እሑድ 23 ጁን 2013

ው-ዝ-ግ-ብ-ግ-ብ --- በ-ኄኖክ ስጦታው



((በመጽሐፍ መልክ ተዘጋጅቶ ከተቀመጠ ዓመታት ካለፉት ጽሑፎቼ አንዱ ላይ ቀንጭቤ ጋበዝኳችሁ፡፡፡፡፡))



…….እዛው መንገድ ላይ ነኝ፡፡ በመንደሬ መጋረጃ ጀርባ፤ ከጌጣጌጥ መሸጫ አብረቅራቂ ደጃፍ ስር፤ ከመንደሬ ጀርባ እገኛለሁ፡፡ አሁን በማልወደው የሰው ጫካ ውስጥ ቆሜያለሁ፡፡ የሕሊናዬ እውነታ ይታየኛል፡፡ በሰው ጫካ ውስጥ ብሆንም እታያለሁ፡፡ አላፊው አግዳሚው እርስ በርሱ ከሚተያየው የበለጠ እኔን ያያል፡፡ እያየም ያልፋል፡፡ ዳር መቆሜን መረዳት ችያለሁ፡፡ ውስጥ ሳይሆን ውጪ መሆን አለብኝ፡፡ ከሰዎች መሀል መሆን የምችል አይመስለኝም፡፡ ዳር ላይ ወጥቻለሁ -- ወይም -- መሀሉ ዳር ሆኗል፡፡

ባዶው እጄ ትከሻዬ ላይ ተንጠልጥሏል፡፡ ምንም ነገር አልያዝኩበትም፡፡ እግሮቼ ላይ እንደቆምኩ ቆሜያለሁ፡፡ ጭንቅላቴን የተሸከመውአንገቴ በትከሻዎቼ መሀል እንዳለ አለ፡፡ ከዚህ ውጪ መሆን ያለብኝን ሆንኩ እንጂ በተለየ የፍራቻ ዓይን እንድታይ የሚያደርግ ነገር የለኝም፡፡

አሁን ይበልጥ ከዳር ቆሜያለሁ፡፡ ቅድም ከነበርኩበት ግን ጋት ያህል ፈቅ አላልኩም፡፡ መንገድ ዘግቼ ይሆን? ሰፊ ቦታ ይታየኛል፡፡ በወዲያኛው ተቃራኒ የእግረኛ መንገድ ላይ ግን እግረኞች ይርመሰመሳሉ፡፡ እኔ ከቆምኩበት ቦታ ጋር እኩል መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ለምን እንደጠበበም ግልፅ ነው፡፡ ሰዎች የሚጓዙት በወዲያኛው መንገድ ስለሆነ ጠበበ፡፡ ለምን እኔ በቆምኩበት መንገድ መጓዝ አቆሙ?

ሰዎች ወደበዙበት መንገድ ተሻግሬ ቆምኩ፡፡ ከምጠላው የሰው ጫካ መደባለቅ ፈልጌያለሁ፡፡ እንደፈለግኩት ሆነና መጀመሪያ ቆሜበት ወደነበረው ቦታ አሻግሬ ተመለከትኩ፡፡ በተቃራኒው በሰዎች ተጨናንቆ ታየኝ፡፡ አሁን የቆምኩበት ጠባብ መንገድ ደግሞ ሰፍቶኛል፡፡ ለምን እንደሰፋኝ ተረድቻለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች እኔ በቆምኩበት ማለፍ አይፈልጉም፡፡ …….


ለምን??!! እኮ እኔ ማነኝ???!!!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ