ረቡዕ 24 ጁላይ 2013

የኔዋ ምርጥ ቮልስ /ዩሴን ቦልት/ በ-ኄኖክ ስጦታው


ከዚህ ቀደም በዚህቹ ጉደኛ ቮልስ መኪናዬ ዙሪያ በጥቂቱ አውርቼላችሁ ነበር፡፡፡ እስቲ ዛሬ ደግሞ ጥቂት ትውስታዎቼን ላካፍላችሁ፡፡

ያው መቼስ የቮልስ ባሉካ የሆንኩ ሰሞን የወረት ነገር በጥቂቱም ቢሆን ደባብሶኝ ነበር፡፡ መኪናዋን ማሽከርከር እንደጀመርኩ ወዳጅ ዘመዶቼን ሁሉ በመኪናዋ መስኮት ነበር ሰላም የምለው፡፡ መሬት የምረግጠው ከቤት ስወጣና እቤት ስገባ ነው፡፡ ቁርስ፣ ምሳ ፣እራት የምመገበው እዚህቹ መኪና ውስጥ ነበር፡፡ ጥቂት ጓደኞቼ በጣም ስናፍቃቸው ይደውሉና “ኧረ በጣም ናፍቀኸናል፤ መቼ ነው በአካል የምናገኝህ?” ይሉ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በአካል እንደማያገኙኝ ቁርጡን ሲያውቁ ይህን ውሳኔ አስተላለፉ፡፡“በተገኘበት ቦታ ከመኪናው ላይ ተጎትቶ እንዲወርድ!!!” 

ደግነቱ እነሱ ጎትተው እኔን ከማውረዳቸው በፊት የፍሪሲዮን ካቦ ተበጠሰና ቮልሴን እያስጎተትኩ ጋራጅ ገባሁ፡፡ ያኔ በአካል ጋራጅ ድረስ መጥተው አገኙኝ፡፡ መኪናዋ ተሰርታ እስክታልቅ ድረስ ከጋራጅ አልወጣም ብዬ ነበር፡፡ ሜካኒኩ “ሲያልቅ እንጠራሀለን፡፡ በቃ፣ ሂድ” በማለቱና በእነሱ ጉትጎታ እጅግ አዝኜ ወጣሁ፡፡ መኪናዬ ተጠግና ስትወጣ በድጋሚ ጠፋሁባቸው ፡፡ 

ለቮልሴ የዘመኑን ሲዲ ማጫወቻ ያስገጠምኩላት ሰሞን ጓደኞቼ ብቻ ሳይሆኑ አገርም “ጉድ!” አለ፡፡ ጥቂቶች “ለቮልሱ ሲዲ ማጫወቻ ገጠመለት” አሉ፡፡ ብዙዎቹ ደግሞ “ለሲዲ ማጫወቻው ቮልስ ገጠመለት፡፡”

ከሁሉም የሚገርመኝ አንድ ሰሞን ወንድሜ ይነዳት ነበር፡፡ ከግቢ ውስጥ አውጥቶ መቶ ሜትር ያህል ያሽከረክርና የዋናው አስፓልት መንገድ ላይ አቁሞ በታክሲ ይንቀሳቀስ በነበረበት ሰሞን ይህቺው ቮልስ ቅፅል ስም ወጥቶላት ጠበቀኝ፡፡ እሱንም የነገረኝ ወንደሜ ነው፡፡ 

“እንዴት ናት ቮልሴ?” ብዬ ስጠይቀው፡-
“ምን እዚህ ሰፈር መች ያስነዱና!?? ቁጭ ብለው ቅፅል ስም መስጠት ነው ስራቸው፡፡ መኪናዋን ማን እንዳሏት አልሰማህም!? ” 
“ማን አሏት!?”
“ዩሴን ቦልት” 
እንደዚህ ጊዜ ስቄ አላውቅም፡፡ ወንድሜ መቶ ሜትር እየነዳ በመቶ ሜትር ጃማይካዊ ሯጭ ስም አስጠርቶልኝ አረፈው፡፡  

ይችው መኪና አንድ ከባድ ችግር አለባት፡፡ ጭንቀት አትችልም፡፡ ልብ ድካም ያለባት ይመስለኛል፡፡ በቃ፣ የተጨናነቀ አደባባይ መሀል ገባታ ቀጥ ነው! ጭንቀቷ ሌሎችን መኪና ይበልጥ እስኪያጨናንቅ ድረስ የአደባባዩን ውጥረቱን ታንረዋለች፡፡ እንደዚህ ሲሆን ከሶስት ያላነሱ ትራፊኮች ወደኔ ይመጣሉ፡፡ ያው ከቆመች መምጣታቸው እንደማይቀር ስለማውቅ የሞተር ቀሚሷን/ኮፈኗን/ ከፍቼ “ፖምፔታዋን/ ፊውል ፓምፕ” በውሃ እያቀዘቀዝኩ እጠብቃቸዋለሁ፡፡

“ከሥራ ክፉ ኩርኩር ግፉ” እንዲሉ . . . በጣም ጥቂት ሰው በቀር “መሀል አደባባይ ላይ ቮልስ ብንገፋ ስማችን ይጠፋል” ብለው ስለሚያስቡ ትራፊክ ፖሊስ እስኪመጣ ድረስ ከመጠበቅ በቀር አማራጭ እንደሌለኝ በሹፍርና አጭር ዘመኔ የቀሰምኩት ጥበብ ነው፡፡ ቮልስ ለመግፋት ዝንባሌ ያላቸው ጥቂቶቹም ቢሆኑ ከገፉ በኋላ እጃቸውን ዘርግተው በተራዬ ብር ወደነሱ እንድገፋ ስለሚጠይቁ አይመቹኝም፡፡ትራፊኮቹ ግን ገንዘብ የሚጠይቁኝ ሞተር ሲጠፋ ሳይሆን እኔ ሳጠፋ ነው፡፡ ከእነሱ ብዙዎቹ፣ “የቮልስ ሹፌር የሆነው በጣም ቢቸግረው ነው” ብለው ስለሚያስቡ መክረው የሚለቁ ናቸው፡፡ /አቦ መካሪ ትራፊክ አትጡማ/

እንደምንም ከተጨናነቀው መንገድ በተራፊክ እያስገፋሁ ልክ ነፃ መንገድ ሳገኝ ሞተሩ በራሱ ጊዜ ተረክ ብሎ ይነሳል፡፡  
  
የገዛኋት ሰሞን ባትሪዋ የኋላ መቀመጫ ስር ነበር፡፡ የመቀመጫው ታች ጥምዝምዝ ሽቦዎች አሉ፡፡ ከእነሱ በላይ እንደ እንቅብ የሚመስል የደረቀና የሳር ባህርይ ባለው ግብዓት መቀመጫው ተደልድሎ ጨርቅ ለብሷል፡፡ ይሄ ጥምዝምዝ ሽቦ ከመቀመጥ ብዛት በመላላቱ ሰው ሲቀመጥበት ወደ ባትሪው ወርዶ ከ“ኔጋቲሽ” እና ከ“ፖዘቲቭ” አካሉ ጋር እየተነካካ “ማሳ” (እሳት) ይፈጥራል፡፡ ይህን “ጥበብ” ያወቅኩት በተግባር ነው፡፡ ሁለት ጓደኞቼን . . . አንዱን ከፊት ሌላውን ከኋላ ጭኜ ስዘውር ከኋላ የተቀመጠው ጋደኛዬ በተረብ መልክ እንዲህ አለ፡-

“መቀመጫው በጣም ይሞቃል፡፡ ሃሃሃ . . . "ኤሲ" አስገጠምክለት እንዴ!?”

“ሞተሩ ከኋላ ስለሆነ ሙቀት ወደውስጥ ገብቶ ይሆናል፡፡” አልኩት በባለሙያ አገላለፅ ልበ ሙሉ ሆኜ፡፡

“አይመስለኝም” አለ እየትቁነጠነጠ፡፡ “ወደዳር አድርገውና እንየው፡፡ መቀመጥ አልቻልኩም . . .” እያለ ሳለ መኪናዋ ጨሰች፡፡ የኋላ በር እንኳን አልኖራት፡፡ ተፈጥፍጦ አንድ ነገር ይሆን ነበር ፡፡ድንጋጤ አስፈንጥሮ እላያችን ላይ ጣለው፡፡ እንዴት እንዳቆምን ትዝ አይለኝም፡፡ ጥቂት ሮጥ ሮጥ ብለንም ነበር፡፡ የሆኑ ሰዎች ለዚሁ ጉዳይ ያጠራቀሙት የሚመስል እጅግ የቆሸሸ ውሃ እያመጡ ወደውስጥ ይረጩ ጀመር፡፡ ብቻ እሳቱ "ወደሌሎች" ሳይዛመድ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ 

ታዲያ ያኔ (መኪናዋ እየተቃጠለች ሳለ) እኔ ባልለውም ዛሬ ድረስ እንዲህ ብሎ ነበር ይባላል፡፡ ውሃ እየደፉ እሳቱን ሊያጠፉ የሚረባረቡትን ሰዎች፡-

“ተውዋት! ትቃጠል! እኔንም እንዲህ ነበር ያቃጠለችኝ!!!”

ሰኞ 22 ጁላይ 2013

ውዝግብግብ …."ያላዘነው ውሻ እኔ ነበርኩ" በ-ኄኖክ ስጦታው





ዛሬ ደግሞ አንድ ወጣት ተሰቅሎ ሞተ፡፡ ወጪ ወራጁ ደረቱን በጆቹ ጠፍሮ መንሾካሾክና መረጃ መለዋወጥ ጀመረ፡፡ ሁሌም በሚሞት ሰው ላይ እንዲህ አይነት ነገር ይንፀባረቃል፡፡

“ቅድም ሰላም ብሎኝ ነበር ያለፈው፤ የሚሞት አይመስልም ነበርኮ” ትላለች አንዷ ለሌላዋ፡፡

 “ትላንት ከኛ ጋር ነበር ያመሸው፤ ምንም የተለየ ነገር አይታይበትም ነበር” ይላል ሌላው፡፡

“ሌሊት ውሻ ሲያላዝን ሰምቼ ደግሞ ማንን ሊገፋ ነው ይህ ሟርተኛ እያልኩ ሳስብ እንቅልፍ ባይኔ ሳይዞር ነጋ፡፡” አንዲት እናት ከጎናቸው ላሉ እኩያቸው ሲናገሩ ሰማሁ፡፡

ቀባሪዬ፣ እኔ ነኝ ውሻው፡፡ ሌሊት እንቅልፍ እንቢ ሲለኝ አላዘንኩ፡፡ እንደውሾቼ ጮህኩ፡፡ የሞት ጠረን ሸቶኝ ግን አልነበረም፡፡ ታንቆ መሞት ለዚህች መንደር አዲስ አይደለም፡፡ የሚሞት ባይኖር እንኳን የሚረዳ አይጠፋም፡፡ የጥሩንባ ድምፅና የውሻ ማላዘንን በሚፈራ ማህበረሰብ “የሞት መልእክተኛ” ተብዬ ለመፈረጅ ጊዜ አልፈጀብኝም፡፡ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ብቻ ውሻው እኔ እንደነበርኩ ሁሉም ነዋሪ አወቀ፡፡ ምሽት ላይ ከታጣቂዎች ጋር  ተፋጠጥኩ፡፡

“ሌሊት ስትጮህ ታይተሃል!” አለኝ አንዱ መሳሪያ ታጣቂ፡፡

“እና?”

“ምን “እና” ትላለህ? ለምን ሰላማዊ ሰውን ትረብሻለህ?” አፈጠጡብኝ፡፡

“እናንተ ለምን እኔን ትረብሻላችሁ?”

“ተነስ እንሂድ”

“አልነሳም!”

“መታሰር ትፈልጋለህ?” በሚያባብል ድምፀት ሌላው ተናገረ፡፡

“መታሰር ምንድነው?” መለስኩለት ጤነኛ እንዳልሆንኩ አንዴ ደምድመዋል፡፡ የትም ይዘውኝ ሊሄዱ እንደማይችሉ አውቃለሁ፡፡ ሊደበድቡኝ ይችላሉ፡፡ ሊያጠቁኝ አቅሙ አላቸው፡፡ ሰላማዊ ሰው ረብሼ ይሆናል፡፡ ለእኔ ግን ሰላማዊ ሰው በውሻ ድምፅ የሚረበሽ አይደለም፡፡ ቀድሞ እራሱን ባጉል እሳቤ የበጠበጠ ሰላማዊነቱ አይታየኝም፡፡

“አማኑኤል መግባት ትፈልጋለህ?” ብረት አንጋቹ ጠየቀኝ፡፡ የሱ ግንዛቤ አማኑኤልን ጥላቻ እዚህ የተቀመጥኩ መስሎት ይሆናል፡፡ ከዚህ የተሻለ ስፍራ ሊሆን ይችላል፡፡ ማገገሚያ አያስፈልገኝም፡፡ ግን ማየት ፈለኩ፡፡

“አዎ! አማኑኤል ውሰዱኝ!” ለመንኳቸው፡፡ ደጋግሜ ወተወትኳቸው፡፡ ማሰሪያ ገመዳቸው ተበጣጠሰ፡፡ አማኑኤልም ሊወስዱኝ አይችሉም፡፡ ታዲያ ለምን መጡ? ሊያስፈራሩኝ? ሊደበድቡኝ? እስኪሰለቹኝ ድረስ ኃይለ - ቃል ወረወሩብኝ፡፡ የማያደርጉትን ዛቱብኝ፡፡ ሰላማዊ ሰው ብረብሽ ከባድ እርምጃ እንደሚወሰድብኝ አስጠንቅቀው ነገሩኝ፡፡ በእነርሱ ዘንድ እብድ መሆኔ አስንቆኛል፡፡ በእኔ ዘንድ ሰላማዊ ሰው መሆናቸው አስንቋቸዋል፡፡ በመሰሎቻቸው ላይ የሚያደርሱት ቅጥቀጣ ለካስ እብድ መሆናቸውን ስላላመኑላቸው ነው! እብድ መሆኔን ማመናቸው ነፍስ ባጠፋም እንዳይፈርዱብኝ ያደርጋቸዋል፡፡ ምክንያቱም እብድ ነኛ! ህጉም ቢሆን ከጎኔ የሚቆመው ሰዎች ሰብአዊነቴን ስለሚዳፈሩ ሳይሆን ወንጀለኛ መሆን ስችል ብቻ ነው፡፡

 የሰላማዊነት ሎጅክ በነፍጥ አንጋች እና በኔ መካከል ልዩነት አለው፡፡ ዛሬ ባልጮህ ሰው አልበጠብጥም፡፡ ፍርሃታቸውን አልቆሰቁስም፡፡ አስተሳሰባቸው የወለደው ፍራቻ ይበቃቸዋል፡፡ ውሻ በጮኸ ቁጥር ግን ያስቡኛል፡፡ በኔ ላይ በሚጥሉት ሽርደዳ ሰላሜን ቢዳፈሩም እንቅልፍ አጥተው የሚፈሩትን ሞት አላስታውሳቸውም፡፡ ይህን ሳደርግላቸው ግን በመጮሄ የማገኘውን ሰላምን እየሰዋሁላቸው መሆኑን ይረዱት፡፡ እነሱም ይህ ውለታዬን አንድ ቀን ለመሬት ይከፍሉልኛል፡፡ ይሞታሉና!

አሽ-ሙጥ በ Henok Sitotaw

ቅዳሜ 20 ጁላይ 2013

ውዝግብግብ …. ዘዶሮ ማነቂያ /ከሌላኛው ምዕራፍ የተቀነጨበ/ --- በ-ኄኖክ ስጦታው




ውሾቼን ገደሏቸው! መርዝ የተቀባ ስጋ ሰጥተው ውሾቼን ገደሏቸው፡፡

ቀባሪዬ፣ መግደል እንጀራ በሆነበት አገር እንደመኖር ውስብስብ ነገር እንደሌለ ተረዳሁ፡፡ “ውሾች ለጤና ጠንቅ ናቸው” በሚል መርዝ አበሏቸው፡፡ ውሾች የመኖር መብት አላቸው፤ ፍጥረት ናቸውና፡፡ ባለቤት የሌላቸው መሆናቸው ግን አስገደላቸው፡፡ ልከላከል ሞክሬ ነበር፤ እንዳይበሉት ለማድረግ ጥሬ ነበር፤ ገዳዮቹን ለማባረር ጥሬ ነበር፤ ግን ብቻዬን ነኝ! ውሾቼኮ የበጋ ወዳጆቼ ናቸው፡፡ ይህ ክፉ ክረምት ውሾቼን ዳግም እንዳላያቸው የመሰናበቻ ጊዜ ሆነ፡፡ አለቀስኩ፣ ጮህኩ፣ ጉልበቴ ደክሟል፡፡ በጎረምሶች እጅ እግሬ ተይዟል፡፡

 የመንደሪቷ ነዋሪዎች የውሾቹን አሟሟት በማየት ለራሳቸው ደስታን ሲፈጥሩ እውነቴን ነው የምልህ ይበልጥ ጠላኋቸው፡፡ ለዚህች መንደር ነዋሪዎች የሞት ስቃይ ማየት የሚፈጥረውን ደስታ ማጣጣም አዲስ አይደለም፡፡ ሰዎች የሞት ቅጣት ይበየንባቸው የነበረበት ቦታ እዚህ መሆኑን እወቅ! ከብዙ ዓመታት በፊት የሞት ፍርደኞች በአደባባይ ይሰቀሉ እንደነበር ቦታ ላይ ነኝ፡፡ ይህ ታሪክ የማይረሳው ሰው በአደባባይ በሞትና በህይወት መሀል በነፍስ ከስጋ ለመለየት የሚደረግ መንፈራገጥን ምንነት የተገለጠበት ቦታ ነው፡፡ ይግባህ! የማወራው ድሮ ማነቂያ ስለነበር ስፍራ ነው፡፡ በክር አንገትህ ታንቆ መሞት ምን እንደሆነ የምታይበት ስፍራ፡፡ መንደሬን ያወካት መሰለኝ፡፡ ሞትን ወደህ ሳይሆን ተገደህ መጎንጨት ሰውን ሳይሆን የሞትን ክብር መንካት ነው፡፡

 መርዝ የተለወሰ ስጋ የበሉ ውሾች ሲዳከሙና ለሀጫቸውን ማዝረክረክ ሲጀምሩ ቦት ጫማና የጎማ ጓንት ያጠለቁ ገዳዮች በእጃቸው የያዙትን የብረት ማነቂያ አንገታቸው ውስጥ እየከተቱ አነቋቸው፡፡

ተፈጥሮ በህይወት ጉዞ ውስጥ ከለገሰቻቸው ሞቶች የበለጠ የሰዎች ፈጠራ ውጤት የሆነ የመግደያ ብልሃቶች ዘግናኝ ናቸው፡፡ ምስኪን….፣ ውሾቼ ሰዎችን ማመናቸው አሳዘነኝ፡፡ ትላንት በአደባባይ፣ ሊያውም በጠራራ ፀሐይ ጎዳና ላይ ሲተኙ ኮቴም ሆነ የመኪና ጥሩንባ አይቀሰቅሳቸውም ነበር፡፡ ሰው በመኖሩ ብቻ መኖር የቻሉ አድርገው የወሰዱ ይመስለኛል፡፡ ሰው ሳይኖር መኖር የሚሳነው ሰው ብቻ መሆኑን አውቀዋለሁ፡፡ ውሾቼ አለቁ! እንቁራሪቶቼም ለህፃናት መጫወቻ እየሆኑ ነው፡፡ ከሞት የተረፉትን በጋ ላይ አልሰማቸውም፡፡ የውሾቼ በድን መኪና ላይ ሲጫን የሞት ትርኢቱ ተደመደመ፡፡ የመንደሬ ለቅሞ አዳሪዎች ወደሬሳነት ተለውጠዋል፡፡ ገና ለገና አብደው ሰው የጎዳሉ በሚል ፍራቻ የመኖር መብታቸውን አጡ፡፡ አንድ ቀን እኔም `ጭራቅ” ሆኜ ደማቸውን እንዳልመጥ ይገድሉኝ ይሆናል፡፡ እጅ እግሬን ጠፍረው ይዘውኝ የነበሩ ወጣቶች ለቀውኝ ሄደዋል፡፡ ምሽት ብርታት እስቲሰጠኝ ባለሁበት መቆየትን መረጥኩ፡፡

ቀባሪዬ፣ ይህች የሰዎች ታንቆ መሞቻ መንደር ከስሟ ጀምሮ የብቻዬ እንጉርጉሮ እንዲያገረሽ አደረገብኝ፡፡

አንቺ ዶሮ ማነቂያ የሆንሽው ዶሮ ማነቂያ ሆይ! ዛሬ ምኒሊክ አደባባይ የሆነው ስፍራሽ ላይ የነበረው ትልቅ ዋርካ ይታየኛል፡፡ ያን ጊዜ አለመፈጠሬ ዋርካሽ በፈረሰኛው ምንሊክ ሃወልት ቢተካም፣ የግሪኮች ጣሪያ አልባ (አንፊ) ቴአትር የመሰለው ዘመንሽን ውስጤ በከሰተልኝ ዋርካሽ የጥቁር ብካይ ሂደትሽ ይታየኛል፡፡ አንቆ መግደልን “ፍትህ” ነው ብለው የሚያምኑ ነገሥታቶችሽ አጣብተውሽ ከሄዱት ክፉ ባህርይ ጋር ዛሬም ያው መሆንሽ፣ ዛሬም ማነቂያ መሆንሽን አወጋሻለሁ፡፡

ዓርብ 19 ጁላይ 2013

ብሌንን ያስታወሰኝ “ንቅሳት” ወ “ንክሳት” - ኄኖክ ስጦታው



ካፌ ውስጥ ነኝ፡፡ አንድ ሰው ከፊቴ እጀ ጉርድ ካናቴራ አድርጎ ካፑቺኖውን ይጠጣል፡፡ ቡና ከረባቴን አዝዤ ሰውየው ላይ አፈጠጥኩ፡፡ በእጆቹ ክንዶች ላይ ተነቅሷል፤ ተነቃቅሷል፡፡

በደህና ጊዜ የረሳሁትን “ታቱ”ዬን አስታወሰኝ፡፡

የንቅሳት ጠበብት ፡- “ንቅሳት ዘመን የማይሽረው ውጨ-ተውብሆ ነው” ይላሉ፤ ሊሆን ይችላል፡፡ እናቴ አንገቷ ላይ ተነቅሳለች፤ የአጎቴ ልጅ ደግሞ ድዱ ላይ ጉራማይሌ ተነቅሷል፡፡ እኔ . . . ሃሃሃ . . . ክንዴ ላይ ተነቅሼ ነበር፡፡ ጓደኞቼ ንቅሳቴን ዓይተው “ተነክሰህ ነው ተነቅሰህ?!” እያሉ ሲያላግጡብኝ አስፈግፍጌ አስጠፋሁት፡፡ /አስጠበስኩት ብል ይቀለኛል፡፡/ ጥሎት ያለፈውን ጠባሳ ስመለከት እውነታቸውን እንደሆነ አረጋግጣለሁ፡፡ አሁን ነዋ ከንቅሳትነቱ በላይ ንክሳት እንደሆነ የሚያስታውቀው፡፡
  
ሰውየው….
በእጆቹ ክንዶች ላይ ተነቅሷል፤ ተነቃቅሷል፡፡ በቅጥልጥል የእንግሊዘኛ ፊደል የተጻፈ ነው፡፡ ትርጉሙን ለመረዳት ለማንበብ ሞክሬ አልተሳካልኝም፡፡ እንኳን ተቀጣጥሎ እንዲሁ በ“ARIAL font” ተጽፎም አይነበብልኝም፡፡

 የድሮው ንቅሳት አንገት እና ጥርስ ብሎም ግንባር እና አገጭ ተኮር ነበር፡፡ ዘመንኛው ንቅሳት ጥቂት የማሸጋሸግ ሂደት ይስተዋልበታል፡፡ አንገት ላይ የነበረው፣ ወደ ደረት . . . ድድ ላይ የነበረው ወደጆሮ ግንድ  . . . የተጨመሩት ደግሞ፣   ጀርባ ላይ እና እምብርት ላይ ያሉት ናቸው፡፡ /ዘለቅ ብዬ አላየሁም እንጂ ሌላም፣ ሌላም ቦታ ላይ ተነቅሰው ይሆናል፡፡/

ንቅሳታሙን ሰው ምን እንደተነቀሰና ለምን እንደተነቀሰ ልጠይቀው አሰብኩ፡፡ ግን፣ ምንስ ቢነቀስ እኔ ምን አገባኝ?? አልኩና ተውኩት፡፡  ለምን ጥያቄውን ከእራሴው አልጀምርም፡፡እኔ ለምን ነበር የተነቀስኩት?!

“ብሌን” የተባለች ቆንጆ ወደድኩና ተነቀስኩ፡፡ የተነቀስኩ ሰሞን ከቅጥነቴ የተነሳ “ቆዳ ቅብ” አይት ነበርኩ፡፡ ታቱ የሠራልኝ ሰው ብዙ  አሪፍ አሪፍ ዓይነት አማራጭ ምስሎች ነበሩት፡፡ ግን ምኔ ላይ ይንቀሰኝ?? አልወደድኩትም እንጂ የሚመጥነኝ “ታቱ” አግኝቶልኝ ነበር፡፡ ልክ እንደ እጅ አምባር ሆኖ ክንድ ላይ የሚነቀስ፡፡ ትርጉም አልባ ነገር ከመነቀስ እስከነአካቴው አለመነቀስ ይሻላል፡፡ “ብሌን” ብለህ ነቅሰኘኝ አልኩት፡፡ ነቃሹ “አይሆንም” ብሎ ሞገተኝ፡፡ “ብሌን” ሶስት ፊደላት ነው፡፡ ክንድህ ደግሞ ወደታች እንጂ ወደጎን ቦታ የለውም፡፡ ስለዚህ “የዓይን ምስል” ይሻልሃል፡፡ አለና አሳመነኝ፡፡ ተነቀስኩ፡፡ የንቅሳቴ ቀለም ባግባቡ ሳያጠግግ ከብሌን ጋር ተለያየን፡፡ እንዴት እንደተለያየን አላውቅም፡፡ ስጠረጥር ግን “ለምን የአባቴን ስም አብረህ አልተነቀስክም??” በሚል አኩርፋኝ ሊሆን እንደሚችል እጠረጥራለሁ፡፡

እና አሁን በካፌ ውስጥ ካፑቺኖ የሚጠጣውን ሰው ሰውነት እና ቅጥልጥል የበዛበት ንቅሳት ሳስብ አንድ ነገር ተገለፀልኝ፡፡ ይህን ጊዜ እኮ “ብሌን ኃይለ ማርያም” ብሎ ይሆናል የተነቀሰው!

አንተ ሰውዬ፤ ልብ በል!!   “ንቅሳት ዘመን የማይሽረው መዋቢያ ቢሆንም ለተነቃሹ ግን ልዩ ምልክት ነው፡፡”


ሰኞ 15 ጁላይ 2013

“የፒያሳ አመልህን ይዘህ ቦሌ አትሂድ” - ኄኖክ ስጦታው



ወደ ቦሌ አካባቢ ሄደህ ፣ መዝናናት ካማረህ እባክህን ከማጨብጨብ ተቆጠብ፡፡

ከእለታት በአንድ የተረገመች ቀን እንዲህ ሆንኩላችሁ፡፡ ደምበል አካባቢ ካለው “ላ ፓራዚያን ካፌ” እግር ጥሎኝ ገባሁ፡፡ ከውስጥ መግባት ፈርቼ ወይም ሸሽቼ ከበረንዳው በስተቀኝ ወዳለችው የመናፈሻ ሳምፕል ወደመሰለችኝ “መናፈሻ” ገብቼ ተቀመጥኩ፡፡ ለደቂቃዎች ዞር ብሎ የሚያየኝ አስተናጋጅ አጣሁና በጭብጨባ ለመጥራት እጄን ማፋተግ ጀመርኩ፡፡ ያው …. ፒያሳ የለመደብኝ አመሌ አገረሸ፡፡

/ፒያሳ እኮ ካላጨበጨብክ የሚታዘዝህ አስተናጋጅ ጥቂት ነው፡፡ ኧረ አንዳንዴማ፣ አስተናጋጅ ለመጥራት ልታፏጭ ሁሉ ትችላለህ፡፡ የምመክርህ ነገር ቢኖር የፒያሳ አመልህን ይዘህ ቦሌ አትሂድ ፡፡/

ይህ አመሌ አገሸና ማጨብጨብ ጀመርኩ፡፡ አጨበጨብኩ፡፡ ዝም!
ደጋግሜ አጨበጨብኩ፡፡ ጭጭ!

የጭብጨባዬ ድምጽ “ላውድ” ላይ አድርጌ ቀወጥኩት፡፡ አሁን ዘዴዬ ሠራ መሰል አንዲት አስተናጋጅ መጣችና ቁልቁል በመመልከት “ምን ይጠበስ?!?” በሚል አስተያየት ታየኝ ጀመር፡፡

“ምንድን ነው?! ሳጨበጭብ አትሰሙም እንዴ!??!” አልኩ ቁጣ ባጠቃው ድምፀት፡፡

“ይኸው ልጨፍር መጣሁ እኮ!!” አለች እጆቿን ወገቧ ላይ አድርጋ፣ ትከሻዋንም “እስከስ” እያደረገች፡፡

ኧረ፣ መውረግረግ!!!


ምነው እጄን በቆረጠው! ምነው አቅሜን አውቄ እዛው ፒያሳ ባጨበጭብ!! ሃሃሃ /ባላጨበጭብስ/

ቅዳሜ 13 ጁላይ 2013

የጋሽ ሙኼ የአኗኗር ዘይቤ እና ብር ብር የሚሸቱ አባባሎች - ኄኖክ ስጦታው



ጋሽ ሙኼ “ወጪ ቆጣቢ ናቸው” ፡፡ ቁርስ ቤታቸው በልተው ይወጣሉ፡፡ ምሳቸውን ደግሞ አንዱ ምግብ ቤት/ረከስ ያለ ዋጋ ካለበት/ ይመገባሉ፡፡ ሁሌም ታዲያ አንድ አይነት ምግብ ነው የሚያዙት፡፡ ፍርፍር!!

ጥብስ ፍርፍርም ሆነ ቋንጣ ፍርፍር አይወዱም፡፡ /አይመቻቸውም ማለት የሚቀል ይመስለኛል፡፡/ የፆም ፍርፍር ብቻ!

/ከጨጓራ ህመም ማስታገሻ መድሃኒት አቅም እንኳን ርከሹን ነው የሚገዙት፡፡ በተለይ እንደ ጉንፋን ከረሜላ የምትመጠጠዋ ኪኒና እንደ “ገንዘብ” ነው የሚወዷት፡፡/

ጋሽ ሙኼ ብራም ናቸው፡፡ ብራቸው አንዴ ወደ ኪሳቸው ከገባ በድጋሚ ከኪሳቸው የሚወጣው ባንክ ቤት ውስጥ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ለሥራ ጉዳይ ቢሯቸው በጠዋት ሄጄ ካጣኋቸው ፣ በቃ ባንክ ቤት ሄደዋል ማለት ነው፡፡ ማውጣትማ ሞታቸው ነው፡፡ ባንክ ቤት ገንዘብ ካላስገቡ ቀኑ ይጨልምባቸዋል፡፡ ሰው ያስጠላቸዋል፡፡ እንዲያ የሚያፈቅሩትን ፍርፍር ገበታ ላይ ማየት ያስጠላቸዋል፡፡

ባገኙኝ ቁጥር አንድ ጥያቄ አላቸው፡-

“ምን ይዘህልኝ መጣህ??” ይሉኛል፡፡

ይህ ጥያቄያቸው ወደአማርኛ ሲተረጎም “ብር ይዘህ መጥተሃል ወይ?” ማለት ነው፡፡ ያው፣ ቀብድም ይሁን ቀሪ ክፍያ መያዝ አለብኝ፡፡ የሚከፈል ነገር ከሌለ ደግሞ ወደፊት ከማሠራው ሥራ ላይ የሚታሰብ ብር ቆጥሬ መስጠት አለብኝ፡፡ ምንም ከሌለኝ ግን ቁጣቸውን የመቋቋም አቅም ሊኖረኝ የግድ ነው፡፡

“ባዶ እጅህን አትምጣ አላልኩህም?!!?” ይላሉ ሠራተኞች እየሰሙ፡፡

“ለሰላምታም ቢሆን መምጣት አልችልም?!?”

“በደረቁ ሰላም ብትለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡”

“ሁለተኛ አልመጣብዎትም” ብዬ ልወጣ ፊቴን ሳዞር እንደልጅ አባብለው ወደ ካፌ ይወስዱኝና ይመክሩኛል፡፡ /ሃሃሃ… “ይመክሩኛል” የሚለው ቃል አባታዊነትን እንዲወክል ሆን ተብሎ የገባ ቃል እንደሆነ ታሳቢ ተደርጎ ይነበብልኝ፡፡/

“ይህችን ምክር ስማ” ይሉና ይጀምራሉ፡፡

“በእርጅና ዘመን እንዲሆንህ ተስፋ
ገንዘብ ኪስህ ካለ፣ ኪሶችህን ስፋ”

ገንዘብ ላይ ቢስቆነቆኑም በሌላ ነገር ደግ ናቸው፡፡ “ስነቃል” ሲያጽፉኝ መሰሰት የሚባል ነገር አያውቁም፡፡ ለዚህም ነው መሰል ብር ባይኖረኝም እንኳን “ምን ይዘህልኝ መጣህ??” እንደምባል እያወቅኩ እሳቸው ዘንድ እማልጠፋው፡፡

“ሃብታም ማለት . . .” ይሉኛል “ሃብታም ማለት ፣ ብዙ ገቢ ያለው ሳይሆን ካገኘው ላይ ብዙ የሚቆጥብ ነው፡፡”

“እንደ እርሶ ማለት ነው” እላለሁ በሆዴ፡፡

“ሀብታም መሆን ከፈለግክ እጅህን ቶሎቶሎ ኪስህ አትክተት” ይሉኛል፡፡

“እንደ እርሶ ማለት ነው” እላለሁ - በሆዴ፡፡

በሚያሳዝን ሁኔታ የብዙ ሰው ምክር ሰምቼ ተሳክቶልኛል፡፡ የጋሽ ሙኼ ምክሮችን ለመተግበር ግን ሳልችል ቀርቻለሁ፡፡ እንኳን ብር ኖሮኝ ባይኖረኝም እንኳን፣ እጄ ልምድ ሆኖበት ኪሴን ያፈቅረዋል፡፡

ግልባጭ ፡- አሽ-ሙጥ በ Henok Sitotaw

ዓርብ 5 ጁላይ 2013

ውዝግብግብ -- በ ኄኖክ ስጦታው


የውዝግብግብ ምናቦች ንሸጣዬ ሲበረታ እየቀነጨብኩ የማስነብባችሁ ነው፡፡ ሌላኛውን ምልከታ በሌላ ጊዜ …..

………. የተቀነጨበ…….

የጥቁርና ነጭ ቤቶችበምርጧመንደሬ ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው ያንተን መምጣት ይጠባበቃሉ፡፡ በዚህች መንደሬ ሲመሽ ብቻ የሚታዩህ አነዚህ መጠጥ ቤቶች የግድግዳቸው ቀለም ጥቁርና ነጭ መሆኑ ለምን እንደሆነ ሁሌ ያሳስበኛል፡፡

ሴተኛ አዳሪዎች የገንዘብ ዕድገት ሲያገኙ የሚከፍቷቸው እነዚህ ቤቶች በድራፍት ራሱን ባሟሟቀ ጠጪ ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ የሚደምቁ ናቸው፡፡ ቀባሪዬ አነዚህ ቤቶች የሚሰየሙት በሴተኛ አዳሪዋ ስም ነው፡፡አበዛሽ ፐብ” “ሣራ ፐብ”… የስም አይነት ታነባለህ፡፡ ሴቶችም ላያዊ ውበታቸው ወንዶችን የሚያማልል ዓይነት ቢጤ ነው፡፡

በእንደዚህ አይነት ቤቶች ለመዝናናት ኪስህን መተማመን ይኖርብሃል፡፡ ሴቶችም የዋዛ እንዳልሆኑ እንተን መስዬ እኖር በነበረ ጊዜ አውቀዋለሁ፡፡ ግራ እንደገባኝ የሚኖረው ግን እኝህ ቤቶች የተቀቡት ቀለም ነው፡፡ አንዳንዴ በውስጤ ጥቁርና ነጭ መሆኑ በደስታና ሀዘን ልፈታው እሞክራለሁ፡፡ መቼስ ሴቶቹ ሀሳቤን ቢሰሙ በእብደቴ እንደሚደሰቱ አምናለሁ፡፡

እርግጥ ነው ጊዜያዊ ደስታ የማያልፍ መከራን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህን ስልህ በሽታ ሸምተህ ትወጣለህ እያልኩህ ልደሰኩርልህ አይደለም፡፡ የዚህች መንደር ሴት አዳሪዎች ኤድስ ምን እንደሆነ ካንተ የበለጠ ያውቃሉ፡፡ ኮንዶም የህይወት ከለላቸው አድርገው ይኖራሉ፡፡ ዛሬ ለእነሱ በኮንዶም ስለ መጠቀም ልታስተምራቸው አትችልም፡፡ ላንተ ግን ያስተምሩሃል፡፡

የሴት አዳሪዎች ትልቁ ችሎታ አንተንም ሆነ ሌላውን እኩል የማስተናገድ ብቃትን መያዛቸው ነው፡፡ ገንዘብ ይኑርህ እንጂ ሁሉም ነገር ያንተ ነው፡፡ ፈገግታቸውን አይሰስቱብህም፡፡ ክፈልበት እንጂ ቢራም ሆነ ውስኪ ቀምሰው ይባርኩልሃል፡፡ የሴት አዳሪ ክብርን በግልፅ ታይበታለህ፡፡ አዎ! እራሳቸውን የሚያከብሩ እንጅ ራሳቸውን አፍቃሪ መሆናቸውን ለማወቅ ጊዜ አይፈጅብህም፡፡ ሥጋቸውን ሸጠው ያተርፉብሃል፡፡ አልኮል ሸጠው ያተርፉብሃል:: ቤተኛ ከሆንክ ደግሞ አንተኑ ከነነፍስህ ሸጠው ያተርፉብሃል፡፡ ለእነሱ ቢዝነስሽርሙጥናነው፡፡ ውበት ኃላፊ መሆኑን ካንተ በላይ ያውቁታል፡፡ ስለዚህም በጊዜ ቋሚ ንብረት ያላቸው ሴት አዳሪዎች ሆነዋል፡፡

ማክሰኞ 2 ጁላይ 2013

“ፍትሃዊ የሥጋ ክፍፍል” - ኄኖክ ስጦታው

እኩል መስተንግዶ ለሁሉም ሰው- በሁሉም ቦታ!!”





ይህ ጽሑፍ የልኳንዳ ማስታወቂያ ሊመስል ይችላል፡፡ ((ልኳንዳ ቤት ሥጋ መብላት ለከፋ ለችግር ይዳርጋል፡፡ ምክናያቱ ግልፅ ነው፡፡ አቅም ያናጋልና፡፡)) እውነታው ይህ ነው፡፡ ለእኔ፡፡

አንዳንዴ ግን ሥጋ እሳፈጣለሁ፡፡የመጣው ይምጣ፤ ከልኩ አያልፍም፤ ሺህ ዓመት አይኖር፤ የበላና የተማረ ወድቆ አይወድቅም፤ ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት ዳገት ላይ ይለግማል….” ቅብርጥሶ ቀብርጥስጥሶ ሃሳቦች ከአቅም በላይ ሆነው ሲሰለጥኑብኝና አምሮቴ ሲገንን ልኳንዳ ቤት አገባለሁ ….. ዛሬ አንዱ ቤት እንደገባሁት ማለት ነው፡፡

የቅንጦት ምግባችንሥጋነው፡፡ አትክልትማ ዘመናችንን ሙሉ ስናላግጥበት ኖረናል፡፡

በልጅነት ዘመኔ ዓውድ ዓመት እንዲመጣ የሚያስመኙኝ ሁለት ነገሮች ነበሩ፡፡ አንደኛው ትምህርት ቤት ይዘጋል፡፡ /በዓል... ቅዳሜና እሁድ እንዳይውል እጸልይ ነበር/ ሁለተኛው ደግሞ ቀይ ወጥ እንደጉድ ይበላለታል፡፡ /አቤት እንዴት ያለ ትዝታ ነው!? /

ከሁሉም የማልረሳው ትዝታ፣ ለመሥራት ረጅምና አሰልቺ ጊዜ የሚወስደው ዶሮ ወጥ እስኪደርስ አላስችል ብሎኝ ከቁሌት ካልሰጣችሁኝ ብዬ ኩሽና ውስጥ የምረብሸው ነገር ነው፡፡

ያኔ ታዲያ ቤታችን የሚሠራው ቀይ ወጥ የራሱ የሆነ ቅደም ተከተል ነበረው፡-

የመጀመሪያዎቹ ሁለት እና ሶስት ቀናት ----- ቅባት እና አንኳር ሥጋ የበዛነት

ቀጥሎ፣ ------ በድንች ወጥ ውስጥ ጥቂት ሥጋ ጣል ጣል ያለበት

በመጨረሻ ------- ሽሮ ወጥ ውስጥ በስህተት የገቡ ሥጋዎች /ቦዘና/

የመጨረሻው መጨረሻ ----- ልሙጥ ሽሮ ነው፡፡

አንዳንዴ ጊዜ፣ ቤታችን ከገጠር ዘመድ ይመጣል፡፡ ያኔ ታዲያ መደዳውን ከምንበላው ሽሮ ጣልቃ ሥጋ ወጥ ይገባና የሽሮን ታሪካዊ ሚና ይሽረዋል፡፡

/ገጠር ያሉ ዘመዶች ሲመጡ በእነሱ አጠራርዳቦ ቆሎከእጃቸው አይለይም፡፡የተቆላ ዳቦቢባል የሚሻል መጠሪያው እንደሚሆን አስባለሁ፡፡ እውነት ለመናገር ለብዙ ዓመታትዳቦ ቆሎማለት ከዳቦ ትንሽ አነስ ያለ፣ ከሽንብራ ቆሎ በመቶ እጥፍ የተለቀ ይመስለኝ ነበር፡፡/

የልጅነት ትዝታዬን እዚህ ጋር ልግታውና ዛሬ ያጋጠመኝን ልኳንዳ ቤት ትንሽ ላሞጋግስ፡፡

በቲፕ ሰበብ ሙስናው ይበልጥ ደርቷል፡፡ በተለይ በስጋ ቤቶች፡፡ እኔና ጓደኞቼ አንድ ኪሎ ስጋ ለመመገብ አንድ ኩንታል ስጋት ተሸክመን የገባንበት ቤት እስከዛሬ ካየኋቸው ቤቶች በብዙ መንገድ ይለያል፡፡

የሥጋ ቆራጮቹ ጋወን ንጣት፣ ቁጥር እየጠሩ የሚጯጯሁ አስተናጋጆች አለመኖር፣ ደህናውን ሥጋ እንዲቆርጥላቸው የሚሹ ደንበኞች ሥጋ ቆራጩን ለመደለል /ጉርሻ ቢጤ ብር እንዳይሸጉጡ/ መከልከላቸው ……. ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በስንት ድርድር ገንዘብ አጋጭተን የገባንባቸው ሥጋ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ አሻጥሮች እዚህ የሉም፡፡ ወይም አላጋጠመንም፡፡

እውነቴን ነው፣

ብዙ ቦታ ላይ የሚያጋጥመን ““-ፍትሃዊ የሥጋ ክፍፍል”” እዚህ ቤት ተሽሮ ማየቴ የነጋዴዎቻችንን ብስለት መጨመር ገምግሜበታለሁ፡፡

ልኳንዳ ቤቱ እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ጽፎ ሳይ ደስ አለኝ፡፡

ለምንሰጠው መልካም መስተንግዶ ሲባል
ለቆራጮች ጉርሻ መስጠት አይፈቀድም!!”

ጽሑፌን ለመደምደም ይህን አልኩ፡፡

እኩል መስተንግዶ ለሁሉም ሰው- በሁሉም ቦታ!!”