፠
፠
ውሾቼን ገደሏቸው! መርዝ የተቀባ ስጋ ሰጥተው ውሾቼን ገደሏቸው፡፡
ቀባሪዬ፣ መግደል እንጀራ በሆነበት አገር እንደመኖር ውስብስብ ነገር እንደሌለ ተረዳሁ፡፡ “ውሾች ለጤና ጠንቅ ናቸው” በሚል መርዝ አበሏቸው፡፡ ውሾች የመኖር መብት አላቸው፤ ፍጥረት ናቸውና፡፡ ባለቤት የሌላቸው መሆናቸው ግን አስገደላቸው፡፡ ልከላከል ሞክሬ ነበር፤ እንዳይበሉት ለማድረግ ጥሬ ነበር፤ ገዳዮቹን ለማባረር ጥሬ ነበር፤ ግን ብቻዬን ነኝ! ውሾቼኮ የበጋ ወዳጆቼ ናቸው፡፡ ይህ ክፉ ክረምት ውሾቼን ዳግም እንዳላያቸው የመሰናበቻ ጊዜ ሆነ፡፡ አለቀስኩ፣ ጮህኩ፣ ጉልበቴ ደክሟል፡፡ በጎረምሶች እጅ እግሬ ተይዟል፡፡
የመንደሪቷ ነዋሪዎች የውሾቹን አሟሟት በማየት ለራሳቸው ደስታን ሲፈጥሩ እውነቴን ነው የምልህ ይበልጥ ጠላኋቸው፡፡ ለዚህች መንደር ነዋሪዎች የሞት ስቃይ ማየት የሚፈጥረውን ደስታ ማጣጣም አዲስ አይደለም፡፡ ሰዎች የሞት ቅጣት ይበየንባቸው የነበረበት ቦታ እዚህ መሆኑን እወቅ! ከብዙ ዓመታት በፊት የሞት ፍርደኞች በአደባባይ ይሰቀሉ እንደነበር ቦታ ላይ ነኝ፡፡ ይህ ታሪክ የማይረሳው ሰው በአደባባይ በሞትና በህይወት መሀል በነፍስ ከስጋ ለመለየት የሚደረግ መንፈራገጥን ምንነት የተገለጠበት ቦታ ነው፡፡ ይግባህ! የማወራው ድሮ ማነቂያ ስለነበር ስፍራ ነው፡፡ በክር አንገትህ ታንቆ መሞት ምን እንደሆነ የምታይበት ስፍራ፡፡ መንደሬን ያወካት መሰለኝ፡፡ ሞትን ወደህ ሳይሆን ተገደህ መጎንጨት ሰውን ሳይሆን የሞትን ክብር መንካት ነው፡፡
መርዝ የተለወሰ ስጋ የበሉ ውሾች ሲዳከሙና ለሀጫቸውን ማዝረክረክ ሲጀምሩ ቦት ጫማና የጎማ ጓንት ያጠለቁ ገዳዮች በእጃቸው የያዙትን የብረት ማነቂያ አንገታቸው ውስጥ እየከተቱ አነቋቸው፡፡
ተፈጥሮ በህይወት ጉዞ ውስጥ ከለገሰቻቸው ሞቶች የበለጠ የሰዎች ፈጠራ ውጤት የሆነ የመግደያ ብልሃቶች ዘግናኝ ናቸው፡፡ ምስኪን….፣ ውሾቼ ሰዎችን ማመናቸው አሳዘነኝ፡፡ ትላንት በአደባባይ፣ ሊያውም በጠራራ ፀሐይ ጎዳና ላይ ሲተኙ ኮቴም ሆነ የመኪና ጥሩንባ አይቀሰቅሳቸውም ነበር፡፡ ሰው በመኖሩ ብቻ መኖር የቻሉ አድርገው የወሰዱ ይመስለኛል፡፡ ሰው ሳይኖር መኖር የሚሳነው ሰው ብቻ መሆኑን አውቀዋለሁ፡፡ ውሾቼ አለቁ! እንቁራሪቶቼም ለህፃናት መጫወቻ እየሆኑ ነው፡፡ ከሞት የተረፉትን በጋ ላይ አልሰማቸውም፡፡ የውሾቼ በድን መኪና ላይ ሲጫን የሞት ትርኢቱ ተደመደመ፡፡ የመንደሬ ለቅሞ አዳሪዎች ወደሬሳነት ተለውጠዋል፡፡ ገና ለገና አብደው ሰው የጎዳሉ በሚል ፍራቻ የመኖር መብታቸውን አጡ፡፡ አንድ ቀን እኔም `ጭራቅ” ሆኜ ደማቸውን እንዳልመጥ ይገድሉኝ ይሆናል፡፡ እጅ እግሬን ጠፍረው ይዘውኝ የነበሩ ወጣቶች ለቀውኝ ሄደዋል፡፡ ምሽት ብርታት እስቲሰጠኝ ባለሁበት መቆየትን መረጥኩ፡፡
ቀባሪዬ፣ ይህች የሰዎች ታንቆ መሞቻ መንደር ከስሟ ጀምሮ የብቻዬ እንጉርጉሮ እንዲያገረሽ አደረገብኝ፡፡
አንቺ ዶሮ ማነቂያ የሆንሽው ዶሮ ማነቂያ ሆይ! ዛሬ ምኒሊክ አደባባይ የሆነው ስፍራሽ ላይ የነበረው ትልቅ ዋርካ ይታየኛል፡፡ ያን ጊዜ አለመፈጠሬ ዋርካሽ በፈረሰኛው ምንሊክ ሃወልት ቢተካም፣ የግሪኮች ጣሪያ አልባ (አንፊ) ቴአትር የመሰለው ዘመንሽን ውስጤ በከሰተልኝ ዋርካሽ የጥቁር ብካይ ሂደትሽ ይታየኛል፡፡ አንቆ መግደልን “ፍትህ” ነው ብለው የሚያምኑ ነገሥታቶችሽ አጣብተውሽ ከሄዱት ክፉ ባህርይ ጋር ዛሬም ያው መሆንሽ፣ ዛሬም ማነቂያ መሆንሽን አወጋሻለሁ፡፡
በማነቅ ስያሜና ድርጊት ህልውናሽን ያገኘሽው የኔ ምርጥ መንደር፣ በጉያሽ የታቀፍሻቸው ወጣቶች ቀይና ነጭ በሚል የሽብር መጠሪያ ጉሮሮ ለጉሮሮ በተናነቁበት ዘመንሽ የመንደሮችሽ ቀዳዳዎች የማነቂያ ሸምቀቆ ከመሆን ያለፈ በውስጥሽ ለተፈለፈሉ ማቲዎች ምን ፈየዱላቸው? እነ “ብቅ እንቅ” ሰፈር ስያሜያቸውን እንዴት አገኙ?? የፈሰሰ ደምኮ መጠፋፊያ ብቻ ሳይሆን የእርቅ መሰረት፣ የሰላም መሀላ መሆን ይችላል፡፡ በልጆችሽ ፍቅር አልባ አእምሮ ግን ጎራ ለይቶ መደፋፋትን በመምረጥ ድንግል አፈርሽን በደማቸው አርክሰው ደም የለመደ የደም ሱሰኛ መሆኑን በመንገር ጆሮዬን ይቧጥጡታል፡፡
መሬትሽን “እኔን ያየ ይቀጣ” ብሏል ደም አጠጥተው መተናነቃቸው በፈጠረው ደም መፋሰስ “ግብርሽ ነው” ይሉሻል፡፡ አንቺ የኔ ምርጥ መንደር፤ ከማህፀንሽ እንቧይ ቆርጠው፣ ከጡትሽ ተጣብተው በረከትሽን የተቋደሱ ሁሉ እንደ ፍጥረት መንገዳቸው መለያየት ሳይሆን እንደፍጡርነታቸው ለእኔ አንድ ናቸው፡፡ ውሾችም ቢሆን እንኳን፡፡
ክፋት አስበው አእምሮዎችን በፈጠረው የመግደያ ጥበብ ለሚጠፉ ሁሉ ኢ-ፍትሃዊ አሟሟት እስከተጎነጩ ድረስ የመሬት ግብር ደም መሆኑን ለማሳወጅ አልነሳም፡፡ መጠማትሽን አውቀዋለሁ፡፡ መራብሽን እረዳለሁ፡፡ ሁላችንም ብንሆን ቦጥብጠን የምንበላውን፣ ጨልፈን የምንጠጣውን አንቺኑ ነው፡፡ የተራብሽው የግፍ ሬሳን አይደለም፡፡ መጠማትሽን ደም አያረጥበውም፡፡ የመተናነቂያ አንፊ መሆንሽ ግን የልጆችሽ ጭፍግ ወዳድ መሆን ያመጣው ውጤት አንጂ የደም ልክፍት ተጠናውቶሽ አይደለም፡፡ መንደሮችሽ ነጭና ቀይ ሽብሮች በተነሳበት ወቅት “ብቅ - እንቅ” መሆናቸው የዋርካሽ ጥላ አጥልቶብሽ ናፍቆትሽን ለመወጫ “ምሴን ሰጡኝ” እያልሽ አይደለም፡፡ መሬትሽ የደም አዙሪት አልተጠናወተውም፡፡ አሁን አሁን የልጆችሽ በኑሮ መማረር ታንቆ መሞትን በራሳቸው እጅ መጎንጨት፣ የአባዜሽን ውላጅ ሳይሆን ወኔ ቢስ መሆናቸው ያመጣላቸው ከንቱ ዘዴ እንጂ ያንቺ ሸምቀቆ አቀባይነት አልታከለበትም፡፡
እውነት እውነት እልሻለሁ፤ ግብርሽ በፍትሃዊነት ሰበብ የፈሰሰ ደም አይደለም፡፡ በጤና ጠንቅነት ፍራቻ “አብሉኝ፣ አጠጡኝ” ብለው ያላስቸገሩ ለቅሞ አዳሪ ውሾችን ምስክሮቼ ናቸው፡፡ “የጤና ጠንቅ” ውሾችሽ አይደሉም፡፡ በየጥጋጥጉ የሚደፉ አተላዎችሽ እንኳን የሚፈሩት ሰይጣንን ቀትር ጠብቶ አይጠራባቸውም፡፡ በየመንገዱ ዳሩ በቀንና ሌት የሚሸቱ የካቲኻላ ውጤቶች እንኳን ለዚህች መንደር ነዋሪዎች በሽታ የመቋቋም ችሎታ ሰጧቸው እንጂ የጤና ጠንቅ አልሆነባቸውም፡፡
አንቺ የኔ ምርጥ መንደር፤ ያልተወለዱብሽ እንኳን አንዴ ካዩሽ በፍቅር ይወድቁልሻል፡፡ ከየትም የትም ቢሆን አንቺን ሽተው ይመጣሉ፡፡ ውበትሽ አይደለም ፍቅር የጣላቸው፡፡ የልጆችሽ “እንግዳ ተቀባይነት” አይደለም ሱስ ያስያዛቸው፡፡ የደም ሱስሽ እያዳፋ አላመጣቸውም፡፡ ፉንጋነትሽ አላሸሻቸውም፡፡ በውስጥሽ የሚፈፀሙ አሰቃቂ የሞት ትርኢቶች በውስጥሽ የታቀፉትን እንጂ መጤዎችን ሱስ አላጣመዳቸውም፡፡ ስውር ፍቅርሽ ግን በረጅም ገመድ አስሯቸዋል፡፡ ገመዱ በእጅሽ ነውና ነገም ካንቺ ጋር ናቸው፡፡
ዶሮ ማነቂያ ሆይ፤ ስምሽ በውስጥሽ ያለውን መተናነቅ ቢዘምርም፣ ያለፍትህ የፈሰሱ ደሞች ያህል አይጮህም፡፡ አንቺን ተደግፈው የቆሙ ቤቶች ጣሪያ የፊሊተር ጠላ ቀለም መስሎ ምስኪን መሆንሽን ቢያንፀባርቅም በውስጣቸው የተጠለሉ ነፍሶች ግን የደም ውርስ እንዳወረሻቸው ቆጠሩ እንጂ በደም እንዳጠቡሽ ለአንዲት ሰከንድ እንኳን መች ትዝ ይላቸዋል፡፡ አንገታቸውን ጠምዝዘውና አዙረው የሚጥሉዋቸው የአጉል እምነት ውጤት እንዲሆኑ የተገደዱ ዶሮዎች መች ባንቺ ላይ እንደወደቁ አገናዘቡና! “ነጭ፣ ዳልቻ” በሚል የቀለም አባዜ የቆዳ ቀለም በማማረጥ የሚታረዱ በጎችሽ እውነት አላቸው፡፡ ምሽትን ጠብቀው እሳት የሚጨመሩ፣ ከርቤና ድኚዎችሽ እገር ጎትት ሆነው የእለት እንጀራቸውን የሚጠብቁ ሴተኛ አዳሪዎችሽ ደፋቸውን ከማንፃት የዘለለ መች ኳሉሽ - አስዋቡሽ? ሰካራሞችሽ ሸኑብሽ እንጂ መች አጠቡሽ? አስመለሱብሽ እንጂ መች ዘሩብሽ? በላይሽ ላይ ወደቁ እንጂ መች በላያቸው ተደፋሽባቸው? አፈር ጠጠርሽን በእግራቸው ጠለዙ እንጂ እነሱ እንደሚሉት “እንቅፋት” መች ሆንሽባቸው፡፡ አይናቸውን በጌሾ ጋርደው “እንቅፋት መታኝ” አሉ እንጂ “አይናቸውን” ጋርደሽ መች ወገሩኝ አልሽባቸው?.... ሽንፈትን ማመን የተሳናቸው መሆናቸው ደብድበውሽ፣ እንቅፋት ሆነውብሽ፣ ሊያሸንፉሽ ሊሳናቸው ባንቺው አላከኩ እንጂ መቼ ቂምሽ ተቀጣጥሎ ገሞራን ተፋሽባቸው?
ቀባሪዬ አሁን እየመሸልኝ ነው፡፡ ዝሎ የነበረው ሰውነቴ የቀድሞው ጥንካሬውን አግኝቷል፡፡ ቅድም እጅ እግሬን ይዘው የነበሩ ጎረምሶች ባጠገቤ እያሾፉንኝ አለፉ፡፡ ከተናገሩት ውስጥ አንድ ነገር ይበልጥ ተሰማኝ፡፡ “ይሄ ቀዌ ውስጡ ያለው ሰይጣን ነው እኮ ሃይል የሰጠው” የሚል፡፡ አዘንኩላቸው ለእኔ ያልታየ ሰይጣን ለእነሱ ተገልጦላቸዋል፡፡ “ከንቱዎች! ከንቱዎች ናችሁ!” ብዬ ጮህኩባቸው፡፡ የውሾችን ድምፅ አወጣጥ እያስመሰሉ በመጮህ አሾፉብኝ፡፡
“እናንተ ስቃይ የሚያስደስታችሁ ከንቱዎች ውስጤ እንኳን ሰይጣን የለም” ብዬ መለስኩላቸው፡፡
“ዉዉ…ዉዉ…ዉዉ፡፡” እያሉ አላገጡብኝ፡፡
“እኩይ ምግባር በውስጣችሁ ከምትጠቀጥቁ ቆሽሻችኋልና ታጠቡ፡፡ እራሳችሁን አሽሞንሙናችሁ የሴቶችን ዳሌና ቂጥ ከማየት የከረፋ ስብእናችሁ ላንዳፍታ እንኳን ምን ምን እንደሚሸት ለመገንዘብ ሞክሩ!”
“ዉዉ…ዉዉ…ዉዉ፡፡”
“ዛሬ አለኝ ብላችሁ የምትመፃደቁበት ወጣትነት ነገ እሳት የነካው የፀጉር ዘለላ ያህል የሚኮማተር መሆኑን ለማወቅ ሞክሩ፡፡ ነገ በኔ ኑሮ የምትቀኑባት ጊዜ መሆኗን እወቁ”
“ዉዉ…ዉዉ…ዉዉ፡፡”
በእኔ ላይ አሿፊዎች ቁጥራቸው ጨምሯል፡፡ ውሾች ለመሆን ፍፁማዊነት የሌላቸው ሁሉ የተገደሉ ወዳጆቼን ማሾፊያ ሲያደርጉ ማየቴ ከንግግሬ አላናጠበኝም፡፡ ኃይሌን ጨመሩልኝ እንጂ፡፡
“እናንተ በህልም አለም እንኳን ከዚህች መንደር ውጪ የሆነ ድርጊት ማየት የማትችሉ ጉስቁሎች፣ ከሞት ትርዒት ውጪ ደስታን መፍጠር የተሳናችሁ ናችሁ፡፡ ለእናንተ አታሎ መብላት ጀብድ ነው፡፡ የውሾቼ አቅም ግን ከመኖር የዘለለ በህይወታችሁ ላይ የቀነሱትም የጨመሩትም ለውጥ የለም”
“ዉዉ…ዉዉ…ዉዉ፡፡”
“ሲቸግራችሁ መዝረፍ… ሲርባችሁ መቀማት ስትጠግቡ ጠጥታችሁ “ክብሬ” ነው ብላችሁ የምትኮፈሱበት ስጋችሁን መሸከም አቅቷችሁ በውድቅት ሌት መሬት ላይ ስትድሁ፣ ትውኪያችሁን ከመላስ የዘለለ ውሾቼ መች ተተናኮሏችሁ?”
“ዉዉ…ዉዉ…ዉዉ፡፡”
“ትላንት እንደናንተው ሲያሾፉብኝ የነበሩ ጓደኞቻችሁ እስቲ ዛሬ ጥሯቸው፡፡ ልቅ የድሪያ ውጤታቸው ያወረሳቸውን በሽታ ተደብቀው እያስታመሙ እንደሆነ ለእናንተ አልነግራችሁም፡፡ እናንተም ነገ እንደነሱ መሆናችሁ እንደማይቀር እወቁ፡፡ ያኔ እንዲህ “እዩኝ እዩኝ” ልትሉ አይደለም ከራሳችሁ ትደበቃላችሁ፡፡”
እውነቴን ነው የምልህ እነዚህ ፈሪዎች ካንደበቴ የሚረጩ ሀቆችን መቋቋም አልቻለም፡፡ ከፊቴ ለመበታተን ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ ትዝ አለኝ፡፡ አሁን ትዝ አለኝ “ሟርተኛ” እንደሚጠሉ እረስቸው ነበር፡፡ የውሾቼ ሞት ለዚህች መንደር ሰዎች ለካስ አንድ ነገር ቀንሶላቸዋል፡፡ የቻልኩትን ያህል ተከትዬ ተናገርኳቸው፡፡ እንዲህ አልኳቸው፡-
“የእኔ “ትሞታላችሁ” ትንበያ አይገድላችሁም፡፡ አትፍሩ፡፡ የውሾቼ ማላዘን ሞትን አይጠራባችሁም፡፡ ነገን ያለማሰብ በሽታችሁ ነው የምትጠሉትን ሞት የሚጠራባችሁ፡፡ እርስ በእርስ አለመተማመናችሁ፣ በመዋሰብ ጥንውት መዝቀጣችሁ የፈጠረው ገደብ የለሽ ስሜት መዋጣችሁ ነው ሞተን ባንቀልባ ያሳዘላችሁን፡፡ ውስጣችሁ ቆሽሿል፡፡ ታጠቡት፡፡ ያን ጊዜ ቢያንስ መኖር ቀላል መሆኑን ትረዱታላችሁ፡፡ ያኔ መሞት ከመኖር እንደሚከብድ ታዩታላችሁ፡፡ የእድር ጥሩንባ በሰማችሁ ቁጥር አትሳቀቁም፡፡ የሚያላዝን ውሻ ይናፍቃችኋል፡፡ ሀቁ ይህ ነው፡፡” ከተከተልኳቸው ወጣቶች አንዱ ብቻ ይህን አለ፡-
“ዉዉ…ዉዉ…ዉዉ፡፡”
ሰማይ ድረስ በሚሰማ ድምፀት አፌን አላቅቄ ሳቅሁ፡፡ “ሃ..ሃ..ሃ..ሃ..” ሳቄን እንጨረስኩ ልክ ውሾቼ ሲያላዝኑ እንደምሰማው አይነት ድምፀት ከውሾቼ ባልተናነሰ ማውጣት ቻልሁ፡፡ ደገምኩት፡፡ ሌቱን ሙሉ ደጋግሜ ጮህኩ፡፡
“ዉዉ…ዉዉ…ዉዉ!!!”
በ-ኄኖክ ስጦታው
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ