ዓርብ 5 ጁላይ 2013

ውዝግብግብ -- በ ኄኖክ ስጦታው


የውዝግብግብ ምናቦች ንሸጣዬ ሲበረታ እየቀነጨብኩ የማስነብባችሁ ነው፡፡ ሌላኛውን ምልከታ በሌላ ጊዜ …..

………. የተቀነጨበ…….

የጥቁርና ነጭ ቤቶችበምርጧመንደሬ ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው ያንተን መምጣት ይጠባበቃሉ፡፡ በዚህች መንደሬ ሲመሽ ብቻ የሚታዩህ አነዚህ መጠጥ ቤቶች የግድግዳቸው ቀለም ጥቁርና ነጭ መሆኑ ለምን እንደሆነ ሁሌ ያሳስበኛል፡፡

ሴተኛ አዳሪዎች የገንዘብ ዕድገት ሲያገኙ የሚከፍቷቸው እነዚህ ቤቶች በድራፍት ራሱን ባሟሟቀ ጠጪ ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ የሚደምቁ ናቸው፡፡ ቀባሪዬ አነዚህ ቤቶች የሚሰየሙት በሴተኛ አዳሪዋ ስም ነው፡፡አበዛሽ ፐብ” “ሣራ ፐብ”… የስም አይነት ታነባለህ፡፡ ሴቶችም ላያዊ ውበታቸው ወንዶችን የሚያማልል ዓይነት ቢጤ ነው፡፡

በእንደዚህ አይነት ቤቶች ለመዝናናት ኪስህን መተማመን ይኖርብሃል፡፡ ሴቶችም የዋዛ እንዳልሆኑ እንተን መስዬ እኖር በነበረ ጊዜ አውቀዋለሁ፡፡ ግራ እንደገባኝ የሚኖረው ግን እኝህ ቤቶች የተቀቡት ቀለም ነው፡፡ አንዳንዴ በውስጤ ጥቁርና ነጭ መሆኑ በደስታና ሀዘን ልፈታው እሞክራለሁ፡፡ መቼስ ሴቶቹ ሀሳቤን ቢሰሙ በእብደቴ እንደሚደሰቱ አምናለሁ፡፡

እርግጥ ነው ጊዜያዊ ደስታ የማያልፍ መከራን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህን ስልህ በሽታ ሸምተህ ትወጣለህ እያልኩህ ልደሰኩርልህ አይደለም፡፡ የዚህች መንደር ሴት አዳሪዎች ኤድስ ምን እንደሆነ ካንተ የበለጠ ያውቃሉ፡፡ ኮንዶም የህይወት ከለላቸው አድርገው ይኖራሉ፡፡ ዛሬ ለእነሱ በኮንዶም ስለ መጠቀም ልታስተምራቸው አትችልም፡፡ ላንተ ግን ያስተምሩሃል፡፡

የሴት አዳሪዎች ትልቁ ችሎታ አንተንም ሆነ ሌላውን እኩል የማስተናገድ ብቃትን መያዛቸው ነው፡፡ ገንዘብ ይኑርህ እንጂ ሁሉም ነገር ያንተ ነው፡፡ ፈገግታቸውን አይሰስቱብህም፡፡ ክፈልበት እንጂ ቢራም ሆነ ውስኪ ቀምሰው ይባርኩልሃል፡፡ የሴት አዳሪ ክብርን በግልፅ ታይበታለህ፡፡ አዎ! እራሳቸውን የሚያከብሩ እንጅ ራሳቸውን አፍቃሪ መሆናቸውን ለማወቅ ጊዜ አይፈጅብህም፡፡ ሥጋቸውን ሸጠው ያተርፉብሃል፡፡ አልኮል ሸጠው ያተርፉብሃል:: ቤተኛ ከሆንክ ደግሞ አንተኑ ከነነፍስህ ሸጠው ያተርፉብሃል፡፡ ለእነሱ ቢዝነስሽርሙጥናነው፡፡ ውበት ኃላፊ መሆኑን ካንተ በላይ ያውቁታል፡፡ ስለዚህም በጊዜ ቋሚ ንብረት ያላቸው ሴት አዳሪዎች ሆነዋል፡፡


አንቺ የጥቁርና ነጭ ቤት ባለቤት ሆይ! ፈገግታሽ ያማልላል! ቤትሽ ሲመሽ ኑልኝ በሚል ጥሪ ይፈታተናል፡፡ ገላሽ ለፍትወት መወጫ ብቻ ሣይሆንእድሜ ቀጥልመድሃኒት መሆኑን የሚያምኑ ብዙ አጃቢዎች አሉሽ፡፡ አዛውንቶች ነጭ ፀጉራቸውን አጥቁረው ይከቡሻል፡፡ ወጣቶች ወጣትነታቸውን ወጥረው ይንጎማለሉልሻል፡፡ ሁሉም ያንቺ ደንበኞች አስመሳዮች ናቸው፡፡ አዛውንቱም ቢሆን እውነትን አንቆ የገደለ ነው፡፡ መኖር ከሰጠው ሀቅ ውስጥ የፀጉሩን ቀለም ገሏልና፡፡ መፈጠር የሰጠውን ፀጋ ደብቆ የውሸት ጥርሱን ያሳይሻል፡፡ ወጣቱም ቢሆን ወኔ ቢስ ወጣትነትን ከመሸከም የዘለለ ጀብድ የለሽ ነው፡፡ሸርሙጣእንደሚጠላ ለመሰሎቹ ሲዘምር ኖሮ ዛሬ ከጭንሽ ደስታን ሊሸምት ይመጣል፡፡ አንቺ ፊት ተንጎማልሎ ጀግንነቱን እንድትነግሪው ይፈልጋል፡፡ ውስኪ ስለጠጣባለሃብትመሆኑን እንድታምኝለት ይሻል፡፡ በዛሬ ወጪው ነገ ፀጉሩን እንደማይነጭ ሁሉ መክፈል ሲያበዛ ታዘቢው፡፡ አምናለሁ አንቺ ከኔ የተሸለ ደንበኞችሽን ታውቂያቸዋለሽ፡፡ ውሸታም ስለሆነ ብቻ ትክክለኛ ስምሽን አትናገሪም፡፡ አጭበርባሪ ስለሆነ ሂሳብሽን ቀድመሽ ትቀበያለሽ፡፡ ስሜታዊ ስለሆነ ባለጌ ወንበር ላይ እግርሽን ሳትገጥሚ ትቀመጫለሽ፡፡ መሸርሞጥን አስተማረሽ እንጂ መች መፈጠርሽ ለዚህ ሆነና?! ማስመሰልን አስተማርሽ እንጂ መች ማስመሰልን ሸጥሽለት?! በሽታ ይዞልሽ መጣ እንጂ መች በሽሸሽ ጠበቅሽው፡፡

ቀባሪዬ በጥቁርና ነጭ ቤቶች ውስጥ የምታገኛት እህትህ አስመሳይ ሆና አልተረዳችምኮ፤ አስመሳይ አድርገህ ወሰድካት እንጂ፡፡ ሴሰኝነት ተጠናውቷት ገላዋን እንደማትቸረችር እወቅ፡፡ ካንተ ሰፍሳፋነት፣ ካንተ ውሸታምነት የተወለደች እንደሆነ ተረዳ፡፡ ዛሬ ግን ማስመሰልን ተክናልሃለች፡፡ ዳግም እንድትገላት ስለማትሻ በሩቁ ትቀርብሃለች፡፡ ሌላው ቀርቶ ልታገባት እንደማትፈልግ ሁሉ እንድታገባት አትመኝም፡፡ አንተ ከሷ ጋር እንዳትታይ ጨለማን ተገን ስታደርግ ትስቅብሃለች፡፡ በፈሪነትህ ምክንያት ቀኗን ሌት አድርጋለች፡፡ እወቅ! አንተ ሲነጋልህ ለሷ ሌት ነው፡፡ ላንተ ሲመሽ ለሷ ቀን ነው፡፡ የአንድ አዳር ኮንትራትህን ልትሸምት ስትሄድ በገንዘብህ የገዛሃት ይመስልሃል፡፡ ግን እራስህን እየሸጥክላት መሆኑን ላነድ አፍታም አስበኸው አታውቅም፡፡ የዘር ሀጥያትህ በማህፀኗ እንዲቀመጥ ዛሬ አትሻም፡፡ ቢያንስ እቃህን በላስቲክ እንዴት መያዝ እንዳለብህ ታስተምርሃለች፡፡

ከፊል ደመናማ እና ከፊል ፀሃያማበህይወትህ ውስጥ ይከሰታሉ፡፡ በተስፋማነት እና በተስፋ ማጣት እንመስላቸዋለን፡፡ ሁለቱም ግን ለዕይታ አንድ ናቸው፡፡ ከፊል ደመናማ ከፊሉ ፀሃይ ነው፡፡ ከፊል ፀሃያማ ከፊሉ ደመና ነው፡፡ እስካሁን የመኖሬ ምክንያት ይህ ነው፡፡ ዛሬ ምኖረው ዘይቤ ከፊል ፀሃያማ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ደመና የለም እያልኩህ እንዳልሆነ ትረዳኛለህ፡፡ ውስጤ የሚያውቀው ግን ከፊል ፀሃያማ የሆነውን ሳስብ ብቻ ነው፡፡

ለምን እንደተፈጠሩ ስጠይቃቸው መልስ በሌላቸው የዚህች መንደር ጉስቁሎች መሃል ቆሜ ይህን አስባለሁ፡፡አይኔ ድንቡሽቡሽ ያለ ህፃን የታቀፈ ኮረዳ ላይ ያረፈ ይመስለኛል፡፡ ቤተሰቦቿን ሳውቃቸው አቃፊዋ በሽንቷ የምትጫወት ልጅ ነበረች፡፡ ዛሬ የልጅ እናት ሆናለች እንኳን ማርያም ማረችሽ ሚጡ፡፡ ላንቺ መኖር ከፊል ደመናማ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ጨለማ እንደሆነ በልጅነት ፊትሽ ላይ ይነበባል፡፡ ማህበረሰቡዲቃላ ወልዳለችበሚል እሳቤ አውግዘውሻል፡፡ አምናለሁ! ከእንግዲህ ከእኩዮችሽ ጋር አትጫወቺም፡፡ ልጅሽን ለማሳደግ የሌሎች ባሪያ መሆንሽ ያሳዝነኛል፡፡ ይበልጥ ደግሞ ይህን የመሰለ ህፃን እዚህ መንደር መወለዱ ያሳዝነኛል፡፡

ቀባሪዬ ከፊቴ የዳመነ ፊት ይታዬኛል፡፡ በሀዘን የተሰበረ ውስጥ ይታየኛል፡፡ ተስፋ የቆረጠ ህይወት ይታየኛል፡፡ ምኑንም የማያውቅ የሚስቅ የሚቦርቅ ህፃን ይታየኛል፡፡ይህ ህፃን መሞት አለበት!” ብዬ ጮውኩ፡፡እዚህ መንደር መኖር የለበትም!” ብዬ ጮውኩ፡፡ ጩኸቴ ተቃውሞ አስነሳ፡፡ የሰው ጫካ ተፈጠረ፡፡ አስፈራራኝ፡፡ ሮጬ መውጣት ነበረብኝ፡፡
ቀባሪዬ አምላክም ቢሆን እኮህፃናቶች ወደኔ ይምጡ አትከልክሏቸውይላል፡፡ ነፍስ ሳያውቁ የሚሳሳቱ ነፍሶች የሚፈጥሯቸው ውልዶች አሳዘኑኝ፡፡ ህይወት ምን እንደሆነች ሳያውቁ ሳይፈልጉ የወለዱ ልጃገረዶች አሳዘኑኝ፡፡ የዚህች ጥቁር አለም ጉስቁልነታቸው ባሻገር የርካሽ አስተሳሰብ ጭዳ መሆናቸው ውስጤን ቦረቦረው፡፡ የኑሮ ምሬት በእናቱ ላይ ሲበዛ ይህ ህፃንባንተ ነው እንዲህ የሆንኩትእየተባለ ከሚያድግ ቢሞት ይሻላል፡፡

በዚህ መንደር ብዙዎች ህፃናት በእናታቸው አባት ይጠራሉ፡፡ በዚህች ጉስቁል መንደር ህፃናቶች በብሶት መግለጫ ስሞች ይጠራሉ፡፡ ይህ ጨቅላ የእነዚህ አካል ሆኖየሴት ልጅበሚል እሾሃማ ቃል እየተላጋ ከሚያድግ ቢሞት እመርጣለሁ፡፡ ለእናቱም ነፃነት ነበር፡፡

ቀባሪዬ እኔየሴት ልጅነኝ፡፡ እንዳንተ ሴትን ማጣጣል ፈልጌ አይደለም፡፡ ለእኔ ሴት ሳትፀዳ የተፈጠረች ሆና አትታየኝም፡፡ እንዲያውም ፈጣሪ አንተን ለመስራት ከፈጀበት ጊዜ በላይ ለሴት ያዋለ ይመስለኛል፡፡ ካንተ የበለጠ መከራን መቋቋም ትችላለች፡፡ ካንተ የበለጠ ውስጧ በጥንካሬ ተሞልቷል፡፡ የበታች አድርገህ ስትገዛት የበላይህ ሆና ትገዛልሃለች፡፡ በትዕግስት ትገዛሃለች፡፡ አንተ ግን ይህን ክስተት አትረዳውም፡፡

ሴት ሲወለድልህ ይከፋሃል፡፡ዲቃላታመጣብኛለች ብለህ ትፈራለህ፡፡ መኖር ምን እንደሆነ ግን አትነግራትም፡፡ አታውቀውማ! አንተ ምስኪን ጉስቁል ፍጡር፣ ሴት ውሻ እንደማታሳድግ ሁሉ ሴት ልጅህንም እረስተሃታል፡፡ ከሴት መፈጠርህን ግን ዘንግተሃል፡፡ ሴትን ክብር በነሳህ መጠን ክብርህን እየጣልክ መሆኑን አትርሳ! እንድታዝን ብታደርጋትም መፅናናት በጇ ነው በመሆኑ ቂም አትይዝብህም፡፡ ተስፋ ማድረግን አትተውምና፡፡

ቀባሪዬ፣ሟርተኛተባልኩልህገፊተባልኩልህ! ለምን መሰለህ? ህፃኑ በሳምንቱ ሞተ፡፡በቡዳ አይኑ በልቷት ነውተባልኩልህ፡፡ ይበልጥ በመገለሌ ግን አላዘንኩም፡፡ አይኔን ግን ፈጣሪዬ ይኖርበታል ብዬ ወደማሰበው መሬት ጣልኩና የፃድቁን ዕዮብን ቃል አነበብኩ፡፡

እሱ ሰጠ፣ እሱ ነሳ፣ የእግዚአብሄር ስም የተባረከ ይሁን!”


እኔ እንዴት ባንተ መፈጠር መወሰን እችላለሁ?! የመፈጠር ትልቁ ችሎታ ሙት ስላልኩህ አለመሞትህ ነው፡፡ ለዚህም አልሞትኩም፤ እኖራለሁ፡፡ ያንተን ጥቁር ምላስ የመኖር ሕልውናዬን አያናጋውም፡፡ ህይወትና ሞት በምላስና በአይን የሚደመደም ተራ ውሳኔ አይደለም፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ