ጋሽ ሙኼ “ወጪ ቆጣቢ ናቸው” ፡፡ ቁርስ ቤታቸው በልተው ይወጣሉ፡፡ ምሳቸውን ደግሞ አንዱ ምግብ ቤት/ረከስ ያለ ዋጋ ካለበት/ ይመገባሉ፡፡ ሁሌም ታዲያ አንድ አይነት ምግብ ነው የሚያዙት፡፡ ፍርፍር!!
ጥብስ ፍርፍርም ሆነ ቋንጣ ፍርፍር አይወዱም፡፡ /አይመቻቸውም ማለት የሚቀል ይመስለኛል፡፡/ የፆም ፍርፍር ብቻ!
/ከጨጓራ ህመም ማስታገሻ መድሃኒት አቅም እንኳን ርከሹን ነው የሚገዙት፡፡ በተለይ እንደ ጉንፋን ከረሜላ የምትመጠጠዋ ኪኒና እንደ “ገንዘብ” ነው የሚወዷት፡፡/
ጋሽ ሙኼ ብራም ናቸው፡፡ ብራቸው አንዴ ወደ ኪሳቸው ከገባ በድጋሚ ከኪሳቸው የሚወጣው ባንክ ቤት ውስጥ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ለሥራ ጉዳይ ቢሯቸው በጠዋት ሄጄ ካጣኋቸው ፣ በቃ ባንክ ቤት ሄደዋል ማለት ነው፡፡ ማውጣትማ ሞታቸው ነው፡፡ ባንክ ቤት ገንዘብ ካላስገቡ ቀኑ ይጨልምባቸዋል፡፡ ሰው ያስጠላቸዋል፡፡ እንዲያ የሚያፈቅሩትን ፍርፍር ገበታ ላይ ማየት ያስጠላቸዋል፡፡
ባገኙኝ ቁጥር አንድ ጥያቄ አላቸው፡-
“ምን ይዘህልኝ መጣህ??” ይሉኛል፡፡
ይህ ጥያቄያቸው ወደአማርኛ ሲተረጎም “ብር ይዘህ መጥተሃል ወይ?” ማለት ነው፡፡ ያው፣ ቀብድም ይሁን ቀሪ ክፍያ መያዝ አለብኝ፡፡ የሚከፈል ነገር ከሌለ ደግሞ ወደፊት ከማሠራው ሥራ ላይ የሚታሰብ ብር ቆጥሬ መስጠት አለብኝ፡፡ ምንም ከሌለኝ ግን ቁጣቸውን የመቋቋም አቅም ሊኖረኝ የግድ ነው፡፡
“ባዶ እጅህን አትምጣ አላልኩህም?!!?” ይላሉ ሠራተኞች እየሰሙ፡፡
“ለሰላምታም ቢሆን መምጣት አልችልም?!?”
“በደረቁ ሰላም ብትለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡”
“ሁለተኛ አልመጣብዎትም” ብዬ ልወጣ ፊቴን ሳዞር እንደልጅ አባብለው ወደ ካፌ ይወስዱኝና ይመክሩኛል፡፡ /ሃሃሃ… “ይመክሩኛል” የሚለው ቃል አባታዊነትን እንዲወክል ሆን ተብሎ የገባ ቃል እንደሆነ ታሳቢ ተደርጎ ይነበብልኝ፡፡/
“ይህችን ምክር ስማ” ይሉና ይጀምራሉ፡፡
“በእርጅና ዘመን እንዲሆንህ ተስፋ
ገንዘብ ኪስህ ካለ፣ ኪሶችህን ስፋ”
ገንዘብ ላይ ቢስቆነቆኑም በሌላ ነገር ደግ ናቸው፡፡ “ስነቃል” ሲያጽፉኝ መሰሰት የሚባል ነገር አያውቁም፡፡ ለዚህም ነው መሰል ብር ባይኖረኝም እንኳን “ምን ይዘህልኝ መጣህ??” እንደምባል እያወቅኩ እሳቸው ዘንድ እማልጠፋው፡፡
“ሃብታም ማለት . . .” ይሉኛል “ሃብታም ማለት ፣ ብዙ ገቢ ያለው ሳይሆን ካገኘው ላይ ብዙ የሚቆጥብ ነው፡፡”
“እንደ እርሶ ማለት ነው” እላለሁ በሆዴ፡፡
“ሀብታም መሆን ከፈለግክ እጅህን ቶሎቶሎ ኪስህ አትክተት” ይሉኛል፡፡
“እንደ እርሶ ማለት ነው” እላለሁ - በሆዴ፡፡
በሚያሳዝን ሁኔታ የብዙ ሰው ምክር ሰምቼ ተሳክቶልኛል፡፡ የጋሽ ሙኼ ምክሮችን ለመተግበር ግን ሳልችል ቀርቻለሁ፡፡ እንኳን ብር ኖሮኝ ባይኖረኝም እንኳን፣ እጄ ልምድ ሆኖበት ኪሴን ያፈቅረዋል፡፡
ግልባጭ ፡- አሽ-ሙጥ በ Henok Sitotaw
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ