2013 ጁን 29, ቅዳሜ

ግማሽ ህልም


*
*

እኔና ጓደኛዬ አብረን ያለንበትን መኪና በተደጋጋሚ ትራፊክ ፖሊስ ያስቆምና ይቀጣዋል፡፡ ጎን ለጎን በፈረስ እየጋለብንም ከሆነ ከየት መጣ ሳይባል ትራፊክ ይይዘንናሕገወጥ ግልቢያ አድርጋችኋል! መንጃ ፍቃድ!!”ይለናል፡፡

ጓደኛዬ ከኔ የበለጠ በመማረሩ የትራፊክ ሞተርሳይክል ከአሮጌ ተራ በርካሽ ገዝቶ አሸክሞ መጣ፡፡ /ይኼኛው ሞተር ሳይክልየኢትዮ- ቻይና ወዳጅነት መንገድከመሰራቱ በፊት በእርዳታ ያገኘነው አይነት ስለሆነ ለመንዳት ብዙም አልተቸገርኩም፡፡ /

በመጀመሪያ እሱን ከኋላዬ አስቀመጥኩና አቀማመጡን እንደቻለበት እና እንዳልቻለበት በሚገባ አጤንኩ፡፡ ለከረፉ አይሰጥም፡፡ መቼስ ፖፖ ላይ የተቀመጠ ብላቴና ቢያስመስለውም፡፡

ጉዞ ወደአቢዮትአደባባይ ! ሞተሯ በጣም ፈጣን ናት፡፡ ከመቼው እንደደረስን አላስታውሰውም፡፡ አብዮት አደባባይ ላይ ቀይ መብራት ይዞን እንደቆምን አንድ ጥቁር እና ግዙፍ ትራፊክ ከሩቁ በክፉ አይን እየተመለከተን እንደሆነ አስተዋልኩ፡፡

የሞተሯን አቅጣጫ ወደ ኢሚግሬሽን አዞርኩና የመብራቱን መልቀቅ ተከትዬ ተንቀሳቀስኩ፡፡ የሞተሩ ጉልበት ከመንተፋተፉ ባሻገር ካንዴላውን ዘይት ሳያገኘው እንደማይቀር ጠረጠርኩ፡፡

አሁን ስለካንዴላ የማሰቢያ ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ አንደምንም ብለህ ከኋላ ካለው ትራፊክ ወታደር እራሳችንን እናድን፡፡አለኝ ጓደኛዬ፡፡ አልሰማሁትም፡፡ ብሰማውም ለውጥ አልነበረውም፡፡ እንደዛ በብርሃን ፍጥነት ከአዲሱቅድመ ዓያትመንደር እዚህ ያደረሰን ሞተር እየተንተፋተፈ እኛ ወደፈለግንበት ሳይሆን ወዳልፈለግንበት ማምራት ጀመረ፡፡ የነዳጅ መስጫውን ብረግጠው ከባድ ማርሽ ባስገባ ምንም ለውጥ አላመጣም፡፡

እናም እንደፈራነው ሆነ፡፡ ትራፊክ ፖሊሱ ጋር ስንደርስ ፍሬኑን ሳልይዘው ሞተሩ በራሱ ጊዜ ቆመ፡-

በቃ! ተበላን!!” አለኝ ጓደኛዬ ወደጆሮዬ ውስጥ ገብቶ፡፡ እንዳለውም አልቀረ፡፡ ትራፊኩ፡-

መንጃ ፍቃድ!!” አለ ወታደራዊ ሰላምታውን አቅርቦ ሲያበቃ፡፡

ምን አጠፋሁ ጌታዬ? ” አልኩት እየተርበተበትኩ፡፡

ሃሳብ በመቀየር አቅጣጫ በመቀየር . . . ደንብ ተላልፈሃል፡፡

ዋሌቴን አውጥቼ መንጃ ፍቃዴን ስበረብር አጣሁት፡፡ የዕቁብ ደብተር ብቻ ነው እንዴ የያዝኩት?? ይሄን እቁብ ደግሞ መቼ ነው የጀመርኩት??

ብቻ፣ ውስጡ ሃምሳ ብር አስገብቼ ለትራፊኩ አቀበልኩት፡፡ ምንም አላለም፡፡ የብሩን ፎርጂድ አለመሆን አጥንቶ ሲያበቃ ደብተሩን ብቻ መለሰልኝ፡፡

ይኼ ሞተር በተደጋጋሚ ጥፋቶች ይታወቃል፤ ታርገው ለሌሎች ትራፊኮች የተበተነ ሲሆን ካስቆሟችሁ ይህን ጽሑፍ አሳዩዋቸው፡፡ብሎ በብጣሽ ወረቀት ላይ የሆነ ነገር ጽፎ ሰጠኝ፡፡ አንድ ቃል ብቻ ነው የተነበበልኝ፡-

የተቀጣ!”


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ