2013 ኖቬምበር 12, ማክሰኞ

*የሆድ አምላክ __~ኄኖክ ስጦታው

*የሆድ አምላክ __~ኄኖክ ስጦታው

ለማግኘቱ፣ ለማጣቱ
ለመውዛቱ፣ ለመንጣቱ
“እንጀራ” ነው ለሀበሻ፣
“እህል ውኃ” ምክንያቱ፡፡

ሕልውናው የጸናበት፣
መወጣጫ መሰላሉ
“የሆድ አምላክ” ተቀብቷል፣
 ይገለጣል “በእህሉ!”
ለረገጠው መሬት ሳይሆን፣
ከእግሮቹ በታች ላለው
ለማይነካው ሲንጠራራ፣
ለሰማይ ነው የቀረበው፡፡
“እህል ውኃ” በሀበሻ፣
አምላካዊ ክብር ለብሶ
“በጡር አለው” ተሰቅዞ፣
 “በክቡር ነው” ተወድሶ
ተሰጥቶ ነው ለሰማያት፣
የሚዘራው ምድር ታርሶ
“የሆድ አምላክ” ካለበቱ፣
 ከእኛው ሀገር ምግብ ነግሦ፡፡

*        *        *

የት ነው ያለህ የሆድ አምላክ?!
ላነገሡህ ምን አደረክ?!
ላመለኩህ መች አጠገብክ?!
ምዕመንህ ጠኔ ጥሎት፣ የሚበላው ተቸግሮ
በእርጥባን መኖር በቅቶት፣ ሀገር ላገር ተዟዙሮ
“የሆድ አምላክ” እውነት ካለህ፣
እስቲ ይጥገብ ለዘንድሮ?!?
____________

2003 .
ኄኖክ ስጦታው፣ -ሞት የግጥም መድበል

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ