ዓርብ 23 ዲሴምበር 2016

“ማሳ – ደግ”

(ኄኖክ ስጦታው)

በእንክርዳድ ማሳ ጥቂት ስንዴ በቅሎ
ይስፋፋ ጀመረ “እሕል ነው” ተብሎ።
*
ስንዴ ለሆድ ሲባል፣ በሰው መኮትኮቱ
ተነቅሎ ቢጣልም፣ እንክርዳድ ነው ብርቱ 
ሳይዘሩት ይበቅላል፣ የት ይሂድ ከርስቱ?!
*

ኮትኩቶ ማሳደግ፣ ቀልቦ ማደለብ፣ የሰው ታላቅ ዘዴ
“ ደረሰ… በሰለ…” የሚሉኝ በዙሳ ፣ ሊበሉኝ ነው እንዴ?!

ረቡዕ 21 ሴፕቴምበር 2016

መንገድ የግጥም መድበል ገበያ ላይ ዋለ


ውድ የእልፍኜ ታዳሚታን፣ ከዚህ በፊት "ነቁጥ" (1994ዓ/ም) እና "ሀ–ሞት"(2005ዓ/ም) ለሕትመት በቅተዋል። እነሆ "መንገድ" የተሰኘው ሶስተኛው የግጥም መድበል ታትሟል። መፅሀፉ ሁለት ፊት ያለው ሲሆን የገጣሚ አበባ ብርሃኑ "ጠፈጠፍ" የተሰኘው የግጥም መድብል ጋር ተዳብሎ ለገበያ ቀርቧል።

(አከፋፋዩ ጃፋር የመጻሕፍት መደብር ነው )

የመጻሕፍት መደብሮቻችን አድራሻ

1,  ለገሃር ኖክ ነዳጅ ማደያው አጠገብ ተወልደ ህንፃ

2, ጊዮርጊስ የአውቶብስ ጣብያውን ወረድ እንዳሉ

3, ሳሪስ አዲሱ ሰፈር መግቢያ

4, ቃሊቲ ገብርኤል ቤ/ክ አጠገብ

ያስታውሱ:-

ከጃፋር መጻህፍት መደብር መጻሕፍት ሲገዙ ሁሌም…… ከዓመት እስከ ከዓመት ከዋጋው ቅናሽ ተደርጎ ነው።

ከኢትዮጵያ ውጪ ላሉ አንባቢያን henoksitotaw65@gmail.com ቢፅፉልኝ በአድራሻችሁ የሚደርስበት መንገድ ተመቻችቷል 

ማክሰኞ 6 ሴፕቴምበር 2016

ከራስ ባህሪይ ጋር ጦርነት

አንድ የቼሮኬ አዛውንት ለልጃቸው ልጅ ይህን ታሪክ አጫወቱት፣
"የእኔ ልጅ፣ በሁለት ተኵላዎች መካከል ታላቅ ጦርነት ተፈጠረ። አንደኛው ተኩላ #ክፉ ነው። ይህም ማለት፣  ቁጣ፣ ቅናት፣ ስግብግብነት፣ ቂመኝነት፣ በየበታችነት ስሜት እና በውሸት የተሞላ ነው።
“ሌላኛው ተኩላ ደግሞ #ጥሩ ነው። ይህም ማለት… ደስታ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ተስፋ፣ ትህትና፣ ደግነት፣ አዘኔታ፣ እና ሀቀኝነት ያሉት ነው።”
ህፃኑ ልጅ እንዲህ ሲል አያቱን ጠየቀ፦ "የትኛው ተኵላ አሸነፈ?"
አዛውንቱ ለጥቂት ጊዜ ያክል ዝም ብለው ቆይተው ይህን መለሱ፦
"አሸናፊው ያለው ከውስጥህ ነው።"

ማክሰኞ 5 ጁላይ 2016

"አምስቱ ሞኞችና ሌሎችም ታሪኮች…"

(ኄኖክ ስጦታው)

‘ሙሽራው በዘገየ ጊዜ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ።’
(የነቁት ግን ይህን  ለማንበብ ችለው ነበር)

ከአሥሩ ደናግላን መካከል አምስቱ ሞኞች ናቸው። አምስቱ ግን አንድ። አምስት ደናግል ብልሆች አንድ ብርሃንም ለመፍጠር መዘጋጀታቸውን የተመለከተ የዚህ ዘመን "አዛዥ" እንዲህ ሲል ሰማሁት፦

‘ለአንድ ኩራዝ አምስት ሰው ምን ያደርጋል?! አራታችሁ ተመለሱና ከአምስቱ ጎን ቁሙ!! ብርሃን ለመለኮስ አንድ ሰው ይበቃል!!! ዳይ!!!’

የተባረሩት አራቱ ብልሆችም፣ አምስቱን ጅሎች አስተባብረው ስሞታ ለማቅረብም ወደመምህራቸው አቀኑ። እንዲህ ሲሉ ጠየቁ፦

‘ጌታ ሆይ፣ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን ሳናገለግልህ ቀረን?’

እርሱም ተናገረ። በርግጥ መልሱ ግልፅ ቢሆንም፣ ማንም አልሰማውም ነበር።  

‘ታዲያ ለምን ትጠይቁኛላችሁ? እኔስ ብሆን ያደረኩት ይህንኑ አይደል?!…’ 
☆   

ነገሩ እንዲህ ነው። አንድ የግብረ ገብ መምህር የዳርት ውድድር አዘጋጀ። ለተማሪዎቹ። ዳርቱ ነጭ ወረቀት ተለብጧል። ኢላማውን በነጩ ወረቀት ላይ የሚስለው እራሱ ተወዳዳሪው ነው። ለምሳሌ፣ በነጭ ወረቀት የተለበጠው ዳርት ላይ  የሚጠላውን ሰው ስም ይፅፋል። የፃፈውን ስም በፍላፀው አነጣጥሮ ከመታው ‘ጥላቱን ’ እንደተበቀለ ያህል ይረካል ።

ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ሁሉም ተማሪ  የራሱን ጥላቻ ለመውጋት ኢላማ ይሆነኛል ያለውን ታናናሽ ምልክቶችን በዳርቱ ላይ አኖረ ። ኢላማውን ለመውጋት አነጣጥረው የወረወሩት ሁላ የራሳቸውን ኢላማ ባይመቱም እንኳን፥ በስህተት የሌሎችን ኢላማ ክፉኛ ወጋግተውት ነበር።

እናም በመጨረሻ፣ የዳርቱን መጫወቻ የሸፈነው ነጭ ወረቀት ሲገለጥ የኢየሱስ ምስል ክፉኛ ተወጋግቶ ለሁሉም ታየ። ይህን ያደረጉት የግብረ ገብ  መምህሩ ነበሩ።

የራሱን ኢላማ  ለመምታት አነጣጥሮ የወረወረው ተሜ ሁላ እንዲህ የሚል ንግግር ከመምህሩ አንደበት ተላለፈለት፦

‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል’
በሌላ ጊዜ፤ 

ሁለት አማኞች ስለ ሃይማኖት እያወሩ ነበር።

አንደኛው ለሌላው፣ "አንዳንዴ ፈጣሪን… ለምን ድህነት፣ ረሃብ፣ ኢፍትሐዊነት… በአለም ላይ ሊያስወግድ እንዳልቻለና የሆነ ነገር እንዲያደርግ በፀሎት ብጠይቀው እወድ ነበር።" ሲለው ሁለተኛው አማኝ ተገርሞ ፦

"ታዲያ እንዳትጠይቀው ምን አገደህ?!" ሲል ይጠይቀዋል ።

እናም፣ የመጀመሪያው አማኝ እንዲህ ሲል መለሰ፦ "አምላክ ፤ እነዚህኑ ጥያቄዎች እኔኑ መልሶ እንዳይጠይቀኝ ሰግቼ ነዋ!" 
።።።።።።።።።።።።።።

እኔም ይህን አልኩኝ፦

‘ከዚህ በኋላ የምትጠይቀኝን መልሼ እጠይቅሃለሁና ስትጠይቀኝ ተጠንቅቀህ  ጠይቅ!’

*መነሻ ሃሳብ (ማቴዎስ 25…)

ሐሙስ 23 ጁን 2016

ውጣ—ውረድ

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)

“ነበር” ላይ ሊያበቃ፣ የ“ነው” ባይ  አቅጣጫ፤
ከ"ነው" እና "ነበር"፣ የታል የኔ ምርጫ?


መድረሻው መነሻ
          መነሻው መድረሻ
ጠይቅ “የታል” ብለህ… “የታል ውጣ—ውረድ”?
(ሕይወት መሰላል ነው፤ የእርብራብ መንገድ!)

የጥያቄ ምላሽ፣ በምጥ ላይወለድ
“እውነት” ካስጨነቀህ፣
  በስንዝር ቦታ ላይ፣ ጋት ጨምር… ተራመድ
መልሱን ተወውና፣ መጠየቅን ውደድ
                    ውጣ
           ወይም
ውረድ!

ሐሙስ 9 ጁን 2016

ፀሐይ

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)
የልቤን መሻት ለማድረስ፣ ውጣ ውረዱ ሲበዛ 
የመንፈስ ብርታት ልትሆነኝ፣ ሙቀቷ ሕይወት ሊነዛ
ፀሐይ ምድር ደርሳለች፣ ፍኖተ ሃሊብ ተጉዛ፡፡
ዝለቂ ከዋሻው ብርታቴ፣ ስንፍና ሰበቡን ይጣ
“ፀሐይ ልሞቅ ነው” በማለት፣ እኔም ከዋሻው አልውጣ፡፡

ረቡዕ 8 ጁን 2016

ወጣ ያሉ የግዕዝ ቅኔያት

ወጣ ያሉ የግዕዝ ቅኔያት

በአጋጣሚ አግኝቼ ያነበብኩት መጽሐፍ ነው። “ቅኔያዊ የእውቀት ፈጠራ“ ይሰኛል ርዕሱ። በማርዬ ይግዛው ተሰናድቶ በ የጀርመን የባህል ማዕከል፣ 2006 ዓ.ም የታተመ ነው።

“…አብዛኛዎቻችን ቅኔ ኃይማኖታዊነት ብቻ የሚንጸባረቅበት ይመስለን ይሆናል። ቅኔ የማይዳስሰው ነገር የለም። የጾታ ተራክቦን (የግብረ—ሥጋ ግንኙነትን) እና መዳራትን ጨምሮ።…” እያለ ይቀጥላል የመጽሐፉ ትንታኔ።
ቀነጫጭቤ ጋበዝኳችሁ፦

ቅኔ ፩

ኢይጠፍእ ሕልጽ እሳት ላዕሉ ወታህቱ፣
እስኪት ጉልጥምት እስመ ተዳፈነ ቦቱ።
ትርጉም፦
          እምስ የላይና የታቹ እሳት አይጠፋም፤
          ቁላ/ጉልጭማ (እንጨት) ተዳፍኖበታልና።
ምስጢር ፦

ጉልጭማ የተዳፈነበት እሳት እንደማይጠፋ ቁላ የሚገባበት እምስም ሙቀት አይለየውም። በተለምዶ እሳት የሚጠፋው በውሃ፣ ሙቀት የሚበርደውም በቀዝቃዛ ነገር ነው። እምስ ግን ራሱ የቁላን ትኩሳት የሚያስታግሰው በማይጠፋ ሙቀት ነው እንጂ ከቀዘቀዘ አስተናጋጅነቱ ይቀራል።

እሳቱ/ሙቀቱ የማይጠፋ የሚለው የመራባት የሰው እንስሳዊ ህይወት ምንጭ መሆኑንም ያመላክታልና በዚህ ግልፅ ወሲባዊ ቅኔ ውስጥም ስለ ሕይወት ቁም ነገር አልጣበትም።

ቅኔ ፪

እታገኝ ደመርኪ እምላእለ ክብርኪ ክብር፣
ለነዳይ እስኪት እስመ ወሀብኪ ቂንጥር።

ትርጉም ፦
         እታገኝ በክብር ላይ ክብር ጨመርሽ
         ለድሃው ሰው ቁላ ብልት በመጽውተሽ። (መጽውተሽዋልና)

ምስጢር ፦
ይህ ቅኔ እማሆይ ገላነሽ እታገኝ የተባለች ልጃቸው ስታገባ የተቀኙት ነው ይባላል። ሰሙ በዚህ ዓለም ለተራቡ ሰዎች የሥጋ ብልት ሳይቀር የሚመጸውቱ ሰዎችን ይገልፃል። ባለቅኔዋ እታገኝ የተባለችው ልጅ ስታገባ ለተራበ ቁላ የሚገባውን ምግብ በመስጠት የጽድቅ ሥራ ማድረጓን አስመስጥረዋል።

ዓርብ 27 ሜይ 2016

ጭምብል

ጭምብል

በፈገግታ ተከልለን፣ የክፋት ጥርሶች ስናገጥ
እኩይ ሥራችን ገፅ ሆኖ፣
            አድርጎናል መልከ-ቅይጥ።
“አስመሳይነት”
               መንታ ስለት፣
                          በጥርስ ሞረድ ሲሞዠጥ
አንደበት በውሸት ሲከፈት፣ ገፅ በጭምብል ሲለበጥ
ሰይፍ ይወጣል ከአፎት፣ መልካም ልቦችን የሚቆርጥ።

~Paul Laurence Dunbar
ውርስ ትርጉም ፦ ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ

ሐሙስ 26 ሜይ 2016

"የለ_ዓለም"

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ) 

"ከዚህ ቀደም በሰው ልጅ በማንም ያልተሞከረ አዲስ ሃሳብ እና የአፃፃፍ ስልት እውን አለ?"

የአጻጻፍ ቅርፅ ሃሳብ የማስተላለፊያ መንገድ ነው። የስነጽሑፍ አላባዊያን የተውጣጡት፣ ከተለያዩ ቀደምት ፀሐፍት ስራዎች ተወራራሽ መዋቅረ ውጤት (ውበት) አንፃር መሆኑም የሚያሳየው ይሄንኑ ነው። 

ይነስም ይብዛ፣ እያንዳንዱ ሰው በተመሳሳይ ሃሳብ ላይ በተመሳሳይ መንገድ ንፅረተ—ዓለምን ለመግለፅ ቢሞክር አንዳች ልዩነት አያጣውም። kahlil gibran "jesus the son of man" ላይ ሃሳቡን ለማስተላለፊያነት ከተጠቀመበት ቅርፅ በዋንኛነት ሊገለፅ የሚችለው ተፅፎ ያነበበውን ታሪክ መድገም ወይም መተንተን አልነበረም። በአንፃሩ ግን ተፅፎ በነበረው ውስጥ ጥያቄ ጭሮበት ያለፈውን ታሪክ እስከ ምናቡ ጥግ አሰላስሎና ጥያቄ ለነበረው መልስ ሰጥቶ፣ ወይም፣ መልስ ለነበረው ታሪክ አንዳች መጠይቅ በመቀመርና ተጨማሪ ታሪክን በማዋቀር ላይ የተመሰረተ አጻጻፍ ስልት ነበር የተጠቀመው። 

ሌሎች ፃህፍት በርሱም ሆነ የፈጠራ ስራዎቹ ላይ "ተፅእኖ" እንዳላሳደሩ የሚናገሩት ውስጥ አዳም ረታ ተጠቃሽ ነው። ታዲያ መንገዱም ሆነ (እውነቱ) ከ"ከየት መጣ" ጥያቄ "እከሌ" ተብሎ የሚጠቀስ ተዛማጅ አካል አለመኖር አይደለም። በምን ወጣ እንጂ።

የፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍ እና ታይታኒክ ፊልም ታሪካዊ መዋቅራቸው ተመሳሳይ ነው ማለት፣ የታይታኒክ ፊልም በፍቅር እስከ መቃብር መፅሀፍ ላይ ተፅእኖ አሳድሯል ማለት ነው? 

ችግሩ የተዳቀሉ ቅርፆች ስርወ ምንጭ፣ እከሌ የሚባል አንድ ሰውን ለማመሳከር ከአለመቻል ይወለዳል። ይህ ውስብስብ "ወጥነት" ሳይሆን በግልፅ ቃል ‘ቅይጥነት’ ነው። ቅይጥ ውጤት ደግሞ በቀያጭ ግብአት ተፅእኖዎች ሊያመልጥ አይቻለውም። 

አዲስ ቅርፅ ከየት ተወለደ ጥያቄን ፍፁም የሚያደርገው ሐቅ ግን አለ። ሃሳብን (ጭብጥ) እንደ ፅንስ፣ ውልደቱንም እንደ ውበት (ቅርፅ) ብንወስደው የውሻ ልጅ ቡችላ…ነው፤ የቡችላስ አባቱ ማነው?! ያስረገዘው ነው ወይስ ያደረገው?! የቡችላ አባቶች ብዛት፣ የእናቱን ማንነት ከጥርጣሬ ላይ አይጥልም። 

የሐሳብ ምንጭም ሆነ ድርቅ፣ ሰው ነው። ምልከታ የማንም ሆነ የምንም፣ ከአንድ ገበታ አብረው እንደተመገቡ ሁለት ሰዎች ይመሰልብኛል። 
አበላሉ እንዳለ ሆኖ አወጣጡ ላይ ግን ብዙ ልዩነት አለ። 

አዲስ መንገድ ሆነ አዲስ ሃሳብ "የለ_አለም!"

ቅዳሜ 21 ሜይ 2016

ለምን አልስቅ?!

እስቃለሁ!
(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)

የክልከላ እና የተግሳፅ ህግ ተሸብበን ሳቅ አልባ ሆንን። የሳቅ መንስኤዎች በሙሉ ከጊዜ ወደጊዜ እየተመናመኑ መጡ። ሳቅ አጠር ሆነን የሚስቁትንም አሳቀቅን። የሚያስቀው አያስቀንም። ለቀልድም ሆነ ጨዋታ መራር ትርጉም ፍራቻ ቁጥብ ሆንን። የክልከላ ህግ ለስሜት ቅድመ ሳንሱርነት ተሹሞ በላያችን ላይ ሰለጠነ። ስሜት ፈንቅሎት እንዳይወጣ በሳቃችን ላይ ከመርግ የከበደ ጭፍግ ቆለልንበት።

የሚስቅና ሌሎችን ለማሳቅ የሚወድ እንደ "ተራ ቧልተኛ" ተቆጠረ። መሳቅም ሆነ ማሳቅ ከበደ። ለአሳሳቅ ስልት ተበጀለት።

እንዴት እንደማይሳቅ የሚመክሩ ጭፍግ መካሪዎች በዙ። ሳቃቸውን አፍነው የሚወቅሱ በዙ። በፍራቻ ተሸብሸው የሚገስፁ በዙ። በይሉኝታ ታፍነው ፊታቸውን የሚጨፈግጉ በዙ። በንዴት ቱግ ብለው የሚንጨረጨሩ በዙ። "አያስቅም" የሚሉ በዙ።

ሳቅ ጠፋን። አሳሳቅ ጠፋን። ከአዘኑት በላይ ያዘንን መሳይ፣ በሚስቁት ላይ የምንበሳጭ…  የተውሶ ፊቶች ጥርቅም ሆንን። ሳቅ ጠፋን! አሳሳቅ ጠፋን። በላያችን ላይ እንዴት እንደሚሳቅ የሚያስተምር ትምህርት ቤት ተከፈተ።

እናም ዛሬ ከዚህ በታች ያለውን ቀልድ ከአመት በኋላ ድጋሚ ሳነበው በድጋሚ ሳቅኩ።

————
አንድ ሰሞን በአንድ አገር ዋና ከተማ ውስጥ ብዙ የጦር መሳሪያ ስለጠፋ የቤት ለቤት ፍተሻ ተጀምሮ ነበር፡፡ ሁሉም ተፈትሾ፣ ተፈትሾ ጳጳሱ ቤት ይደረርስና እዛ ገብተው ሁሉንም ክፍሎች ፈትሸው ምንም ስላልተገኘ በስተመጨረሻ እሳቸው ወደ ተቀመጡበት ሄደው ሲፈትሹ በጣም ብዙ መሳሪያ ያገኛሉ፡፡ ፈታሾቹም ተገርመወው፡-

“ይሄን ሁሉ መሳሪያ ከየት አገኙት?” ብለው ሲጠይቋቸው ፡-

“ሚኒስትሩ በስለት ያስገባው ነው”

የሁለት አህዮች ወግ

ሁለት አህዮች … እያወሩ ነው።

የመጀመሪያው አህያ፣ “የእኔ ባለቤት እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ በዱላ ይደበድበኛል” ይለዋል በምሬት።

ሁለተኛ አህያ፣ “ታዲያ ለምን ትተኸው አትሄድም?”

የመጀመሪያ አህያ፣ “እሱስ እውነትህን ነው። እንዳልከው ለማድረግ በተደጋጋሚ አስቤ ነበር። ነገር ግን እጅግ በጣም ውብ እና መልካም ፀባይ ያላት ሴት ልጁን ሳስብ ሃሳቤን እቀይራለሁ።” 

ሁለተኛው አህያ፣ “እንዴት ማለት? አልገባኝም”

የመጀመሪያው አህያ፣ “አሳዳሪዬ በዚህች ቆንጆ ልጁ ሲበሳጭ… ‘አህያ ካልሆነ በቀር የሚያመዛዝን ሰው አያገባሽም!’ ሲል ይናገራታል፤ እኔም የምታገሰው ይህ ሁኔታ እስከሚፈጸምበት ጊዜ ብቻ ነው።”

ዓርብ 20 ሜይ 2016

ቆይታ (ከቀብር አስፈፃሚዎቹ ጋር)


☞ኄኖክ ስጦታው

ለሞት ያለኝ ግንዛቤ ግልፅና አጭር ነው። ሞት እድገት ነው፤ መወለድም እድገት። "የሰው ልጅ ከሞት በኋላ ያለውን ካለማወቅ ፍራቻ አያሌ መሸሸጊያ ፈጥሯል" ያለው ዲካርት መሰለኝ ።

ጓደኞቼ "እንሳለም" ብለው ሚካኤል ቤተክርስቲያን ጋር መኪናዋን አቆሙ።"ዛሬኮ አርሴማና ተክልዬ ይነግሳሉ፤ አትሳለምም?"

"አልሳለምም፤ እናንተ ደርሳችሁ እስክትመጡ ቀብር አስፈፃሚዎቹ መደብር ውስጥ እጠብቃችኋለሁ።"

ወደ ሬሳ ሳጥን መሸጫና ማደሻ መደብር አመራሁ። ብዙ አይነት የአስክሬን ሳጥኖች ተደርድረዋል። ሁለት አይነት አበቦች (በወረቀት ተሰርተው ቀለም የተነከሩ እና ከበቀሉበት የተዘነጠፉሸአበቦች) ደጃፉ ላይ አየሁ። ፊትለፊት ሆነው እይታዬን ያልሳቡት ለምን ይሆን? ስልኬን አውጥቼ ፎቶ ማንሳት ጀመርኩ።

ሰዎች እንዳላዩ ሆነው ከሚያልፏቸው ነገሮች አንዱ እንደዚህ አይነት መደብሮችን ነው። መደብሩ በራፍ ላይ አበቦች አሉ። ከአበቦቹ በላይ ያሉት በላይ በላያቸው የተደራረቡ ሳጥኖች ግን አበቦቹን ጋርዷቸዋል። አ አ!  አይደለም። አስክሬን ሳጥኑ ከፊት ካልሆነ በቀር አበቦቹን እንዴት ከዕይታ ሊጋርዳቸው ይቻለዋል?

"ሄይ፣ ፎቶ ማንሳት ክልክል ነው!" የሚል ድምፅ ሰማሁ። ሁለት ወጣቶች ወደኔ መጡ።

ፎቶ ማንሳት ክልክል መሆኑን የሚገልፅ ምንም ምልክት የለም። ለምን ክልክል እንደሆነ ጠየኩ።

"የአስክሬን ሳጥኖቹ ዲዛይን ይሰረቅብናል። አይቻልም።"

"የሳጥኑ ዲዛይን ከሌላው በምን እንደሚለይ ማወቅ እችላለሁ?"

"የማትገዛ ከሆነ ብነግርህ ምን እጠቀማለሁ?"

"እኔ ባውቅ ምንስ የምታጣው ነገር አለ?"

"ለምንህ ነው ማወቅ የምትፈልገው?" ሲል ሌላኛው ጠየቀኝ።

"በቃ፣ ደስ ይለኛል። ሳጥኖቹን በቅርብ ሆኜ ባይ፣ አብሬያችሁ ውዬ ቀብር ባስፈፅም ደስ ይለኛል። በተለይ ከሳጥኖቹ መሐል የማስታወሻ ፎቶ ብነሳ… ደስ ይለኛል" አልኩ። እውነቴን ነበር።

እርስ በራሳቸው ተያዩና ፈገግ አሉ። ወደ ውስጥ እንድገባ ፈቀዱልኝና ትልቅ አልበም እንድመለከት ጋበዙኝ።
ለጨዋታ መጀመሪያ ያክል "ስራ እንዴት?" አልኩ።

"እግዚአብሔር ይመስገን"
(ምሥጋና ጥሩ ነው) 😱

የሚያምር የሬሳ ሳጥን አየሁና ዋጋውን ጠየኩ፦

"12ሺ ብር።" አለ።

"ዋጋው እንደዚህ የተወደደበት ምክንያት ምንድነው?"

"በኤምዲኤፍ ነው የተሰራው። እንደምታየው የሳጥኑ የላይኛው ክፍል ሙሉ መስታወት ነው። አስክሬኑ በሱፍ ሽክ ተደርጎ ይገነዛል።"

"ዋጋው አስክሬኑ የሚለብሰውን ሱፍ ጨምሮ ነው? "

"ልብሱን ቤተሰብ ነው የሚያዘጋጀው።"

"ለሴቶች ሲሆንስ?"

"አይቀንስም"

ሳቅኩ።
"ዋጋውን አልነበረም የጠየኩህ። አስክሬኑ የሴት ከሆነ ምን አይነት ልብስ ነው የምትገነዘው?"

እርስ በራሳቸው ተያዩ። መቼስ ሱፍ አያለብሱ።
ሁለተኛው መለሰልኝ፦
"የአገር ባህል ልብስ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ባለሙሉ መስታወት ሳጥኖችን ግን እስካሁን የተጠቀምነው ለወንዶች ነው።"

"የአሜሪካ ሳጥንም አለን።" አለ ሌላኛው።

"የትኛው ነው?"

"እዚህ የለም። አልበሙ ላይ ላሳይህ…።" አልበሙን ተቀብሎኝ ገለጥ ገለጥ አድርጎ "ይኸው!" አለ።

ያምራል።

"ዋጋው ምን ያህል ነው?"

"35 ሺ ብር"

"እ?"
ደገመልኝ። በሰላሳ አምስት ሺህ ብር የ1972 አዲስ ብራንድ አፍሮ ቮልክስ መሸመት የሚችል ብር እንደሆነ አሰብኩት። የገረመኝ ግን ሌላ ነበር፦
"ሳጥን አስመጪ አለ ማለት ነው?"

"አስመጪ የለም። ከአሜሪካ አስክሬን ይመጣበትና የአገር ውስጥ ሳጥን ላይ ብር ጨምረን ከቤተሰቦቹ ላይ እንገዛዋለን።"

"እዝጎ!" (አልኩ በውስጤ)

እሑድ 8 ሜይ 2016

ተራማጅ እሳቤ ፺፩

(ኄኖክ ስጦታው)

ባለሶስት ፉርጎ ነው፤ ይጓዛል ባቡሩ፤ ቆየሁ ተሳፍሬ 
            የኋላኛው – ትላንት፣
            የፊተኛው – ነገ፣
            መሀለኛው – ዛሬ …
*
የታለፈ ትላንት፣ ያልተኖረ ነገ፣ ሃሣብ ውስጤ ሰርጎ
(ወጥሮ ይዞኛል)
         ፊት ላይሆን—ወይ ኋላ፣ መሐለኛው ፉርጎ።

ዓርብ 6 ሜይ 2016

ልዩነቱ ግልፅ ነው

ዮናስ ጨርጨር ስጋ ቤት ምሳ ልበላ ገብቼ ሳለ…ቴዲ አፍሮ ፊት ለፊቴ ካለው ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ ሥጋ እየበላ ነው።
ልዩነታችን አሰብኩት።
ግልፅ ነው!
እኔ ስጋ ቆራጩን አውቀዋለሁ፤ እሱን ግን ስጋ ቆራጩ ያውቀዋል 

ዓርብ 22 ኤፕሪል 2016

ፍተላ

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)

ከዕለታት ባንዱ ጠዋት ነው።
ሌሊቱን ኦቭረን ጠዋት ላይ ነዳጅ ልቀዳ ማደያ ውስጥ ገባሁ።

"የስንት ልቅዳልህ?" አለ ነዳጅ ቀጂው።

"ደብል ቅዳልኝ" በግማሽ ልብ ሆኜ ነበር የመለስኩለት።

"የምን ደብል?"

ግሮሰሪ እንዳልገባሁ ትዝ ሲለኝ ፦ "ፉል አድርገው። የሃምሳ ብር!" አልኩት።

በግርምትና በድንጋሬ ከላይ እስከታች አይቶኝ እንዲህ አለ፦

"ላይተር ነው የምታስሞላው?"

እሑድ 10 ኤፕሪል 2016

Rumi "ልብስና ሰው"

"ይታዩኛል ብዙ ሰዎች
ዕራፊ አልባ፣ ልብስ የለሾች፤
ይታዩኛል ብዙ ልብሶች
በውስጣቸው የሉም ሰዎች።"

~ ሩሚ
ትርጉም ኄኖክ ስጦታው

ረቡዕ 16 ማርች 2016

የችሎት *ዳ ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ

የችሎት *ዳ
ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ

ታግሼው
ታግሼው
ታግሼው
ታግሼው
ታግሼው
የተናገርኩት ቃል፣ ፍርድ ቤት ቀረበ
የክሱ ሙሉ ቃል፣ ይላል "ተሳደበ"¡
"ተ*ዳ"
*
ታግሼው
ታግሼው
ታግሼው
ታግሼው
ታግሼው
ታግሼው
ዝም ያልኩት ተዘሎ፣ ለችሎት ቀረበ
ሰምቶ ፈራጅ ዳኛ፣ ክሴን አነበበ…

"ተቃውሞ"

ዝም!

"ማቅለያ"

ዝም!

"አቤቱታ"

ዝም!

ዳኛው…
"ዝም ያለ ተከሳሽ፣ ወንጀሉን አመነ"፣ ብሎ አነበነበ
ይሄኔ ተናገርኩ፣ ቃሌ ተከተበ

"ከፍድ በፊትና ከመክሰስ ቀድሞ፣ ማነው የታቀበ?!
ትእግስት ያለው ማነው፣ ከዚህ ክሴ ቀድሞ፣ ዝም እንዳልኩ ያሰበ?!"
*

ችሎት ተ-----!

ረቡዕ 9 ማርች 2016

ተነሳ ተራመድ - ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ

ተነሳ ተራመድ
---------
"ተነሳ ተራመድ! ክንድህን አበርታ!
ላገር ብልፅግና ለወገን አለኝታ!!"
እምም…
*
መነሻችን መቼ ጠፋ?! ለመበልፀግ ስንገሰግስ
ተፈጥሮን ፊቷን አዞረች። እንዴት ወደኛ እንመልስ?!
*
"ተነሳ ተራመድ! ክንድህን አበርታ!
ላገር ብልፅግና ለወገን አለኝታ!!"
*
"ተፈጥሮ የግብአት ምንጭ፣ ተፈጥሮ የእድገት አለኝታ
ኢንዱስትሪ ነው መርሃችን፤ ድህነት ድባቅ ይመታ!!"
*
"ተነሳ ተራመድ! ክንድህን አበርታ!
ላገር ብልፅግና ለወገን አለኝታ!!"
*
የኃያላን ተሞክሮ ውጤት፣ የእድገት ጉዞ ትግበራ
ተፈጥሮን ሚዛን አስቶ፤ ለዜጎች ፍላጎት ሲሰራ
ዋስትና በገንዘብ ተለካ፤ ብልፅግና በሸቀጥ ተመራ…
ውራ የመሆን ጨዋታ፣ አይመራምና በጭራ…
ተቀበል!
*
"ተነሳ ተራመድ! ክንድህን አበርታ!
ላገር ብልፅግና ለወገን አለኝታ!!"
*
ወደፊት መጓዝ እንዳለው፤ ወደኋላም እንመለስ
ተፈጥሮን ማጥናት አይበቃም፣ ኗሪ ጎጆውን ሲቀልስ።
*
"ተነሳ ተራመድ!
ክንድህን አበርታ!
መጥረቢያ ነው ጠላትህ፣ አንተን በድርቅ የመታ!!!
"ተነሳ" ሲሉህ ተነሳ!
አምባገነን ነው ተፈጥሮ፣
"እንዳያልፉት የለም" ከማለት፤ የእልቂት ታሪክ ሞነጫጭሮ
ወደኋላ እንመለስ፣ እርቅ እንፍጠር ከተፈጥሮ
የደን ታሪክ ይሰራ፣ የደም ታሪክ ተሽሮ።
*
ተፈጥሮ ለጨቆኗት ጨቋኝ ነች፤ 
Sep 20, 2015 1:42:12 AM

ረቡዕ 2 ማርች 2016

ጥያቄ ጥያቄ ጥያቄ

አንዳንዴ፣ ራሴን እንዲህ ስል እጠይቀዋለሁ፦
ሰፊውን አለም  ማን አጠበበው?

እውነት ጀግና ማለት ለአገሩ የሞተ ነው?  የገደለ?

ለአገር መሞት ማለት፣  በሌላው መገደል ብቻ ነው? ወይስ መግደል?

የመሞት ዓላማው ከመግደል በመጠኑም ቢለይም ስንኳን ፣ ሰውን ያክል አምሳያ መግደል በርግጥ ጀግነት ነው?  ወይስ አረመኔነት? ወይስ ተፈጥሯዊ የሆነ የማንነት መገለጫ?!

ለአገር መሞት ነው ጀግንነት? ወይስ ፣ በሰው መገደል ነው ጀግንነት?!

እራሱ «ጀግንነት» ምንድነው?!

ክብር ነው?
ስሜት ነው ?
ወይስ
ሌላ?

ጀግና ማለት፣ ላመነበት አላማ የተገደለ ነው?! ወይስ… የገደለ?!

ገድሎ የሞተው ፣ ሞቶ ካሸነፈው የሚለየው በምንድነው?
በሕይወት?
በሞት?
በድል?
በሽንፈት?

. .
.
.
.
.
.
.
.
. .
ከጦርነቱ የተረፈ በርግጥ ጀግና ነው ?!

.
.
በርግጥ የቱ ነው ጠባብ?!

አገር ከዓለም ይጠባል?!

ዓለም ከአገር ይሰፋል?!

አስፍቶ ለተመለከተው በርግጥ ዓለም የአገር አካል ናት? ወይስ

ዓለም ከሰፈር ትጠባለች?!

እናም፣ ጥያቄው ማብቂያ የለውም። መልሱ ግን ይብሳል¡

“ቀልድ የማያውቁ ቀልዶች”

“ቀልድ የማያውቁ ቀልዶች”

“ብሶት ሲኾመጥጥ የቀልድ ቡኾ ይሆናል።”

አባባሉ የአለማየሁ ገላጋይ ነው። ከዚህ በታች ላሉት “ቀልድ የማያውቁ ቀልዶች” መግቢያ የተጠቀመው።

✧✧✧
ወጣቱ የጋራ መፀዳጃ ውስጥ ቁጭ ብሏል። ብዙ ሰዎች እየመጡ ያንኳኳሉ፦

“ሰው አለ!” ወጣቱ ነበር። እንዲህ እየመለሰ ከተቀመጠበት ሳይነሳ፣ ከገባበት ሳይወጣ ብዙ ቆየ። በሁኔታው ብስጭትም፣ ህመምም የተሰማቸው አዛውንት ድምፃቸውን ጎላ አድርገው፦

“ማነህ የኔ ልጅ፣ መቼም ሽንት ቤቱ የጋራችን ነው። እኛም ልንጠቀም ነው አመጣጣችን። ለረጅም ጊዜ ስለቆየህ ምን አለ ብትወጣ?” አሉት።

ወጣቱ ከውስጥ ሆኖ ንቅንቅ ሳይል “ቢወጣስ የት ይኬዳል?”
✧✧✧

ሴትዮዋ ጤፍ አስፈጭተው በመመለስ ላይ ናቸው። ተሸካሚው ከፊት ከፊት እየሄደ ቤታቸውን በውል በወለማወቁ ፣ “ቤትዎ በየት በኩል ነው?” ሲል አቅጣጫ ይጠይቃቸዋል።

ሴትየዋ ለፀብ እንደተዘጋጀ ወገባቸውን ይዘው፦
“ምን አልክ? ቤቴን ነው የጠየኸኝ? እንዴት ያለኸው ነህ? የአንድ ሺ አምስት መቶ ብር ጤፍ እቤት ይቀመጣል? ቀጥታ ወደባንክ! ከዛ እየተቀነሰ ነው የሚቦካው”
✧✧✧

አባወራው ቤተሰቡን መመገብ ተስኖታል። ስለዚህ ያገኙትን ለልጆቹ እያቃመሱ ከባለቤቱ ጋር ጦም ማደር ግድ ሆነ። በይበልጥ ሚስቱ እጅግ ተጎሳውላለችና ቤተሰቡ ለጎረቤት አፍ እንደተጋለጠ አባወራው ጠርጥሯል። ስለዚህ አንድ ዘዴ ዘይዶ ጠዋት ሽማግሌ ሰበሰበ፦

“ምንድነው ችግሩ?” አሉ ሽማግሌዎች።

“ይኸው አንደምታዩት ነው። ብዪ እላለሁ፣ ብዪ እላለሁ…” አለ አሉ።

ሚስት አልተማከረች ኖሮ “የታል የሚበላው?” ብትል

“ሳገኝ አልኩሽ’ንጂ” አለ አሉ።
✧✧✧

አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ፣ በህብረተሰቡ የኑሮ ውድነት ደረጃ ላይ የአሰሳ ጥናት እያካሄደ ነው አሉ። ጥናት አድራጊው ወደ አንድ ሊስትሮ ጠጋ ብሎ አንዳንድ የመግባቢያ ጥያቄዎችን ካቀረበ በኋላ ፦

“እስኪ አሁን ደግሞ ወደ ቀን ወጪህ እንግባ”

“እሺ”

“ጠዋት ቁርስህን ምን ትበላለህ?”

“ሻይ በዳቦ”

“ምሳህንስ?”

“ባይ በዳቦ”

ጥናት አጥኚው፣ ልጁ በደሰቦና በሻይ ከዋለ እራቱን አጠራቅሞ በደንብ ሊበላ ነው ብሎ “እሺ ማሙሽዬ እራትህንስ?” ቢለው ልጁ ድንግጥ እያለ፦

“በልቶ ለመተኛት?!” ሲል መልሶ ጠየቀው…።
✧✧✧

"ቀልድ የማያውቁ ቀልዶች"
ዓለማየሁ ገላጋይ
"ኢህአዴግን እከሳለሁ" የወግ ስብስብ መጽሐፍ የተቀነጨበ

እሑድ 28 ፌብሩዋሪ 2016

የ“ሸኖ ቤት ሃሳቦች”

‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬የ“ሸኖ ቤት ሃሳቦች”
(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)

‪‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬
የ“ሸኖ ቤት ሃሳቦች” የማንበብ ሱስ የተጠናወተኝ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ነበር፡፡ በርግጥ ብዙዎቹ ሃሳቦች በጨዋ ቋንቋ “ፀያፍ” ተብለው የሚነገሩ ቢሆንም ብሶትና ምክርን በጨዋ ገለፃ የሚቀርቡ ሃሳቦችም አይታጡም፡፡ ያም ሆኖ ሕዝብ የሚጠቀምባቸው መፀዳጃ ቤቶች ስገባ በግድግዳው ላይ የተጻፉ ጽሑፎችን ማንበብ ያዝናናኛል፡፡

ሸኖ ቤትን ለመውደድ የፎክሎር ተማሪ መሆን አይጠይቅም፡፡ ከማይረቡ መፅሐፍት የተሻለ ምልከታን እና ሂዩመርን በሸኖ ቤት ሃሳቦች መቃረሜ በራሱ ለመፀዳዳት የማባክነውን ጊዜ የሚክስ ቁምነገር አላጣበትምና፡፡

“የዘርሲዎች ፍቅር” የተሰኘው ልቦለድ መፅሃፍ ላይ አንድ ገፀባሕርይ አስታውሳለሁ፡፡ በተለይ መፀዳጃ ቤት ስገባ ብዙ ጊዜ ትዝ ይለኛል፡፡ (አብሮኝ ይገባል - - ብል ይቀላል፡፡) ይህ ሰው ቁምነገርን የሚቃርመው ከመፀዳጃ ቤት ነው፡፡ ግድግዳ ላይ የሚጻፍ ግራፊቲ አልነበረም የሚያነበው፡፡ ሰዎች “ካካቸውን” የጠረጉበትን ወረቀት ሰብስቦ ኪሱ በመክተት እና በማንበብ ነበር፡፡

እነዚህ የግድግዳ ላይ ጽሁፎች ስለምንስ ይጻፋሉ? ግባቸው ምንድነው? ... ምክንያቱን እርሱት፡፡ ከየት መጡ የሚለው ምርምር አያሳስበኝም፡፡ ባለቤት አልባነታቸው በራሱ በቂ ምክንያት ነው፡፡ ምክንያት ከስም ይጀምራልና፡፡ ማንነቱን ለማወጅ የመፀዳዳት ባህሉን አደባባይ ላይ ከሚፈጣጥም ሰው ምንም አልጠብቅም፡፡ ማንነቱን በመጸዳጃ ቤት ግድግዳ ላይ የሚያሰፍር ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ግን ታዳሚ ነኝ፡፡ (እስቲ ዛሬ የተመረጡ ትውስታዎቼን በሹካ ጨልፌ ላካፍላችሁ፡፡)

ለመጀመሪያ ጊዜ ካነበብኳቸው ውስጥ የሚመደብ የመፀዳጃ ቤት ሃሳብ እንዲህ የሚል ነበር፡-

“God is dead!” -Nietzshce
“Nietzshce is dead!” -God

ያኔ ይህን ሳነብ ያልገባኝ ብዙ ነገር ነበር፡፡ በርግጥ ኒቼ “እግዚአብሔር ሞቷል” በሚለው ግንዛቤው ዛሬም ድረስ (ሞቶም) ያወዛግባል፡፡ በሕይወት በነበረበት ጊዜ “እግዚአብሔር ሞቷል ፤ ሰዎችም ነፃ ወጥተዋል...” እያለ መስበኩን የተረዳሁትም ከጥቅሱ በኋላ ነበር፡፡ አመታት አልፈው፡፡ የኒቼን ሞት ጠብቆ እግዚአብሔር እንዲህ ማለቱን ግን መፀዳጃ ቤት እንደ ትንቢት ቀድሞ አሳውቆኛል፡፡ ጥበብ ከጲላጦስ መፅሐፍ ላይ ይህን ጥቅስ ሳነበው አልደነቀኝም፡፡ ጥቅሱን ሲያስታውሰኝ ግን የሆነ ነገር ግን ሸቶኝ ነበር፡፡ ያም ጠረን፣ ይህን አባባል ያነበብኩበት መፀዳጃ ቤት አጉል ጠረን ነበር፡፡

በአንድ ኮሌጅ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ያነበብኩት ደግሞ እንዲህ የሚል መልዕክት ግድግዳው ላይ ተፅፎ አነበብኩ፡- “ምን ግድግዳው ላይ ታፈጣለህ!? አርፈህ አትፀዳዳም!?” ሆሆሆ... ሰዉ ጨምሯል!

በሌላ ዩኒቨርስቲ መፀዳጃ ቤት ውስጥም እንዲህ አይነት ትዕዛዝ አጋጥሞኝ እንደነበር አልረሳውም፡፡ በደቃቅ ጽሑፍ የተጻፈ መልዕክት ከመጸዳጃው በር ላይ ሰፍሮ አየሁና ከቅምጤ በመጠኑ ብድግ ብዬ ላነብ ስሞክር ያገኘሁት መልዕክት አስደንግጦ “የሚያስቀምጥ” ነበር፡፡ሃሳቡ እንዲህ የሚል ነበር፡- “ሰው ማለት አንተ ነህ፡፡ አሁን ወደነበርክበት ተመልሰህ አርፈህ እራ! ” የሚል ትዕዛዝ ፡፡

የሸኖ ቤት ግድግዳ ላይ ከተፃፉ ሃሳቦች ሌላው የማርከኝ እንዲህ የሚል ነው ፡-

“ቺክህን ጥሩ ነገሮች እንዴት እንደምታሳያት በማሰብ አትጨናነቅ፡፡ አሁን እየጣልክ ያለውን እንቁላል ግን ጠብሰህ እንዳታበላት አደራ! ስትጨርስ ውሃ ድፋበትና ከሌሎች እይታ ሰውረው!”

የሸኖ ቤት ግድግዳ ሃሳቦች አንዳንዴም ፍልስፍና ይቃጣቸዋል፡፡ በአንድ የሕዝብ መፀዳጃ ቤት ውስጥ ያነበብኩትሃሳብ ለዚሁ ምስክር ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-

[“መኖር ማለት፣ በምታባክነው ጊዜ የምታጣው ብኩንነት ነው፡፡ ለመኖር ስትል ከምታባክናቸው ሰዓታት ትልቁን ቦታ የሚይዘው ምን እንደሆነ ታውቃለህ?”

“አውቃለሁ” ካልክ ተሳስተሃል! በዚህ ሰዓት ማራት አልነበረብህም!!”]

ትውስታዬን ተደብቄ በተጠቀምኩበት የሴቶች መጸዳጃ ቤት ግድግዳ ላይ ባነበብኩት ልቋጭ፡፡

“በወንዶች ከሚነገሩ ብ-ዙ ውሸቶች መሃከል የማላምነው “ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም” የሚሉትን ብቻ ነው፡፡”

ሐሙስ 25 ፌብሩዋሪ 2016

አዳም… (ኄኖክ ሥጦታው ናሁሰናይ)

አዳም…
(ኄኖክ ሥጦታው ናሁሰናይ)


"ጥፋት"፣ "ታዛዥነት" …
ቢጋጩ ከድንጋይ
                "ተቃጠልኩኝ" አትበል…
                 እሳት ፈጥረው ብታይ።
*
ፍላጎቱን ሳይኖር፣ "ሕግን" ያከበረ፣
በተጻፈው እንጂ፣ ራሱን መች ኖረ?!
*
አዳም ሰው አትስማ፣ ከትዛዝ ላይወጣ
"ሕግ ጣሰ" ይበል፤ "በበላው ተቀጣ"
የኖርከውን ሳይኖር፣ ያስብ ምን እንዳጣ!
*
አዳም ተለመነኝ፤ አንተ ኑረህ ብላ…፣ ቅጣት ምናባቱ

ያልበላው ይታዘዝ… ሕግን ማክበር "መብቱ…"
*
አዳም በአፈርህ፦
ብላ… ደግመህ ብላ… የሕግ አጥር ይፍረስ
"አምላክ ይጠራኻል"፤ ክልከላውን ስትጥስ!

ማክሰኞ 23 ፌብሩዋሪ 2016

በቮልስ ያጉረመረምንበት ሰርግ ትዝታ

ይህ ትዝታ ይደንቀኛል። ጋራጅ የተዋወቅኩት ሰው ሰርግ ላይ መላው የቮልስ ባሉካዎች በአጃቢነት ተጋብዘን ነበር። አጃቢ መኪኖች በጠቅላላ ቮልስ ዋገን ናቸው። እውነት ለመናገር በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ሾልሶች አንድም የቀረ አይመስልም።

ሰርጉን ለማሳመር  አጃቢ የሆኑት ቮልሶች ራሳቸው በመካኒክ ታጅበው ነበር። በቮልስ የሚታጀብ ሰርግ ያለመካኒክ የማይታሰብ ነበር። (መካኒኮቹ መንገድ ላይ ለሚበላሽ መኪና ፈጣን ጥገና እያደረጉ ጉዞው ቀጠለ።)

ታዲያ ያኔ መናፈሻ ውስጥ የነበረ አሙቁልኝ አዝማሪ እንዲህ ብሎ ፈተለ፤

"ጉርምርሜ ና ጉርምርሜ
ያሆ በሌ፣ ያሆ በሌ ፣ ጉርምርምርምርም…
ባባው ቮልስዬ ፣
ያሆ ቮልስዬ፣ ያሆ ቮልስዬ… ጉርምርምርምርምርም… (ተቀብለን አስተጋባን)
አዝማሪው ቀጠለ፦

ሚስቱን  ያገኘው…
ያሆ በሌ…  ያሆ በሌ… ጉርምርምርምርምርም…
ጉርምርሜ በግሩ ሲያዘግም!"

(ይህኔ የምር አጉረመረምን)

ሰኞ 22 ፌብሩዋሪ 2016

የኄኖክ እልፍኝ HENOK'S PAD: hamot የግጥሞች-ስብስብ-በኄኖክ ስጦታው [PDF]

የኄኖክ እልፍኝ HENOK'S PAD: hamot የግጥሞች-ስብስብ-በኄኖክ ስጦታው [PDF]: hamot የግጥሞች-ስብስብ-በኄኖክ ስጦታው[PDF]

ሠአት ሠሪው

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)

ሠአት ሠሪው ደጃፍ ላይ ቆሜያለሁ። ከውጭ ሆኖ ለሚመለከት ሰው ምንም የሚማርክ ውበት ላትመለከት ይችላል። የደጁን መስታወት ታክኮ የቆመው መደርደሪያ ያገለገሉ ሰዓታት ማረፊያ ሁነዋል። የተበላሹ፣ የተጠገኑ፣ የማይጠገኑ፣ ያልተጠገኑ፣… ሠአቶች ተሞልቷል። እኔ እራሴ ሁሌ የማያቸው ሰዓቶች እዚህ ምን እንደሚሰሩ አይገባኝም። አሰሪዎቹ ቢወስዷቸውና ሰዓት ሠሪው ያገልግሎቱን ቢያገኝ መምረጤን ግን አልሸሽግህም። 

መስታወቱ ላይ ሶስት ጥቅሶች አሉ። በእጅ የተሞነጫጨሩና ለንባብ የማይማርኩ ቢሆኑም፣ ከማንበብ የሚያግተኝ ነገር የለምና በታላቅ መስህብ ስሜት ተውጬ ተጠግቼ አነበብኳቸው፦

የመጀመሪያው እንዲህ ይላል፦

" ተመልከት ፤ እኔ ማንን የምጠብቅ ይመስልሃል? ጊዜ ከሌለህ እዚህ ምድር ላይ ሌላ ምንም ነገር አትጠብቅ!"

በለው ብሶት!! ሁለተኛውን አነበብኩት። 

"ሳምንቱን ሙሉ ክፍት ነው፤ የዕረፍት ቀናትን ጨምሮ" ይላል ።

አባባሉ የቁጥር መጭበርበር ያለበት ቢመስለኝም የሰዓት ሠሪው ቤት እዚሁ መሆኑ ታስቦ የተፃፈ መሆኑንና ደንበኞች ይህን ሊገነዘቡ የተቀመጠ (የቤት ስራ) መሆኑንአምኜ ወደሶስተኛው ጥቅስ አመራሁ።

ሶስተኛው ግን ለራሴም ገራሚ ነበር ፦

"ልክ እንደ ሰዓት የሚበላሽና እንደ ሰዓት ጠጋኝ የሚሰራ ሰዓት የለም!"

እናም ፣ እንዲህ እያልኩ ወደውስጥ ገባሁ፦

"የዛሬው ጥሩ ይመስላል፤ መቼስ እስከዛሬ ከለጠፍኳቸው ይሻላል!"

እሑድ 21 ፌብሩዋሪ 2016

☆እግረ-መንገድ

(ኄኖክ ስጦታው ናኁሰናይ)
‪‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬

የምሰማው ሁሉ አልጥምህ ብሎኛል፡፡ የሬዲዮኑን ጣቢያ እየቀያየርኩ የሚጥመኝ ፕሮግራም ፍለጋ ጀመርኩ፡፡ ዘፋኙ ሁሉ ዘማሪ ሆኗልና! . . . ሬዲዮኑን ዘጋሁትና ቲቪ ከፈትኩ፡፡

በቲቪ፣ የአንድ አዲስ ምርት አምራች ድርጅት ማስታወቂያ እየተላለፈ ነበር፡፡ አስተዋዋቂው፣ ድምፁን ከሌላ ሰው የተዋሰው ይመስላል፡፡ በግነት በተዋቀረ ድምጽ እንዲህ እያለ ነበር፡-

“ልብ ይበሉ! ምርታችን በአይቱ አዲስ እና አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ ነው!!”

በለው ውሸት!

“አዲስ እና አስተማማኝ” ማለት ምን እንደሆነ የገባቸው አልመሰለኝም፡፡ አዲስ ከሆነ አስተማማኝነቱ ገና አልተረጋገጠም ፤ የተረጋገጠ ለመሆን ከዚህ ቀደም የሚታወቅ መሆን አለበት፡፡ ይህን እንኳን አያስቡም፡፡

ተጨማሪ ውሸት ሽሽት ቲቪውን ዘጋሁትና ከቤት ወጣሁ፡፡ ትንሽ በእግሬ ዞር ዞር ብዬ ብመለስ እንደሚሻል በማሰብ ነበር አወጣጤ፡፡

ማምሻ ግሮሰሪ የማውቀው አንድ ሰው ከሩቁ “እንኳን አደረሰህ!” ሲለኝ፡፡ “እንኳን!” አልኩት ከሩቁ፡፡

“እንኳን ምን? ” አለና መልሶ ጠየቀኝ፡፡

“እንኳን ብቻ!” ብዬ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡

“አይ አንቺ ሰው ፤ በጊዜ አግለሻል መሰል...” ሲል ከጀርባ ይሰማኛል፡፡ ሰው ግን በዓል ሲመጣ ብቻ ነው እንዴ “መድረሴ” ትዝ የሚለው?

መንገዱ ጭር ብሏል፡፡ አንድ ሰው ብቻ ከሩቅ ይታየኛል፡፡ የሆነ ነገር እያወራ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ እየቀረብኩት ስሄድ ምን እያለ እንደሆነ ተሰማኝ፡፡
“የበግ ቆዳ ያለው? ” እያለ ነበር፡፡

አጠገቤ ሲደርስ ወደኔ እያየ ጮክ ብሎ ፤ ”የበግ ቆዳ ያለው!” አለ፡፡ ዝም ብዬው አለፍኩ፡፡ “ሰዉ ዛሬ ምን ነክቶታል?! ” ስል አሰብኩ፡፡ እውነት የበግ ቆዳ ቢኖረኝ መንገድ ለመንገድ ይዤው የምዞር መስሎት ይሆን?!

ሳላውቀው ብዙ ርቀት በእግሬ ተጓዝኩ፡፡ .... አምስት ሴቶች ከሩቅ ይታዩኛል፡፡ ታክሲ እየጠበቁ መሆን አለበት፡፡ እየቀረብኳቸው ስሄድ አለባበሳቸውን ለየሁት፡፡ አራቱ ሴቶች ነጭ የአገር ባሕል ልብስ ለብሰሰዋል፡፡ አንዷ ግን በጅንስ ተወጣጥራለች፡፡ ፀሐዩን ሽሽት በዣንጥላ አናቷን ከልላለች ፡፡ ተስፋ ቆርጣ መሆን አለበት ከመሃከላች ወጥታ በእግሯ መጓዝ ስትጀምር አየኋት፡፡

ነጭ የለበሱት አራቱ ካሉበት አልተንቀሳቀሱም፡፡ በአጠገባቸው ሳልፍ ከመሃከላቸው አንዷ፡- “ወንድም ፤ ሰዓት ይዘሃል? ” ስትል ተሰማኝ፡፡

“አዎ!” አልኳትና መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ ልጅቱ ስንት ሰዓት እንደሆነ እንድነግራት እየጠበቀች ነበር መሰለኝ፡፡ ግን የጠቀየቀችኝ ሰዓት መያዜን ነው፡፡ እርሱንም “አዎ” ብያታለሁ፡፡

ዣንጥላ የያዘችው ሴት ከፊት ከፊቴ ስትሄድ አየሁ፡፡ የሚገርም ጀርባ አላት፡፡ እውነት የተፈጥሮ ከሆነ መቀመጫዋ ያምራል፡፡ (ሴቱ እንደ ውስጥ ሱሪ የሚጠለቅ አርቴፊሻል መቀመጫ መጠቀም ጀምረዋል አሉ! ) ይሁን ፡፡ መጠቀማቸው ክፋት የለውም፡፡ የሚቆረቁር ወንበር ላይ ሲቀመጡ እንዳይቆረቁራቸው ከሆነ መልካም ነው፡፡ (ምቾት በሌለው ወንበር ላይ ረጅም ሰዓታት ለሚቀመጡ ወንዶችም ይህ ዘዴ ይጠቅማል መሰል፡፡ )

ሰውነቷ ያምራል፡፡ ዕድሜዋን ለመገመት ሞከርኩ፡፡ በጥቂት ዓመታት ብትበልጠኝ ነው፡፡ “ታላቄ” እንደሆነች ሳስብ አንድ አባባል ትዝ አለኝ፡፡ “ከእያንዳንዷ ታላቅ ሴት ጀርባ መቀመጫዋን የሚያይ ወንድ አይጠፋም!” ሆሆሆ . . . ለጀመሪያ ጊዜ ፈገግ አልኩ፡፡
‪‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬‬
“ልመለስ!? ወይስ መንገዴን ልቀጥል!?” . . . ስል አመነታሁ፡፡ ሉፒዶ (ሽፍደት) ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ይህ ተፈጥሮ ግን መገለጫው ብዙ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው እንደየምልከታው ግንዛቤ የሽፍደት አካል መረጣውም ይለያል፡፡

የሰውነት አካላት ሁሉ የዚህ ምልከታ ውጤት ናቸው፡፡ በርግጥ መቀመጫዋ የሚያምር ሴት አይቶ “አሪፍ መቀመጫ አላት” ያለ ሁሉ ይህቺን ሴት ተመኛቷታል ማለት አይደለም፡፡ ማድነቅም ሌላው ተፈጥሮ ነውና፡፡ ከፊቴ ያለችውም ሴት ለእኔ እንደዚሁ ናት፡፡ ያየሁትን ማራኪ ሰውነት አለማድነቅ እንደማልችለው ሁሉ፣ ያደነቅኩትን ማራኪ ሰውነት ሁሉም አልመኝም፡፡ ይህም ተፈጥሮአዊ ነው!

ጥቂት መንገድ የመግፋት ሃሳብ አጋደለና መጓዜን ቀጠልኩ፡፡ ከፊቴ ግን ታላቅ ውሳኔ የሚሻ ነገር እየተውረገረገ ነው፡፡ ከቤቴ የወጣሁት ዳሌ ለመከተል አልነበረም፡፡ አሁን ግን ባጋጣሚ ዳሌ ተከታይ ከመሆንም አልፌ አድናቆት ገላጭ አባባል ቀማሪም እየሆንኩ ነው፡፡ ʿይህን ታላቅ ዳሌ እስከምን ድረስ ነው የምከተለው?! ከዚህ በላይ ከመከተል፣ ዳሌዋን ስካን ማድረግ ይቀላል፡፡ʾ ስል አሰብኩ፡፡

በነገራችን ላይ ፤ ከኋላ መሆን መከተል ነው ያለው ማነው?! (ከእረኛን ተመልከቱ፡፡ ከብቶቹን የሚያግደው ከፊት ከፊታቸው እየሄደ አይደለም፡፡ በጉዞ ላይ ያሉ ከብቶች ካያችሁ ፣ ከኋላቸው እረኛ መኖሩን አትዘንጉ) በዚህ ምሳሌ ብቻ ተገፋፍቼ ለዚህ ታላቅ ዳሌ እረኛ የሆንኩት እንዳይመስልብኝ ስል ርምጃዬን አፍጥኜ አለፍኳት፡፡ አሁን ተራው የርሷ ነው፡፡

ሴቶች ግን . . . ወንድን ከጀርባው ሲመለከቱት ምኑን ይሆን ቀድመው የሚያት?! (ዋሌቱ እንደማይሆን ግን ርግጠኛ ነኝ፡፡)

አልፌያት ጥቂት እንደተራመድኩ ፡- “ይቅርታ፣ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ እችላለሁ?” የሚል ድምጽ ሰማሁ፡፡ እኔን እንደሆነ ርግጠኛ ሆኜ ፊቴን አዞርኩና ልናገር ስል አንድ ነገር አገደኝ፡፡ ዳሌ ዳሌዋን ሳይ ያላየሁት ሌላ ሰው የስልክ እንጨት ፖል ተደግፎ ቆሞ ነበር ለካ፡፡ እሱን ነበር የጠየቀችው፡፡ እምም . . . ተረፈች፡፡ እንኳንም እኔን አልጠየቀች!

በጣም ከሚያናድዱኝ ጥያቄዎች አንዱ ይህ ነው፡፡ “አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ?” ብሎ መጠየቅ በራሱ አንድ ጥያቄ ነው፡፡ እንዲህ ብለው የሚጀምሩ ሰዎች ሌላም ችግር አለባቸው፡፡ ያስፈቀዱት አንድ ጥያቄ ለመጠየቅ ሆኖ ሳለ መልሱን ተከትለው ተከታታይ ጥያቄ ማዥጎድጎዳቸው ነው፡፡

የመጀመሪያውን ፈገግታ የፈጠረው ስሜት በምን ፍጥነት ጥሎኝ እንደጠፋ እንጃ፡፡ ብሽቅ!

መቼስ በበዓል ቀን ታክሲ ከመጠበቅ ታክሲ መሸከም ይቀላል፡፡አውቶቢስ ፊርማታ ሳገኛ ቆምኩ፡፡ በእግሬ የመጣሁትን መንገድ በእግሬ የመመለስ አቅም አልነበረኝም፡፡ ታክሲ ቢጠፋ እንኳን ባስ እንደማላጣ ርግጠኛ ነበርኩ፡፡

(ሞራል)፡-
ጥቂት ሰዎች የባሷን መምጫ በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡ እኔም እነርሱ ወደሚያዩበት አቅጣጫ አፍጥጫለሁ፡፡ አልፌያት የመጣኋት ቆንጂዛ አልፋኝ ከሄደች ቆይታለች ፡፡ (ማሳለፍ ትልቅ ችሎታ ነው፡፡ ማለፍም፡፡) አለማለፍ ግን ደካማነት፡፡ አለማድነቅ ስሜትን ለሌላው አለማሳወቅ ነው፡፡ ለራስ የተሰማን የአድናቆት ስሜት መሸሸግም ያው አልሸሹም ዞር አሉ ነገር፡፡ የአድናቆት ስሜትን ለሌላው ለማሳወቅ ሲባል ግን እንደኔው ሁሉ ተረጋግተው የሚጓዙትን ሰዎች መልከፍ ግን በነፃው መንገድ ላይ ነፃነትን ከመንፈግ አይተናነስም!!

አድናቆት በሰፊ ቦታ ጠባብነትን ማግዘፍ ሳይሆን ሌላ ስፋትን መጨመር ነው ብዬ አምናለሁና፡፡ ስለዚህም በማለፍ አምናለሁ፡፡ በማሳለፈፍም፡፡

ማሳሰቢያ፡- የእግረ መንገድ ወግ እንደ መዋቅር የተጠቀምኩበት መንገድ፣ ቅርፅ እንጂ እውነተኛ ገጠመኝ አይደለም፡፡ ምልከታን የመግለጫ አንድ መንገድ እንጂ፡፡