2013 ጁን 29, ቅዳሜ

ከሰባራ ባቡር እስከ ዮሐንስ ሰፈር (የቮልስ መኪና ትዝታዬን የቀሰቀሰው የዘንድሮው የመንግስት ባጀት መዝጊያ)

በ-ኄኖክ ስጦታው

/ቮልስ ዋገን ገዝተህ “ፒምፕ” ለማድረግ ቁም ስቅልህን የምታየው ወዳጄ፣ ይሄ ነገር አንተንም ይመለከታል እና አድምጠኝማ፡፡/ አውነቴን ነው፤ ቮልስ ለማደስ የሚወጣ ገንዘብ መኪናው ዋጋ ላይ ከአንድ መቶ ብር በላይ እንደማይጨምር ከራሴ ተሞክሮ ብትማር ነው የሚያዋጣህ/

ሁሌም የማስታውሰው ተረብ አለ፡፡ ቮልስ መኪና እንደገዛሁ “ልወዝወዘው በእግሬ” የሆነ ወዳጄ ክፉኛ ሞራሌን ያደቀቀበት ተረብ፡፡ መቼስ ላይችል አይሰጥም ነውና ቻልኩት፡፡ እንደማያልፍ የለ አለፈ፡፡ መኪናዋን የገዛኋት ሰሞን መልኳ ጠይም ነበር፡፡ ጠይምነቷ የቅብ ሳሆን የዝገት መሆኑን ልብ በሉ፡፡ ይህ ወዳጄ መኪናዋን እንዳያት ሆዱን ይዞ ስቆ ሲያበቃ፡-

“እንዴ !!! ይህችን መኪናን ያመረተው ፋብሪካ እኮ አሁን ዲዲቲ ማምረቻ እንደሆነ ታውቃለህ??! ” አለኝና ድጋሚ ሳቀ፡፡ ጥርሱን ባረግፈው ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ጥርሱን እንዲያረግፈው ረግሜው ማለፍ መምረጤ ግን ጠቅሞኛል፡፡ ቮልሷን መኪና ለማድረግ(ይቅርታ፣ መኪና ለማስመሰል) ያወጣሁት ወጪ ላይ የጥርስ ዋጋ ቢታከልት “እርም መኪና” የሚያስብል ነበረ፡፡

“የአገልግሎት ዘመኗን ድሮ ገና ከጨረሰች ቮልስ ጋር ለምን ትዳረቃለህ??” ያለኝ ባለሃብትም ነበር፡፡
/መኪና እና ስቴኪኒ በማይጣልበት አገር ውስጥ ነን፡፡ ለማን ብለን ነው የምንጥለው/

የሰባራ ባቡር አካባቢን የማውቀው በዚህች መኪና ዘመን ነው፡፡ ዲኮር አድራጊዎቹም የሆነ የሆነ ቦታ ሲያገኙኝ “እንዴት ናት ቮልስህ??” ብለው ከሚጠይቁኝ ጥያቄ ተነስቼ መቼም ቢሆን እንደማይረሱኝ ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ፡፡ ካለማጋነን፣ አዲስ መኪና ለማስዋብ ከሚለጠፍ ስቲከር ተቆርጦ የሚጣለውን አንስቼ የኔዋ መኪና ላይ በመለጠፍ ለማስዋብ ያደረኩት ጥረት ከመኪናዬ በላይ እኔን እዲያስታውሱ ያስገድዳቸዋልና፡፡

ሰሞኑን የባጀት መዝጊያ ወቅት ነው፡፡ እግር ጥሎኝ በሰባራ ባቡር አካባቢ ሳልፍ ቮልሴ ትዝ አለችኝ፡፡ እንዳስታውሳት ምክንያቱ ደግሞ የመንግስት ተሸከርካሪዎች ዲኮር በማስደረግ ተጠምደው አይቼ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ መኪኖች አዲስ ናቸው፡፡ ምን እያደረጉ ነው??

ስቲከር ያስለጥፋሉ!

መጋጫ ያስገጥማሉ!

በመብራት እና ፈረፋንጎ ላይ የሚገጠሙ “ክሮሞችን” ያስለጥፋሉ!

የወንበር ልብስ ያለብሳሉ . . . .

ይህ ሁሉ መኳኳል ለምን አስፈለገ?? ለነዚህ መኪናዎቹ በውበት ላይ ውበት መጨመር ለዕድገታችን “መሳለጥ” ፋዳው ምንድነው??? ሚጢጢዬ ስቲከር ለማስለጠፍ የሚወጣ ገንዘብ /“ፈርቅ”ን ጨምሮ/ ዘርፈ ብዙ ሽንቁር ላላት አገራችን ስንት ቀዳዳ ይደፍናል?? /ያውም በያንዳንዱ ግዢ ላይ አየር የሚይዙ ፐርቸዘሮች በበዙባትአገር/

መኪናዎቹ'ኮ አዲስ ናቸው፡፡ ምንም ባይደረግባቸውም ያምራሉ፡፡ መሽቀርቀራቸውን ለምን ፈለጉ??? ወይስ ባጀቱ ቢመለስ ተመልሶ የማይመጣ መስሏቸው??

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ