2013 ኖቬምበር 12, ማክሰኞ

“ሀ-አይሞትም “ለ”ም ገና ይወለዳል! -- ቱዋ (ጋርጋንቱዋ)


“ሀ-አይሞትም “ለ”ም ገና ይወለዳል!

Written by ቱዋ (ጋርጋንቱዋ)

አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ ጥቅምት 30 ቀን 2006ዓ.ም

ጥበብ ለሁሉም ሰው ትገባለች ወይንም ትገባለች (“ገ” ይጠብቃል)? የሚለው ጥያቄ ሰርክ ያጭበረብረኛል። ነገር ግን ድርጊታችን ጥያቄውን መልሶልኝ አገኝና ወደ ተጨባጩ እውነታ አመዝናለሁ፡፡ በተጨባጩ እውነታ ላይ፣ ድርጊታችን እንደሚያሳየኝ፤ ጥበብ ብለን የምንጠራቸውን የፈጠራ ውጤቶች የምናቀርበው ለብዙሀኑ ማህበረሰብ ነው፡፡ ስለዚህም ቢገባቸው ነው የተገባችው እልና ጭጭ እላለሁ፡፡ ሳይገባኝ የተገባኝ አንድ የግጥም መጽሐፍ እጄ ገባ። ገጣሚው ሄኖክ ስጦታው ነው፡፡ የመጽሐፉ አርዕስት “ሀ-ሞት” የተሰኘ ነው፡፡ መጀመሪያ በችኮላ ሳገላብጠው ብዙም አልመሰጠኝም፡፡ እንደ ሌላው መጽሐፍ ማከማቻው ላይ ጣል አደረኩት፡፡ ጠብ በማይሉ ግጥሞች ለብዙ አመታት ተንገላትቻለሁ፡፡ ትንሽ ቀናት አለፉ፡፡

ሌላ ሰው መጽሐፉ ጥሩ መሆኑን ለማስረገጥ እየመረጠ ያነብልኝ ጀመረ። መጽሐፉ ያው ሆኖ ሳለ…አንዴ ሳይጥመኝ በኋላ መልሶ ለምን እንደጣመኝ ለማወቅ በመፈለጌ ወደ ማሰላሰል ገባሁኝ፡፡ ማርሴል ፕሮስት የግጥምን ምንነት “The superimposition of two systems: thought and meter” ብሎ ይገልፀዋል፡፡ ምጣኔ/ምት/ ዜማ እና ሃሳብ አብረው እንዲስማሙ የተገደዱበት ልዕለ ህግ ነው እንደማለት፡፡ በምጣኔ እና ምት ዜማ መፍጠራቸው የተፈጥሮ ጉዳይ ነው፡፡ በግጥም ቤት መድፋት ወይንም መምታት ለጥበብ ብለን የምናደርገው ሳይሆን ለተፈጥሮአችን እውነት ስለሆነ የምንከተለው፣ ሳንመርጥ የተገደድንበት ነገር ነው። ግዴታችንን መወጣታችን ነው ውበቱ፡፡ ጤነኛ መሆናችንንም ገላጭ ነው። Superimpositio n የተባለውም በዚሁ የተፈጥሮ ግዴታችን ምክንያት ነው፡፡ ከምጣኔው፣ ከምቱ እና ከዜማው በኋላ ግን የሰው ግዛት ይጀምራል፡፡ በዜማው፣ በምቱ እና በምጣኔው ውስጥ ለማወቅ የምንሞክረው ሃሳብ ( ጭብጥ) ግን ከሰው ልጅ የነፃነት ምርጫ (volition)  የመጣ ነው፡፡

ያለ ሃሳብ እና ሃሳብ የሚፈጥረው ትርጉም በዜማ እና በምት ብቻ የሚመጣ ጭብጥ የለም። ጭብጥ ከሌለ “እና ምን ይጠበስ?!” የሚለው ጥያቄ ይመጣል። የሁለቱ የግዴታ ጥምረት ውጤት ትርጉም ያለው ውበት፣ እውነት…እና ጥበብ ይሆናል። ቅድሚያ ለቅርጽ መገዛት ወይንም በመጀመሪያ “ሃሳቡ ይቀድማል” ማለት፤ ሁለቱን ከመጣመር አያግዳቸውም፡፡ ከታገዱም ውበት አይሆኑም፡፡ መጀመሪያ ለሴት መብት መታገል ዞሮ - ዞሮ ወንዱን መግደል እስካልሆነ ድረስ ነው እድገት የሚሆነው እንደማለት፡፡ ጥበብም ይሄንኑ መሰረት የሚከተል የጥምረት ህግ ነው፡፡ ነገር ግን፤ እኔ ዛሬ መግለጽ የፈለኩት “ግጥም ማለት ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ አይደለም። ትርጉምን ሳናውቅ ግጥም ግን ይሰማናል፡፡ ሰው እስከሆንን ድረስ ትርጉሙን ባናውቅም ቅኔ መፍጠር እንችላለን። የግጥሙን ትርጉም እንጂ የግጥምን ትርጉም የማወቅ ግዴታ አልተጣለብንም፡፡ አሁን ወደ ዋናው አጀንዳዬ ልመለስ፡፡ ግጥም እንዲነበብ እና እንዲወደድ ማንበብ መቻል እና የሚነበበው ነገር የሚወደድ ተደርጎ መፃፉ ብቻ እንደማይበቃ የተረዳሁት በ”ሀ-ሞት” የግጥም መድበል ነው ብያለሁ፡፡

ገጣሚው ነዋሪነቱን ተጠቅሞ ያበረከተው የጥበብ ስራው ከእኔ ነፃነት እና ምርጫ ጋር የሚገናኘው እንዴት ነው?... በሚል ጥያቄ የተጭበረበረብኝን (መጽሐፉን መጀመሪያ ለብቻዬ አለመረዳት በኋላ በሰው ምርጫ ጥቆማ አማካኝነት መልሶ መረዳት)…ለማስተካከል ተነሣሁ፡፡ ምናልባት በመጀመሪያ ራሴ መጽሐፉን ሳገላብጥ ባገኘሁዋቸው ግጥሞች ምክንያት ሊሆን ይችላል እንደ መናቅ ብዬ የተውኩት፡፡ በብዙ አሰልቺ ግጥም እና አቀራረብ የተጉላላ ሰው፣ በሰለቸ አይኑ ስለሆነ አዲሱንም የሚመለከተው ሊጭበረበር ይችላል፡፡ ለምሳሌ “በግ ሳር እና በግ” የሚለው ግጥሙ፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆነኛል፡፡ በፊት…/በግ ነበርን/ሣር ቅጠሉን እየቃረምን፡፡/አሁን/ሣር ሆነናል/ በጐች ይታዩናል፡፡ ግጥሙ ምንም የሚወጣለት ነገር የለም፡፡ የተለመደ ከመምሰሉ በስተቀር፡፡ በ90 ዎቹ አጋማሽ አካባቢ “ድሮ አህያ እንዳልነበርክ በጅቦቹ መሀል አህያ ሲበዛ ዛሬ ጅብ ሆነሀል” አይነት የበዕውቀቱ እና የኑረዲን ኢሣ የሃሳብ ጥምዞች ጋር የተወራረሰ ስለመሰለኝ …”ጥሩ ሲደጋገም ይሰለቻል” ብዬ ሊሆን ይችላል፤ መጀመሪያ ችላ ያልኩት፡፡

በእርግቦች መሀል/እርግብ ተመስላ /”እርግብናት”/ያልናቱ/ላባ ተከልላ/ ስትከፍተው አፏን/አየን ጥርስ አብቅላ/ ይሄም ከሚሊኒየሙ በፊት የተፃፉ ወይንም የታሰቡ ግጥሞች የሃሳብ አጠቃለል እና “ለካ” የሚለውን ድሮ ከሚታሰበው የተቃረነ፣ ያፈነገጠ… የፍለጋ ጭብጥ የሚቋጠርበትን የዘመን መንፈስ የሚያስታውሰኝ በመሆኑ ሊሆን ይችላል …መጀመሪያ መጽሐፉ አይገባኝም (ገ ይጠብቃል) ያልኩት፡፡ አመተ ምህረቶቹን ከግጥሞቹ አስቀድሜ ብመለከት ኖሮ ግን፤ ተመስጦ ላገኝ የምችለው፤ ወይንም ተመስጦን የሚሰጠኝ ያልተደጋገመው፣ አዲሱ (ኦሪጅናሉ) በመሆኑ፤ ትላንትን ሳይሆን ዛሬን የሆኑት ላይ እንደሚገኙ መጠርጠር ነበረብኝ፡፡ እንደእኔ ዛሬ የሚገኘው የሚሊኒየሙን ወንዝ ከተሻገርን…የአምስት አመት የእድገት እና የትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለማስፈፀም መንፈራገጥ ከጀመርን በኋላ ያሉት አመታት ሂደት ውስጥ ነው፡፡ …የኑሮ ውድነቱም፣ የልማታዊ መንፈራገጦችም፣ የነፃነት አፈናዎችም…የነዋይ ፍቅር እና የፎቅ ፎንቃ…እና የተለያዩ እጥረቶች (በውጥረት መልክ) የተከሰቱብን በእነዚህ አምስት ዓመታት ሂደት ነው፡፡ ከሄኖክ ግጥሞች ውስጥ ማተኮር የነበረብኝ ገጣሚው በዚህ ሂደት ሳለ የፃፋቸው ላይ መሆን ነበረበት፤ ግን ይሄን መጀመርያ ላይ ማድረግ አልቻልኩም፡፡

ለስህተቴ ራሴን ይቅርታ እላለሁ! በነፃነት አንድን አዲስ ስራ ለመመልከት፤ አይን እና መስተሀልይ ብቻ በቂ አይደሉም፡፡ ነፃነት በመሰልቸት እና ለአመታት በተደጋገሙ አታካቾች የፈጠራ ተብዬ ውርጅብኝ…አይንም በፍዘት አይን ሞራ ይጋረዳል፡፡ መስተሀልይም ሁሉንም ነገር እንደ አዲስ የመመርመር (የህፃን ልጅ የየዋህነት) ቅልጥፍናውን ያጣል፡፡ የሄኖክ ስጦታው “ሀ-ሞት” የግጥም መድበልን በአዲስ እይታ ለማየት የሌላ ሰው እርዳታ አስፈልጐኝ ነበር። የሚረዳኝ በማግኘቴ ላየው ቻልኩ፡፡ በ2004  ዓ.ም የፃፈው “የቱባ ክር ጫፎች” ይኼንኑ የእኔን መሰል ችግር በግዝፈት ኢትዮጵያን አሳክሎ ያቀረበበት ነው፡፡ “የለውም ጫፍ ብሎ ቆርጦ የሚጀምር አራት ጫፍ ያገኛል፣ ክሩን ሲተረትር/ጫፍ መያዝ በጥጦ፤ በጥሶ መቋጠር/ኢትዮጵያን አድርጓታል የብዙ ጫፍ ሀገር/ሞልቷታል እያዬ አያልቅም ቢቆጠር/አያሌ ጫፍ ወራጅ፣ ዕልፍ ቆርጦ ጀምር/ተብትቦ የሚተው ደህነኛውን ድውር/ለመፍታት ሲነሳ ጠቅሎ የማይጀምር” ምናልባት ደረጀ በላይነህ በአለፈው አመት (ይመስለኛል) ባቀረበው አንድ መጣጥፍ፤ ግጥም ሞቷል የተባለው ውሸት መሆኑን፤ የሞተው አዲስ ባለመውለዱ ቢሆንም… የተረገዙ እና ቀን እየገፉ የመጡ መኖራቸውን ነግሮን ነበር፡፡

እኔም በዚህ የሄኖክ መጽሐፍ ይሄንኑ ብያኔውን ተቀብያለሁ፡፡ ማለት የሚፈልገውን ማለት መቻል ራሱ የህያውነት ምስክር ነው፡፡ የበረከት በላይነህን “የመንፈስ ከፍታ” ይዘን የሄኖክን “ነፃነት” ብናክልበት ከፍዘታችን መንቃታችን እርግጥ ይሆናል፡፡ “የቆጥ ላይ ቅስቀሳ ፩” የሚለው ግጥም ቀስቃሽ የሚፈልግ እንቅልፋምን ሳይሆን ቀስቃሽ የማይፈልግ አንቂን የሚዘክር ነው፡፡ ምናልባት ሳይቀሰቀስ ለመንቃት የቻለው ራሱ ገጣሚው ሊሆን ይችላል። ቀድሞ የነቃ፤ ቀስቃሽ እንጂ ተቀስቃሽ ሊሆን አይችልም፡፡ የገጣሚውን መንቃት ከራሱ በስተቀር እማኝ ሊሆን የሚችል ባይኖርም፤ በግጥሙ አማካኝነት ግን የሱን መንቃት እና የኛን መተኛት እንገነዘባለን። የተኙት ቀስቃሾች የነቁትን ሲቀሰቅሱ:- “ነግቷል! ነግቷል! ነግቷል! /ይሉናል/ይሉናል/ይወተውተናል/ተነሱ ተነሱ ተነሱ/ይጮኻሉ እነሱ/እየቀሰቀሱ…፡፡/ተቀስቅሰን በጩኸቱ/ተበስሮልን መንጋቱ፤/አደባባይ ስንወጣ/ቀስቃሻችን ከየት ይምጣ” ሄኖክ እና “ሀ-ሞት” እኔን የቀሰቀሱኝ ወደ አንድ መልዕክት ነው፡፡ “አሁንም የበፊቶቹ አይነቶች አሉ” ወደሚል ንቃት ተቀሰቀስኩኝ፡፡ በትጋት መከታተል አለብኝ ከእንግዲህ፡፡ ገጣሚዎች አሁንም አሉ፡፡ “ሀ ቢሞት “ለ” ይወለዳል፡፡ ውልደት ካለ ደግሞ ሞት አለ።

የበፊቱ አተያይ በመደጋገም ማርጀቱን ያሳየናል። ሲሞት ደግሞ ትክክለኛ ውልደት መኖሩ አረጋጋጭ ነው። ሄኖክ ወደ ሞት የሚያደላ አለመሆኑን “የሽንታችን ውጤት”፣ “እኔ ሰራሽ ሀውልት”፣ “ሐውልቱ ይበላ” የሚሉ ግጥሞቹ ገላጭ ናቸው፡፡
ሀውልት የሞቱትን መዘከሪያ መሆኑ አያጠራጥርም። ሀውልት ቆፍሮ ለማውጣት የሚታገሉት ከውልደት ጋር አንድነት የላቸውም፡፡ ከውልደት ጋር አንድነት የሌላቸው ገጣሚያን ሞልተዋል፡፡ ሞልተዋል ብቻ ሳይሆን፤ በጥበብ ወጣትነት ትኩስነት ቋንቋ አንፃር “ሞተዋልም”። ታሪክን ለማዋለድ የሚጥር፤ ራሱን ለማዋለድ ከሚጥር ጋር የዘመን ልዩነት ይፈጥራሉ፡፡ ራሱን ለማዋለድ ከሚጥር ደግሞ እውነትን ለመውለድ የሚጥር የመሞት እድሉ ጠባብ ነው፡፡ የወለደው እውነት ወቅትን፣ ጐሳን፣ ሃይማኖትን ወይንም ሌላ ጊዜያዊ አጥርን መሰረት ያደረገ እስካልሆነ ድረስ፡፡ ይህንን የተሳካ ውልደት ማከናወን የቻሉ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሀውልት አይሆኑም።

ከዘመን ዘመን እነሱም እንደ ስራቸው… ውልደት ናቸው። ክርስቶስን እንደ ጥበበኛ (እኔ) ስለምመለከተው የውልደት ትንሳኤ ተምሳሌት ነው፡፡ የፈጠረው ጥበብ በገፀ ባህሪዎች ላይ ሳይሆን በሰው ላይ የተሳለ፣ የታነፀ፣ ሁሌ ውበት እና እውነት የሆነ ፈጠራ ነው፡፡ ሄኖክ ወደ ፊት የሚያደላ ገጣሚ ነው፡፡ አጥንት ለቃሚ፣ መቃብር ቆፋሪ፣ ሃውልት አምላኪ አይደለም። “ቀን መቼ ይቆማል” በሚለው ግጥሙ ይሄንን ማለቱን እርግጠኛ ነኝ፡፡ “ሕግ ለውጥ ሆኖ፣ ዓለም ስትፈጠር/ ተጓዥ እንዲሆን ነው ህይወት ያለው ፍጡር/ ከእድሜ ሰረገላው ይዞን ከሚከንፈው/ ካሰረን ሰንሰለት በሞት ከሚፈታው/እራሱን ያስጣለ የታለ ቋሚ ሰው” በትልቁ እስር ቤት (ውልደት/ሞት) መሀል ቤት ካለው የፖለቲካ ስርዓት እስር ቤት አንፃር የእግረ ሙቁን ድርብርብ እያወዳደረ ይመዝናል፡፡ ወደ ሜታፊዚክሳዊው እስር ቤት ሳይሆን ወደ የስርዓቱ እስር በበለጠ ይጮኻል፡፡ ምናልባት የህይወት እስር ቤት ከውልደት በኋላ ቢጮሁም ከሞት በስተቀር መፍትሔ ስለሌለው ይሆናል፡፡

የፖለቲካ (የስርዓት) እስር ቤት ግን ለማሻሻል ይቻላል፡፡ ነፃነቱን በሚፈልግ… እና የሚፈልገውን መግለጽ በቻለ የሰው ነፍስ አማካኝነት የሚያስተጋባ ጥርት ያለ ጩኸት አለ፡፡ የሄኖክ ስጦታው የግጥም መድበል የዚሁ ፍላጐት መግለጫ ይመስላል፡፡ “ሲሻው ካባ ለብሶ፣ ሲሻው ካባ አውልቆ/ ሲሻው አፈር መስሎ፣ ሲሻው ተብረቅርቆ፣ ሲሻው ካኪ ለብሶ፣ ሲሻው ቁምጣ ታጥቆ/ከዘመን ተማስሎ፣ ከበላይ ተጣብቆ/ሥሩን እየጠቃ፣ ሥርዓቱን ዘልቆ፤ /ያልበላው ከበላው፣ እየተቀበሉ/ሶስት ሺህ ዓመታት፣ ታቾቹ ተበሉ” “ታቾቹ ተበሉ” የሚለው ግጥም፤ ለሰው ልጅ ጭቆና የተፃፈ ቢሆንም፤ የሚገልፀው ግን በአለም ውስጥ ስላለው የሰው ልጅ በአጠቃላይ ከመሆን ይልቅ ለሀገራዊ የሰው ልጅ የተነጣጠረ ነው፡፡ ወደ General ሳይሆን practical ፡፡ ለሦስት ሺ አመት የተፈራረቀው መልከ ብዙ ጨቋኝ ዛሬም አለ እያለ ነው፡፡ እየተለዋወጠ የሚደጋገመው ሸራፋ ፍትህ ግን እንዲቀየር ፍላጐቱ ነው፡፡ ገጣሚው፤ “መቼስ ምን ይደረጋል!” እንደ ሸራፋነቱ እውነታውን እንቀበለው የሚል አይደለም፡፡ ገጣሚው የጐደለውን እውነት የሚያስሰው በሌላ ማንም ቀዳሚ ላይ ተንተርሶ አይደለም። ከዚህ በፊት የቀደሙት ስህተት ከነበሩ፤ ዕርምት የሚመጣው ከራሱ ጋር እና ከውስጡ በወጣ እውነት ብቻ ነው። ይኼንንም እምነቱን በተለይ ከሚሊኒየሙ በፊት በነበሩ የራስ ፍለጋዎቹ ወይንም ፍላጐቶቹ ላይ በተደጋጋሚ ገልፆታል፡፡ ከቀደሙት ጋር በማጨብጨብ ከሚወለዱት ጋር መቆዘምን (በዚያ ወቅት) በፃፋቸው ግጥሞቹ ላይ መታዘብ ይቻላል፡፡ ለተለመደው ስህተት ከመከፈት…ላልተለመደው ግን የሚናፈቀው እስኪገኝ መከፋት እና ወደ ብቸኝነት መቆለፍን (መቆዘም) መርጧል፡፡

ይኼንንም በተለይ በ”ራስ ምስል” ፩፣፪ እና ፫ ቁልጭ አድርጐ ገልፆታል፡፡ “አሁን ነኝ ጥያቄ፤/አሁን ነኝ፣ መልስ አልባ፣/አሁን መልስ የለኝም፤/አሁን አልጣባ፡፡/ አሁን ማንበብ ቀርቷል፤ /አሁን ሰው መቁጠሩ፤/አሁን ብቻዬን ነኝ፤/አሁን ዝግ ነው በሩ፡፡/ ( ገፅ  55-1998  ዓ.ም) ይህ ከላይ የጠቀስኩት “የራስ ምስል” ቁጥር አንድ ነው፡፡ ሁለት እና ሶስትም ተመሳሳይ መልዕክት ነው ያላቸው፡፡ ሁሉንም ትቶ “ዘግቶ” ከተቀመጠ በኋላ ነው ወደ ሚሊኒየሙ “ከፍታን ጨምሮ” “ስበትን ቀንሶ” በሀይል የወጣው፡፡ ሲወጣ ይዞ የወጣው አንድ ድምጽ ነው፤ “ነፃነት” የሚል ድምጽ፡፡ ከሚሌኒየሙ በኋላ የፃፋቸው ግጥሞች የከረመውን ውሸት ለመጣስ የሚጮሁ የነፃነት ድምፆች ናቸው፡፡ ማጠቃለያ በዚህ በአጭር ማጠቃለያ ማለት የፈለኩት አንድ ነገር ነው፡፡ ውበት እና እውነትን መግለጽ ከሆነ የጥበብ ተልዕኮ…መጀመሪያ ግን እውነትና ውበትን ለማብቀል መሬቱ እና ከባቢ አየሩ በፍርሃት እና ግራ መጋባት ወይንም የሌላን አላማ ማስፈፀሚያ በሆኑ ያረጁ አስተሳሰቦች እና የጥበብ አመለካከቶች የተበከለ መሆን የለበትም፡፡ ከሆነ ደግሞ፤ ውበትን ፈጣሪው እና እውነትን ገላጩ፤ ከዚህ አሉታዊ ቀለበት (እስር ቤቱ) ሰብሮ መውጣት አለበት፡፡

ገጣሚው የሞከረውም ይሄንን ነው፡፡ ጥበብን ለጥበብነቱ ወይንም ውበትነቱ ከመጠበቡ በፊት በመሸንቆጥ ከሆነ አሉታዊውን መንፈስ የሚያባርረው የጥበብ ገለፃ ለዚህም ተግባር ታገለግላለች፡፡ ዋና ተግባሩዋ ይህ ሆኖ፤ ዋናውን ተግባር እንዳታከናውን የነፃነት አየር የሚያሳጥራት ደግሞ “ተራው” ከሆነ፤ ተራውንም ተራ ባልሆነ ሃይሏ… ጠበሏን ረጭታ ማባረር ትችላለች፡፡ የሄኖክ ስጦታው (ተሰጥኦው) ይሄንን ማድረግ ነው። “ሀ” አይሞትም ገና “ለ” ይከተላል፡፡ ለገጣሚው (በአጠቃላይ) ተስማሚ የገለፃ ነፃነት እስኪፈጠር በድን መስሎ መቆምም መፍትሔ አይደለም። መሮጥን ማብዛት ነው የሚሻለው፡፡ ከፍታውን መርጦ፡፡ ገጣሚውም “ስበት” በሚለው ግጥሙ ይሄንኑ ይላል፡፡

 የህይወት ጐዳና፣ ፈተናው የበዛ፣
መቆምም ይከብዳል፣ መሮጥን ላበዛ…
 ቢበዛ መፈተን በሃይለኛ ንፋስ፤
ደግሞም ከፍ ሲሉ፣ ውሽንፍሩ ቢብስ፣
መፍትሔው አንድ ነው፣ ካሰቡት ለመድረስ፣

ከፍታን ጨምሮ፣ ስበትን መቀነስ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ