ዓርብ 28 ጁን 2013

“ፍሩት” ቅድመ-ክትባት---- ኄኖክ ስጦታው




ወዳጄ ነው፡፡ የፍራፍሬ ጭማቂ መሸጫ ሱቅ አለው፡፡ የኑሮ ዘይቤው እና አመለካከቱ በሁለት ነገር የተገደበ ነው፡፡ በፍራፍሬ ጥቅም እና በፍራፍሬ ጥቅም ብቻ፡፡ ጭማቂ ልጠጣ በሄድኩባቸው ጊዜያት ሁሉ የገንዘብ መቀበያው ሳጥን ውስጥ  አላጣውም፡፡ የበሰለ ብርቱካን የመሰለ ፊቱን በፈገግታ አጅቦ ሰላም ይለኛል፡፡ ጭማቂው እስከሚመጣ አንዳንድ ፍልስፍናዎቹን ያዥጎደጉድልኛል፡፡

“የኛ ሰው ሲታመም ብቻ ነው አትክልትና ፍራፍሬ ይዘንለት የምንሄደው፡፡ በጤነኛነቱ ሰዓት ግን አረቄ ካልጋበዝንህ ብለን እናስጨንቀዋለን፡፡” ይለኛል፡፡

“እና ምን ማድረግ ነበረብን???” ብዬ እጠይቀዋለሁ ምን እንደሚለኝ ለመስማት፡፡

“ፍራፍሬ ሳትታመም በፊት ከተመገብክ እንደ ክትባት ነው፡፡ ከታመምክ በኋላ ግን ለጠያቂዎች የምታቀርበው የቡና ቁርስ ይሆናል፡፡” ይለኛል፡፡


ከሰባት ዓመታት በፊት ፣ ካልተሳካው አብዮት ጋር ተያይዞ የስራ ማቆም አድማና የንግድ ቤቶች መዘጋትን ተከትሎ ሥራው ላይ ከባድ ፈተና ገጥሞት እንደነበር የነገረኝን አልረሳውም፡፡ ለጭማቂ እና ለችርቻሮ ያዘጋጃቸው አትክልትና ፍራፍሬዎችን  “በመኪና ጭኜ እቤት አስገባሁ፡፡” አለኝ፡፡

“አስገብተህ ምንአደረግከው??” ስለው፡-

“ለሰፈር ሰው በነጻ አከፋፈልኩና በምትኩ ፍቅር ገዛሁበት” አለኝ፡፡


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ