የቆሻሻ ወደብ
______(ኄኖክ ሥጦታው)
የስልጣኔ ዝቅጥ መጣያ፣ የጥራጊያቸው ወደብ ነን፤
የጣሉትን የምንለቅም፣ ካልጣሉልን የምንለምን፤
ፈረስም ነን
ለነዚሁ፣ እንዳሻቸው የሚያደርጉን፤
ካሻቸው የሚለጉሙ፣ ካሻቸውም የሚጋልቡን፤
ካሻቸው የሚጭኑ፤ ካሻቸውም የሚዋጉብን፡፡
የገደልም ማሚቶዎች ነን፤ የጮኹትን የምንደግም፤
በለኮሱት ስንቃጠል፤ በቃ
ሲሉን የምንከስም!
በስማ በለው ተብትበውን፣ “በቁሳቸው” እንዳጨቁን፣
ስንዳክር ዳናው ጠፍቶን፣ እስከ መቼ
እንዘልቃለን!?
ሲጋልቡን ስንጋለብ፣ የጫኑንን ስንሸከም፤
የጣሉትን ስንለቅም፣ የሚሉትን ስንደግም!
እንደ አራስ ልጅ
በሰው ጀርባ
እስከ መቼስ እንዘልቃለን!?
እስከ መቼስ እንከርማለን!?
______________
መስከረም 2005ዓ.ም
ኄኖክ ሥጦታው - "ሀ-ሞት"
የግጥም መጽሐፍ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ