዘመን የዕድሜ ምጥ
እውነት አንቺ እሷ ነሽ እርግጥ?!
መምሰል ትመስያለሽ
ማከልማ ታክያለሽ
የደም ግባቷን ተላብሰሽ
መጠሪያዋን ተሰይመሽ . . . .
ያቺን የኔን .... ያቺን የኔን
የኔን የመጀመሪያዬን
የጥንቴን የልጅነቴን
የስንት ዘመን ሕመሜን
የሕልም ዓለም ሰመመኔን
የት አረግሻት? የት ደበቅሻት?
ዋጥሻት? . . . .
አጥንቷን በአጥንትሽ ለብሰሽ
ወዟን በላቦትሽ ታጥነሽ
በልጅነቷ ልጅ ሆነሽ
ገጿን በግንባርሽ ነድፈሽ
አበቧን አደብዝዘሽ
መልኳን በመልክሽ አክስለሽ
ቡቃያዋን በዕድሜሽ ውጠሽ
በስም ብቻ እሷን ሆነሽ
ማነሽ? እውነት አንቺ ማነሽ
እኮ ንገሪኝ እሷ ነሽ?


ግድየለም ንገሪኝ ሐቁን
እርግጥ አንቺ እሷ ነሽ አሁን!
ንገሪኝና ላውጣ እርሜን
የስንት ዘመን ረሃቤን
ይጋረጠው ዓይንሽ ዓይኔን
እርግጡን ብቻ የሐቁን
የሰማይ የምድር እውነቱን
የቁርጡን የእርሙን የእቅጩን
በይ እስቲ አንቺ እሷ ነሽ አሁን?!

ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን
እሳት ወይ አበባ መጽሐፍ

6 አስተያየቶች: