2012 ዲሴምበር 31, ሰኞ

ከሞተች ቆይቷል


ሰዓሊና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ

ከሞተች ቆይቷል ብዙ ዘመን ሁኑዋል
ብዙ ነበር ጊዜው
ግን ፎቶግራፍዋ፣ ደብዳቤዋም አለ
በጠጉርዋ ጉንጉን የጠቀለለችው
ምን ቀነ ቀጠሮ ነው
ቀን የቀን ጎደሎ
የቀን ጥቁር መጥፎ፡፡
አበባ ሄድኩ ይዤ …
እዚያ አበባ አልጠፋም
በመቃብርዋ ውስጥ አበባ ተኝትዋል፡፡
ስሜቴ ፈነዳ ገላዬን በተነው
ነፍሴን ነቀነቃት
እንባዬ ወረደ ጉንጬን አረጠበው
ለተረሳ ነገር እንዴት ያለቅሳል ሰው!
ለተረሳ ነገር
ምን ጊዜው ቢረዝም . . .
የዚህ አለም ጣጣ እንከራተተኝ
የዚህ አለም ስቃይ እየቦረቦረኝ -
ሲጨንቀኝ ሰውነት
ፍቅሬ ይሁን ያንቺ የኔ መቃብር ቤት፤
ህይወት ነዶ ጠፍቶ ሞት ፍሙን ሲያዳፍን
ያን ጨለማ ጉዋዳ ሄጄ ልተኛበት፡፡
ይመስላል ዘላለም . . .
የወደዱትን ሰው አይን አይኑን ሲያዩት
ይመስላል ዘላለም  አድማስ አልፎ አድማስ፤
ምጥቀት አልፎ ምትቀት፣ ጠፈር አልፎ ጠፈር
ይመስላል ዘላለም ሰው ባካል የሚኖር፡፡
ድሮ አውቀዋለሁ፤
ተረድቼዋለሁ፤
ፀሃይ ጥቁር ስትሆን
ቀን ቀንን ሲያጠላው ሌት ሌትን ሲሸፍን
እረስቼው እንደሁ፡፡
እንዴት አንቺን ልርሳ፣
ነፍሴ አብሮዋት የሚኖር የፍቅርሽ ጠባሳ፡፡
“ፍቅርሽና ፍቅሬ የተወሳሰበው
አልበጠስ አለኛ ብስበው ባስበው”
ማ ነበር . . . ማ ነበር
          ማ ነበር እንደዚህ፣ ብሎ የገጠመው?
ይመስላል ዘላለም
አንች የኔ እመቤት ብት ነበረ
አንት የኔ ጌታ
          አንት የኔ ጌታ ብላን የነበረ
አንች የኔ እመቤት
          ይመስላል ዘላለም፡፡
እንባዬ ወረደ፣ ልቤን አቃጠለው፣ ልቤ ተነደለ
የሰቀቀን እሳት አካሌን ሲያነደው ደደሜ ገነፈለ
የደም ጥቁር እንባ . . .
የቅጠል ጭማቂ አረንገዋዴ አበባ
የደም ጥቁር እንባ
ቆዳ የሚያሳርር መንፈስ የሚያባባ
አልቀሰቅሳትም . . .
ቡዳ እስዋን አይበላም ቢስ እስዋን አያይም
አልቀሰቅሳትም በነፍሴ ተጉዤ እጠይቃታለሁ
አለ ትዝታዋ . . .
          አውቃለሁ - አውቃለሁ
በመቃብርዋ ውስጥ ጢስ እንጨት ይጨሳል
ከርቤ፣ ብርጉድ እጣን . . .
መቃብርዋ ሽቱ
ጣፋጭ መአዛ አለው አጥንትዋ ታቦቱ
መቅደስ ቤተልሄም ቅኔ ማህሌትዋ . . .
እጣኑ ይጨሳል ይታጠናል ቤትዋ
ፍቅሬ ሙሽራዬ
እሜቤቴ ፍቅሬ ያለም አለኝታዬ
አቴትዋ ይታጠናል
ልዩ መአዛ አላት ማግሪፍ፣ ዲዩር፣ ሻናል
በመቃብርዋ ውስጥ ጢስ እንጨት ይጨሳል
በመቃብርዋ ውስት አበባ ተኝትዋል
ፍቅሬ ፍቅሬ  ፍቅሬ፣ ፍቅሬ ፍቅሬ ፍቅሬ
እመቤቴ ፍቅሬ እመቤቴ ፍቅሬ፣ እመቤቴ ፍቅሬ እመቤቴ ፍቅሬ
ፍቅሬ ሙሽራዬ ፍቅሬ ሙሽራዬ፣ ፍቅሬ ሙሽራዬ ፍቅሬ ሙሽራዬ
ፍቅሬ አለኝታዬ ፍቅሬ አለኝታዬ፣ ፍቅሬ አለኝታዬ ፍቅሬ አለኝታዬ
እንባዬ ወረደ . . .
እንግዲህ ይበቃል - ይቅር፣ ይቅር - ይብቃ
በድካም - መድከም፣ ባሳብ ሃሳብ አለ
ባዘን . . .ባዘን . . .ሃዘን . . .

ሰዓሊና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ

1 አስተያየት: