ቅዳሜ 9 ማርች 2013

ረሃብ ስንት ቀን ይፈጃል?- ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን



ረሃብ ቀጠሮ ይሰጣል?
ወይስ ቀን ቆጥሮ ይፈጃል?
"የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል"
ይባላል፡ ድሮም ይባላል፡
ይዘለዝላል ይከትፋል
ብቻ እስከሚጨርስ ድረስ፣ ሆድ ለሆድ ጊዜ ይሰጣል?
ወተት አንጀት ነጥፎ ሲላብ
ሆድ ዕቃ ደርቆ ሆድ ሲራብ
ተሟጦ አንጀት በአንጀት ሲሳብ . . . .
የጣር ቀጠሮው ስንት ነው
ለሰው ልጅ ሰው ለምንለው 

ላይችል ሰጥቶት ለሚያስችለው
ስንት ቀን ነው? ስንት ሌሊት ነው? . . . .
የማዕዱ ወዝ ሳታጥጥ
አድባሩ አብዳ ሳትፈረጥጥ
ጥንብ ሳይተርፋት ሜዳ-አይጥ
የቤት ድመት ሳታማምጥ
በእመቤቷ አስከሬን ብካይ
እሷም ዋይ አንጀቷም ዋይ-ዋይ
ውሻም በጌታው ሥጋ ላይ
ቸነፈር በጣለው ሲሳይ
አይ! . . . .
ስንት ቀን ትሆን የራብ አዋይ? . . . .
እስቲ እናንተ ተናገሩ፣ ተርባችሁ የምታውቁ

ከቸነፈር አምልጣችሁ፣ ተርፋችሁ እንደሁ ሳታልቁ
ትንፋሽ ቀርቷችሁ እንደሆን፣ ያስችላችሁ እንደሁ ጥቂት
ቀጠሮ ይሰጣል እልቂት?
ስንት መዓልት? ስንት ሌሊት?
ጥንብ አንሳው ሳይወርድ በፊት፣ ሳይሞዠርጣችሁ ጥፍሩ
በጣረ-ሞት አክናፋቱ፣ አንዣቦ በመቅሰፍት እግሩ፣
አንደበት ተርፏችሁ እንደሁ፣ ሳትነግሩን ከምትቀሩ
ካስቻላችሁ ተናገሩ።
ቆሽት-ሲቃው ሲያጣጥር፣ ሰቀቀኑን ሳያጋግል
እስትንፋስ ስልምልም ሳትል
ቀጠሮ ይሰጣል ረሃብ? ለስንት ቀን ለስንት ያህል?
ስንት ሰዓት ነው የራቡ አቅም?
ለኔ ብጤማ ትርጉሙ
የሁለት ፊደል ድምፅ ነው፣ 'ራብ' የሚሉት ከነስሙ
እንጂ የኔ ብጤውማ
የት አውቆት ጠባዩንማ፣
ብቻ ሲነገር ይሰማል
ይህንን ሁለት ፊደል ቃል፡...
ቃሉማ ያው በዘልማድ፣ ይነገራል ይለፈፋል
ይተረካል ይዘከራል
ይደጋገማል ይተቻል
እንጂ እንኳን ጠባዩንና፣ የራብ ዕድሜውን የት ያውቃል?...
እና እምታውቁት ንገሩን፣ እውነት ራብ ስንት ቀን ይፈጃል? . . . .
በጣር አፋፍ ላይ ያለህ ሰው፣ ራብ እንዴት ነው የሚያዛልቅ
ለስንት ቀን ቀን ይሰጣል፣ አንደበትክን ሳይሸመቅቅ
ሸረሪት በልሣንህ ላይ፣ የድር ትብትቡን ሳይሠራ
ቁራና ቀበሮ በቀን፣ ከቀየህ ድባብ ሳይደራ
ጥንብ አንሳ ሊጭር ሳይመጣ፣ ቅምቡርስ ከጐጆህ ጣራ
እንደፍካሬ ኢየሱስ ቃል፣ በጣር ምፅአትን ሳትጠራ
አንደበት ሳለህ ተናገር
የምታውቅ የራብን ነገር
አስከሬንህ ከየጥሻው፣ ተርፎ እንደሁ ሳይቀረቀር
ስንት ደቂቃ ስንት ፋታ፣ ቀጠሮው ስንት ትንፋሽ ነበር
ቆሽት አርሮ ሳይፈረፈር
ትናጋህ በድርቀት ንዳድ፣ ጉሮሮህ ሳይሰነጠር? . . . .
የሆድ ነገር ስንት ያቆያል? ቀጠሮ ይሰጣል እልቂት?
ስንት መዓልት? ስንት ሌሊት?
ስንት ሰዓት ነው ሰቆቃው፣ ስንት ደቂቃ ነው ጭንቁ
እስቲ እናንተ ተናገሩ፣ ተርባችሁ የምታውቁ
ስንት ያቆያል? ስንት ያዘልቃል? . . . .
እውነት ራብ ስንት ቀን ይፈጃል?

--------
ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን 

1 አስተያየት: