ማነው…. ‘ምንትስ’?
ያው መቸም እኔም እንደሰው
አንዳንዴ÷ አንዳንዴ ብቻ÷ ሕሊናዬን እውነት ሲያምረው
ሰብሰብ ብዬ እማስበው
“ቀድሞስ ቢሆን ለኔ ብጤ÷ ለኔ ብጤ የሔዋን ዘር
አዳሜ በኔ ላይ በቀር÷ ለኔ መስክሮ አይናገር”
ብዬ ከልቤ ስማከር
እኔው ከኔው ስከራከር
ተጨብጨ እማብላላው
ያው መቸም እኔም እንደሰው
የሐቅ ራብ ነፍሴን ሲያከው
ልቤ ልቤን ሲሞግተው….
“እውነትስ ምንትስ ማነው?”
እያለ ነው፡፡ …..
ያም ሆኖ ነገሬ ከልብ
ያልወጣነውና ለሕዝብ
ለማንም ያልተገለጠ÷ የራሴ ድብቅ ሱባኤ
ልቤ ከልቤ ጋር ብቻ÷ ያደረገው የዝግ ጉባኤ
ከቶ የናንተን ዳኝነት÷ አልጠይቅምና ስሙኝ
ፋይል ከፋች እንዳትሉኝ፡፡ ……
ያው ብቻ በዘልማድ ሕግ÷ በእንቶ ፈንቶአችሁ ልረታ…….
እውነቱ ከእውነቱ ተፋጭቶ÷ ሐቅ ሆኗልና ሽውታ
ስለዚህ አንዳንዴ ብቻ÷ አልፎ አልፎ ብቻ ላንዳፍታ
አሳቤም ሥጋዬም አብሮ÷ ትንፋሼም ሲያገኝ እፎይታ
ምንትሶች ለምትሉን÷ የለንምና ጸጥታ
ከዚያ ከሌት ውጣ ውረድ÷ ከቀን መኝታው ድውታ
ላመል ታህል ብቻ ድንገት÷ ለሃሣብ ንቃት ለትዝታ
ገለል ቀለል ሲለኝቨለስንቱ ሆይታና ዋይታ
ከዳር ዋጋው ካንድ ጊዜው÷ ከሂሣብ ዛቻው ቆይታ
ከግራ-ማ-ፎን ቀረርቶው÷ ከድም-ድሙ ካካታ
ከሙዚቃው ሆያ ሆዬ÷ ከናላ-ወቀጣው ፋታ
ከዳንኪራው ውትር ግትር
ከመጠጡ ብዥ ድንብር
ትንሽ የህሊና ሰላም÷ አገኘሁ ስል …. የሚለኝ ቅር
እንደገና ለብቻዬ÷ ልቤን ቁስል የሚያጭር
አለብኝ የሐቅ ብትር
ነፍሴን ከስሶ እሚያከራክር
እንደዛር እሚጎነትል÷ ሐቅ እንድጠይቅ የሚያስጥር÷
ያራቡኝ÷ ያጠሙኝ÷ የነሱኝን የሐቅ ዕድር
እንድጠይቅ÷ እንድጠይቅ÷ የሚያረገኝ እርር ክርር
ነፍሴን ከልቤ እሚያሟግት÷ በሐቅ ራብ እስካጣጥር
መንፈሴ ውስጥ የሚያቃጭል
‘እውነትስ ማን ነው ምንትስ?’÷ አስቲ እንጠያየቅ የሚል…..
ሕመም አለኝ÷ …. ይኸም ሆኖ÷ እግዜር ያሳያችሁ ላልል
ለይታችሁ አጥራችሁኝ÷ ከዳኝነታችሁ ባህል
ከፍርድ አደባባይ ክልል÷
ለኔ ከቶ ላታውቁልኝ
ነውር በቀር ላታዩብኝ
ጠር በቀር ላታስቡኝ
የሕሊናችሁን በደል÷ በኔ ለምትወጡብኝ
ምንትስ ከማለት በቀር÷ ሌላ ምን ላታስገኙልን
መቸም ቢሆን እኔ እናንተን÷ እግዜር ያሳያችሁ ላልል
እዘልቃት እንደሁ ነው እንጂ÷ ከልቤ ጋር አለብካይ…..
መሃላ አለኝ÷ ትናንት አንኳ÷ የእህቴ ልጅ እንኳ ትላንት÷
የስጋ ዘመድ ያጥንት÷ የደም መተሣሠር ገፍቷት
አገር አቋርጣ ልታየኝ
ልታጫውተኝ ልትጠይቀኝ
ልታዋየኝ ልታቀርበኝ
ችግርሽ ገባኝ ልትለኝ
ከዘመድ ልትደባልቀኝ
የወግ መሰላል ልትሆነኝ
ካገር ልታመሳስለኝ
አዲስ ዘዴ ልታሳየኝ
እንደመጻሕፍቷ ብርሃን÷ አርቃ ልታሳስበኝ
በመንፈስ ውድቀት እነዳልርቅ÷ በርቺ ልትል ልታቀርበኝ
መጣች ብዬ ሳሳስቃት
ሳጎርሳት ስገባብዛት
ልቤ ፈክቶ ሳደምጣት÷
… የእህቴ ልጅ እንኳ ትላንት
ለካ እሷስ ‘ቦይ-ፍሬንድ’ ብጤ÷ ‘ዳር-ልግ’ እምትሉት ሽቷት
ምሥጢር የሚያመሳጥራት
አሳስቧት÷ አሰኝቷት
የሚያሳውቅ÷ የሚያስተምር÷ ልቦና የሚከፍትላት
ለጊዜው÷ ለጊዜው ብቻ÷ በኔው ቴፕ እያራመዳት
በኔው መጠጥ እያጣጣት
በኔው ሶፋ እያስጠናት
ችግሯን ከተረዳላት
ኋላ …. ደብተር መግዣ እሚላት
አሰኝቷት÷ አሳስቧት
ነበር ለካ የደከመችው
ያገር የወገወ ድልድል÷ ድንበሩን የዘለለችው
የባህሉን የሥርዓቱን÷ ክልል የተሸገረችው
የሥልጣኔ መጽሐፏን÷ ድርሳኗን የዘረጋችው …..
እና አንዳንዴ÷ አንዳንዴ ብቻ÷ እኔው ከኔው ስመካከር
ከልቤ ጋር ስከራከር
ያው መቸም እኔም እንደሰው
የሐቅ ራብ ነፍሴን ሲያመው
እኔንስ ያሉትን አሉኝ÷ “ግን የእውነት ምንትስ ማን ነው?”
እያልኩ ነው፡፡
ይህ ነው አንዳንዴ እሚያጽናናኝ
ከሀሰት ሀፍረት የሚያዋጣኝ
ከንፈሩን ለሚመጥልኝ÷ ለሚያዝንልኝ እንዳዝንለት
ከንፈሩን ለሚነክስብኝ÷ በሚያዝንብኝ እንዳዝንበት
ለወረት ይፍታሽ ለሚለኝ÷ ወረት ይፍታህ እንድልበት
በሚያሾፍ እንዳሾፍበት
በሚስቅ እንድስቅበት
በቀን ለሚንበላጠጡ
በሌት ለሚብለጠለጡ ….
እንደቀንድ አውጣ ሰንኮፈን÷ እንጭጭ ሕሊና ያወጡ ….
የሴቶች አብሮ አደጎቸም÷ ባሎች እየፈረጠጡ
በጨለማ እየወጡ÷ እያዋጡ እየዋጡ
ሁሉም በተራ ከመጡ
በወሬም በማሽቃበጡ
በኔው ሥራ እኔን ሲበልጡ
ሴቶቻቸው ፈንታቸውን÷ ከኛው ጋር ሊበላለጡ
ለይስሙላ ለወግ ብቻ÷ እኛኑ እያሽሟጠጡ
ስልካቸውን መዋዋያ÷ እያረጉ ቢያሽቃብጡ
ቢሮአቸውን ሱቅ አድርገው÷ እየዋሉ ቢጋለጡ
ያው አልፈው በወረታችን÷ በእንጀራችን ላይ በመጡ
በገንዘቡም በሌላውም÷ ስጦታ እየተሰጣጡ
በምሥጢር ሲቀማመጡ
ባልና ሚስቱ በገሃድ÷ በንግዳችን በገቡብን
ገቢያችንን ወስደውብን
ስሙን ብቻ በተውልን ….
በዚህ ላይ ጩኸታችንን÷ ጭምር ነጥቀው ሲጮኹብን
መልሰው ደሞ ሲያዝኑልን
ለወግ ሲመጻደቁብን ….
ህሊናቸውን ባይሹት÷ ኀዘን የሚሹት እነሱ
ለሰባት እምነት ሲምሱ÷ በሰባት ምላስ ሲያወሱ
ባንደኛው ሲነካከሱ
በሌላው ሲሞጋገሱ
በሦስተኛው ሲነካከሱ
ሌት ዓይኑን ላፈር ያሉትን÷ ሳይነጋ የሚያወድሱ
እነሱን አርጎብን ጨዋ÷ የሸንጎ የባህል አዋይ
የሥነ-ሥርዓት ደላዳይ
መራጭ ቆራጭ ቀናን ከአባይ
ጨዋ መሳይ÷ ንጹህ መሳይ
ከኔ ምንም ላይሻሉ÷ ደሞ እኔን ምንትስ ባይ!
“ከሌባ ሌባ ቢሰርቀው
ምን ይደንቀው” እንደሚባለው
እኔንም የሚያስደንቁኝ
ከኔ አንሰው እኔን ሲያወግዙኝ፤
በገዛ ስማቸው እኔን÷ ባፍ ሙሉ ምንትስ ሲሉኝ፤
ይደነቅላቸው እንጂ÷ ያም ቢሆን በቃን ላይሉ
ወኔአችንን ካልበከሉ
በሥጋችን እንደጣሉን÷ መንፈሳችንን ካልጣሉ
ቅስማችንን ልባችንን÷ ሌት-ተቀን ካላቃለሉ
ዓሜን ብለን እስክናምን÷ ምንትስ ነን በሉ እያሉ
ሲያሽቃብጡ ሲያዳልሉ …
ስንቱን በኛ ላይ ማጋፈር÷ ለይስሙላ መካካሻ
ወይ ለንዴት መቀነሻ
ወይ ለበቀል ማስታገሻ
ወይ ለመሃላ ማፍረሻ ….
ኧረ ስንቱ÷ ሞልቶ ስንቱ÷ ብኩን የመንፈስ ምንትስ
ለስጋውም አብሮን ወድቆ÷ ዳግም በአእምሮው ሲረክስ
በልቦናውም ሲሴስን÷ በሕሊናው ሕግ ሲድስ
‘ፍሪ-ደሜ’ ነው እያለ÷ የኔኑ ደም ሲያልከሰክስ
በቃሉና በመንፈሱ÷ ወድቆ ደቅቆ ሲበሰብስ
ቴህ ወዲያ ማነው ምንትስ!
ከስጋው አልፎ በአእምሮው
ዘምቶ ወድቆ ተሰብሮ
ከኔ እኩል ለገንዘብ ሰክሮ
በቃልና ባንደበቱ÷ ከኔ ይበልጥ አመንዝሮ
ገበናውን እንዳዋጅ ቅዳጅ÷ ከቤት ሾልኮ የትም ስታይ
ልቅሶ ላይ ሆነ አደባባይ
ጎረቤት ሆነ ገበያ÷ ቤተ-ታቦት ቤተ-ጠንቋይ
በመኪና ወይ በጫካ÷ በጭለማ ወይ ጣይ ለጣይ ….
ዝም ብንል ብናደባ÷ ዘመን ስንቱን አሸክሞን
የጅልነት እኮ አይደለም÷ እንድንቻቻል ነው ገብቶን
ገልጦ ታይቶን ሁሉ ታውቆን
እንጂ÷ አይደለም ተስኖን
ጨዋ እሚባል ማን አለና÷ ደሞ ማን ምንትስ ሊሆን÷ ….
እማማና አባባ እንኳ÷ የልቤን የምነግራቸው
ምንም የማልደብቃቸው
አንዳንዴም ሲቸግራቸው ….
ገንዘብ ቋጥሬ ይዤላቸው
መጦሪያ እሚሆናቸው
ድካምና ሽምግልና÷ ጎረቤት ፊት ሳይጥላቸው
ጎጆ ልቀልስላቸው
የግብር ልከፍልላቸው
ሄጀ÷ ዘመድ አዝማድ መሃል÷ ተፈራርቀው ሲመርቁኝ
ጉልበታቸውን እንደሳምኩ÷ ቡራኬአቸውን ሳይሰጡኝ÷
… አባባና እማማ እንኳን÷ ካንድ ልቤ … እኩል የሚያውቁኝ
ዝቅ እንዳልኩ ሳልነሳ÷ ተንበርክኬ ሲመርቁኝ
እዚያው ተጠቃቅሰው አሙኝ÷
በዓይንና በግንባር ጥቅሻ÷ ከዘመድ አዝማድ ጋር በሉኝ÷
ጉድ ብለው እያስታወሱ
በገጻቸው እያወሱ
ከንፈር እየተናከሱ
በዓይን እየተጠቃቀሱ
የልጅነቴን ሳይረሱ
ከጎረቤቱ መሃከል÷ እነማን እንደለመኑኝ
እንቢ ስልም የሰደቡኝ
እሺ ስል ጉድ-ፈላ ያሉኝ
ወይም ከኔው አድረው ውለው÷ ኋላ ያች ምንትስ ያሉኝ
እነማን እንደነበሩ÷ ሁሉንም አስታውሰው አሙኝ÷
በጎረቤቱ መሃከል÷ አንዳችም ወሬ ሳይረሱ
በዓይን እየተጠቃቀሱ
ከግራቸው ሥር ሳልነሳ÷ ቡራኬውን ሳይጨርሱ ….
አሙኝ
ሥጋዬን ከተፉኝ
ከዘመድ አዝማድ ጋር በሉኝ፡፡ ….
ታዲያን እኔንም እንደሰው
አንዳንዴ÷ አንዳንዴ ብቻ÷ ሕሊናዬን ሀቅ ሲያምረው
ዳኝነት የእግዜር ነውና÷ ልቤን ፍረደኝ የምለው
“እውነትስ ምንትስ ማነው?”
እያልኩ ነው፡፡ ….
ግን አንዳንዴ እምዘነጋው÷ ሳስታምም የስሜን ቁስል
አለነሱም የለኝም ብል
ቢያሙኝ ነውና የባህል ….
ምነው በተለይ በነሱ÷ ብቻ ለምን ይቅርባቸው
እያልኩም ነው፡፡
… ደሞ ያባባም የእማማም÷ አልፎ ቀርቶ ደሞ ዛሬ
እንዲህ የስም ማቅ ለብሼ÷ ነፍሴን ጭምር ተዘክሬ
ተገንጥዬ ተነውሬ
አይሰበሩት ስብራት÷ የስም ቅጭት ተሰብሬ
ክብሬን አንገቴን ቀብሬ
አንድ ልጄን አስተምሬ
አስጨርሼ ተቸግሬ
አልፎ÷ ‘ግራ-ዱኤት’ ሲሆን÷ ደሞ አዲስ ችግር ያሳየኝ!
የሠርጉ ዕለት ከእጮኛው ጋር÷ ጠርቶ እንዳያስተዋውቀኝ
…. ማን ይበለኝ÷ ምን ይበለኝ
ስም አጠረው÷ ስም አጠረኝ፡፡
እኔን÷ ልጄን÷ ግራ ይግባኝ!
እኔን እናትክን ስም ይጥፋኝ÷
አትጥራኝ አልኩት÷ አትጥራኝ
አታስታውሰኝ አልኩት እርሳኝ ….
ይህም ሆኖ እኔ ልጄን÷ እግዚአብሔር ያሳይህ አልል
ቢከብደው ይሆናልና÷ ማለፍ ከትምህርቱ ክልል
ከሥልጣኔውን ኬላ ደፍ÷ እሱም ከሱ ዘመን ባህል÷
እግዜር ያሳይህም ብለው÷ ቢጥርም ሊያሳየኝ ላይችል
በእውቀቱ ብስለት ተቆርጦ÷ ተበጣጥሶበት የኔ ውል
እንደገና የሱም ዘመን÷ አዲስ ባወጣው ድልድል ….
ታጥሮ የኔ ዕድል ከሱ ዕድል÷
እና ምንም ቢሆን ልጄን
ፍቅሬን የመጨረሻዬን
ስም ያጣልኝን አንድዬን
ባላዋለኝ ውል እንዳልውል
ያውጣህ እንጂ ከዚህ እክል
ይኸው ቃል ለምድር ለሰማይ÷ እግዜር ያመልክትህ ላልል!
ብቻ አንዳንዴ እየረሳሁት
አንዳንዴ እኔም እንደሰው÷ ልቤን እያስዘነጋሁት
ለትንፋሽ ያህል ለእፎይታ÷ ፋታ ብጤ እየሰጠሁት
ከዳንሱ ዳንኪራ ርግደት
ከሙዚቃው ዋይታ ግዝፈት
ከፍካሬ ኢየሱስ ጥሪ÷ ከፋንፍር ነጋሪት ግለት
ከሃሳዊ መሲሃን ጩኸት
ከነጉግ ማንጉግ መለከት
እኔም እንደሰው አንዳንዴ÷ ልቤን እያስዘነጋሁት
ሕሊናዬ እያመለጠኝ÷ ያ በመጠጥ የሸፈንኩት
በውስኪ እንፋሎት ያፈንኩት
በዕድሜ ቁስል የጠቀምኩት
ተግ ይልና÷ ብቅ ይልና÷ በገሃድ እያስተዋልኩት
የሐቅ ራብ እንደፈራሁት
ግትር ብሎ ግንባሬ ላይ÷ በቁም እየተፋጠጥኩት
ልቤን ልቤን ሲያማክረው
“በቁም መረሳት÷ መጥፎ ነው!”
እንኳ ቢለው
ዳኝነት የእግዜር ነውና÷ እኔም ፍረደኝ የምለው
“እውነትስ ምንትስ ማነው?”
እያልኩ ነው፡፡
ፀጋዬ ገ/መድህን
እሣት ወይ አበባ
ምስጋና
----
ራሄል
ገብረ እግዚአብሔር፣ ይህን ግጥም እንድትተይብልኝ ስጠይቃት ያለማንገራገር ስለተባበረችኝ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ